
ሞጣ፡- ሞጣ ከተማ የምትገኝበትን ወረዳ ጨምሮ በአካባቢው የሚገኙ አስር ወረዳዎች በአቅራቢያቸው የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ግንባታ እንዲከናወን እና ዞን እንዲሆኑ ጥያቄ መቅረቡ ተገለፀ።
የሞጣ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ ይሄነው ዋለ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ አካባቢው በቀጣይ ለኢንቨስትመንት ይበልጥ ምቹ እንዲሆንና የከፍተኛ ትምህርት ተቋም እንዲገነባ ህብረተሰቡ ጠይቋል። ሞጣ ከተማ ከደብረ ማርቆስ 202 ኪሎ ሜትር የምትርቅ በመሆኑ የአካባቢው ነዋሪ ጉዳይ ለማስፈፀም እየተሰቃየ ይገኛል። ለዚህ ደግሞ በአቅራቢያ የሚገኙት አስር ወረዳዎች አንድ ላይ በመሆን ዞን እንዲሆኑ ጥያቄ ለሚመለከተው ቀርቧል።
በተለያዩ ጊዜ መሰረተ ልማት ባለመሟላቱ ሞጣ ማደግ ባለባት ጊዜ ሳታድግ የቀረች ከተማ ነች ያሉት ምክትል ከንቲባው፤ በአሁኑ ወቅት መሰረተ ልማት እየተዘረጋና የመብራት አቅርቦት እየተሻሻለ የመጣ በመሆኑ ህብረተሰቡ ከተማዋ ይበልጥ እንድታድግ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ግንባታና የዞን እንሁን ጥያቄ እያቀረበ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።
ወደ ከተማው በርካታ ባለሀብቶች እየመጡ መሆናቸውንና አንዳንዶቹ ፋብሪካ አቋቁመው ወደ ምርት መግባታቸውን የተናገሩት ምክትል ከንቲባው ሌሎች ባለሀብቶች ወደ ከተማዋ በመምጣት ኢንቨስት ማድረግ እንደሚችሉም ተናግረዋል።
እንደምክትል ከንቲባው ገለፃ በከተማዋ የኢንዱስትሪ መንደር የሚገነባባቸው ቦታዎች ተዘጋጅተዋል። በቱሪዝም ዘርፉ ደግሞ በከተማው የሚገኙ ሀይማኖታዊ ስፍራዎች ውስጥ ከሚገኙ ቅርሶች ውስጥ የሞጣ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ብዙ ዓመት ያስቆጠረ በመሆኑ ቦታው እየተጎበኘ ይገኛል። በከተማ ውስጥ የሚገኙ የተፈጥሮ ዋሻዎችና ፏፏቴዎችን የማስተዋወቅ ስራም እየተከናወነ ይገኛል።
ከህዝቡ የመሰረተ ልማት ይሟላልን ጥያቄ በብዛት ይቀርብ ነበር የሚሉት አቶ ይሄነው የባህርዳር ፈለገ ሰላም አስፓልት ኮንክሪት መንገድ መሰራት ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው። ከሞጣ ደቡብ ጎንደር የሚደርስ መንገድ ስራ ተጀምሯል።
ከሞጣ ቤዊ ደብረ ማርቆስ ያለው መንገድ ለመገንባት ዝግጅት ተደርጓል። የመንገዶቹ መገንባትም የህብረተሰቡን ኢኮኖሚ ከማሳደግ ባለፈ ከተማዋን የኢንቨስትመንት እድልና የትራንስፖርት አማራጭ ያሰፋል እንዲሁም ለከተማው ወጣቶች የስራ እድል ይፈጥራል ብለዋል።
የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የባህርዳር ፈለገ ሰላም መንገድ ግንባታ በመረቁበት ወቅት እንደተናገሩት፤ ሞጣና በአካባቢው የሚገኙ ወረዳዎች በአሁኑ ወቅት የልማት ተጠቃሚነታቸው እያደገ በመምጣቱ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ይገንባልንና የዞንነት ጥያቄ ማንሳታቸው ተገቢ ነው።
ነገር ግን የሞጣ ከተማ ከደብረ ማርቆስ 202 ኪሎ ሜትር ከባህርዳር ደግሞ 120 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኝ በመሆኑና በደብረ ማርቆስና በባህርዳር ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ስለሚገኙ በቅርቡ በሞጣ ከተማ አይገነባም። በቀጣይ መንግስት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ሲያስፋፋ በእቅድ ውስጥ ይካተታል። የዞን እንሁን ጥያቄም ሰፊ ጥናት የሚፈልግ በመሆኑ ነዋሪው ለመንግስት ጊዜ መስጠት አለበት።
አዲስ ዘመን መስከረም 12/2012
መርድ ክፍሉ