በዓይነ ህሊና ወደ 1960ዎቹ እንመለስ። እንመለስና በዘመኑ የነበሩ ወጣቶችን እናስታውስ። በወቅቱ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በክረምት ወቅት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ለመስጠት ወደ ገጠሩ የሀገሪቱ ክፍሎች ይሰማሩ ነበር። በዚያም የአርሶ አደሩን ልጆች የማስተማርና ሌሎችም የበጎ ፍቃድ ተግባራትን ይከውኑ ነበር። ወጣቶቹ የበጎ ፍቃድ ተግባራቸውን በሚያከናውኑበት ወቅትም ቀልባቸውን የሚያሸፍት ሌላ ጉዳይ ተገነዘቡ። በጥቂት ፊውዳሎች የተነሳ ጭሰኛ የሆነው አርሶ አደር እጅግ መራራና አስከፊ ህይወት!
በጊዜው የአርሶ አደሩን መሬት በማን አለብኝነት የተቆጣጠሩት ጥቂት ፊውዳሎች የአርሶ አደሩን ቤተሰብ ጭምር ባሪያቸው አድርገውና ከምርቱ እስከ 75 በመቶውን እየዘረፉ ህይወቱን የምድር ላይ ሲኦል አድርገውበት ነበር። በገዛ ሀገሩ የባርነት ህይወት እንዲኖር ተፈርዶበት ቁም ስቅሉን ያይ የነበረው ጭቁን አርሶ አደር ህይወት የወጣቶቹን ስሜት ነካ። ባረጀው ፊውዳላዊ አገዛዝ ምክንያት አብዛኛው የከተማውም ነዋሪው ቢሆን ህይወቱ ከሞቱት በላይ ከቆሙት ደግሞ በታች የሚባል ዓይነት ነበር።
ይህን ሁኔታ የተገነዘቡት ወጣቶች ከንፈራቸውን በኀዘኔታ መጥጠው ቁጭ አላሉም። መሬት ላራሹና ያረጀው ፊውዳላዊ አገዛዝ ይወገድን የመሳሰሉ ትልልቅ የህዝብ ጥያቄዎችን አንስተው በአመጽ አገርን ያንቀጠቅጡ ጀመር እንጂ። ከመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት እስከ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ያስተባበረውን ትግል ለማኮላሸት አሻጥር፣ ድብደባ፣ ግድያና አፈናን የመሳሰሉ የቀቢጸ ተስፋ እርምጃዎች ቢወሰድባቸውም ጥያቄው ቅዱስና ህይወትም ቢከፈልበት የሚያኮራ ነበርና እርምጃውን እንደ ትግል ማቀጣጠያ ነዳጅ ተጠቅመው ፊውዳላዊውን አገዛዝ ለግብዓተ መሬት አበቁ። ወጣቶቹ የከፈሉት አኩሪ መስዋዕትነት የገበሬውን ህይወት ዋጅቶ ለከተማውም ህዝብ ትሩፋት ሆነ!
የ1960ዎቹ ወጣቶች በከፈሉት መስዋዕትነት ጊዜያዊ አስተባባሪ በሚል ካባ ወደሥልጣን የመጣው ደርግም ቃሉን በልቶና ህዝብ ጫንቃ ላይ ተጭኖ ኢሰብዓዊ ተግባሩን ሲያጧጡፍም የህዝብ ክንድና አለኝታ የሆኑት ወጣቶች እጃቸውን አጣጥፈውና አሜን ይሁን ብለው አልተቀመጡም። ህዝባዊ መንግሥት ይመስረት፣ ሰብዓዊና ዴሞክራሲዊ መብቶች ይከበሩና አፈናና ጭቆና ይቁም በሚሉ መፈክሮች እሳቱን ፊት ለፊት ተጋፈጡት እንጂ። ይህንን ተከትሎ ደርግ በመዘዘው የጥፋት ሰይፍም በሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች መተኪያ የሌላት ውድ ህይወታቸውን ለሀገርና ለህዝብ ሲሉ መስዋዕት አድርገዋል።
ደርግ በአፈሙዝ እንጂ በሰላማዊ ንግግር እንደማያምን ሲረዱም ከሰሜን አስከ ደቡብ ከምስራቅ እስከ ምእራብ ወጣቶቻችን አንድ ሆነው ውድ የሆነውን የወጣትነት ህይወታቸውን ለአገርና ህዝባቸው ሰውተው አኩሪ ፍልሚያ አድርገው በታሪክ ልዩ ቦታ የሚይዝ መስዋዕትነት ከፍለዋል። በአኩሪ መስዋዕትነታቸውም ታሪካቸውን በደም ጽፈው ፋሽስታዊውን ስርዓት ከመቃብር አውርደዋል።
ይህ የወጣቶቻችን ለሀገርና ለህዝብ መስዋዕት የመሆን አኩሪ ታሪክ አሁንም እንዳልቆመ የሚያሳዩ በእውነታ ላይ የተመሰረቱ ማስረጃዎች አሉ። ኢህአዴግ ይዞት የተነሳውን ክቡር ዓላማ ስቶ በዘረፋና በኢሰብዓዊ መብት ረገጣ ሲዳክርና ፍትሃዊነት ሲጠፋ ነበልባሎቹ ወጣቶች ቄሮ፣ ፋኖ፣ ዘርማ፣ ኤጀቶ ወዘተ በሚሉ ሥያሜዎች ተደራጅተው ይህ አካሄድ አያዋጣም ይስተካከል ብለው ፊት ለፊት ታግለውታል።
ኢህአዴግ የወጣቱን ቁጣ ያስታግስልኛል በሚል በኃይልም ሆነ ከልብ ባልሆኑ የመደለያ እርምጃዎች ለማስተንፈስ ቢሞክርም ፊት ነስተው ትግላቸውን አቀጣጥለዋል። የከፈሉት መስዋዕትነትም ሜዳ ላይ ወድቆ አልቀረምና በኢህአዴግ ውስጥ ያልተጠበቀና ያልተገመተ ለውጥ እንዲከሰት ሆኗል። በየዘመናቱ ወጣቶቻችን በደማቸው የጻፉት የህዝብን እንባ የማበስ ትግልና መስዋዕትነት አኩሪ ነውና ለዘላለም ሲዘከር እንደሚኖር ጥርጥር የለውም።
በየዘመኑ በህዝብ ላይ የሚደርስ ጭቆናና ግፍ አላስችል ብሏቸው የተነሱ ወጣቶች የአፍላነት ዘመናቸውን ለትግል ሲሰውና መተኪያ አልባ ህይወታቸውን እንደሻማ ሲያቀልጡ ከዚሁ በተቃራኒው ትግሉን ጥላሸት ለሚቀባና ለሚያኮላሽ ተግባር የተሰለፉ የበግ ለምድ የለበሱ ተኩላዎችም አልጠፉም። እነዚህ ኃይሎች የትግሉን ጎራ የተቀላቀሉ በመምሰል ተገቢነት የሌለውና ትግሉ በጥፋት እንዲፈረጅ የሚያደርጉ ተግባራት ሲፈጽሙ ታይተዋል፤ እየታዩም ነው።
ምንም ዓይነት ምክንያት ይኑር በትግል ስም ዘረኝነትን ለማስፋፋት ጥረት ማድረግ፣ ሀብትና ንብረትን ማውደም፣ የወንድምና እህትን ህይወት ማጥፋት ወዘተ እንባ አፍሳሽ እንጂ እንባ አባሽ ተግባራት በፍጹም ሊሆኑ አይችሉም። በተለይም በአንዳንድ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚማሩ ወጣቶች እዚህ ግባ በማይባልና ውሃ በማይቋጥሩ ምክንያቶች ተነሳስተው ሰላምን ሲያውኩ ንብረት ሲያወድሙና ለህይወት መጥፋት ምክንያት ሲሆኑ መመልከት እንቆቅልሽ ይሆናል። ይህን መሰል አጥፊ ተግባራት የሚፈጸሙት ማንኛውም ጥያቄ በህጋዊ መንገድ ቀርቦ ምላሽ ማግኘት በሚችልበት ሁኔታ ውስጥ መሆኑ ደግሞ ከጀርባ ተሁኖ ወጣቶቹን ለጥፋት የመጠቀም ፍላጎትና ተግባር እንዳለ በግልጽ ያመለክታል።
እንጨት ሽጠው፣ እንጀራ ጋግረው፣ ጠላ ጠምቀውና የጉልበት ሥራ ሠርተው ፍዳቸውን አይተው ነገ ያሳልፉልኛል ብለው ወደ ትምህርት ቤት የላኳቸው ወጣት ልጆቻቸው በወገኖቻቸው መቀጨታቸውን ሰምተውና ተስፋቸው መጨለሙን አይተው እናቶች ያነቡትን እንባ የጥቂት እናቶች እንባ ሳይሆን የአገር እንባ ነው።
ሀገራችን ዛሬም ድረስ የምትታወቀው በድህነቷ ነው። በሚሊዮን የሚቆጠረው ህዝባችን የዕለት ጉርሱን እንኳን የሚሞላው ፍዳውን አይቶና መከራውን በልቶ ነው። ረሃብና ችግር ጎድቷቸውና ጧሪ አጥተው በየእምነት ተቋማቱ እንባቸውን የሚያፈሱና እጃቸውን ለልመና የዘረጉ እናቶችና አባቶች ቁጥር በጣም ብዙ ነው። ድህነት ከመቅረፍ አንጻር ከሠራናቸው ሥራዎች ይልቅ ያልተሠሩት እጅጉን ልቀው ይገኛሉ። ይህንን ትልቅ የቤት ሥራ ሠርቶ አገርን ከድህነት የማላቀቁና የህዝብን እንባ የማበሱ ኃላፊነት የተጣለው ደግሞ የነገ የሀገሪቱ ተስፋ በሆኑ ወጣቶች ላይ ነው። ሀገራችንና ህዝቦቿ በተለይም እናቶች ፍትህን አስፍነውና ጨለማውን ገፈው ብርሃን ያላብሱናል ብለው ተስፋ የጣሉትም በወጣት ልጆቻቸው ላይ ነው። ስለሆነም ወጣቶች ኢፍትሃዊነትንና ሌብነትን አምርረው በመታገል እንዲሁም ከጥላቻና ከጥፋት በመራቅ የህዝብንና የአገርን እንባ ሊያብሱ ይገባል እንላለን!
አዲስ ዘመን ታህሳስ 12/2011