
አዲስ አበባ፡– የተሻሻለው የመድኃኒት አቅርቦት መመሪያ 60 በመቶ የመድኃኒት ፍጆታን በሀገር ውስጥ ለመሸፈን የተቀመጠውን ግብ ለማሳካት የሚረዳ መሆኑን የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት አስታወቀ። መመሪያው የሀገር ውስጥ አምራቹን የሚያበረታታ መሆኑም ተመልክቷል።
የተሻሻለውን የመድኃኒት አቅርቦት መመሪያ በተመለከተ መግለጫ የሰጡት የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አብዱልቃድር ገልገሎ፤ እንደተናገሩት ከግንቦት 26 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ ሥራ ላይ የዋለው መመሪያ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን የሚያበረታታ ነው። በዚህም የሀገር ውስጥ የማምረት አቅምን በማሳደግ እንደ ሀገር 60 በመቶ የሚሆነውን የመድኃኒት ፍጆታ በሀገር ውስጥ ምርት ለመሸፈን የተያዘውን ግብ ለማሳካት እድል የሚፈጥር ነው ብለዋል።
መመሪያው በሀገር ውስጥ የሚመረቱ መድኃኒቶች እና የህክምና ቁሳቁሶች የሀገር ውስጥ አምራቾች ብቻ ተሳታፊ በማድረግ ያለምንም የገንዘብ ጣሪያ ለጨረታ መቅረብ የሚያስችል ስለሆነ፤ የፈለጉትን ያህል እንዲያመርቱ እንደሚያስችል ተናግረዋል።
በሌላ በኩል በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሚፈጸም ጨረታ ማቅረብ የሚቻለው ገንዘብ መጠን ሶስት ቢሊዮን ብር የተደረገ መሆኑን አመልክተው፤ በውስን የገንዘብ ጣሪያ ደግሞ ሁለት ቢሊዮን እንዲሆን ተደርጓል። እንዲሁም በማምረት ሂደት ግብዓቶችን ከሀገር ውስጥ ለሚጠቀሙ ኢንዱስትሪዎች የማበረታቻ ሥርዓት መዘርጋቱን አስረድተዋል።
ከዚህ ቀደም አንድ መድኃኒት በጨረታ ለመግዛት 200 ቀን ያህል እንደሚወስድ የተናገሩት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ጨረታ አየር ላይ የሚውልበት የወራት ጊዜ ወደ 15 ቀን ዝቅ እንዲል እና ሌሎች ለግምገማ፣ ለቅሬታ የሚሰጡ ቀናት ዝቅ እንዲሉ በማድረግ ጨረታው በአጭር ጊዜ መፈጸም የሚቻልበት ሁኔታ መፈጠሩን ጠቁመዋል።
ዶክተር አብዱልቃድር እንደገለጹት፤ የሀገር ውስጥ አምራቾችን በማበረታት ሂደት ውስጥ አሁን ያለው የሀገር ውስጥ መድኃኒት አምራች ኢንዱስትሪዎች አቅም ተጠንቷል። ከዚህ ጋር ተያይዞ ከዚህ ቀደም የሀገር ውስጥ አምራቾች የማምረት አቅም ስምንት በመቶ ነበር። በአሁኑ ጊዜ 30 በመቶ ደርሷል። የሚመረቱ የመድኃኒት እና የህክምና ቁሳቁስ አይነቶችም 97 እንደደረሱ እና በዘንድሮ ዓመት ከአምራቾች ጋር የ11 ቢሊዮን ብር ውል ለመግባት እንደተቻለ አስረድተዋል።
የካንሰር መድኃኒትን ጨምሮ የአንዳንድ መድኃኒቶች ተጠቃሚዎች ቁጥር እንደ ሀገር ዝቅተኛ በመሆኑ፤ የሀገር ውስጥ አምራቾች ስለማያዋጣቸው ለማምረት ፍላጎች እንደሌላቸው በመግለጽ፤ እነዚህን መድኃኒቶች በአፍሪካ ህብረት በኩል በጥምር ግዢ ከሌሎች አፍሪካ ሀገራት መግዛት የሚቻልበት መንገድ በመመሪያ መዘርጋቱን አስረድተዋል።
መድኃኒት ሆነ የህክምና ቁሳቁስ ከግዢ ጀምሮ እስከ አጠቃቀም ልዩ ጥንቃቄ እና የቴክኖሎጂ እውቀት የሚፈልግ መሆኑን በማንሳት፤ አዲሱ መመሪያ እነዚህን ነገሮች ታሳቢ በማድረግ በገንዘብ ሚኒስቴር በኩል እንዲፈጸም ተደርጓል ሲሉ አመላክተዋል።
ዓመለወርቅ ከበደ
አዲስ ዘመን እሁድ ሰኔ 1 ቀን 2017 ዓ.ም