
ብላቴ ፡- “መከላከያ ሠራዊት የትኛውንም ውጊያ በብቃት መወጣት የሚያስችል አቅሙን እያጠናከረ በመሄድ ላይ ይገኛል ሲሉ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ አስታወቁ።
የብላቴ ልዩ ዘመቻዎች ኮማንዶ ማሰልጠኛ ማእከል 43ኛ ዙር ካራማራ ኮርስ መሠረታዊ ኮማንዶ ሠልጣኞችን በትናንትናው እለት በደማቅ ሥነሥርዓት አስመርቋል።
ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በመርሃ ግብሩ ባደረጉት ንግግር ፤ባለፉት ዓመታት በሥነ ልቦና እና በአካላዊ ብቃት የተገነቡ የኮማንዶና የአየር ወለድ ምርጥ አሃዶች እንዲሁም ስፔሻል ፎርሶች በብዛትና በጥራት ሠልጥነው ወደ ሥራ ገብተዋል። የዛሬ ተመራቂዎችም ከነዚያ የላቀ ብቃትን ከተላበሱ እና እንደወርቅ በእሳት ተፈትነው የዳበረ ልምድ ባለቤት ከሆኑ ጀግኖች ጋር ስለምትቀላቀሉ ኩራት ሊሰማችሁ ይገባል ብለዋል።
መከላከያ ሠራዊታችን ባልተቋረጠ ሁኔታ ዝግጁነቱን እያጠናከረና አቅሙን ወደ ላቀ ደረጃ እያሸጋገረ በመሄድ ላይ መሆኑን አመልክተው፤ የታሪካዊ ጠላቶቻችን ተላላኪ ባንዳዎች በኢትዮጵያ እና በሕዝቦቿ ላይ የሚመኙት የእልቂት ድግስ መቼውም ቢሆን እውን እንደማይሆን ገልጸዋል።
ሞቷን ሲመኙ እነርሱ ይሞታሉ ፣ ውድቀቷን ሲመኙም እነርሱ ይወድቃሉ፣ ለሕዝቦች እልቂትና መበታተንን ሲደግሱ እነርሱ ቀድመው እንደሚበታተኑ እየተረጋገጠ መምጣቱንም ገልጸው፤ኢትዮጵያ በመቃብራቸው ላይ ትቆማለች።
ይህን ሀቅ ጠላቶቻችን እየመረራቸውም ቢሆን ሊውጡት የሚገባ ነው ሲሉ ፊልድ ማርሻሉ አስገንዝበዋል። ጠላቶቻችን እንደሚመኙልን ሳይሆን በሀገር መከላከያ ሠራዊታችን መሠረት ሀገራዊ ልማታችን እና የሕዝባችን የብልፅግና ጉዞ ያለምንም እንቅፋት እየቀጠለ እንደሆነ አመልክተው፤ በየትኛውም ሥርዓት ያልተሞከረው የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም የማስከበር ጥረት በተስፋ ሰጪ ጉዞ ላይ የሚገኝ ስለሆነ መጪው ጊዜ የኢትዮጵያ ከፍታ የሚረጋገጥበት እንደሚሆን ጥርጥር የለውም ብለዋል።
ዛሬ ሀገራችን ከምን ጊዜውም በላይ በቴክኖሎጂ፣ በሰው ሃይል፣ በአደረጃጀት፣ በተቋማዊ አሠራርና በትጥቅ አስተማማኝ ሠራዊት ገንብታለች ያሉት ጠቅላይ ኢታማጆር ሹሙ፤ ሠራዊታችን መከፈል ያለበትን መሥዋእትነት ሁሉ ይከፍላል እንጂ የሀገሪቱ ብሄራዊ ጥቅም በተላላኪ ባንዳዎችና በላኪዎቻቸው ተደናቅፎ ሕዝቦቿ ሁሌም በድህነት ውስጥ እንዲኖሩ አይፈቀድም። ይህን ቁርጠኝነቱንም መከላከያ ሠራዊታችን በተግባር አሳይቷል ሲሉ ገልጸዋል።
ዛሬ ለምረቃ የበቁት የ43ኛ ካራማራ ኮርስ ኮማንዶ ትናንትና ከነበረው ሳይንሳዊ የአሠለጣጠን ዘዴ በላቀና ዘመኑን በሚመጥን ደረጃ ማንኛውንም የውጊያ አይነት በብቃት መወጣት በሚችሉበት ሁኔታ ሥልጠና የወሰዱ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ የሥልጠና ላይ የቆይታ ጊዜያቸውም ከፍ እንዲል በመደረጉ ከፍ ያለ የኮማንዶ አቅምን የፈጠሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ሠልጣኞች በሁሉም አይነት የአየር ጸባይ እና የመሬት ግጽታዎች ብቃት ያለው ሥልጠና በመውሰድ አስቸጋሪና ፈታኝ ሁኔታዎችን በማለፍ፣ በመሠረታዊ ኮማንዶነት የተመረቁ መሆናቸው ከነባሩ ሠራዊት ጋር ተቀላቅለው የትናንት እና የዛሬ ጀግኖችን ታሪክ በመድገም ሀገራቸውንና ሕዝባቸውን እንደሚያኮሩአመልክተዋል።
ኢትዮጵያን ለማፍረስ ያልሞከረ፣ ጥረት ያላደረገ የለም ያሉት ፊልድ ማርሻሉ ፤ኢትዮጵያ ግን ከነግዝፈቷ፣ ከነሰፊው ሕዝቧ፣ ከነ ሰፊው ግዛቷ፣ ቆይታለች፤ ኖራለችም። ያቆዩትም ጀግኞች ልጆቿ ናቸው ብለዋል ።
ሁል ጊዜ ጀግኖች ወራሪዎችን በሚመክቱበት ጊዜ ጎን ለጎን ባንዳ ይፈጠራል ያሉት ፊልድ ማርሻሉ፣ አሁንም ሀገር ውስጥ ሆነው ከታሪካዊ ጠላቶቻችን ጉርሻ እየተቀበሉ መሠረተ ልማት የሚያፈርሱ፣ አርሶ አደሩን የሚያውኩ፣ ባለሀብቶችን የዘረፉ ፣ ትራንስፖርትን ያወኩና ትምህርት ያስቆሙ ከጠላት የበለጠ ጥፋት ለማድረስ የሚሞክሩ አሉ። ነገር ግን ይህ እኩይ ዓላማቸው አይሳካላቸውምብለዋል።
ኢያሱ መሰለ
አዲስ ዘመን እሁድ ሰኔ 1 ቀን 2017 ዓ.ም