
በትናንትናው ክፍል ሁለት እትማችን በለውጡ ዋዜማ ስለታዩ የፖለቲካ ሃይሎች የአቋም መዋዠቆች፤ በፈተና ውስጥ ትልቅ ነገርን መሥራት / ማሳካት ይቻላል በሚሉት እና ፤ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀጥተኛ የፕሮጀክቶች ክትትሎች ለተነሱ ጥቄዎች ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ምላሽ ሰጥተዋል፤ በዛሬው እትማችን የቃለ መጠይቁን ሶስተኛ ክፍል እንደሚከተለው አቅርበነዋል።
ኢቲቪ ፡- ኢኮኖሚው ላይ ቪዝብል የሆኑ የሚታዩ ለውጦች እንዳሉ ይታመናል። ከዚያው ጋር አብሮ የሚነሱ ጉዳዮች ደግሞ አሉ። በተለይ የኑሮ ውድነቱ በማህበረሰቡ ዘንድ የሚነሱ ጥያቄዎች ናቸውና ምንድን ነው መፍሔዎቻቸው ይላሉ? እያደገ ካለው ኢኮኖሚ በአንድ ወገን የሚታይ ነገር አለ በሌላ በኩል ደግሞ የኑሮ ውድነቱ የሚኖሩ ጉዳዮች አሉ። እንዴት አስተሳስረን መፍትሔ ማምጣት እንችላለን ይላሉ ?
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ይሄ በጣም ሰፋ ያለ ሃሳብ የያዘ ግን ደግሞ መሠረታዊ ጥያቄ ነው። ግን ቀድሜ ወዳነሳሁልሽ ጉዳይ ነው የሚመልሰን። አሁንም የዚህን ጉዳይ እውነታ በየሌየሩ ሽንኩርቱን እየላጥን ካላየን በቀረ የተዛባ ግንዛቤ እና ያልተስተካከለ ድምዳሜ ላይ እንደርሳለን። ለምሳሌ የኑሮ ውድነትን እንደ ምሳሌ እናንሳ ወይም ኢንፍሌሽን የዋጋ ግሽበትን ይሄን አጠቃላይ የኢኮኖሚ ችግር እኛ በሶስት ነው የከፈልነው። እዳ አለ ብዬሻለሁ፤ ደመሞዝ መክፈል አንችልም።
መበደር አንችልም፤ ፕሮጀክቶች ቆመዋል። ምን ብናደርግ ነው ካለንበት ጣጣ፣ መከራ ወጥተን ወደተስተካከል ነገር ወይም ወደ ተሻለ ነገር የምንገባው ብለን በሶስት ምዕራፍ ከፈልነው። የመጀመሪያው ምዕራፍ ማፍታታት ነው። ፕሮጀክት ተሳስሯል፤ ብድር መክፈል ብድር መበደር ተሳስሯል፤ ኤክስፖርት የሀገር ውስጥ የንግድ እንቅስቃሴ ተሳስሯል፤ ማፍታታት ያስፈልጋል። አቧራውን ማራገፍ ያስፈልጋል። በአንዳንድ ጉዳይ እሴት መጨመር ያስፈልጋል። በአንዳንድ ጉዳይ ሕግ መቀየር ያስፈልጋል። በአንዳንድ ጉዳይ ከፈት ከፈት ማድረግ ያስፈልጋል። እንከፋፍተው ንፋስ ይግባበት። እምክ እምክ የሚለውን የታሸገውን ነገር ፈታ ፈታ እናድርገው የሚል ውሳኔ ነበር የወሰነው።
እንግዲህ ለውጡ ከመምጣቱ በፊት ለአስራ ምናም ዓመታት ኢትዮጵያ ውስጥ አጠቃላይ ከሃያ ዓመት ያላነሰ ጊዜ ኢንፍሌሽን ኮንቲኒየስሊ እያደገ መጥቷል። ያው የነበረው አጠቃላይ ሁኔታ የሚታወቅ ሆኖ ኢንፍሌሽን ግን ተቋርጦ አያውቅም፤ ሃያ ዓመት። ኢንፍሌሽን አንድ ዓመት አጋጥሞ ሲገራ፣ ሁለት ዓመት አጋጥሞ ሲገራ፣ ሶስት ዓመት አጋጥሞ ሲገራ እና አስር አስራ አምስት ዓመት አጋጥሞ ሲገራ አንድ አይደለም። በደንብ ሥር እየያዘ ስለሚሄድ መልሶ ማስተካከሉም በዚያው ልክ ፈታኝ ነው የሚሆነው።
አንደኛው ፈተና የነበረብን ዕዳ መኖሩ ብቻ ሳይሆን ግሽበቱ ለዓመታት እያደገ፣ እየቀጠለ የመጣ፤ ሳይቋረጥ። ይሄ ችግር ነው፤ ይሄ በሽታ ነው። እዚህ በሽታ ላይ ደግሞ ኢንፌክሽን መጣ። ሰው ለታመመበት ጉዳይ ህመም መድኃኒት እየወሰደ ሳያገግም ኤንፌክሽን መጣ ማለት ሕይወቱን ሊቀጥፍ የሚችል አደጋ መጣ ማለት ነው። ኢንፌክሽኑ ምንድን ነው? አንደኛው ኮረና ነው። ገና ምንኑም ሳንይዘው ኮረና የሚባል ነገር መጥቶ ከእሳቤያችን ከሥራችን የሚያደናቅፍ ሆነ።
ኮረና እንዴት ነው ያደናቀፈን? አግዙን ብለናቸው እናግዛችኋለን በርቱ ያሉን ሀገራት ኮረና ሲመጣ የእነሱ ጣጣ ገዘፈና፣ የእነሱ ችግር በዛና የእኛ ጉዳይ ሁለተኛ ችግር ሆነባቸው። እኛን ለማየት ጊዜ የላቸውም በጣም ተወጥረዋል እነሱ። ኮረና ሲባል በሽታ ብቻ አይደለም ብዙ የተሳሰረ ጉዳይ በውስጡ ስላለ ነው።
የዩክሬን ጦርነት መጣ። የዩክሬን ጦርነት ድራማቲክ የሆነ ሽፍት ነው ያለው። ወደ አፍሪካ የሚፈሰውን የድጋፍ መጠን በከፍተኛ ደረጃ ቀንሶ ወደዚያ እንዲሄድ አድርጎታል፤ በከፍተኛ ደረጃ። አቴንሽን የሚሰጡ፣ የሚያግዙ ተቋማት ፤ ሀገራት፣ ግለሰቦች ትተውን ወደ ዋናው ጉዳያቸው ገቡ። ኢንፌክሽን ነው ይሄ። ችግር አለብን ተደግፈን ከችግሩ እንዳንወጣ ደግሞ ተጨማሪ ችግር ተደረበበት ማለት ነው። ንግድ የሚያስተጓጉል፤ ርዳታ የሚያስተጓጉል። ድጋፍ የሚያስተጓጉል።
ግጭት የሀገር ውስጥ ግጭት ተፈጠረብን። ከግራ ከቀኝ በሶስት ወር እገባለሁ፤ በአምስት ወር እገባለሁ የሚሉ ኃይሎች ግጭት አበዙብን። እነዚህ ግጭቶች ሙሉ አቅማችንን ማዋል በሚገባን ነገር እንዳናውል በገንዘብም፣ በጊዜም፣ በጉልበትም ወሰዱብን። ኢንፌክሽኖች ናቸው። በነበረው መከራ በነበረው ችግር ላይ ተጨማሪ ችግር ነው።
ሶስተኛው ባለፉት ሃያ ዓመታት ከኮረና በፊት በነበረው ጊዜ የኢትዮጵያ ኢንፍሌሽን በያመቱ እያደገ ሲመጣ የዓለምም ኢንፍሌሽን በዚያው ልክ ተናጋ ሊባል አይችልም። የጨመሩባቸው ሀገራት ይኖራሉ። ግን ባሁኑ ደረጃ ዓለምን የሚያናጋ ጉዳይ አልነበረም ኢንፍሌሽን። ኮኮረና በኋላስ የዓለም ሁሉ መከራ ሆነ። እንደ አይኤምኤፍ የ2024 የአምናው ሪፖርት እንደሚያሳየው ቱርክ 58 ፐርሰንት ነበር ኢንፍሌሽኗ።
ባለፉት ሃያ ዓመታት ከፍተኛ ዕድገት ካመጡ ሀገራት አንዷ ቱርክ ናት። ትራንስፎርም ያደገረች ሀገር ናት። ግን ባለፈው ዓመት በነበረው አጠቃላይ ሂደት 58 ፐርሰንት ግሽበት ነበረባት። ግብጽ 33 ፐርሰንት ግሽበት ነበረባት። አርጀንቲና ከ200 በላይ ግሽበት ነበረባት። ይሄ የአይኤምኤፍ ሪፖርት ነው። አሜሪካ እንኳን እዛ የሚኖሩ ዜጎቻችን እንደሚነግሩን ድሮ እንቁላል የሚገዛበትን ዋጋ ድሮ ስቶር ሄደው ሱፐርማርኬት ሄደው የሚያገኟቸውን ዕቃዎች በቁጥርም አያገኙም በዋጋም ጨምረዋል።
እምብዛም አሜሪካ ነዳጅ ወጣ ወረደ ይባላል እንጂ ብዙ ዋጋ የተረጋጋ ነው። አሁን እንደዚያ አይደለም። ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት አለ። ዓለምን ነው የናጠው ማለት ነው። ዓለምን ሲንጥ ደግሞ ኢንፖርት የሚደረጉ ኢንፍሌሽኖች አሉ። እዛ ሲረበሽ እንደኛ በኢንፖርት ላይ ቤዝ ያደረጉ ኢኮኖሚ ያለው ሀገር ደግሞ ኢንፖርት ያደርጋል።
የቆየ ችግር አለን። ላዩ ላይ ኢንፌክሽን መጣ፤ ይሄ ችግር ደግሞ ከእኛ አልፎ የዓለም ችግር ሆነ። ይሄ ሲደማመር ችግሩን ለመፍታት የምንወስድበት መንገድ በምዕራፍ ካልተከፈለ በቀር በቀላሉ የሚፈታ ሆኖ አናገኘውም። እና በመጀመሪያው ምዕራፍ ፈታታነው አቧራውን ለማራገፍ ሞከርን። ቫሊዩ ለመጨመር ሞከርን እሴት ለማከል ሞከርን።
በሁለተኛው ምዕራፍስ በሁለተኛው ምዕራፍ ማንሰራራት ነው ያለብን። መዝለል ነው ያለብን። ቀስ ያለው አካሄድ እንክሪመንታል የሆነው አካሄድ ካለንበት ችግር አያወጣንም። ያን ለማድረግ ደግሞ ሶስት ነገር ላይ እናተኩር። አንደኛ ተቋም እንገንባ፣ እንፍጠን፣ በእያንዳንዱ ሥራዎቻችን ላይ እንፍጠን፣ እንፍጠር ፈጠራ ይታከልበት ፈጠራ ከሌለ፣ የፈጠርነውን ነገር ለመከወን ፍጥነት ከሌለ በፍጥነት የሚከውን ተቋም ከሌለ መዝለል አንችልም። እንክርመንታል ነው የሚሆነው ያ ደግሞ ከሆነ የምናስበውን ውጤት አናመጣም ብለን ወሰንን። ልክ እንደ ቅድሙ በሌየር ማየት እንዲያስችልሽ ነው የማነሳው።
ተቋም መገንባት አለብን ሲባል የነበረ የሰው ኃይል ኢትዮጵያ ውስጥ የነበረው የመንግሥት ሠራተኛ ቁጥር አንዳንዱን ጉዳይ ለመከወን በቂ አይደለም። በነገራችን ላይ ባለፉት ስድስት ሰባት ዓመታት በአቬሬጅ የኢትዮጵያ መንግሥት ለደመሞዝ የሚያወጣው ገንዘብ በየዓመቱ በአቬሬጅ 21 ፐርሰንት ይጨምራል። በየዓመቱ 21 ፐርሰንት ይጨምራል። ወጪው። ያ የወጣው ወጪ እያንዳንዱ ሠራተኛ ጋር ይደርሳል ወይ የተባለ እንደሆነ አይደርስም። ለምንድን ነው የማይደርሰው የመንግሥት ሠራተኛ ከለውጡ በፊት 1.7 ነበር። አሁን ከ2.5 ሚሊዮን በልጧል። በዚህ ስድስት ሰባት ዓመታት ውስጥ የመንግሥት ሠራተኛ 44 ፐርሰንት ጨምሯል። 44 ፐርሰ ንት።
ለምንድን ነው በዚህ ልክ የጨመረው? ያልን እንደሆነ አንዳንድ ሴክተር ብቻ እናንሳ። መምህራን ከለውጡ በፊት ከነበረው አንድ ሶስተኛ ቁጥር ጨምረናል። 36 ፐርሰንት የመምህራን ቁጥር ኢትዮጵያ ውስጥ አድጓል። ባለፉት ስድስት ዓመታት ጨምሯል። 36 ፐርሰንት። ድሮ ለመምህር ብለን የምናወጣው ደመሞዝ 36 ፐርሰንት ጨምሯል ማለት ነው፤ ባለው መጠን በጭማሪው አይደለም ባለው መጠን።
ለምን ቅጥር ሰፋ የትምህርት ሥርዓቱ ስብራት አለበት፤ ውድቀት አለበት። ከስብራቱ ደግሞ አንዱ ኤርሊ ቻይልድ ሁድ ላይ አይሠራም። አንድ ልጅ በገጠር እስከ ሰባት ዓመት በሰፈር ሲያውደለድል፣ ሲላላክ፣ እረኛ ሲሆን ቆይቶ ሰባት ዓመት ሲሞላው አንደኛ ክፍል ይላካል። አንደኛ ክፍል ሲላክ የሚጠብቀው ኤክስና ራይት ነው። ጄጅመንት
ነው። ከትምህርት ጋር ልምምድ ያልነበረው ልጅ፣ ከአስተማሪ ጋር ተገናኝቶ የማያውቅ ህጻን ትምህርት ሲሰጥ እንዴት መከታተል እንዳለበት የማያውቅ አብዛኛው ደግሞ ወላጅ ማገዝ የማይችል። አብዛኛው ወላጅ ያልተማረ ስለሆነ ገና ትምህርት ቤት በገባ በጥቂት ወራት ውስጥ ኤክስ ነህ ራይት ነህ፤ ኤክስ ነህ ራይት ነህ የሚባል ጄጅመንት ሳኮለጂካል ሀራስመንት ነው የሚገጥመው። ይሄንን ለማስተካከል ለልጆች መዋያ ያስፈልጋቸዋል፤ ኪንደርጋርደን ያስፈልጋቸዋል በሚል ከ35 ሺህ በላይ መዋዕለ ህጻናት ኢትዮጵያ ውስጥ ተገንብቷል። ከ35 ሺህ በላይ።
ሕዝቡ እንደሚያውቀው ከዚህ ቀደም በሰባት ዓመት ልጆቹን የሚልክ ሰው አሁን በሁለት ዓመት ተኩል በሦስት ዓመት እንደሚልካቸው ያውቃል። ሁሉም ሰው የሚያውቀው ጉዳይ ነው። በሦስት ዓመት ልጅን መዋዕለ ሕጻናት መላክ ምንድን ነው ፋይዳው? ያልን እንደሆነ መልከ ብዙ ነው። ለምሳሌ አንድ መምህር እሱ እና ሚስቱ መምህር ቢሆኑ፤ ወይም እሱ መምህር ሆኖ እሷ ደግሞ ሌላ ሥራ ቢኖራት ልጅ ስትወልድ ልጇን የሚይዝላት ሰው ከሌለ እናት ቤት መቆየቷ ግዴታ ነው። እናት ልጅ ታሳድጋለች፤ አባት ደግሞ ሠርቶ ያመጣል በዚያ ደመወዝ ነው በጋራ የሚኖሩት።
እንደ ሌላው የሠለጠነው ዓለም ሕጻናት ማቆያ የሚባል ቦታ እኛም ጋ እምብዛም የለም። ገና ነው አዲስ አበባ እየጀመርን ያለው እንደምታውቁት። እናም አንድ ሰው ወልዶ በሦስት ዓመቱ ልጁን ሳይከፍል የሚያውልበት ሴፍ የሆነ ቦታ አለ ማለት ለዚያ መምህር በተዘዋዋሪ ደመወዝ ይከፈለዋል ማለት ነው። በቀጥታ ካሹን ስላማይቀበል ላይገባው ይችላል። ግን ደመወዝ ማለት ነው። ብሔራዊ ጥቅም ማለት በግለሰብ የሚመነዘር ጥቅም ብቻ ሳይሆን ኮለክቲቭ ጥቅም ስለሆነ ነው።
ያ ልጅሳ የሚማረው እየተጫወተ ነው። ፈተና የለበትም፤ ኤክስ እና ራይት የለበትም። ኤ ቢ ሲ ዲ የሚያጠናውም እየዘለለ ነው፤ እየዘፈነ ነው። ከልጆች ጋር እንዴት እንደሚውል ያውቃል። መደማመጥን ይማራል፤ ኤ ቢ ሲ ዲ ይማራል፤ በጣም በርካታ ነገሮች በዚያ ሒደት ውስጥ ሁለት ዓመት ሦስት ዓመት ተምሮ አንደኛ ክፍል ሲገባ፤ ኤ ቢ ሲ ዲ እንግዳው አይደለም፤ አስተማሪ እንግዳው አይደለም፤ ከሌሎች ሠፈር ልጆች ጋር መዋል እንግዳው አይደለም።
ባለፈው የነበረበት ዓይነት ሳይኮሎጂካል ሃራስመንት ዜሮ ባይሆንም በከፍተኛ ደረጃ ይቀንስለታል። እዚያም ኢሌመንታሪ ላይ የሚሠራው ሥራ አለ። ያ ብቻውን በቂ አይደለም ዜሮ ለማድረግ። ግን ቢያንስ ቢያንስ ከሰው ጋር የተለማመደ ልጅ ይፈጠራል። አሁን አዲስ አበባ ላይ አንዳንድ ጥናቶች እንደሚያሳዩት በአንድ ጊቢ ውስጥ የሚያድጉ ብዙ ከጎረቤት ጋር የማይጫወቱ፣ በእኛ የተለምዶ አባባል የተሻለ ቤተሰብ የተሻለ ኢንካም ያለው ቤተሰብ ልጆች የሚባሉት ከፍተኛ የሆነ የኮሙኒኬሽን ችግር አለባቸው። ከፍተኛ የሆነ የኢሞሽናል ኢንተለጀንስ ችግር አለባቸው። ሰው ጋ ረዥም ጊዜ ተቀምጠው ሊያወሩ አይችሉም።
ሀብታሞች ልጆቻቸውን ለቲቪ ሰጥተው፣ ለሠራተኛ ሰጥተው፣ ለጊቢ ሰጥተው ከሔዱ ከሰው ጋር እንዴት ሃሳብ እንደሚቀያየሩ የማያውቅ ልጅ ከሆነ ነጋዴም ቢሆን መንግሥትም ቢሆን ምንም ቢሆን ያ ሰው ከሰው ጋር ስለሚሠራ የኋላ ኋላ ስብራት መሆኑ አይቀርም። 36 ፐርሰንት መምህራን ጨምረን አሁን በመቶ ሺህዎች መምህራን ካልጨመርን በስተቀረ በኢርሊ ቻይልድ ሁድ የምንሠራው ሥራ የተሟላ አይሆንም። ለመገንባት፣ ለቁሳቁስ፣ ለመምህራን ደመወዝ ምን ያክል እንደሚወጣ አስዩም።
ጤና ባለፉት ስድስት ሰባት ዓመታት 53 ፐርሰንት የጤና ሙያተኞች ጨምረናል። ከነበረን ጤና ሙያተኛ 53 ፐርሰንት ጭማሪ ተጨምሯል። ለምን? በየሠፈሩ ጤና ኬላዎች በብቃት ስላልነበሩ፤ ወይም ሐኪም ስላልነበረ፤ ያን ካላስፋፋን በቀር ያሉን የሕክምና መስጫ ጣቢያዎች አሁን ያለውን ፖፑሌሽን ማገዝ አይችሉም። በዚህ የሕክምና ሙያ ላይ የሚሠራ ሰው ደመወዝ በቀጥታ ያገኛል ብትይኝ ላያገኝ ይችላል።
ግን በቀን 50 ሰው 20 ሰው የሚያይ ከነበረ በተወሰነ ደረጃ በየቦታው የሚያግዙ ሰዎች ሲፈጠሩ ያ ቁጥር ይቀንሳል ማለት ነው። ያ ቁጥር ቀነሰ ማለት ሁለተኛ ሰው የሥራ ዕድል አገኘ ማለት ነው። ያ ቁጥር ቀነሰ ማለት ብዙ ነገር ለማድረግ ብዙ ጊዜ አገኘ ማለት ነው። ይኼ በቁጥር ያለው ዕድገት ነው። በየዓመቱ 21 ፐርሰንት ጨመረ ስልሽ፤ 21 ፐርሰንት ገንዘብ ኪሳችን ገባ ላይሆን ይችላል። ግን ተጨማሪ ተቋም ስንገነባ የሠፋ ነገር አለ። ተቋም ባንገነባ ኖሮ የማይመጣ ውጤት አለ።
ዘንድሮ ሪፎርሙን ስንሠራ ደመወዝ ጭማሪ ያስፈልጋል፤ ሰዎች ይቸገራሉ ብለን እንደ መንግሥት 91 ቢሊዮን ብር ነው የጨመርነው በዘንድሮው ሰባት ወር ሥምንት ወር ገደማ 91 ቢሊዮን ብር ጨምረናል። አጨማመራችን ላይ የኢትዮጵያ መንግሥት ሠራተኛ እስከ ዛሬ በነበረው ሁኔታ ከታች ያለው አንድ ሺህ ምናምን የሚያገኙ ሰዎች አሉ እዚህ ፕራይሚኒስትር ኦፊስ የሚሠሩ። የ 1200፣ 1300 ደመወዝተኞች አሉ በየቦታው አሉ እንደዚህ።
እንደ ሀገር ሚኒመም ዌይጅ አልሠራንም። እንደ ሀገር ቢያንስ ግን በመንግሥት እንጀምር ሰው አንድ ሺህ ብር እየበላ አንዱ ልጆችም ስላሉት መኖር ስለሚቸገር፤ ከላይ ያለውን እናሳንሰውና በትክክለኛው የደመወዝ ጭማሪ መጠን ከሔድን ታች እያነሰ ላይ ከፍ ከፍ እያለ ነው የሚሔደው በፐርሰንት የምንሔድ ስለሆነ። ያን እንገልብጠው ታች ያለው ሰው ትንሽ ኑሮውን ከፍ እናድርግለት ብለን ከአንድ ሺህ ምናምን ሚኒመም የሚባለውን የመንግሥት ክፍያ አራት ሺህ ስምንት መቶ አስገብተናል፤ ሚኒመም የሚባለውን።
አሁን ከመንግሥት ጨርሰን ወደ ግሉ እንመጣለን፤ እየተዘጋጀን ነው ያለነው። አራት ሺህ ስምንት መቶ ስናስገባ ዝቅተኛ ኢንካም የነበራቸው ደሞዝተኞች ሶስት መቶ ፐርሰንት ጭማሪ መጥቶላቸዋል ። በደሞዛቸው ላይ። ላይ ግን ፐርሰንቴጁ ያንሳል። ለምን አነሰ 91 ቢሊዮን ብር በዓመት ኢንጀክት ከማድረግ በላይ ኢትዮጵያ አቅም የላትም።
ለምን ቅድም ያልኳት ናታ ኢትዮጵያ። 91 ቢሊዮንም ብዙ አምጣ ብዙ ነገር ቀናንሳ ነው ያደረገችው። ከዚያ በላይ ቢጨመር ጠቃሚ ነበር! በጣም ጠቃሚ ነበር። የኢትዮጵያ ደሞዝ በቂ አይደለም፤ የእኔ ደሞዝ በቂ አይደለም። ግን በእንድ በኩል ስብራት እንጠግናለን፤ በሌላ በኩል ለትውልድ ሀገር እንሠራለን ሰም ሀው መሥዋዕት ካልከፈልን በስተቀረ የምናስበውን ነገር ልናሳካ አንችልም።
አሁን ዘንድሮ የፌዴራል መንግሥት ሠራተኛ የፌዴራል መንግሥት ደሞዝ የሚከፍለው 450 ቢሊዮን ብር በልጧል። ከምናስገባው ገቢ፣ ኖት ዓምና ዘንድሮ ከምናስገባው ገቢ ግማሹ የሚውለው ለደሞዝ ነው። 900 ገደማ ቢሊዮን ገቢ እንጠብቃለን ግማሹ ደሞዝ ነው።
በቀረው ግማሹ ነው እንግዲህ ማንኛውም ነገር የሚሆነው። ሰው ደሞዝ ላይ ጥያቄ እንደሚያነሳው ደሞዙን ብትሰሪለት ብታስተካክይለት ደሞዝ ብቻውን ምን ያደርግልኛል ጠመኔ ያስፈልገኛል፤ ኮምፒተር ያስፈልገኛል ማለቱ አይቀርም ለማስተማር ወረቀት ያስፈልገኛል ማለቱ አይቀርም ሀኪምም ቢሆን መድሃኒት ማለቱ አይቀርም።
እነርሱን ሰፖርት ማድረግ ይኖርብናል። ይሄ በተወሳሰበ ችግር ውስጥ ያለ ሀገር የተከማቸ በሽታ እና ኢንፌሽክን ያለው ሀገር በአንድ ጊዜ ያንን ጉዳይ ሰብሮ መውጣት ስለሚያስቸግር ፋውንዴሽናል ሥራዎችን እየሠራን በሂደት ደግሞ በየደረጃው እየፈታን እየፈታን መሄድ ይጠበቃል።
ለምንድነው እንደዚያ የሚሆነው ኑሮ ውድነትን ማስተካከልና ዕድገትን ደግሞ አብሮ ማምጣት ማለት አውሮፕላን እየበረረ መጠገን ማለት ነው። መኪና እየተንቀሳቀሰ እየተጓዘ መጠገን ማለት ነው። ለመጠገን መቆም አለበት፤ ካልቆመ በቀር መጠገን አይቻልም። ለምሳሌ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ፕሮጀክት በሙሉ ብንገታ ምንም ጥርጥር የለውም ኢንፍሌሽን ድሮፕ ያደርጋል።
ህዳሴን ሁለት ዓመት እናቆየው ብልን ድሮፕ ያደርጋል ኢንፍሌሽን። ከፍተኛ ሀብት ኢንጄስት ስለሚደረግበት። ያ ማለት ግን ዛሬ ለምንኖረው ኑሮ ነገ ላለን ዲማንድ መልስ ሊያመጣ ስለማይዘጋጅ የአንድ ሳምንት እፎይታ ነው፤ አንቲ ፔይን ነው። ወዲያው በሽታው አገርሽቶ ሊመጣ ይችላል።
እያደግን ነው ኢንፍሌሽን ለመግራት ያለነው፤ እድገትነቱስ አለ ወይ ባለፈው ስድስት ዓመታት ኢትዮጵያ ውስጥ፤ እንዲህ ስድስት ሰባት ዓመታት የምለው ኮሮናውን ጨምሬ ውጊያውን ጨምሮ ነው እንጂ እነርሱ ከወጡ ስድስት ሰባት ዓመትም አልሞላም። ግን እነርሱን ደምረን ስናይ ዕድገት አለ ወይ ያልን እንደሆነ እውነቱን ለመናገር የኢትዮጵያ ሕዝብ ዓይኑ እንዲገለጥለት ልቦናው እንድከፈት ያገኘውን መልካም ዕድል ያገኘውን የተከፈተ ብርሃን በማስተዋል እንዲጠቀምበት ከከፍተኛ ማሳሰቢያ ጭምር ነው አሁን የማነሳውን ሃሳብ የማነሳው።
ኢትዮጵያ ውስጥ እድገት ሳይሆን ሚራክል ነው ያለው፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ለውጥ ሳይሆን እኛ ለውጥ ልናመጣ ያሰብን ሰዎች ካሰብነው ፍጥነትና ጥራት በላይ ነው ለውጥ እየመጣ ያለው። ይሄን እድገት በተገለጠ ዓይን ማየት ካልቻልን፣ መደገፍ ካልቻልን መጠበቅ ካልቻልን አደገኛ ጣጣ እና መከራ ሊያጣብን ይችላል።
ጥቂት እንዲኬተርስ ብቻ ላንሳ፤ ብዙ ሰው የማያስተውለው ግን ሚራክል ተብሎ የሚሰወድ አንዳንድ ኢንዲኬተር ላንሳ፤ በነገራችን ላይ በዚህ ዓመት ዓመቱን ስንጀምር የኢትዮጵያ የማንሰራራት ዓመት ነው ብዬ ነበር። ዘንድሮ ከፍተኛ የማንሰራራት ዓመት ነው፤ ዘንድሮ አራት አምስት አሥር ዓመት ከደገመች ኢትዮጵያ አበቃ! መከራዋ አበቃ! ዘንድሮ መደጋገም ግን የጋራ ራዕይ፣ የጋራ ጥረት፣ የጋራ ሥራ ነው። ዘንድሮ ምንድነው የተለየው ነገር እንዲህ በኩራት በእምነት የምትናገርለት እንጠብቀውና እናስፋው የምትለው የሚል ጥያቄ ማንኛውም ጤነኛ ሰው ሊያነሳ ይችላል።
ዘንድሮን ለመረዳት ኤክስፖርትን ብቻ እንመልከት፤ ኤክስፖርት ማለት ኢትዮጵያ አምርታ ለውጭ ገበያ አውላ ከውጭ ዶላር የምታገኝበት መስክ ማለት ነው። ከ1983፣ 1984 አይደለም 84 እስከ 98 ያለው አሥራ አምስት ዓመት 84 85 እያልሽ ቆጥረሽ 98ን ስጨምሪ 15 ዓመት ከ84 እስከ 98 ባለው 15 ዓመት ውስጥ ኢትዮጵያ ለውጭ ገበያ ኤክስፖርት አድርጋ ያገኘችው ሀብት 7 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ነው።
የአንድ ዓመት አይደለም፤ የ 15 ዓመት! 7 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር በ 15 ዓመት ነው ያመጣችው፤ መቼ ከ84 እስከ 98። ይሄ ዘመን ብዙ ጉዳይ ያየንበት ዘመን ነው፤ የኢትዮ ኤርትራ ጦርነት 90 የነበረበት፣ የ97 ምርጫ የነበረበት፣ ብዙ ሰው የሚያወራለት ኢንዲዴንት የነበረበት ዘመን ነው፤ እሱን ጨምሮ ነው፤ ከ84 እስከ 98 ባለው ጊዜ ውስጥ ኢትዮጵያ ለውጭ ገበያ አቅርባ ያገኘችው የዶላር መጠን 7 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ነው። ዘንድሮ በአንድ ዓመት ከ8 ቢሊዮን በላይ ገደማ ዶላር ከኤክስፖርት ታገኛለች።
በአንድ ዓመት 8 ቢሊዮን በላይ ዶላር የምታገኝ ሀገር 15 ዓመት ሙሉ ምን ትሠራ ነበር ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል፤ አዕምሮ ያስፈልጋል። ማስተዋል ያስፈልጋል፤ በተገለጠ ልቦና ማየት ያስፈልጋል። ያ 15 ዓመት እንደዚህ አይነት ተዓምር ሰርተንበት ቢሆን ኖሮ ዛሬ የት እንሆን ነበር ብሎ በቁጭት መንፈስ መለወጥን ይጠይቃል።
15 ዓመት 7 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዳላር ኤክስፖርት ያደረገች ሀገር በአንድ ዓመት ውስጥ 8 ቢሊዮን በላይ ዶላር ኤክስፖርት አድርጋለች። ከምንድነው ያገኘችው የሚለውን ደግሞ እንመልከት፤ የሚተሳሰር ጉዳይ ስላለው፤ ለምሳሌ ቡና ከ 84 እስከ 98 በ 15 ዓመት ጊዜ ውስጥ 3 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ነው የሸጠችው ኢትዮጵያ፤ 15 ዓመት 5 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር! ዘንድሮ በአንድ ዓመት 2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ሸጣለች።
ምን ማለት ነው 2 ዓመት ውስጥ 5 ቢሊዮን ብትሸጥ በ15 ዓመት ውስጥ ከሸጠችው በብዙ የበለጠ ማለት ነው። ቡና ነው ያልኩት፤ ከየት መጣ ይሄ፤ ተክለን ነው፣ ደክመን ነው ያመጣነው፤ በዋዛ የመጣ አይደለም፤ በቢሊዮን ተክለን፣ ተንከባክበን፣ ቡናው ሪስፖንድ አድርጎ ነው ዛሬ ለዓለም ገበያ የምናቀርበው ቡና በመጠንም በሚያስገባው ገቢም ያደገው።
ኢማጂን በአንድ ዓመት 2 ነጥብ 5 ቢሊዮን እና በ15 ዓመት 3 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዲፍረንስ አለው፤ ከዚህ ወዲያ ማንሰራራት ከየት ይመጣል። ይሄን መደጋገሙ ነው የሚያስፈልገው። ወርቅን እንመልከት፤ ወርቅ አስደማሚ ነው ባይ ዘ ዌይ፤ አንዱ ይቺ ምድር ስብ አላት፣ ይቺ ምድር ሀብት አላት ይቺ ምድር የተከማቸ የተደበቀ ሀብት አላት፣ ጥያቄ የለውም፤ ያንን መንዝረን መጠቀም የሁላችንም ቅዠት፣ የሁላችንም ምኞት፣ የሁላችንም ጸሎት ነው።
ከ84 እስከ 98 ባለው 15 ዓመት ጊዜ ውስጥ ኢትዮጵያ ወርቅ ኤክስፖርት አድርጋ ያገኘችው 508 ሚሊዮን ዶላር ነው፤ 508 ሚሊዮን ዶላር በ15 ዓመት! ዘንድሮስ! በአንድ ዓመት 3 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር አግኝታለች፤ ስንት እጥፍ 6 እጥፍ! በአንድ ዓመት ያመጣነው የወርቅ ዋጋ በ15 ዓመት ካመጣነው 6 እጥፍ አደገ ማለት ማንሰራራት ካልተባለ ምን ማንሰራራት ይባላል ታዲያ! 15 ዓመት የባከነውን ጊዜ አስቡት! ይሄንን ውጤት አምስት ዓመት ከደገምን ምን እንደሚያመጣ መገመት ለማንም አይከብድም።
ይሄ ኤክስፖርት ነው፤ ሌሎችን አስደማሚ አስደማሚ ዳታዎች በየቦታው ላነሳልሽ እችላለሁ። ኢትዮጵያ ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ በዓይን የሚታይ የሚጨበጥ፣ የሚዳሰስ ለውጥ አለ፤ ማንም ሰው ካለበት ሰፈር በገጠርም በከተማም 5 ኪሎ ሜትር ቢነዳ ቢንቀሳቀስ ለውጥ ያያል። የሚታይ ነው።
ይሄን ለውጥ ግን የጎደለውን እየሞላን፣ ሰስቴይን አድርገን ለልጆቻችን አስተማማኝ ፋውንዴሽን መጣል የኔም የአንችም፣ የእሱም የእሷም የጋራ ዕዳ ነው። አንዱ ጥያቄ አንዱ መላሽ ሳይሆን የጋራ ዕዳ ነው። ማድረግ አለብን፣ መጨከን አለብን፣ መድከም አለብን፣ ዋጋ መክፈል አለብን፣ ለማን ልልጆቻችን! ሳንደክም የሚመጣ ውጤት የለም።
ይሄን የመሰለ ዕድገት እያመጣ ኢኳሊ ኢንፍሌሽን ከ30 ምናምን ገደማ 13 ነጥብ 5 ወርዷል በዚህ ዓመት ከግማሽ በታች አውርደነዋል፤ ኢንፍሌሽን ከ34 13 ነጥብ 5 ወርዶ፤ ኤክስፖርት፣ ገቢ፣ ድህነት ቅነሳ፣ የዕዳ ውዝፍ ከጂ ዲ ፒያችን አንፃር ዲክላይን ማድረጉ ኢትዮጵያ በብዙ መንገድ ከነበረባት በሽታ ብቻ ሳይሆን ከኢንፍሌሽኑም በማገገም ላይ እንደሆነች ያሳያል።
ድና ጨርሳለች ወይ አልጨረሰችም፤ እንዲህ በዋዛ ድና የምትጨርሰው ጉዳይ አይደለም ስብራቱ ብዙ ስለሆነ ፤ ግን የመዳን መንገድ ላይ ነው ወይ ያለችው ምንም ጥያቄ ምንም ጥርጥር የለውም። ጥርጥር የለውም! የገነባናቸው፣ የሰራናቸው፣ ያሳካናቸው የጨረስናቸው፣ የልጆቻችን ዕዳ የቀነስንበት ልክ ኢትዮጵያ በማገገም፣ በመዳን ላይ እንዳለች ማንም ሰው አስረጂ ሳይኖር ሊገነዘብ የሚችለው እውነት ነው፤ ሀቅ ነው፤ እውነትን ደግሞ በዚያ ልክ መቀበል ለማንም ሰው ተገቢ ይመስለኛል። ይሄ ሁለተኛው ነው።
ሦስተኛው ምዕራፍ ምንድነው ያልሽ እንደሆነ ባህል መገንባት ነው። ኤክስፖርት 8 ቢሊዮን ብለን፣ የዘንድሮን የምንፎክርበት ሳይሆን በሚቀጥለው መድገም አለብን። ቡና በሚቀጥለው መድገም አለብን፤ ኢንዱስትሪ መድገም አለብን፣ ማደግ አለብን፣ ባህል መሆን አለበት። ያ ባህል ሲሆን ያለው መዋዠቅ ይረጋጋል። ያለው የኑሮ ስቃይ፤ አይጠፋም ግን ይሰክናል። ኢንፍሌሽን ሙቪንግ ታርጌት ነው።
ቋሚ ታርጌት አይደለም፤ ቋሚ ታርጌት አንዴ አልመሽ ተኩሰሽ የምትመችው ነው። ኢንፍሌሽን ባህሪው እንደዚያ አይደለም። ይቀያየራል፤ የዋጋ ንረት ከልማት ጋር፣ ልማት ባለበት ሀገር ውስጥ ተንቀሳቃሽ ፈተና ነው፣ ተንቀሳቃሽ ታርጌት ነው፤ እየተከተሉ ለማጥፋት ኢቮልፍ የሚያደርግ ስትራቴጂ ያስፈልጋል። ከአዲስ መልክ ጋር የሚያድግ ስትራቴጂ ይጠይቃል።
ለሙቪንግ ታርጌት ቋሚ ዓላሚ አይሳካለትም፤ ለሙቪንግ ታርጌት ኢቮልፍ የሚያደርግ ስትራቴጂ የሚከተል ዓላሚ ግን ያገኘዋል። እኛ በሚንቀሳቀስ ታርጌት ውስጥ ያለን ፈተና አንድ ቦታ ቆመን ሳይሆን እያደግን፣ ኢቮልቭ እያደረግን እንፈታዋለን ብለን እናስባለን።
ይሄ ፈተና የመጣባቸው፣ ይሄ ችግር የመጣባቸው ጉዳይ እያንዳንዱ ቤተሰብ ማስተዋል ያለበት ግን ምንም ጥርጥር የለውም የኑሮ ዘያችን በግራም በቀኝም ተነካክቷል። በብዙ ማስረጃ ማሳየት እችላለሁ፣ በዚያ ምክንያት የሚፈተኑ ሰዎች አሉ፣ የሚቸገሩ ሰዎች አሉ። አሁን በቅርቡ ሐኪሞች ጥያቄ አንስተዋል፤ አብዛኛው ሐኪም ያነሳው ጥያቄ ሌጂትሜት ነው።
ምንም ጥያቄ የለውም ከደሞዝ ጋር የሚያያዝ ጥያቄ አለብን፤ ሌጂትሜት ነው። መምህሩም አለው ሊጂትሜት ነው፣ ሚዲያም አላችሁ ሌጅትሜት ነው፣ እኔም አለኝ ሌጂትሜት ነው፤ ስፔሻል አይደለም። ብዙዎቻችንን የሚነካ ነገር ነው። እንዴት እንፍታው ማስተዋል፣ መስከን፣ ማሰብ ይፈልጋል። ይሄን ደግሞ ለፖለቲካ ዓላማ መጠቀም የሚፈልጉ ሰዎች እንዳሉ ታይተዋል። ይሄንን ደግሞ ለማስተዋል ኢትዮጵያ አሁን እየተሻገረች ይመስለኛል። ለመገንዘብ ብዙ አስረጂ አያስፈልጋትም።
በጣም የሚያሳዝነው ነገር ፔሮል ላይ ፈርመው የማያውቁ፣ ደሞዝ በልተው የማያውቁ፣ የደሞዝን ጠቀሜታና ምንጭ በወጉ የማይረዱ ደሞዝ ጭማሪ እያሉ ሲጮሁ ይሰማል፤ መጀመሪያ ደሞዝ ለምን እንደሚፈለግ ማገልገልን መማር ያስፈልጋል፤ እና ሐኪሞች፣ አስተማሪዎች፣ ወታደሮች፣ ፖሊሶች፣ ሚኒስትሮች፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ሁላችንም የደሞዝ ጥያቄ አለብን። በሰከነ መንገድ አቅማችንን እያገናዘብን በሰከነ መንገድ ምላሽ መስጠት ያስፈልጋል። ይሄን ጉዳይ ግን ከስክነት፣ ከውይይት፣ ከምክክር ከየት እንደምናመጣው ከማሰብ ውጪ መልስ አይገኝለትም። እንዲሁ በጩኸት ብቻ መልስ አይገኝለትም።
ብንጮህና ብናበላሽስ እናጠፋዋለን እንጂ አናለማውም። የጀመርናትን ጭላንጭል እናወድማታለን እንጂ ውጤት አናመጣበትም። ለዚያም ሰክነን እንወያያለን፤ ዊን ዊን በሆነ አፕሮች፤ ሀገርን በማይጎዳ መንገድ መፍትሔ እያበጀንለት እንሄዳለን። ትክክለኛ ጥያቄ ከስሁት እሳቤዎች ጋር ሲቀላቀል ስሁቶችን እያጠፋን ትክክለኛውን ደግሞ ደረጃ በደረጃ እየመለስን ሙቪንግ ታርጌት ቢሆንም ሰም ሀው ያለውን መከራ እየቀነስን በመሄድ ኢኮኖሚውም እያደገ ኢንፍሌሽን የሚቀንስበትን መንገድ እንከተላለን ብዬ ነው የማስበው እኔ።
ኢቲቪ ፦ ኢትዮጵያ የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ትግበራዋን በቅርቡ ተቀላቅላለች። ይህን ሪፎርም ተከትሎ ግን የሚነሱ ትችቶች አሉ። ይህ ሪፎርም በተፅእኖ ውስጥ የመጣ ሪፎርም ነው እንጂ ኢትዮጵያዊ ሪፎርም አይደለም የሚሉ ሃሳቦች ይሰነዘራሉ። እዚህ ላይ እርስዎ ምን ይላሉ?
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)፦ ማንም ሰው ምግብ ከማዘዙ በፊት ሜኑ ማገላበጥ አለበት። ስለራበው ብቻ ሬስቶራንት ሄዶ ምግብ ምግብ አይልም። ወይ ሽሮ፣ ወይ ምስር፣ ወይ ቀይ ወጥ ይላል። ሜኑ ማየት አለበት። የተቸገረ ሰው ለችግሩ ማስታገሻ የሚሆነውን ነገር በሆነ ደረጃ ማወቅ አለበት። እኛ ኢኮኖሚክ ሪፎርም ኢትዮጵያ ያስፈልጋታል፤ ያለችበት ሁኔታ አደገኛ ነው ያልነው አይ ኤም ኤፍ ከሚባል ተቋም ጋር መነጋገር ሳንጀምር ነው።
በነገራችን ላይ ቢሮ ገብቼ የመጀመሪያው የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ስብሰባ ኢኮኖሚክ ኦፕን አፕ ይከፈት የሚል ነበር የመጀመሪያው ውይይት። በዛን ጊዜ እኔ አይ ኤም ኤፍ ጥቁር ይሁን ነጭ በአካል የማግኘት እድል አልነበረኝም። ሁለተኛ በመደመር መፅሃፍ ላይ ቁልጭ ብሎ ተቀምጧል። ኢኮኖሚያችን ተሳስሯል።
ገንዘብ ኦቨር ቫልዩድ ሆኖ ከዓለም ጋር ሊያገበያይ በማይችል መንገድ ታንቆ ኢንቨስትመንት በከፍተኛ ደረጃ እንዳይመጣ አድርጎ በተጨናነቀበት ሁኔታ የሆነ ነገር ካልተፍታታ በቀር ነገሩ እንደማይቀጥል ይታወቃል። እና በቀጥታ ከአይ ኤም ኤፍ ወይም ከዓለም ባንክ ጋር የሚያያዝ ጉዳይ ሳይሆን የእኛ ችግር፣ የእኛ መከራ ሜኑ ማገላበጥ ግድ ብሎት ነበር።
ሜኑ ስናገላብጥ ግን በአንዳንድ ሰው ባህሪይ ቀጥታ ከሜኑ ላይ አይቶ አያዝም። ሽሮ መርጦ እንደሆነ ‹‹ሽሯችሁ ግን እንዴት ነው››? ይላል። ሽሯችን እንደዚህ ነው፤ እንደዚያ ነው ይባላል። ከሽሮ ይልቅ ምስር ብታዝ ይባላል። ሽሯችን ያደረ ነው ትኩሱ ይሻልሃል ይባላል። ሜኑ ቢያይም፤ ሜኑ ቢያገላብጥም አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ደግሞ ምክርም ይጠይቃል።
እኛ መክፈት እንዳለብን ስናምን በጣም በስፋት ትምህርት ለመቅሰም ሞክረናል። ለምሳሌ በአፍሪካ ውስጥ ሪፎርም ከሠሩ ሀገራት መካከል ናይጄሪያ አንዷ ናት። ግብፅ ሁለተኛዋ ናት። ደቡብ ሱዳን ሶስተኛዋ ናት። ናይጄሪያና ግብፅ የተሻለ ኢኮኖሚና በንፅፅር ከፍ ያለ ጂ ዲ ፒ ያላቸው ናቸው። ደቡብ ሱዳን ደግሞ ዝቅ ያለ ኢኮኖሚ ያላት ናት።
እኛ ግን ከፍ ከፍ ካሉት ተምረን ዝቅ ያለችዋ አታስፈልገንም አላልንም። ሶስቱም ጋር ዴሊጌሽን ልከን እንዴት ጀመራችሁ፣ እንዴት ሰታችሁ፣ ምን ገጠማችሁ ብለን ከደቡብ ሱዳንም፣ ከግብፅም፣ ከናይጄሪያም ትምህርት ቀስመናል። ከእነርሱ ብቻ አይደለም ከአርጀንቲናም ተምረናል።
በርካታ በእኛ መሰል ችግር ውስጥ ኖረው ወደ ሪፎርም የገቡ ሀገራት ትምህርት ለመቅሰም ሙከራ አድርገናል። ከአይ ኤም ኤፍ ጋር ተወያይተናል። ከዓለም ባንክ ጋር ተወያይተናል። ከኢኮኖሚክ ማህበራት ጋር ተወያይተናል። በኢኮኖሚ ዙሪያ ትንታኔ ከሚሠሩ ተቋማትና ግለሰቦች ጋር ተወያይተናል። ከብዙ ሀገራት መሪዎች ጋር ተወያይተናል። ጥልቅ የሆነ ውይይት ተደርጎበታል።
ከዚያ ሰብስበን፣ ትምህርት ወስደን፣ የእኛን ችግር አገናዝበን ሀገር በቀል ሪፎርም አንድና ሁለት ብለን በሠራነው ላይ ነው የከፈትነው። ኮሮና ባይመጣ ኖሮ ይህ ጉዳይ ይቀድም ነበር። የሀገር በቀል ሪፎርም አጀንዳ እንደሚታወቀው ደሞዝ መክፈል አልቻልንም፣ ችግር አለብን 10 ቢሊዮን ዶላር ከዚም ከዚያም አምጥተን ኢኮኖሚውን ትንሽ ማስተንፈስ አለብን ነው።
አስተካክለነዋል። ያን ባናደርግ ኖሮማ ዛሬ መነጋገር አንችልም። ሀገር በቀል ሪፎርም ሁለት ላይ ስንደረስ ግን በዛ ልክ ሀብት ልናገኝ አልቻልንም ስለዚህ ሌላ መንገድ ይፈልጋል። የኢኮኖሚክ ኦፕን አፕ የተገባበት ዋና ምክንያት የታጨቀውን፣ የተሳሰረውንና የተቆላለፈውን ኢኮኖሚ ከፈትፈት አድርጎ በር ከፍቶ ነገሩን ለማየት ነው።
እኛ አንድም ቀን ሀገር በቀል ሪፎርም አጀንዳ ስንል፣ የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም ስንል የእኛ ሪፎርም ሀገር በቀል ነው ብለን አናውቅም። የሰው ትልቁ ችግር ይሄ ነው። ሀገር በቀል የሚባለው ልክ እንደጭላዳ ዝንጀሮ፣ እንደ ዋሊያ አይቤክስ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኝ ነገር ማለት ነው። የእኛ ሪፎርም ተጀምሮ እስኪያልቅ የእኛ ነው ማንም ሰው አልገባበትም ከማንም አልተማርንም ሀገር በቀል ነው አላልንም። ኢንዲጂኒየስ የሚባለው ግን ጥቁር አንበሳ ኢትዮጵያ ውስጥ አለ፤ ጥቁር አንበሳ ሱዳንም አለ። ጥቁር አንበሳ ኬንያም አለ።
የአፍሪካ ዝሆን የሚባል ኢትዮጵያም አለ፤ ሌሎች ሀገሮችም አለ። እነዚህ የአፍሪካ ዝሆኖች በሆነ በሆነ ነገር መልካቸው ምናምናቸው ልዩነት ያለው ሊሆን ይችላል። የተቀራረበ ግን የአፍሪካ ዝሆኖች ናቸው። ሀገር በቀል አይደሉም ኢንዲጂኒየስ ናቸው። እኛም ጋር አሉ፤ ኬንያም አሉ፤ ኡጋንዳም አሉ በየሀገሩ ከመልከአ ምድሩ ጋር የተዛመደ ለውጦች ይኖራቸዋል ግን የአፍሪካ ዝሆኞች አንድ ፋሚሊ ናቸው። እነዚህ ኢደጂኒየስ የሚባሉት የእንስሳት ዓይነቶች እኛጋም የሉ ሌላም ጋር ያሉ ሲሆኑ ማለት ነው።
ለምሳሌ ደግሞ ኤክሶቲክ የሚባል አለ። ከውጪ እንዳለ አምጥተን እኛ ጋር የምናደርገው። ባህር ዛፍ ለምሳሌ ኤክሶቲክ ነው ይባልል። ሀገር በቀል አይደለም። ከሌላ ሀገር መጥቶ የተተተከለ ነው። የእኛ ለውጥ ኤክሶቲክ አይደለም። ከሌላ ቦታ እንዳለ መጥቶ የተተከለ አይደለም። ኤክሶቲክ ቢሆን ይሄን ለውጥ አያመጣውም።
እንዳለ ከአይ ኤም ኤፍ ቀድተን፣ ከከበደ ቀድተን ብናመጣው አያመጣውም። ምክንያቱም አይ ኤም ኤፍ ስለ ኢትዮጵያ ያለው እውቀት ውስን ነው። የሚያውቀውን ያውቃል፤ በርካታ ጉዳዮችን ግን አያውቅም። ከእነሱ የምንቀዳው ባእድ ዛፍ ነው እንጂ ሀገር በቀል ዛፍ አይሆንም። የለም አይ ኤም ኤፍ ቢባል ድርሽ አይልም ይሄማ ሀገር በቀል ጭላዳ ዝንጀሮ ነው ካልንም የምንጠብቀው ሀብት ስላለ እኛ ጀምረን የምንጨርሰው ሀብት የለም፤ እሱም ስህተት ነው። ነገር ግን ኢንዲጂኒስ ነው። መሠረቱ የእኛ ነው፣ ፍላጎቱ የእኛ ነው ያውቃሉ በዛ መንገድ አልፈዋል ካልናቸው ሰዎች ደግሞ ትምህርት ተቀስሟል። ከራሳችን ፍላጎትና አቅም ተነስተን፣ ከሌሎች ተምረን የሠራነው ሥራ ነው።
ለምሳሌ አይ ኤም ኤፍን ብቻ ላንሳ የኢትዮጵያን ሪፎርም የእኛን ሃሳብ ከተቀበለ በኋላ አንዱ ያመጣው መከራከሪያ የኢትዮጵያ ሪፎርም 7 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ካገኘ ሊሠራ ይችላል። ሊከወን ይችላል፤ ሳትቸገሩ ማለፍ ትችላላችሁ ብሎ ነበር። የእኛ አቋም ግልፅ ነበር። አይሆንም 7 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር የእኛን ሪፎርም አይሠራውም። ለምን? በርካታ ሠራተኞቻችን ዝቅተኛ ደሞዝ ተከፋይ ናቸው። ደሞዝ ካልጨመርን በቀር ሪፎርሙ አደጋ ይገጥመዋል።
ባንካችን በተለይ ንግድ ባንክ የሚባለው መንግሥት በገፍ ሲበደር ቆይቶ መክፈል የማይችልበት ደረጃ ስለደረሰ በባንክና በመንግሥት መካከል ያለውን ግንኙነት በሕግ መምራት ስንጀምር ይህን ባንክ ካልታደገን በቀር ባንካችን ይወድቅብናል። ንግድ ባንክ ደግሞ የባንኮች ሁሉ አውራ ነው በኢትዮጵያ ውስጥ መታደግ አለብን። እንደዚህ እያልን በጣም በርካታ ጉዳዮችን አንስተን በእኛ ጥያቄና በእኛ ግፊት መሠረት 10 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ተስማምተን ነው የገባነው። በእነሱ ቢሆን 7 ነጥብ 5 ዶላር ነው። ይህስ በቂ ነው? በቂ አይደለም። ገና ተጨማሪ ሀብት ይፈልጋል። ለምን? በጣም በርካታ ጉዳዮች መደጎም ይፈልጋሉ።
በባለፈው ዓመት 350 ቢሊዮን ብር ገደማ የኢትዮጵያ መንግሥት ድጎማ አድርጓል። ነዳጅ እንደጉማለን፣ መድሃኒት እንደጉማለን፣ ሴፍቲኔት እንደጉማለን፣ ማዳበሪያ እንደጉማለን። ሰው እንደሚያስበው አይደለም። ብዙ ነገር ተደጉሞ ነው የሚሄደው። ያንን ድጎማ በዘለቄታው ለማስቀጠል ኢትዮጵያ ያላት አቅምና ገቢ መታየት አለበት በሚል ንግግር አድርገን 10 ነጥብ 5፤ 3 ነጥብ 5ቱን ከአይ ኤም ኤፍ፣ 3 ነጥብ 5ቱን ከዓለም ባንክ 3 ነጥብ 5ቱን ደግሞ የእኛን እዳ በማስተካከል ክሬዲተርስ ኮሚቴ የሚባሉ አሉ ፈረንሳይና ቻይና የመሩት በእነሱ አማካኝነት እዳችን ተሸጋሽጎ ያን በገፍ ስንበደረው የነበረው እዳ ተቆልሎ እንዳይሸጋገርብን በሚቀንስ መልኩ ምን ማለት ነው እዳ ባይስተካከል 2 ቢሊዮን መክፈል ከነበረብን ሪስትራክቸር ሲሆን 1 እና 1 ነጥብ 5 እንከፍላለን ማለት ነው። ወዲያው ነው ምላሹ።
ይህን ተደራድረን፣ ተጨቃጭቀን በብዙ ውጣውረድ ውስጥ ነው የተወሰነው። ከተወሰነ በኋላስ? በኤክስፖርት፣ በገቢ፣ በኢንፍሌሽን ባመጣነው ውጤት ብቻ አይደለም። በቅርቡ በዋሽግተን የዓለም ባንክና አይ ኤም ኤፍ ዓመታዊ ስብሰባ ነበር። በዚህ ዓመታዊ ስብሰባ አይ ኤም ኤፍና ዓለም ባንክም፤ ሌሎች ሀገራትም የአፍሪካ ሀገራትም በአንድ ድምፅ ያወደሱት የኢትዮጵያን ሪፎርም ነው።
ለምን? በጣም በእውቀትና በጥበብ በማስተዋል በምክር ነው የተመራው። በጣም የተሳካ ሪፎርም ነው የተባለው። በእነሱም ዓይን በእኛም ዓይን። የአስራ አምስት ዓመታቱን ኤክስፖርት በዓመት ያመጣነው በሪፎርሙ ነው። አልሠራም የሚባለው ያ ባይሆን ኖሮ ነው። ከአይ ኤም ኤፍ የቀዳነው ኤሶቲክ ቢሆን ኖሮ ደግሞ በዚህ ልክ ውጤት መምጣቱን እጠራጠራለሁ። ምክንያቱም የእኛን ሁኔታ ከእኛ በላይ ስለማያውቁ።
የኢትዮጵያ ኤሊት በጥቅሉ ላለፉት ሃምሳ፣ ስልሳ፣ ሰባና ሰማንያ ዓመታት የኢትዮጵያን መደህየት፣ የኢትዮጵያን ማነስ፣ የኢትዮጵያን መቸገር ሲያዩ በተለይ ወጣ ብለው ሲያዩ አይቆጩም፤ አይንገበገቡም ማለት እኮ አይደለም። ሁሌ ይቆጫሉ። ጃፓን ሄደው ካዩ በኋላ ‹‹ጃፓን እንደምን ሰለጠነች›› ይላሉ። ያስባሉ፣ ያሰላስላሉ፣ ይፅፋሉ ያስተምራሉ።
እንዳንዶች አውሮፓ ሄደው፣ አሜሪካን ሄደው፣ አንዳንዶች ደቡበ አፍሪካ ሄደው ቀንተው ይመለሳሉ። ነገር ግን ጃፓን እንደምን ሰለጠነች፣ ፈረንሳይ እንደምን ሰለጠነች፣ ሲንጋፖር እንደምን ሰለጠነችን ማወቅ አስፈላጊ ቢሆንም ኢትዮጵያ ስለምን ደኸየችን አውቀን እስካልመለስን ድረስ ውጤት አያመጣም።
ኢትዮጵያ ስለምን ደኸየች ምንድን ነው ባህሏ፣ ምንድን ነው እምነቷ፣ ማህበራዊ ስሪቷ ምን ይመስላል፣ ሶሻል ካፒታሏ ምን ይመስላል፣ ማህበራዊ መስተጋብሮቿ ለልማት አስቻይ ናቸው ወይስ ጎጂ ናቸው የሚለውን በጥልቀት መመርመር ይፈልጋል። የእኛ ባህል ከጃፓን ባህል፣ የእኛ እምነት ከጃፓን እምነት የእኛ ሥነልቦናዊ ስሪት ከእነርሱ ስሪት ስለሚለያይ ለአንድ ራእይ፣ ለአንድ ሃሳብ የምንሰጠው ምላሽ አንድ አይደለም።
ምላሻችን አንድ ካልሆነ ደግሞ ውጤቱ አንድ ሊሆን አይችልም። ጃፓንም ትሁን እንግሊዝ እንደምን ሰለጠነችን የኢትዮጵያ ምሁራን ሳይጠይቁ ቀርተው አያውቁም። ክፍተት የነበረውና እኛ ልንሞላ የሞከርነው ኢትዮጵያ ስለምን ደኸየች ለምሳሌ እንዴት መሬት እያላት በዓመት አንዴ ብቻ ታርሳለች? ሁለቴ ለምን አይሆንም? እንዴት ኢትዮጵያ ትለምናለች? የሚለውን ጥያቄ አንስተን ከውጪ የተማርነውንም የእኛንም አዋህደን መሥራት በመጀመራችን በጣም የሚታይ ውጤት ማየት ጀምረናል።
ይህ መርህ ተኮር ፕራግማቲስት ስለሆነ ፣ የእኛ አሠራር በፕራግማቲዝም የተሞላ ስለሆነ፣ ከእኛ ሁኔታ ስንነሳ፣ ከእኛ ሁኔታ ስንማር፣ ከእኛ ችግር ስንነሳ ከሌሎች አንማርም ብለን አንዘጋም። ከሌሎች ጠቃሚ ነገር ካለ ለእኛ ጉዞ የሚያግዝ ነገር ካለ ትምህርት እንወስዳለን።
ነገር ግን የምንማረው ጉዳይ በእኛ ልክ የተሰፋ ነው። በምንማራቸው ተቋማትና ግለሰቦች ልክ ተሰፋ አይደለም። ለምሳሌ አይ ኤም ኤፍ ይሄ ሪፎርም የእኔ ነው ብሎ አይጠይቅም በእርግጠኝነት። እንዴት እንደጀመርነው ያውቃል። እንዴት እንደሠራነው፣ እንዴት አፕሮች እንዳደረግን፣ ቴክኒካል ደረጃ እንዴት መግባባት አቅቶን በመሪ ደረጃ እንዴት ኢንጌጅ እንዳደረግን ያውቃል አይ ኤም ኤፍ።
ክሌም አያደርግም። ባለቤቱ እኛ ሆነን ስናበቃ ከውጪ መማራችን እኛ እየተናገርን ማን ነው ከእኛ ጋር ሳይሠራ ይሄ ሪፎርም የእናንተ አይደለም የሚለን። የት ነበር እዚህ ሪፎርሙ ሲሠራ? የት ነበር ስንጨቃጨቅ?፣ የት ነበር ስንነጋገር? ዝም ብለን የማናውቀውን ነገር አንስተን እፍታ መልቀቅ ይቻላል። እውነት ግን አይደለም። ይህ ሪፎርም ከኢትዮጵያ ሁኔታ የተነሳ ከሌሎች የተማርን በእኛ ልክ የተሰፋ ሪፎርም ነው። ውጤት ያመጣውም ለዚሁ ነው።
በዚሁ አግባብ ማየት ያስፈልጋል። ከማንም አልተነማርንም ብለን አንመፃደቅም። በርካታ ትምህርቶች፣ ድጋፎች አግኝተናል። በነዚያ ትምህርቶችና ድጋፎች ደግሞ ተውጠን የእኛን አቋሞች ትተናል አንልም። አቋሞቻችንን ጠብቀን ነው ውጤት ያመጣነውና በዚያ ሚዛን ቢታይ ጠቃሚ ይመስለኛል።
ኢቲቪ፦ በኢኮኖሚው ውስጥ የመንግሥት የትኩረት አቅጣጫ ወደ አገልግሎቱ ያደላ ነው ለማኒዩፋክቸሪንግ እምብዛም ትኩረት የሰጠ አይደለም የሚሉ ሃሳቦች ይነሳሉ። እውነትነት አላቸው?
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)፦ አጭሩ መልስ የላቸውም ነው። ግን የላቸውም በቂ መልስ አይደለም። እንዴት እንደሌላቸው ማስረዳት ያስእፈልጋል። ፕራዮሪቲ ስንለይ የኢትዮጵያን ችግር አገላብጠን ለመፈተሽ ከሞከርን በኋላ ፕራዮሪቲ ስንለይ በየትኛው መስክ ብንሸራ ይሳካልናል፣ በየትኛው መስክ በአጠረ ጊዜ ውጤት ይመጣል፣ በየትኛው መስክ በመካከለኛ ጊዜ ውጤት ይመጣል ብለን በክፍል፤ በምእራፍ ከፍለን ነው ያየነው።
ጄኔሪክ እውቀቶች አሉ። ኢትዮጵያም የምትመካበት፤ አፍሪካም የምትመካበት ወይም ሁሉም ሰው በእኩል የሚናገራቸው አድቫንቴጅ ተብለው የሚወሰዱ ጉዳዮች ነበሩ። መረመርናቸውና እነዛን አድቫንተጆች እነዛ ናቸው ወይ ብለን መረመርናቸው። ለምሳሌ በየትኛውም ዓለም ብንሄድ፣ በየትኛው ሰሚት ብንሄድ ትልቁም ትንሹም፤ የሚያውቀውም የማያውቀውም አፍሪካ ርካሽ ጉልበት አላት፣ አፍሪካ አብዛኛው ሰው ወጣት ነው።
ይሄ ወጣት ይሄ ጉልበት አንድ ለልማት አስቻይ አቅም ሆኖ ይሠራል። እንደ አንድቫንቴጅ ይወሰዳል የሚል የጋራ እውነት አለ። ሁሉም ሰው የሚናገረው እውቀት አለ። እኛ ጠየቅን ይሄን እውነት ነው ወይ ብለን። ርካሽ ጉልበት አለ ወይ? ሁለተኛ ይሄ ርካሽ ጉልበት የተባለው፣ አፍላ ጉልበት የተባለው ምን ያክል ይዘልቃል? ኤ አይ እየመጣ ነው፣ ሮቦቲክስ አለ፣ አንድ ሰው የሚሠራውን ሮቦት እየሠራ ነው፣ በዚህ ጉልበት ተመጻድቀን ስንት ዓመት ልንቆይ እንችላለን? ይህንን ጉዳይ እንደ አቅም እንደ አድቫንቴጅ ማየት ኢትዮጵያ ያዋጣታል ወይ? አያዋጣትም።
የምንመካበት የጉልበት ጉዳይ በሮቦት ከተተካ ሊያወዳድረን አይችልም። እሱ ብቻ ደግሞ አይደለም፤ ይሄ ጉልበት የተባለውስ መያዝ እንችላለን ወይ? ለመያዝ አቅም አለን? እናስተምረዋለን፣ ትምህርት በነጻ ነው ኢትዮጵያ ውስጥ። አንድ ሰው ዶክተር እስከሚሆን ድረስ በነጻ ይማራል። ዶክተሩ በተመረቀ ማግስት በኋላ ግን የኢትዮጵያ መንግሥት፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ በነጻ አስተምሬሃለሁና ክፈለኝ ልያዝህ የሚልበት መንገድ የለውም ወደ ፈለገበት ገበያ ወዳዋጣው እግሩ ወደመራው ሄዶ ይሠራል።
የተሻለ የሚከፍሉ ሰዎች ይሄ ረከሰ የተባለውን ጉልበት በቀላሉ ያው አንፈልግህም አትምጣብን፣ ቪዛ አንሰጥህም እየተባሉ እየተለመኑ ባህር እያቋረጥን አገልግሎት እንሰጣቸዋለን። እና ይሄ ጉዳይ አስተማማኝ፣ አድቫንቴጅ መወዳደሪያ አቅም አለ እንፈትሸው አልን። የተለመደው እውነት ግን እሱ አነበረም። ለአይ ኤም ኤፍ ርካሽ ጉልበት ያልኩት ትክክል አይደለም ኤ አይ እየመጣ ነው ብለው ላይቀበለኝ ይችላል።
እኔም ከራሴ ጥቅም አንጻር ፈትሼዋለሁ። ሁለተኛው ጥሬ እቃ ነው። አፍሪካ በገፍ ጥሬ እቃ አላት። ተዝቆ የማያልቅ ሀብት አላት የሚል ንግገር ሁሉም ሰው ይናገራል። ልንወዳደርበት ያስችለናል ወይ? እውነት ነው ወይ ብለን መርምረናል። ለምሳሌ አይረን ኦር አፍሪካ ውስጥ በስፋት አለ፤ እውነት ነው ይሄ። ግን ዓለም ላይ ያለው የብረት ክምችት፣ ይሄ ስክራብ የሚባለው፣ ከዚህ ቀደም ጥቅም ላይ የዋለው፣ መልሶ ቀልጦ ተጨፍልቆ ሪዩዝ የሚደረገው። ብረት በጣም ብዙ ነው፣ ስክራብ ገዝተው እሱን ጨፍልቀው፣ በሚፈለገው ሞዳይት ሠርተው ኤክስፖርት የሚያደርጉ አካላት አሉ። አይረን ኦር የሌላቸው፣ ብረት የሚባል የማያመርቱ፣ ስክራቡን ብቻ ሰብስበው ኤክስፖርት የሚያደርጉ አሉ።
እኛ የምንመካበት የጥሬ እቃ ጉዳይ አሁን ሪዩዝ ማድረግ ከተጀመረበት ሥርዓት አንጻር ምን ያክል ሊያወዳድረን ይችላል? እንዲያውም ከሱ አለፍ ብለን እንይ እስቲ፤ ለመሆኑ ወርቅ አፍሪካ ነው ከአፍሪካ ውጪ ነው ያለው? የምንመካበት አንዱ ሀብት እሱ ነውና የት ነው ያለው? እና እነዚህን ጥሬ እቃዎች ለመስታወትም ይሁን ለብረት፣ ለላስቲክም ይሁን ለወረቀት ግብዓት ለመሆን የሚችል ጥሬ እቃ አፍሪካ ውስጥ እንዳለ ቢታመንም ቀድሞ የወጣው ሀብት ግን በሪዩዝ በርካታ ዓመታት ሊያስኬድ እንደሚችል እያየን በዚህ መስክ እንወዳደራለን ብንል ያዛልቀናል ወይ? ያዋጣናል ወይ ጠየቅን ይህንንም።
ሦስተኛ የሚነሳው ገበያ ነው። ገበያ እያደገ ነው፣ እየተሳሰረ ነው፣ ኢ ኮሜርስ እየሰፋ ነው የሚባል ነገር፣ በአፍሪካም የነጻ ንግድ ቀጣና የሚባል ነገር አለ፣ ዓለም ላይም። እውነት ነው ገበያ እየተስፋፋ ነው ያለው፣ ግን እዚያ ገበያ ውስጥ ለመወዳደር የሚያስችል ምርት አለን ወይ፣ ሎጅስቲክስ አለን ወይ? ቡናው አለ፣ ምናምኑ አለ ግን ማድረስ እንችላለን ወይ? በማድረስ ምክንያት ዋጋው ውድ አይሆንም ወይ? ጆግራፊካሊ እስረኛ የሆነች ሀገር አንድ ምርቷን ወስዳ በአንድ መስመር ብቻ ዓለም እያዳረሰች በዚያ ምክንያት ልትወዳደር ትችላለች ወይ? ይሄን ጥያቄ ነው በኖርማሉ ምሁሩም ትንሹም ትልቁም የሚናገረው ነው በለሆሳስ ሲታይ መጠየቅ ግን አለበት፤ አዛላቂ ስላልሆነ።
ሌላው የሚነሳው ታዳሽ ኃይል ነው። አፍሪካ አንታብድ ያልተነካ ሪንዌብል ሪሶርስ አላት ይባላል። ታዳሽ ኃይል አላት ይባላል፤ እውነት ነው ታዳሽ ኃይል አላት። በጂኦተርማል፣ በዊንድ፣ በሶላር፣ በሃይድሮ በጣም አቅሞች አሉ። እነዚህ አቅሞች ግን በጣም ትልቅ ኢንቨስትመነት ይፈልጋሉ። አፍሪካ ደግሞ ካፒታል የላትም ኢንቨስት አድርጋ እነዚያ ላይ አሁን ለማምረት በቂ ካፒታል የላትም። ኢትዮጵያ ለሕዳሴ አንድ ብር ብድር አላገኘችም፤ እሺ ችግር የለውም የሕዳሴው ጭቅጭቅ አለ ብለን እናስብ፣ ለኮይሻ ለኤሌክትሮ መካኒካል ብድር ጠይቃ አላገኘችም። አቅም አለ ብሎ ለዚህ አቅም የማይበቃ ካፒታል ኢንጄክት ማድረግ ካልተቻለ ሊወጣ አይችልም።
ሁለተኛው ራሱ ታዳሽ ኃይል ቢመረት፣ ሕዳሴ ቢመረት ራሱ፣ ኮይሻ ቢስፋፋ ራሱ፣ አሁን ያለው የ3 ዲ ኢንቬንሽን ያመጣው ችግር የለውም ወይ? ከዚህ ቀደም አንድ ሰው መኪና ለመሥራት በጣም ትላልቅ ሼር ያስፈልገዋል። በዚያ ውስጥ ነው ተገጣጥሞ ትላልቅ ኢንዱስትሪ የሚሠራው። አሁን 3ዲ እያንዳንዷን በኮምፒውተር ሠርቶ ፕሪንት ስለሚያደርግ በትንሽዬ ቤት ውስጥ ሊመረት ይችላል። ምክንያቱም እንደዚህ ቀደም በሞልድ አይደለም የሚሠራው። የኢንዱስትሪ ፍላጎትም ቀንሷል። በቅርብ ዓመታት ኢንዱስትሪ ከኢነርጂ የሚፈለገውን እየቀነሰ ነው የሚሄደው፤ ሳይዙም ኢነርጂውም።
አነርጂ ለመቀነስ የማይሠራ ምርምር የለም ዓለም ላይ። ምክንያቱም ከፍተኛ ሎስ አለ። እና 3 ዲውም አፌክት እያደረገው ነው ይህንን ነገር። ከሁሉ በላይ ግን ሎጀስቲክስ የሚባል ችግር አለ። ሃይዌይ፣ ሬይልዌይ፣ ፖርት የሌላቸው ሀገራት ለምሳሌ ጋምቤላ ላይ አምርቼ እኔ ከጋምቤላ አዲስ አበባ ለማምጣት የሚፈጅብኝን ቀን አስቡት። ከአዲስ አበባ ደግሞ ፖርት ወስደዋለሁ። ፖርቱ ደግሞ አንድ መስመር ስለሆነና አማራጭ ስለሌለው፣ ለምሳሌ ኢትዮጵያ ማዳበሪያ በምታስገባበት ሰዓት የጅቡቲ ወደብ ጢም ስለሚል ምንም ነገር ማስገባት አንችልም። ነዳጅ ስናስገባ ሌላ ሊኪውድ ነገር ለማስገባት እንቸገራለን።
ይሄ ፋክት ነው ኢኮኖሚያችን እያደገ በመጣ ቁጥር በዚያው ልክ ፈተናውም እያደገ ይሄዳል። ሎጅስቲክስ ውስንነት ባለበት ሀገር ውስጥ እንዴት ይሆናል? መርምረን ጠይቀን መጨረሻ ላይ የደረስንበት ጉዳይ ብዝሃ ዘርፍ፣ ብዝሃ ተጠቃሚ ካላደረግነው በስተቀር በአንድ ሴክተር ላይ ዲፔንድ ያደረገ ኢኮኖሚክሚ ሙቭመንት የኢትዮጵያን ስብራት አይጠግንም ብለን አመን፤ ብዝሃ ዘርፍ ያስፈልገናል እያልን ነው ያንን ብልፅግና የምናረጋግጠው። በአንድ ጉዳይ ላይ ብቻ መለጠጥ አያዋጣንም። ለምን? የእኛ አልቲሜት ፍላጎት ብልፅግና ነው።
ድህነትን ድምጥማጡን ማጥፋት ነው። መበቀል ነው የምንፈልገው። ያን ብልፅግና ለማረጋገጥ ዲቴል ሴል ኢለመንቶችን ካለየን በቀር የሆነ ነገር መዘን ብቻ የምናሳካው አይደለም። አንድ ሰው ምጣድ ሳይኖረው እንጀራ ለመጋገር አይችልም። ግብርና የግድ ነው። ከፍተኛ ሊመረት የሚችል ውሃ አለን፣ ሰው አለን፣ ያን ተጠቅመን በዓመት ሁለት ሦስቴ ብናርስ በምግብ ራሳችንን መቻል ሁነኛ ነገር ነው። ልንተወው አንችልም ማረስ አለብን።
ሁለተኛ ኢንዱስትሪ ነው። ኢንዱስትሪ ላይ በስፋት ካልሠራን በስተቀር በግብርና ብቻ የምናስበውን ኢንፕሎይመንት በግብርና ብቻ የምናስበውን ኤክስፖርት ልናሳካ አንችልም ምርት ያስፈልገናል። እነዚህም በቂ አይደሉም ቱሪዝም ያስፈልገናል። ታሪክ አለን፣ ባህል አለን እነርሱን ብንሠራቸው በጣም ብዙ ሀብት ያመጣሉ። ይሄም በቂ አይደለም የዘነጋነው ሀብት አለ ማይኒንግ እንጠቀምበት።
15 ዓመት 5 መቶ ሚሊዮን ያወጣንበትን በአንድ ዓመት 3 ሚሊዮን ያወጣነው በዚህ ኢንቴንሽን ነው። በ15 ዓመት 3.5 ሚሊዮን ብር የነበረውን ቡና በዓመት ይሄን ያክል ያመጣነው በዚህ በግብርና ትኩረታችን ነው። ቱሪዝሙም፣ ማይኒጉም፣ ግብርናውም፣ ኢንዱስትሪውም ቴክኖሎጂ ላይ ካልሠራን በቀር ደግሞ ውጤት አያመጣም። ቢኮዝ ሰርቪስ አት ዘ ኢንድ እያንዳንዱን ሰው የሚነካ ነገር ነው ብለን ቴክኖሎጂን አከልንበት ማለት ነው። ቴክኖሎጂን ካከልን በኋላ፣ አምስቱን ከለየን በኋላ ሌሎች ዘርፎች ዋጋ የላቸውም ማለት አይደለም።
መንገድ አንሠራም እኛ? ኢነርጂ ላይ አንሠራም እንዴ? እንደ ኢትዮጵያ ኢነርጂ ላይ የሚሠራ ሀገር አለ እንዴ አፍሪካ ውስጥ? 27፣28 ሺህ ኪሎ ሜትር አስፋልት እየሠራን ነው ያለነው ኢትዮጵያ ውስጥ። እዚህ አዲስ አበባ ውስጥ እኮ መቶ ኪሎ ሜትር አስፋልት ነው እየሠራን ያለነው። ይሄ የፕራዮሪቲ ፕራዮሪቲ መሆን ይችላል እኮ። ባለፉት አምስት ዓመታት የሠራነው ሀውሲንግ ቤት እኮ አሥራ አምስት ዓመት ከተሠራው ይበልጣል። አይሠሩም ማለት አይደለም ዋናው የልማት ፒላሮቻችን ግን አምስት ናቸው።
ኢንዱስትሪ ኢትዮጵያ ታምርት ያልነው ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ፋብሪካዎች 47፣ 48 ፐርሰንት ገደማ ብቻ ያመርቱ ነበር። ካላቸው አቅም ከሃምሳ በታች ያመርቱ ነበር። ግማሹ መሬት ይቸግረዋል፣ ግማሹ ኢነርጂ ይቸግረዋል፣ ግማሹ ፋይናንስ ይቸግረዋል፣ ግማሹ ዶላር ይቸግረዋል ብዙ ምክንያት አለ። ይሄንን በሴክተር፣ በሰብሴክተር ደረጃ፣ በፋብሪካ ደረጃ እያገዝን እየፈታን አሁን 65 ፐርሰንት ደርሰናል። ሰው ቀጥሯል፣ ታክስ ጨምሯል በዚያው ልክ። በዚህ አያበቃም፤ እኛ ወደቢሮ ስንመጣ ኢትዮጵያ የገነባችው ሦስት ኢንዱስተሪያል ፓርክ ነው። ሃዋሳ፣ ኮምቦልቻ እና መቀሌ። ከዚያ በኋላ እኛ አሥር ገንብተናል። አሁን 13 አለን። እነዚያ የገነባቸው 13 ፓርኮች 20 ፐርሰንት፣ 15 ፐርሰንት ብቻ የተያዙ ነበሩ። አሁን ሲታይ በድምሩ ከ80 ፐርሰንት በላይ ሼሪክ ተይዘዋል።
ከፓርኮች ውጪ ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ ሰዎች የፋብሪካ ባለቤት እንጂ የፓርክ ባለቤት የመሆን ልምምድ አነበረም። አሁን ማንም ሰው እዚህ አቃቂ ወጥቶ፣ እዚህ ዱከም ወጥቶ ሰዎች ያላቸውን ፓርክ ማየት ይችላል፤ የግለሰቦች ፓርክ እየገነባን ነው። እሱም አይበቃም ብለን ነፃ የንግድ ቀጣና ድሬዳዋ ላይ፣ እዚህ ቢሾፍቱ አካባቢ እየሠራን ነው። ኢንዱስትሪ በባህሪው አይታይም። ለምሳሌ ወንጪ ይታያል፣ ሰው ይሄዳል ፎቶ ይነሳል ይለጥፋል፣ ገንዘብ ያለው ይሄዳል ይዝናናል ይናገራል። ሆን ብሎ ግን ሰው ፋብሪካ ሄዶ አያይም፣ ልክ እንደ ጎርጎራ እንደ ወንጪ ሰው እስቲ ፋብሪካ ልይ ምን እንዳለ ብሎ መኪና ነድቶ አንስቶ አይጎበኝም። በዚህ ምክንያት ምን እንዳለ አያይም። አስገራሚ ሥራ ነው የተሠራው። በቅርብ የገጠመኝን አንድ ነገር ላንሳ፡-
አንድ ከአሜሪካ የመጣ ወጣት ኢትዮጵያን ይወዳል፣ ኢትዮጵያ ምን እንዳለ ግን አያውቅም፣ እና እዚህ አቃቂ አካባቢ አንድ ኢንዱስትሪያል ፓርክ እየገነባ ያለ ባለሀብት አለ፣ የእሱን ኢንዱስትሪያል ፓርክ እንዲያይ ላክነው። እና ልጁ “ማንም ሰው ቪዲዮ ወይ ፎቶ አንስቶ ይሄ ነገር ኢትዮጵያ ውስጥ ነው ቢለኝ ላምን አልችልም። ጊቢው፣ መስኩ አረንጓዴ የሆነ፣ በጣም ትልልቅ ሼድ፣ ኢንድ ቱ ኢንድ የሚሠራበት፣ መኪና የሚመረትበት፣ ብረት የሚጨፈለቅበት፣ በስሪ ዲ ዲዛይን የሚደረግበት ኢንዱስትሪ በግለሰብ ደረጃ በዚህ መጠን ኢትዮጵያ ውስጥ አለ ቢባል አላምንም” ነው ያለው። እውነቱን ነው ማየት ይፈልጋል፣ የሚሠሩ ሥራዎችን ካላየናቸው አይገባንም።
ኢንዱስትሪ በባህሪው እንደሌሎቹ አይደለም። ትንሽ ይዘገያል። ለምሳሌ አንድ ሰው ፋብሪካ ለመትከል መሬት ወሰደ ዲዛይን ሠራ እንበል፤ ፋብሪካው እኮ እዚህ የለም ያዘዋል፣ ፋብሪካው ይመረትበታል፣ ተጓጉዞ ቅድም ባልነው የሎጀስቲክስ ችግር ይመጣል፣ ከዚያ ደግሞ ይተከላል፣ የሙያተኛ ችግር ደግሞ አለ፣ ይበላሻል፣ ስፔር ፓርት የለም፣ ይጠገናል። እንደዚያ ሆኖ ሪስፖንድ ለማድረግ እንደ ቱሪዝሙ፣ እንደ ግብርናው፣ እንደ ቴክኖሎጂው ፈጣን አይደለም ጊዜ ይፈልጋል። አሁን በዚህ ዓመት የኢትዮጵያን እድገት ከሚያመጣቸው ሴክተሮች አንዱ ኢንዱስትሪ 13 በመቶ ያድጋል ያልነው እኮ ግብርናው ስድስት ፐርሰንት ነው የሚያድገው።
እስካሁን ኢንቨስት እያደረግን ነበር አሁን ደግሞ ሪስፖንድ የሚያደርግበት ሲዝን ደርሷል ማለት ነው። በቅርብ ዓመታት ይሄ እየሰፋ ይሄዳል። ባለፉት ዓመታት ሁለት ዓመት እኮ በጣም ትላልቅ ሄቭ ኢንዱስትሪስ ገንብተናል። ለምሳሌ ለሚ ሲሚንቶ ፋብሪካ ማለት እኮ በጣም ትልቅ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የሲሚንቶ ችግር ፈትቶ እኮ ኤክስፖርት እናድርግ እያልን ነው። ለሚ ሲሚንቶ ፋብሪካ ኢትዮጵያ እስካሁን ያሏት ሁሉ ተደምረው የሱን ግማሽ ያመርታል ለሚ። ግን ሰው አያያቸውም፣ ለሚ ካልሄደ፣ ፋብሪካዎችን ሄዶ ካላየ። ስንት መኪና ነው ኢትዮጵያ ውስጥ? እነርሱን ሄዶ ካላየ በስተቀር የተሟላ ግንዛቤ አይኖረውም።
ሰርቪስን በሚመለከት ግን ትኩረት የተሰጠው ነው፣ ማራከስ ትክክል አይደለም። ሰርቪስ የኢኮኖሚ እድገት መቋጫው ነው። ማሳረጊያው እሱ ነው።
ለምሳሌ የአሜሪካ ትልቁ ኢኮኖሚ የሚባለው እኮ ግብርናውና ኢንዱስትሪው ተደምሮ ሰላሳ ፐርሰንት ቢሆን ነው። ከሰባ ፐርሰንት በላዩ ሰርቪስ ነው። ማንም ያደገ ሀገር አልቲሜትሊ ቢገር ሼር ያለው በእድገት ውስጥ ሰርቪስ ነው። ለምን መሰለሽ በቅርቡ ዘመን ገበያ የሚባል ኢኮሜርስ ኢትዮጵያ ጀምራለች።
ዘመን ገበያ የጀመርንበት ዋናው ምክንያት ምርት እያለ ዲማንድ እያለ መሀል ላይ ባሉ ደላላዎች ምክንያት ምርትን ከፈላጊው ማገናኘት ችግር ሆኗል። በባለፈው ፋሲካ እንቁላል አዲስ አበባ ሃያ ብር ሲባል ወጣ ተብሎ አስር አስራ ሁለት ብር ነበር። እነዚያን እንቁላሎች ከፈላጊው ጋር ማገናኘት ግን ሲስተም አልነበረም፤ ሎጂስቲክስም ሲስተሙም ችግር ነው ደላላውም ብዙ ስለሆነ።
አሁን ዘመን ገበያ ከተጀመረ ሃያ ቀን ቢሆነው ነው። ከሁለት ሺህ በላይ አይተምስ አሉት። ሽንኩር አለው ቃሪያ አለው በግ አለው ሞተር ሳይክል አለው ባጃጅ አለው የሌለው ነገር የለም። ገና ሃያ ቀኑ ነው። አራት ሚሊዮን ገደማ ሽያጭ አከናውኗል በዚህች ቀናት ውስጥ። ይሄ የኢትዮጵያ አሊባባ ማለት ነው። ጥቅሙ በጣም ብዙ ነው። አሁን በቅርቡ የአረፋ በዓል አለብን ለአረፋ በዓል ሰው በግ በዘመን ገበያ ቨርቹዋሊ ያዛል ዴሊቨር ይደረግለታል።
መሃል ላይ ያለው ደላላ መሃል ላይ ያለው ሰው በከፍተኛ ደረጃ ይቀንሳል ወይም ወደ ትክክለኛ መስመር ይገባል። ሰርቪስ ማለት ይሄ ነው። በጉ አለ ፈላጊው አለ በጉና ፈላጊው እያለ ቴክኖሎጂ ባለመኖሩ ሎጂስቲክስ ባለመኖሩ የገበያ ሥርዓት ያልተዘረጋ በመሆኑ ተጠቃሚው የሚጎዳበትን ሥርዓት ይቀንሳል ማለት ነው። ሰርቪስ ከሌለማ ምርት ምን ዋጋ አለው አይደርስማ፤ አይደርስምኮ!
አንድ ቀላል ምሳሌ ላምጣልሽ አንድ ጃኬት ይሄ ጃኬት ዱባይ መቶ ሃምሳ ዶላር ከሆነ ዱባይ ባልገዛው ጀርመን ስሄድ መቶ ሃምሳ አምስት መቶ ስድሳ ሊሆን ይችላል። አሜሪካ ስሄድ መቶ አርባ አምስት ሊሆን ይችላል። ቻይና ስሄድ መቶ ሰላሳ ሊሆን ይችላል። ኢትዮጵያ ይሄው ጃኬት ይሄው ሱፍ መርካቶ ላይ አምስት መቶ ይሆናል፤ በብር አይለም በዶላር።
ዶላር ኢትዮጵያ ፤ ዶላር ዩኤኢም፤ ዶላር ቻይናም እኩል ሆኖ ሲያበቃ ለሚሰጠው ግብር፤ ለትራንስፖርቱ አስር ሃያ ብር ይጨምር ችግር የለውም፤ ሦስት አራት እጥፍ እንዴት ይሆናል። ዘ ሴም ኳሊቲ ያለው ምርት ፤ዘ ሴም ቫልዩ ባለው ዶላር በዚህን ያህል ዲፈረንስ ለምን ይለያያል፤ ያንን ያየን እደሆነ የሰርቪስ ችግር ነው። የገበያ ትስስር ችግር ነው። ያን የገበያ ችግር የምንቀርፈው ሲስተም በመዘርጋት ነው።
ዘመን ገበያ የጀመርነው ያንን ችግር ለመቅረፍ ነው። ለምሳሌ የፋይናንሻል ሴክተሩ ላለፉት መቶ ዓመታት ኢትዮጵያ ውስጥ ካሽ ነው አጠቃላይ የምንገበያየው። ሞባይል መኒ ጀመርን ትናንትና ሦስት ዓመታችን ነው። በሶስት ዓመት ውስጥ ሞባይል መኒ ሰርፓስ አደረገ የካሽን ትራንዛክሽን። ትሪሊየንስ ነው እንቅስቃሴ የሚያደርገው።
ድሮ አንድ ሰው ብድር ለመበደር መታወቂያ አምጣ ፎቶ አምጣ ወላጅ አምጣ የሚባለውን ነገር ቨርቹዋሊ በሞባይል መበደር የሚችልበት ዕድል ማግኘት ማለት ለፋይናንሻል ኢንኩሉዥን ሃሳብ ያላቸው ሰዎች ሃሳባቸው እዲወለድ ለማገዝ ከፍተኛ ጥቅም አለው። ቴክኖሎጂው ከሌለ ግን በሀገር ጫፍ ብድር ማድረስ የምንችልበት ምንም እድል የለም ማት ነው።
ሰርቪስ ሲባል የተመረተውን የተፈጠረውን ነገር ለተጠቃሚ ለማድረስ የሚያቀል መንገድ ማለት ነው። የተመረተውን ነገር ተጠቃሚው ጋር በትክክለኛው ዋጋ እዲደርስ የሚያርግ ማለት ነው። እሱ እያደገ መሄዱ ጥርጥ የለውም የኢትዮጵያም ኢንዱስትሪ ይሰፋል ግብርናው ይሰፋል እያደገና እየወረሰ የሚሄደው ግን ሰርቪስ ነው። እና ሰርቪስ ኢንዱስቱሪው ላይ ትኩረት ተሰጥቶ ሳይሆን የሚነካን እሱ ስለሆነ ነው።
በቅርበት የምናየው ሲወደድም ሲከስርም የምናየው እሱ ስለሆነ ነው እንጂ እኛ አምስት ዘርፍ እንደ ፒራል ለይተን ለእነሱ ደግሞ ደጋፊ የሆኑ ዘርፎች ጨምረን ነው እየሠራን ያለነው። ብዝኃ ዘርፍ ነው ብዝኃ ተዋናይ ነው ብዝኃ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ ነው። በዚያም ነው ሙልአት ባለው መንገድ ሲግኒፊካንት የሆነ የእድገት መንገድ ውስጥ የገባነው ማለት ነው። በዚያ መንገድ ቢታይ መልካም ነገር ይመስለኛል።
/ይቀጥላል/
አዲስ ዘመን እሑድ ሰኔ 1 ቀን 2017 ዓ.ም