የአሸዋ ሜዳው “ፔሌ”

በብዙዎች ዘንድ “ፔሌ” በሚለው ቅጽል ስሙ ይታወቃል። በድሬዳዋ ኮካኮላ ክለብ በመጫወት የእግር ኳሱን ዓለም በይፋ ተቀላቅሏል። የሦስት ክለቦችን ማልያ ለብሶ ለ16 ዓመታት ተጫውቷል። ለቅዱስ ጊዮርጊስ አምስት ዓመት፣ ለመድን አምስት ዓመት እንዲሁም ለቡና ገበያ ለስድስት ዓመታት በድምሩ ለ16 ዓመታት እግር ኳስን በሀገሪቱ ታላላቅ ክለቦች በመጫወት ድንቅና የማይዘነጋ የእግር ኳስ ጊዜ አሳልፏል።

አስደናቂ የኳስ ተሰጥኦ የተካነው አሰግድ በዘመኑ ኢትዮጵያውያንን የእግር ኳስ ታዳሚዎች ጮቤ አስረግጧል። መነሻውን ከድሬዳዋ አሸዋ ሜዳ ያደረገው አሰግድ በቡና ከሌላኛው ኮከብ ከካሳዬ አራጌ ጋር የነበረውን ጥምረት ብዙዎች አይረሱትም። በዘመኑ የነበሩ የእግር ኳስ ተመልካቾች “ሁለቱ ኮከቦች ጥምረታቸው እንደ ኢኒየስታ እና ሜሲ ነበር። ሁለቱም እጅግ አስደናቂ የኳስ ክህሎት አላቸው” ሲሉ ይመሰክራሉ።

በ1990ዎቹ በተለይ በቡና ገበያ ስፖርት ክለብ በሚያደርጋቸው ድንቅ እንቅስቃሴዎች፣ በግብ አይምሬነቱ የብዙዎችን ቀልብ የገዛው አሰግድ ተስፋዬ፣ በአንድ ውድድር ዘመን አምስት ጊዜ ሀትሪክ በመሥራት ባለ ክብረወሰን ነው። በብሔራዊ ቡድን ደረጃም ብዙ ግቦችን በማስቆጠር ከምንጊዜም ከፍተኛ ጎል አቆጣሪዎች ተርታ ይሰለፋል። በዚህ አንቱታን ያተረፈው አሰግድ ተስፋዬ፣ ሮማሪዮ፣ ዢሬስ፣ አሰግድ ፔሌ እና በመሳሰሉ ቅፅል ሥሞቹ ይታወቃል።

ኢትዮጵያ ቡና የመጀመሪያውን የኢትዮጵያ ዋንጫ ባለቤት ሲሆን ዋነኛ መንስኤ እሱ ነበር። በአዲስ አበባ ስታዲየም ድንቅ ግብ በማስቆጠር ክለቡን በአፍሪካ ደረጃ ለመጀመርያ ጊዜ ለቻምፒዮንስ ሊግ ክብር አብቅቷል። እንዲሁም በቀድሞ አጠራር ቡና ገበያ በአንድ ጨዋታ 5 ጎሎችን የሲሼልሱ ሴንት ሚሼልስ ላይ በኢንተርናሽናል ጨዋታ ያስቆጠራቸው ግቦች የማይዘነጉ ናቸው። በዚህም ኢትዮጵያዊው ሮማርዮ የሚል የአድናቆት መለያ ተሰጥቶት ነበር። በደቡብ አፍሪካ ክለቦች የመጫወት እድል አጋጥሞት በወቅቱ ከሀገሩ ውጪ መጫወት እንደማይፈልግ ገልፆ ነበር።

የ23ኛው የዩጋንዳ የምስራቅ አፍሪካ ዋንጫ ላይ የውድድሩ ኮከብ ግብ አግቢ ነበር። በሴካፋ ክለቦች ታሪክ ኢትዮጵያዊው ቀዳሚ ኮከብ ግብ አስቆጣሪም ነበር። በ1988 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ቻምፒዮንስ ሊግ ጥምር ግብ አስቆጣሪ እና የአዲስ አበባ ኮከብ ጎል አስቆጣሪ ጭምር ነበር።

በእርሱ ዘመን ከተፈጠሩ አጥቂዎች በፍጥነት ዝግ ያለ ቢሆንም በአስተሳሰብ ፍጥነቱ ኮከብነቱን ደጋግሟል” ሲሉ ብዙዎች ይመሰክሩለታል። ከምስራቅ ኢትዮጵያ ኮከብነት አንስቶ እስከ ምስራቅ አፍሪካ ኮከብነት አንፀባራቂ የእግር ኳስ ሕይወት አሳልፏል።

የጨዋታ ዘመኑ ከተጠናቀቀ በኋላም ከእግር ኳሱ ላለመራቅና በሙያው ለሀገሩ መልካም ነገር ሠርቶ ለማለፍ በማሰብ “አሰጌ ስፖርት አካዳሚ”ን በመክፈት የነገ የሀገር ተረካቢ ታዳጊዎችን እስከ ህልፈተ ሕይወቱ ድረስ በማሰልጠን በእግር ኳሱ የራሱን ዐሻራ ለማስቀመጥ በብርቱ ጥሯል። የአሸዋ ሜዳው ፔሌ ከሜዳ ውጪ ባለው ባህሪም ይታወሳል። ተጫዋቾች ሲታመሙ ፣ ችግር ላይ ሲወድቁ ቀድሞ ደራሽና ድጋፍ እንዲደረግላቸው ያስተባብራል። በፈገግታና ቀልድ አዋቂነቱ ይነሳል። ቂም እና ቁጣ የእሱ መገለጫ አይደሉም።

ግንቦት 26 ቀን 2009 ዓ.ም በድንገት በመታጠቢያ ክፍል ውስጥ ወድቆ በ 47 ዓመቱ ሕይወቱ ያለፈው ታሪካዊ ኮከብ የአንድ ሴት ልጅ አባት ነበር። ጋዜጠኛ ሰዒድ ኪያር የአሰግድ ተስፋዬን ህልፈት አስመልክቶ ሲዘግብ፡-

“እውነተኛ የኳስ ጀግና፣ የደቻቱ ፍሬ፣ የአሸዋው ሜዳ አብዶኛ፣ አጭሩ የፍፁም ቅጣት ምት ክልል ባለሟል፣ ቀንደኛው የጎል ሰው፣ ለድሬዳዋ “ፔሌ” ለቅዱስ ጎርጊስ እና መድን “አለንዥሬስ”፣ ለኢትዮጵያ ቡና “ሮማርዮ” የነበረው የጎል ማሽን አሰግድ ተስፋዬ በሚወደው እግር ኳስ ሕይወቱን ባሳለፈበት ሜዳ ጀምሮ እዛው እስትንፋሱን ጨረሰ” ማለቱ ይታወሳል።

ቦጋለ አበበ

አዲስ ዘመን እሁድ ሰኔ 1 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You