አዲስ ዘመን ጋዜጣ በኢትዮጰያ የጋዜጠኝነትና ሥነ ጽሑፍ ታሪክ Oሻራውን እያኖረ 84 ዓመታትን ተጉዟል

አዲስ አበባ፦ አዲስ ዘመን ጋዜጣ በየጊዜው ራሱን እያሳደገና ዘመኑን እየዋጀ 84 ዓመታትን ዘልቋል ሲሉ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የህትመት ሚዲያ ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ፍቃዱ ከተማ ገለጹ። አቶ ፍቃዱ ከተማ እንደተናገሩት፤ “አዲስ ዘመን” ጋዜጣ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ለአዲሲቱ ኢትዮጵያ አዲስ ዘመን መጥቷል ያሉትን መነሻ በማድረግ ከ84 ዓመታት በፊት ግንቦት 30 ቀን 1933 ዓ.ም ተመሥርቷል (መታተም ጀምሯል)። ቀድሞ ሌሎች ጋዜጦች ቢኖሩም ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት መመሥረት ግን አዲስ ዘመን ጋዜጣ ከፍተኛውን ድርሻ ይወስዳል ብለዋል ።አዲስ ዘመን ጋዜጣ ባለፉት 84 ዓመታት የኢትዮጵያን የየእለት ሁነት በመዘገብና ታሪክ

እየሰነደ የሚገኝ ጋዜጣ ነው ያሉት አቶ ፍቃዱ፤ ጋዜጣው የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በእንግሊዝኛ፣ በአረብኛ፣ በኦሮሚኛ፣ በሲዳሚኛ፣ በትግርኛ ቋንቋ የሚያሳትማቸውን ጋዜጦች የወለደ መሆኑንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት አዲስ ዘመንን ጨምሮ ዘ ኢትዮጵያን ሄራልድ፣ አል አለም፣ በሪሳ፣ ወጋህታ፣ በካልቾ የሚል መጠሪያ ያላቸውን ጋዜጦች እንደሚያሳትም ጠቅሰው፤ ይህም አዲስ ዘመን ጋዜጣ ለተቋሙ መስፋፋትና ለጋዜጦቹ ህትመት መሠረት መሆኑን የሚያሳይ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እና አዲስ ዘመን የኢትዮጵያን 84 ዓመት ከፍታና ዝቅታ፤ ኀዘንንና ደስታ በመዘገብና በመሰነድ ዛሬ ላይ ደርሰዋል ያሉት አቶ ፍቃዱ፤ የኢትዮጵያ 84 ዓመት የታሪክ ማህደር የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት መሆኑንና ይህም በፎቶና በጋዜጣ ተሰንዶ በተቋሙ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

አዲስ ዘመን ኢትዮጵያ በበፊቱ ጊዜያት ምን ትመስል እንደነበር በፎቶና በጽሁፍ የሚያስረዳ ጋዜጣ መሆኑን ተናግረው፤ የጋዜጣው ይዘትም ጊዜውን እና ወቅቱን ይመስል እንደነበር ተናግረዋል። ከዚህም ባለፈ የጋዜጣውን ይዘትና ቅርጽ የማሻሻል ሥራም በየጊዜው ሲከናወን እንደመጣም ተናግረዋል።

ለአብነት በ2010ዓ.ም ጥናት በማድረግ የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ቅርጽን ከአርበ ሰፊ ወደ አርበ ጠባብ ተደርጓል ያሉት አቶ ፍቃዱ፤ በዚህም ተነባቢና ተጽዕኖ ፈጣሪ እንዲሆን ተደርጓል። ይህም በመንግሥትና በግል ተቋማት እንዲሁም መንግሥታዊ ባልሆኑ ተቋማት በሽልማትና በሰርተፍኬት ምስክርነት ያገኘ መሆኑን ገልጸዋል።

አሁንም በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ የይዘት ማሻሻያ ለማድረግ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመው፤ ይህም ተነባቢነቱን ይበልጥ ያሳድጋል። በአጠቃላይ አዲስ ዘመን ጋዜጣ በየጊዜው ራሱን እያሰደገና እያዘመነ ለዘመን ኢኮኖሚ፣ ለብላቴናት እና ለናኦታ የልጆች መጽሔቶች አባት ሆኗል ነው ያሉት።

እንደ አቶ ፍቃዱ ገለጻ፤ አዲስ ዘመን ጋዜጣ በዓሉ ግርማን፣ ነጋሽ ገብረማርያምን፣ ማሞ ውድነህን፣ ብርሃኑ ዘሪሁንን የመሳሰሉ አንጋፋ ጋዜጠኞችን እና የሥነ ጽሁፍ ባለሙያዎችን አፍርቷል። አዲስ ዘመን ጋዜጣ ታሪክ ከመሰነድ ባለፈ በኢትዮጵያ ሥነ ጽሁፍ ላይ ዐሻራውን አስቀምጧል።

እንደ አቶ ፍቃዱ ገለጻ፤ አዲስ ዘመን በመንግሥትና በሕዝብ መካከል የመረጃ ድልድይ ሆኖ የሚያገለግል ነው። በዚህም የሕዝቡን ችግር በልኩ ለመንግሥት ተደራሽ እያደረገ፣ የኢትዮጵያን ስኬት ለሕዝብ እያሳወቀ፣ የኢትዮጵያን ገጽታ እየገነባ እና ሀገር ችግር ውስጥ ስትሆን ደግሞ እንደወታደር የታገለ ጋዜጣ ነው። አሁን ደግሞ ጋዜጣውን ወጣት የማድረግ ሥራ እየተሠራ ነው።

አዲስ ዘመን ጋዜጣ የህፃናትንና የወጣቶችን ደህንነት የሚያስጠብቅ፣ የሀገር ገጽታ እንዳይጎዳ የሚያደርግ፣ ኢንቨስትመንትና ልማት እንዲስፋፋ የሚሠራ ተልዕኮ ያለው የህትመት ሚዲያ መሆኑን ተናግረዋል።

ሳሙኤል ወንደሰን

አዲስ ዘመን እሁድ ሰኔ 1 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You