የትናንት ታሪክና የወደፊት ዕቅድ ያለው ሰው ብቻ ነው። ስለ ትናንት ለማወቅ ይጓጓል፤ወደፊት ታሪክንና ባህላዊ እሴቱን ለማስቀጠልም ይሰራል። ለዚህም ይመስላል በወራት፣ በቀናትና በዓመታት ጊዜያትን ከፋፍሎ ክብረ በዓላትን እያስታወሰ የሚያከብረው።
በዓላት የጋራ የሆነ መለያ አላቸው። የመጀመሪያው የአንድነት፣የነጻነትና የፍቅር በዓል መሆናቸው ነው። የመልካም ምኞት መግለጫና ማህበራዊ ህይወትን የሚያስተሳስሩ መሆናቸውም ሌላው ነው። በመስከረም ወር ብዙ የአደባባይ በዓላት አሉ። ከእነዚህ በዓላት መካከል ደግሞ መስቀል አንዱ ነው። በዚሁ የበዓል አከባበር፣ ትርጓሜና ማህበራዊ ፋይዳው ዙሪያ መጽሐፍት አገላብጠንና በባህል መስክ የተሰማሩ ባለሙያ አነጋግረን ያዘጋጀነውን እናካፍላችሁ።
መስቀል ምንድን ነው ?
መስቀል በቀደመው ዘመን ለኃጢአተኞች መቅጫ የነበረ ሲሆን፤ “በእንጨት ላይ የተሰቀለ በእግዚአብሔር ዘንድ የተረገመ ነውና” (ዘዳ፣21:23) እንዲል መጽሐፍቅዱስ የሃጢአተኞች መቅጪያ ተደርጎ ይወሰዳል። በአዲስ ኪዳን ደግሞ ይህ ተግባር ተቀይሮ ለክርስትያኖች ኃይል፣ ጽንዕ፣ ቤዛና መድኃኒተ ነፍስ ሆኖ የሚያገለግል አርማ ሆኗል።
መስቀል በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ ጠላት የራቀበት፤ የጥል ግድግዳ የፈረሰበትም ተደርጎ ይታመንበታል። ምክንያቱም “በእኛ ላይ የነበረውን የሚቃወመንንም በትዕዛዛት የተጻፈውን የዕዳ ጽሕፈት ደመሰሰው። እርሱንም በመስቀል ጠርቆ ከመንገድ አስወግዶታል። አለቅነትንና ሥልጣናትን ገፎ ድል በመንሣት በእርሱ (በመስቀል) እያዞራቸው በግልጥ አሳያቸው።” (ቆላ፣ 2:14) ወይም “እርሱ ሰላማችን ነውና፤ ሁለቱን ያዋሐደ በአዋጅ የተነገሩትንም የትዕዛዛትን ሕግ ሽሮ በመካከል ያለውን የጥል ግድግዳን በሥጋው ያፈረሰ፤ ይህም ከሁለታቸው አንድን አዲስን ሰው በራሱ ይፈጥር ዘንድ ሰላምንም ያደርግ ዘንድ፥ ጥልንም በመስቀሉ ገድሎ በእርሱ ሁለታቸውን በአንድ አካል ከእግዚአብሔር ጋር ያስታርቅ ዘንድ ነው።” (ኤፌ፣ 2:15) ይላልና መጽሐፍ ቅዱስ።
መስቀል በቁም ትርጓሜውም በእምነቱ አስተምሮ ከቤተክርስትያን ጉልላት እስከ ምዕመናን ንቅሳት የሚታይ የድል ምልክት፣ በሰሌዳ ተስሎ በጣት ተመሳቅሎ የሚገኝ የድኅነት አርማ፣ ካህናት በእጃቸው ይዘው የሚፈቱበት፣ ክርስትያኖች በአንገታቸው አስረው ማንነታቸውን የሚመሰክሩበት መገለጫ ሲሆን፤ በሌላ አገባብ መከራ የተጋድሎ ፍኖት ነው።
መስቀልን እንደ አንድ ሃይማኖታዊ ምልክት አድርጎ መጠቀም በመላው ዓለም ላይ የተለመደ ቢሆንም ብዙውን ጊዜም ከአንድ ዓይነት የተፈጥሮ አምልኮት ጋር የተያየዘ ነበር። እናም ይህ አምልኮ ስርዓት በብዛት የሚተገበረው በአደባባይ ነው። ስለዚህም ሁሉም ደመራን ደምሮ ስለመስቀሉ ሃያልነት የሚያወራው ለዚህ ይመስላል። በተለይ ለኢትዮጵያዊያን ትልቅ ቦታን ያጎናጸፈ ነው። ምክንያቱም መስቀልን ታኮ ቱሪስቱ ወደ አገሪቱ የሚተምበት መንገድ ተጠርጎለታል። ዩኔስኮም መዝግቦት በአባል አገራቱ ያለውን ልዩ ባህላዊ መስህብነት ይመሰክርለታል።
ለምን ይከበራል?
በዓለ መስቀል በክርስትና ኃይማኖት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቀራንዮ የተሰቀለበት መስቀል በአይሁድ ከተቀበረበት ሥፍራ መገኘቱን ማስታወሻ በዓል ነው። በምዕራብም ምሥራቅም አብያተ ክርስትያናት ይሄንን መታሰቢያ በመስከረም 3 ቀን ሲያከብሩት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስትያን ደግሞ በየዓመቱ በመስከረም 17 ቀን ታከብራለች። የዚህ ምክንያቱ የተለያየ እንደሆነ ይነገራል።
ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት መስቀል በተአምራዊነቱና በክርስትያኖች ዘንድ ከፍተኛ ክብር የተሰጠው በመሆኑ፣ አይሁድ በቅንአት ተነሣሥተው ለሶስት መቶ ዓመታት ያህል በቆሻሻ መጣያ ጥለውት ቆዩ። በዚህም ተራራ ተፈጠረ። እናም ትክክለኛ የክርስቶስ መስቀል በየትኛው ተራራ ላይ እንዳለ ለማወቅም አስቸገረ። ስለዚህም በ326 ዓ.ም የቄሳር ቆስጠንጢኖስ እናት ንግሥት ዕሌኒ፣ ኪራቆስ በተባለ አንድ የታሪክ አዋቂና ሽማግሌ ጠቋሚነት ደመራ ደምራ በእሳት አቀጣጥላ ዕጣን ባጨሰች ጊዜ፣ የዕጣኑ ጢስ ወደ ላይ ከወጣ በኋላ ተመልሶ ያረፈበትን ሥፍራ አስቆፍራ መስቀሉን አውጥታዋለች። እናም ህዝበ ክርስትያኑ ይህንን በማሰብ መስከረም 16 ላይ ደመራን ይደምራል። በ17 ደግ ሞ የመስቀል በዓልን ያከብራል።
ንግስት ዕሌኒ መስቀሉን ለማውጣት ለሰባት ወራት ያህል ተራራውን ስታስቆፍር ቆይታለች። በዚህም መስከረም 17 ቀን አስጀምራ በመጋቢት 10 ቀን እንዳስወጣችው ይነገራል። ይሁንና በአንዳንድ ሊቃውንት እሳቤ መስቀሉ የተገኘው በ17 እንደሆነ ይገለጻል። ሆኖም አብዛኛው የቤተክርስትያኗ ሊቃውንት ግን “መስቀሉ የተገኘው በመጋቢት 10 ቀን ነው፣ ይህ ወር የዐቢይ ጾም ወር በመሆኑ በዓሉ በመስከረም 17 ቀን ይከበር አሉ። ለዚህም ምክንያት አላቸው። መስቀል ደስታን ማብሰሪያ፤ ነጻነት ማወጃና ዘመድ ከዘመዱ በሚገባ የሚጠያየቅበት ነው። እናም ይህንን ለማድረግ የሚያስችል ወር ደግሞ መስከረም ነው ሲሉ የመቆፈሪያውን ቀን አብነት በማድረግ ያከብሩታል።
ማህበራዊ ፋይዳው
መስቀልም መስከረም ዓውደ ዓመት በዋለበት፣ የዘመን መለወጫ ቀንን ባከበርንበት ወርሃ አደይ ወርሃ ጽጌን ተከትሎ ስለሚመጣ የብርሃን፣ የሰላምና የደስታ በዓል ተደርጎ ይወሰዳል። እናም በዚህ ቀን ኢትዮጵያውያን በልዩ ልዩ ሁኔታዎች ማህበራዊ መስተጋብራቸውን ያጠናክሩበታል። ይህንን በዓል ከሃይማኖታዊና ባህላዊ በዓልነት ባሻገር እንዲራመድ የሚያደርገው ይህ መለያው ነው። ምንም እንኳን ትርጓሜው ሀይማኖታዊ ቢሆንም በተለያየ ቦታ ከእምነቱ ተከታዮች ውጪ ብዙዎች ያከብሩታል። በሀገር ውስጥ እና በውጪ ቱሪስቶች ጭምር ደምቆ ይከበራል።
የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የኮሚኒኬሽን ጉዳዮችና አለማቀፍ ግንኙነት ዳይሬክተር ተወካዩ አቶ ታሪኩ ነጋሽ እንደሚናገሩት፤ መስቀል የፍቅር፣ የእርቅ፣ የወንድማማችነት፣ የይቅርታ፣ የሰላም፣ የደግነት / መልካምነት፣ የተስፋ፣ የብልጽግናና የአንድነት በዓል ነው። ምክንያቱም በንጽህና ወደሚቀጥለው መልካም ጊዜ መሻገርን ይጠይቃልና። ቂምና በቀል፣ ጥላቻና ጥል፣ ግጭትን ይዞ መሻገር ከማይቻልባቸው የአደባባይ በዓላትም ዋነኛው ነው። በዚህ ጊዜ ቂም በቀል ጥልና ግጭት ይዞ እየተገፋፉ በአደባባይ በዓሉን ማክበር አይቻልም። እናም በዚህ ዕለት የማይተዋወቅ እንኳን በዓሉ በሚከበርበት ቦታ ላይ ሲገናኝ ወንድማማችነትን ይመሰርታል። ከዚያም አልፎ ፍቅረኛ ለማግኘት መንገድ ይሆናል።
መስቀል በእምነቱ ተከታዮች ዘንድ በዓለ ነጻነት ተደርጎ ይወሰዳል። ሁሉም ግጭቶች በእርቅና በይቅርታ ይፈታሉ። ይህ ሲሆን ፈጣሪ ምስጋናን፣ ልመናን ይሰማል። ብሩህ ተስፋ ይፈጠራል፤ ወደአዲስ ምዕራፍ መሸጋገርም ይቻላል ይላሉ። አምላክ ጥልን በመስቀሉ እንደገደለ ሁሉ ሰላም፣ ፍቅር፣ ወንድማማችነት፣ መከባበር፣ መቻቻል፣ መረዳዳት፣ መልካምነት የዚህ በዓል ዋነኛ መርህ እንደሆነም ይታመናልና ከእምነቱ ውጪ ያሉ አካላት ሁሉ ይህንን ለማድረግ ይሞክራሉ። ሆኖም ግን የበዓሉ ማህበራዊ ፋይዳ ይሄ ብቻ ነው ሊባልለት አይችልም ባይ ናቸው።
እንደ አቶ ታሪኩ ገለጻ፤ ታሪክ የመጀመሪያው አዳዲስ መረጃዎችና ማስረጃዎች ስለሚገኙበት የመስቀል በዓል አከባበርም እንዲሁ የነበረውን ትረካ አዲስ እያደረገ በየጊዜው የሚያቀርብ ነው። የመማማሪያ፣ ከትናንት የተሻለ ዓለም ለመገንባት የመነሻ መሠረት፣ መልካሙን የማስቀጠያ መንገድ፣ ክፉውን የማረሚያ መስመር በመሆን የሚያገለግል በዓል ቢኖር መስቀል ነው።
መስቀል ሀይማኖታዊና ባህላዊ ክዋኔዎች የሚተገበሩበት ስለሆነ ብዙዎች ይሳቡበታል የሚሉት ደግሞ በቅርስና ጥናት ጥበቃ ባለስልጣን የህዝብና አለማቀፍ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ፋንታ በየነ ናቸው። መስቀል ማህበራዊ እሴትን ከመገንባት አንጻርም የማይተካ ሚና ይጫወታል። ይህ የሚሆነው ደግሞ ተጠቃሚነት ሲሰፋ ነው። ቱሪስት በየጊዜው ወደ አገሪቱ ሲገባ ማህበረሰቡ በሚያየውና በሚያገኘው ገንዘብ ተጠቃሚ ይሆናል። ይህንን ደግሞ መልሶ ባህሉን ለማስተዋወቅና ራሱንም ለማደስ ይጠቀምበታል። ስለሆነም መስቀል ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን እየጨመረ ማህበራዊ እሴትን እየገነባ የሚሄድ በዓል ነው ማለት ይቻላል። መስቀል የመረዳዳት፣ የመደጋገፍ በዓል ነው። ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ መብት የሚሰጥም ባህል ነው። እናም በዘመናት ሂደት ባህሉ ሳይበረዝና ሳይከለስ የተጓዘ እና ለትውልድ የተላለፈም ነው።
አቶ ፋንታ እንደሚያነሱት፤ መስቀል ከማይዳሰሱ ቅርሶች መካከል ሲመዘገብ መሰረታዊ መለያው ለሀገር እና ለህዝብ ከፍተኛ ጠቀሜታ መስጠቱ ነው። ማህበረሰቡም ቀደም ሲል ከሚሰጠው ትኩረት በተለየ መልኩ ጥበቃና እንክብካቤ እንዲያደርግለትና መንግስት ልዩ ትኩረት እንዲሰጠው ያስችላል። አለምም ስለ በዓሉ አገልግሎትና ምንነት እንዲረዳ ያደርጋል። ይህ ደግሞ ወደ አገሪቱ የሚመጣውን የቱሪስት ብዛት እንዲጨምር እድል ያመቻቻል። በዚህም ህዝብና አገር የኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያደርጋል። በዓሉ ሃይማኖታዊ፤ ባህላዊ፤ ማህበረሰባዊም ነው። ስለዚህ ሀይማኖታዊ ነው ብሎ በሃይማኖት ብቻ የሚጠበቅና የሚዘከር፣ ባህላዊ ነው ተብሎ በአንድ አካባቢ ብቻ የሚደምቅ አይደለም። ይልቁንም ማህበረሰባዊ፣ አገራዊና አለምአቀፋዊ በመሆኑ ተንከባከቦ ዘመን ተሸጋሪነቱን ማረጋገጥ ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን መስከረም 11/2012
ጽጌረዳ ጫንያለው