አዲስ አበባ፡- የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርት ሎጀስቲክስ አገልግሎት ድርጅት የወጪና ገቢ ንግድን በባህርና በየብስ ትራንስፖርት በማስተላለፍ፣ አገልግሎት አሰጣጡን በዋጋ፣ በቅልጥፍና በደንበኞች ተመራጭ በማድረግ በ2011 ዓ.ም 18 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱን አስታወቀ።ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ 3 ነጥብ 2 ሚሊዮን ቶን ግምት ያላቸው ስንዴና ማዳበሪያን ለማጓጓዝ የቅድመ ዝግጅት ስራ መስራቱን ገለጸ፡፡
የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሮባ መገርሳ የ2011 ዓ.ም አፈፃፀምንና የ2012 እቅድን አስመልክቶ እንደገለፁት፤ ድርጅቱ የመንግስትን አቅጣጫ ተከትሎ በመስራቱና አስተማማኝ አገልግሎት መስጠት በመቻሉ ከጊዜ ወደ ጊዜ ተወዳዳሪና ትርፋማ ሆኗል፡ ፡ ገቢን በተመለከተ በ2011 ዓ.ም ከ2010 ዓ.ም ጋር ሲነፃፀር አንድ ነጥብ ሦስት ቢሊዮን ብር ብልጫ ማሳየት ችሏል፡፡ የእቅዱንም መቶ ሁለት ፐርሰንት አሳክቷል፡፡ የዕቃ ማጓጓዝ ስራን በተቀላጠፈ ሁኔታ በመስራት ከፍተኛ የሆነ የውጭ ምንዛሬን አስገኝቷል፡፡
ድርጅቱ በ2011 ዓ.ም የገቢ ጭነት አምስት ሚሊዮን ቶን ለማጓጓዝ እቅድ ይዞ አራት ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ቶንኑን ማሳካት መቻሉን የተናገሩት ዋና ስራ አስፈፃሚው ይህም ከፍተኛ ስኬት መሆኑን አብራርተዋል፡፡ በተለይ ደግሞ ብረት፣ ስኳርና ለሲሚንቶ ግብአትነት የሚውል ድንጋይ ከዕቅድ በላይ ማጓጓዝ ተችሏል፡፡ የወጪ ንግድን በተመለከተ ጥሩ ስራ የተሰራበትና ትርፍም የተገኘበት መሆኑን ጠቅሰው በወጪ ንግድ መስክም ቡና ከፍተኛውን ድርሻ መያዙን ተናግረዋል፡፡ እንዲሁም በመልቲ ሞዳል አገልግሎት በ2010 ዓ.ም ከተጓጓዘው የ171 ሺ ኮንቲነሮች በ2011 ብልጫ በማሳየት በቁጥር 192ሺ ኮንቲነሮችን በባህር ትራንስፖርት በማጓጓዝ ከፍተኛ ገቢ ማስገባት ተችሏል፡፡ በ2010 አማካኝ የኮንቲነሮች ወደብ ላይ ቆይታ ስምንት ቀን የነበረ ሲሆን በ2011 በአማካኝ ወደ ስድስት ነጥብ አራት ቀን ዝቅ እንዲል በማድረጉ ከሀምሳ አምስት ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪን ማዳን እንደተቻለ አስታውቀዋል፡፡
አቶ ሮባ እንደገለፁት ከዚህ በፊት ስንዴና ማዳበሪያ ወደ ሀገር ውስጥ ይገቡ የነበረው በውጪ የመርከብ ድርጅቶች አማካኝነት ነበር፡፡ ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ መንግስት በወሰነው መሰረት መጠናቸው ወደ 3 ነጥብ 2 ሚሊዮን ቶን ግምት ያላቸው ስንዴና ማዳበሪያን ለማጓጓዝ በቂና ዘመናዊ መርከቦችን ተከራይተን ቅድመ ዝግጅት በማድረግ ላይ ነን ብለዋል፡፡ እንዲሁም ድርጅቱ በ2011ዓ.ም የነበረበትን የአይሲቲ ሲስተም ችግር በማስተካከል በ2012 ሀያ ሰባት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር ለማግኘት ማቀዱን አስረድተዋል፡፡
አዲስ ዘመን መስከረም 11 ቀን 2012 ዓ ም
ሞገስ ፀጋዬ