
አዲስ አበባ፤ የህዳሴው ግድብ የሲቪል ኢንጂነሪንግ፣ የዋናው ግደብ እንዲሁም
የኤሌክትሮ መካኒካል ግንባታ በጥሩ ሂደት ላይ እንደሚገኝና በቅርቡ እንደሚጠናቀቅ ተገለጸ።
የህዳሴው ግድብ ፕሮጀክት ማናጀር ኢንጅነር ክፍሌ ሄሮ ለኢትዮጵያ ሄራልድ ጋዜጣ እንደተናገሩት በአሁኑ ወቅት የዋናው የሳድል የኮርቻ ግድብና ማስተንፈሻው እንዲሁም የሀይል ማስተላለፊያው ግንባታ በአማካይ 84 ነጥብ አምስት በመቶ ተጠናቋል። የዋናው ግድብ ግንባታ 80 ነጥብ ሁለት
በመቶ፤ የሳድል (ኮርቻ) ግድቡ ግንባታ ደግሞ 96 በመቶ መድረሱንም ጠቁመዋል። በአሁኑ ወቅት በሁለቱም በኩል እየተካሄደ ያለው የግንባታ ፍጥነት ሀገሪቱ ያለችበትን የእድገት ጉዞ የሚያመላክትም ነው ብለዋል።
ኢንጅነር ክፍሌ ጨምረው እንደተናገሩት ከሲቪል ምህንድስናው የማስተንፈሻ ቦይ ግንባታው 96 በመቶ የደረሰ ሲሆን የሀይል ማመንጫ ጣቢያውና መቆጣጠሪያውን የሚያካትተው የኤሌክትሮ መካኒካል ግንባታው 69 በመቶ እንዲሁም ሌሎቹ ስራዎች 57 በመቶ መጠናቀቃቸውንም ገልጸዋል።
አጠቃላይ የግድቡ ግንባታ የሲቪል ምህንድስናውን፤ ኤሌክትሮ መካኒካል፤ የሀይል ማመንጫ ሞተር ግንባታውንና የብረታብረት ስራውን ጨምሮ በዓማካይ 68 ነጥብ አምስት በመቶ ደርሷል። ሁሉም ኮንትራክተሮች በቅንጅት የሚሰሩ ከሆነ እ አ አ በ2022 ፕሮጀክቱ የሚጠናቀቅ ይሆናል ሲሉም
የፕሮጀክት ማናጀሩ አስረድተዋል።
ከዚህ ቀደም ግንባታው በአንድና በሁለት ኮንትራክተሮች ይከናወን እንደነበር ያስታወሱት ኢንጅነሩ በአሁኑ ወቅት እየሰሩ ያሉት ግን በርካታ ኮንትራክተሮች በመሆናቸውና ስራው በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው የኮንትራክተሮቹ በህብረት መስራት የግድቡን ግንባታ በተቀመጠለት የግዜ ገደብ ለማጠናቀቅ እንደሚያግዝ አስገንዝበዋል።
አዲስ ዘመን መስከረም 12 ቀን 2012 ዓ ም
ራስወርቅ ሙሉጌታ