ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የነጻነት እንቅስቃሴ መስራችና ዋና ስራ አስፈጻሚ የሆኑት የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ ኦባንግ ሜቶ ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ጋር ስለሀገራችን ወቅታዊ ሁኔታና አስፈላጊ ስለሆኑ ሁነኛ መፍትሄዎች ህዳር 12/2011 ዓ.ም በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ማህበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብዕ ኮሌጅ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ውይይት አድርገዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ደሳለኝ መንገሻ፣ የማህበራዊ ሳይንስና ስነ- ሰብዕ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ካሳሁን ተገኝ፣ ሌሎች የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮችና ምሁራን ውይይቱን ታድመዋል፡፡
ዶ/ር ደሳለኝ በመክፈቻ ንግግራቸው ዩኒቨርሲቲው በተለያዩ ጊዚያት አዋቂና ታዋቂ ግለሰቦችን በመጋበዝ የህይወት ልምዳቸውንና ያላቸውን ዕውቀት ለዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ እንዲያጋሩ የማድረግ ስራ እየሰራ እንደሚገኝ አውስተዋል፡፡ አቶ ኦባንግ የተደረገላቸውን ጥሪ ተቀብለው ስለኢትዮጵያ አንድነትና የተጀመረውን የለውጥ ጉዞ ለማስቀጠል ያላቸውን የካበተ ዕውቀትና ልምድ ለማጋራት ወደ ተቋሙ በመምጣታቸው ፕሬዚዳንቱ ልዩ ምስጋና አቅርበውላቸዋል፡፡
የውይይቱ ርዕስ “አሁን በሀገሪቱ እየታየ ያለው አወንታዊ ለውጥ ይቀጥላል? (Can the right change be sustained in Ethiopia?)” የሚል ሲሆን፣ አቶ ኦባንግ ለታዳሚ ምቹ በሆነና በሚማርክ አቀራረብ ስለ ወቅታዊው የሀገራችን የፖለቲካ ሁኔታ በተለየ ደግሞ ‘ስለሰው ልጅ ነጻነትና ጠቀሜታ እንዲሁም ስለ ኢትዮጵያ አንድነትና አስፈላጊነት’ ያላቸውን ዕውቀትና የህይዎት ተሞክሮ በመጠቀም በስፋት ተንትነዋል፡፡
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ እንዳስታወቀው ጉባኤው ተሳታፊዎች የቀረበውን የህይወት ተሞክሮና ትምህርት መሰረት በማድረግ የተለያዩ ጥያቄዎችን ጠይቀዋል፤ ገንቢ አስተያየቶችን ሰጥተዋል፡፡ አቶ ኦባንግ አስተያየቶችን በመቀበል ለቀረበላቸው ጥያቄዎች በቂ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡