በሰሜን ሸዋ ዞን ጾታዊ ጥቃትና ጎጂ ባህላዊ ድርጊቶችን በሚፈጽሙ ላይ ተጽዕኖ የመፍጠር እንቅስቃሴ ተጀመረ

በሰሜን ሸዋ ዞን በህብረተሰቡ ውስጥ ሆነው ጎጂ ባህላዊ ድርጊቶችና ጾታዊ ጥቃቶችን በሚፈጽሙ ግለሰቦች ላይ ተፅዕኖ የመፍጠር እንቅስቃሴ መጀመሩ ተገለጸ።እንቅስቃሴው ድርጊቱን የፈጸሙ ግለሰቦችን ከዕድር፣ ከማህበርና መሰል እንቅስቃሴዎች ማግለልና ሙሉ በሙሉ ማስወጣትን ተሳቢ ያደረገ ነው።

በዞኑ ሴቶች፣ ህጻናትና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ የሮምነሽ ጋሻውጠና ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ ጾታዊ ጥቃትን ጨምሮ የተለያዩ ጎጂ ባህላዊ ድርጊቶችን በሚፈጽሙ ግለሰቦች ላይ ሕብረተሰቡ ተጽዕኖ የመፍጠር ሥራን ዕውን ማድረግ ጀምሯል።

በዞኑ ከተወሰኑ ጊዚያት ወዲህ ከሚስተዋለው የሰላም ዕጦት ጋር ተያይዞ ጎጂ ባህላዊ ድርጊቶች ተበራክተዋል ያሉት ኃላፊዋ፤ በአሁኑ ጊዜም በተለይ በሴቶችና ህጻናት ላይ የሚደርሰው ጾታዊ ጥቃት እየተባበሰ መሄዱን ተናግረዋል።

እንደኃላፊዋ ገለጻ፤ በዞኑ በ2016 ዓም በቁጥር 64 የሚሆኑ ጾታዊ ጥቃቶች ተፈጽመዋል። ከነዚህ መሀልም 23ቱ ከስድስት ዓመት ጀምሮ ባሉ ህጻናት ላይ የተፈጸሙ ጥቃቶች ናቸው።ይህ አሀዝ ለፖሊስ ሪፖርት የተደረገውን ብቻ የሚያመለክት ነው ያሉት ኃላፊዋ፤ ድርጊቱ ከዕለት ወደዕለት እየጨመረ መሄዱ የሁኔታውን አሳሳቢነት ከፍ አድርጎታል ብለዋል።

ወይዘሮ የሮምነሽ እንደሚሉት፤ በአሁኑ ጊዜ ወንጀሉን ፈጽመዋል የተባሉ 31 ግለሰቦች በህግ ቁጥጥር ሥር ውለዋል። ተጠርጣሪዎቹን በፍርድ ሂደት ውሳኔ ለማሰጠትም እንቅስቃሴው ተጠናክሮ ቀጥሏል።

በዞኑ የተለያዩ ቦታዎች ያለ ዕድሜ ጋብቻን ጨምሮ ሌሎች ጎጂ ባህላዊ ድርጊቶች ይፈጸማሉ ያሉት ኃላፊዋ፤ ዘንድሮ ግን በተለይ በሴቶችና ህፃናት ላይ ጾታዊ ጥቃት ይብቃ ያሉ የተለያዩ ወረዳ ነዋሪዎች የራሳቸውን ህግና መመሪያ አውጥተው ተፅዕኖ የመፍጠር ውሳኔ መጀመራቸውን ገልጸዋል።

እንደ ኃላፊዋ ማብራሪያ ተጽዕኖ የመፍጠር ተግባሩ ያነጣጠረው ድርጊቱን የፈጸሙ ግለሰቦችን ከዕድር፣ ከማህበርና መሰል እንቅስቃሴዎች በማግለልና ሙሉ በሙሉ በማስወጣት ነው። ይህ ውሳኔም ሞት ባጋጠመ ጊዜ ቀብር እንዳይፈጸምላቸው እስከማድረግ የደረሰ ቁርጠኝነት አለው።

በሰሜን ሸዋ ዞን 31 ወረዳዎች ውስጥ 9 የከተማ አስተዳደሮች ይገኛሉ። ይህ በጎ ጅምር ውሳኔው ባልተዳረሰባቸው አካባቢዎች ጭምር ተጠናክሮ እንዲቀጥል እንፈልጋለን ያሉት ኃላፊዋ፤ በተለይ የዕምነት ተቋማትና የዕድር ማህበራት በማህበረሰቡ ዘንድ ተጽዕኗቸው ከፍ ያለ በመሆኑ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል።

በ2017 ዓ.ም የፍትህ አካላት ድርጊቱን ከመከላከል ባሻገር ጸታዊ ጥቃቶች ተፈጽመው ሲገኙ የህግ ተጠያቂነቱን መጠናከር የሚቻልበትን አሰራር ዘርግተዋል። ኃላፊዋ እንደሚሉትም፤ አሰራሩ ከክልል ጀምሮ የተዋቀረ በመሆኑ የሚመለከታቸው አካላት ጭምር የምክክር ሰነድ ተፈራርመው የጋራ ውሳኔ አሳልፈዋል። ጥቃቱ የወቅቱን ነባራዊ ሁኔታ ምክንያት ያደረገ ከመሆኑ ጋርም በተለየ ትኩረት እየተሰራበት እንደሆነም አክለው ገልጸዋል ።

በዞኑ በጾታዊ ጥቃት ሳቢያ ሥነልቦናቸው የተጎዳና ኤኮኖሚያቸው የሚደገፍ ወገኖች መኖራቸውን የጠቀሱትት ወይዘሮ የሮምነሽ፤ ውጤታማ ተግባር ላይ ለመድረስም ግንዛቤ ከማስጨበጥ ባለፈ የሚመለከታቸውና በጎ አድራጊ ተቋማት በበቂ በጀትና አቅም የታገዘ ድጋፍ ሊያደርጉ ይገባል ሲሉ አስታውቀዋል።

መልካምሥራ አፈወርቅ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ታኅሣሥ 22 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You