አዲስ አበባ፦ በጥራጥሬና ቅባት እህሎች የውጪ ንግድ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በአግባቡ መግታት ከተቻለ ዘርፉ ዋነኛ የውጪ ምንዛሬ ምንጭ ሊሆን እንደሚችል አንድ ጥናታዊ ጽሁፍ አመለከተ። ኢትዮጵያ በቅባት እህሎች እና ጥራጥሬ ምርቶች ያላትን እምቅ አቅም ለመጠቀም ዘርፉን የሚመሩ ተቋማት በጋራ መስራትና መናበብ እንዳለባቸው ተመለከተ ።
የጥራጥሬና ቅባት እህሎች ላኪ ማህበር ከጂ አይ ዜድ ጋር በመተባበር ያስጠናው ጥናት ይፋ ሆኖ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት በተደረገበት ወቅት እንደተገለጸው፤ ዘርፉ ከፖሊሲ ፤ ከህግ እና ከሴክተር መስሪያ ቤቶች አፈጻጸም ጋር የተያያዙ ችግሮች አሉበት።
ጥናቱ እንዳመለከተው፤ ከፖሊሲ ጋር በተያያዘ በርካታ ማሻሻያ የሚፈልጉ ጉዳዮች አሉ፤ የመጀመሪያው እና ለዘርፉ እድገት ማነቆ የሆነው ከመሬት ጋር የተያያዘ፤ ዘርፉን የሚቀላቀሉ ኢንቨስተሮች መሬት የሚያገኙበት ሂደት የሚያስረዝመው ቢሮክራሲያዊ አሰራር ነው።
ሰብሎችን በሰፋፊ የእርሻ መሬት በማምረት በፋብሪካ ፕሮሰስ ለማድረግ የሚፈልጉ አልሚዎች መሬት ለማግኘት በአማካኝ 12 ወራት ይወስድባቸዋል። ይህ ደግሞ ባለሀብቶች ወደዘርፉ በስፋት እንዳይገቡ ማነቆ ሆኗል።
ከቅባት እህል እና ጥራጥሬ ግዥ ጋር ተያይዞ ያለው አሰራር በኢትዮጵያ ምርት ገበያ በኩል ብቻ እንዲያልፍ የተደረገበት ሁኔታ በራሱ ተጨማሪ ችግር መሆኑ በጥናቱ ተጠቁሞ ፤ይህም ተጨማሪ የግዥ መንገዶች እንዳይኖሩ ተግዳሮት መሆኑን አስታውቃል። አሁን ላይ የቀጥታ ግዥ ሂደት እና የውል እርሻ አሰራሮች ወደ ስራ ላይ እየገቡ መሆናቸው ችግሩን በተሻለ መንገድ ሊያቃልሉ እንደሚችሉ፤ ይህም ሆኖ አሁንም አተገባበር ላይ ክፍተቶች መኖሩን በጥናቱ ተጠቁሟል።
ሌላኛው የዘርፉ ፈተና ዓለም አቀፍ የገበያ ዋጋ አለመረጋጋት መሆኑን፤ በተለያዩ የአለም ሃገራት የሚደረጉ ጦርነቶች እና የነዳጅ ዋጋ መጨመር የአለም አቀፍ ገበያው የተረጋጋ እንዳይሆን ማድረጉ። ይህም የአርሶ አደሩን እና የላኪዎችን የዋጋ ግመት በማዛባት ተጠቃሚነታቸውን ችግር ውስጥ መክተቱን አስታውቋል።ችግሩን ለመፍታት መንግስት የወደፊት ውል (ፊውቸር ኮንትራት) እና የሰብል
ኢንሹራንሶች በፖሊሲዎች እንዲደገፉ ማድረግ አለበት። ይሄውም የዋጋ ግመታ መዛባት ቢጋጥምም በተወሰነ መልኩ አርሶ አደሩ እና ላኪውን ከኪሳራ ሊጠብቀው እንደሚችል ጥናቱ አመልክቷል።
እንደ ጥናቱ ውጤት ፤ኤዥያን ሀገራት ከአውሮፓውያኑ ጋር ሲነጻጸር ለጥራት ያላቸው ግምት ዝቅተኛ እና ተለዋዋጭ መሆኑ አብዛኛውን የኢትዮጵያ የወጭ ንግድ የሚፈጸመው ከእነሱ ጋር እንዲሆን አድርጓል። ይህም ሆኖ ሀገራቱ አስተማማኝ የንግድ ማዕከል መሆን አለመቻላቸው እና የሚከፍሉት ክፍያ ዝቅተኛ መሆኑ ኢትዮጵያ ለምታመርተው ምርት ተገቢውን ክፍያ እንዳታገኝ አድርጓል።
እንደ አውሮፓውያን ህብረት ያሉ ሀገራት ለምርት ጥራት ከፍተኛ ትኩረት ቢሰጡም የሚከፍሉት ክፍያ እና የሚወስዱት ብዛት አስተማማኝ ነው። በመንግሥት በኩል ለዚህ የሚያፈልጉ የሰርተፍኬት አሰጣጥ ሂደቶች እና የላብራቶሪ ማረጋገጫዎችን የማዘጋጀት ስራዎችን ሊሰራ ይገባል ።
የድፍድፍ ዘይት እና ተመርቶ የተጠናቀቀ ዘይትን ለሚያስገቡ ባለሃብቶች የሚደረገው የድጎማ አሰራር ሸማቹን ማህበረሰብ የሚጠቅም ቢሆንም ሀገር ውስጥ ያሉ አምራቾችን የሚጎዳ እንደሆነ አመልክቷል።
ሁኔታዎችን በማቻቻል እና የሀገር ውስጥ አምራቾችን በመደገፍ ለድፍድፍ ዘይት የሚወጣውን የውጭ ምንዛሬ ማዳን ይገባል። እሴት የተጨመረባቸውን ምርቶችም ለውጭ ኤክስፖርት እንዲደረጉ በማድረግ የውጭ ምንዛሬን ለማግኘት ሊሰራ ይገባል።
በየክልሉ ያሉ የሰርቪስ አሰጣጥ ሂደቶች እና የሰሊጥ ምርት ወደ ቻይና ሲላክ ክፍያው የሚፈጸመው በንግድ ባንክ ብቻ መሆኑ ኤክስፖርተሮቹን እየፈተነ የሚገኝ ጉዳይ መሆኑም በጥናቱ እንደ ማነቆ የተነሳ ነው።
በውይይቱም ተሳታፊ የሆኑ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ላኪዎች በበኩላቸው፤ የአኩሪ አተር ምርት በውጭ ገበያው ላይ ከፍተኛ ተፈላጊነት ያለው ቢሆንም በሀገር ውስጥ በቂ ምርት መመረት አለመቻሉ እና ገበሬዎች የሚከተሉት የአስተራረስ ዘዴ ኋላ ቀር መሆኑ ለላኪዎች ፈተና ነው።
በመንግሥት በኩል እየተደረገላቸው ያለው የታክስ ማበረታቻ እና የገንዘብ ወለድ መጠን ዝቅተኛ መሆን ጥሩ የሚባል ቢሆንም ባንኮች ለብድር ሲጠየቁ ገንዘብ የለንም ማለታቸው፤ ኤክስፖርተሮች እቅድ የሌላቸው እና አንድን ባለሃብት ስላዋጣው ብቻ እነሱንም የሚያዋጣ ስለሚመስላቸው ወደ ዘርፉ መቀላቀላቸው ለዘርፉ ትልቅ ማነቆ መሆኑን ተናግረዋል። በምርት ገበያ በኩልም የምርት ጥራን ለማስጠበቅ የሚደረገው አሰራር መልካም መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በቅባት እህሎች እና ጥራጥሬ ምርቶች ያላትን እምቅ አቅም ለመጠቀም ዘርፉን የሚመሩ ተቋማት በጋራ መስራትና መናበብ እንዳለባቸው ጠቁመው፤ በቀጣይ ከጥናቱ አጥኝዎች ጋር በጋራ በመስራት ተጨባጭ ለውጥ እንዲመጣ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።
መክሊት ወንድወሰን
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 22 ቀን 2017 ዓ.ም