አዲስአበባ፦ የአረንጓዴ አሻራና የተጎሳቆለ መሬት ማገገሚያ ልዩ ፈንድ ማቋቋሚያና አስተዳደር አዋጅ መውጣት ኢትዮጵያን በዓለም አደባባይ ከፍ የሚያደርግና ተቀባይነቷ እንዲጨምር የሚያደርግ መሆኑን የኢትዮጵያ ደን ልማት አስታወቀ።
6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 12ኛ መደበኛ ስብሰባው የአረንጓዴ አሻራና የተጎሳቆለ መሬት ማገገሚያ ልዩ ፈንድ ማቋቋሚያና አስተዳደር አዋጅን መርምሮ በሙሉ ድምጽ ማፅደቁ የሚታወስ ነው።
ይህን አስመልክቶ የኢትዮጵያ ደን ልማት ዋና ዳይሬክተር አቶ ከበደ ይማም ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፣ የአየን ንብረት ለውጥ፣ ብክለትና ብክነት የምድራችን ዋነኛ ፈተና መሆን ከጀመረ ዋል አደር ብሏል። ለዚህ የዓለም ዋነኛ ስጋት ተጨባጭና ተግባራዊ ምላሽ በመስጠት ኢትዮጵያ ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ናት። ከ2010 ጀምሮ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ሃሳብ አመንጪነትና በመላ ሕዝቡ ተሳትፎ ተግባራዊ በመደረግ ላይ የሚገኘው የአረንጓዴ አሻራ ለዚህ ማሳያ ነው።
ይህን ጥረት ይበልጥ በሚደግፍ መልኩ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአረንጓዴ አሻራና የተጎሳቆለ መሬት ማገገሚያ ልዩ ፈንድ ማቋቋሚያና አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 1361/17 ማፅደቁን ያስታወሱት አቶ ከበደ፤ የአዋጁ መውጣትም የኢትዮጵያ መንግሥት ለተፈጥሮ ሀብትና አካባቢ እንክብካቤ እንዲሁም የአካባቢ ብክለትና ብክነትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ያለውን ሁለንተናዊ ቁርጠኝነት በግልፅ ያሳያል››ብለዋል።
ትግበራው ከመንግሥት በጀት እንዲመደብ የሚያስችል መሆኑንና ደኖችን ለመንከባከብና ለማልማት አረንጓዴ አሻራን ለማስፋፋት አቅም የሚፈጥር መሆኑን ያስገነዘቡት አቶ ከበደ፤ ‹‹ለዘርፉ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት የሀገር መሪ የእለት እለት አጀንዳ ሲሆንና ለውጤታማ ትግበራውም ሀብት ተመድቦለት ወደ እንቅስቃሴ ሲገባም በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመሪያው ነው››ብለዋል።
የአዋጁ መውጣት ኢትዮጵያን በዓለም አደባባይ ከፍ የሚያደርግና ተቀባይነቷን ከፍ የሚያደርግ መሆኑንም አስገንዝበዋል። ኢትዮጵያ በደን ዘርፍ ከልማት አጋሮችና ከሌሎች ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ፋይናንስ ሰጪ ምንጮች እና ከካርበን ግብይት ሥርዓቶች የምታገኘውን ድጋፍና ጥቅም ለማሳደግ የሚያስችል መሆኑንም ጠቁመዋል።
ታምራት ተስፋዬ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 22 ቀን 2017 ዓ.ም