ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ዓለም አቀፍ እውቅና ያላቸው የእውቀት ማዕድ ናቸው። በዚህ ተልዕኳቸውም ከአገር አልፎ ለዓለም የሚተርፉ የምርምር እና ስልጠና ውጤቶች የሚፈልቁባቸው ናቸው። በመሆኑም ተቋማቱ ከዘመናዊ አስተሳሰብ ጋር ተያይዞ ሰፋ ያለ አበርክቶ እንዳላቸው ይታመናል። ከዚህ እሳቤ ስንነሳ የአገራችን ዩኒቨርሲቲዎችም የጋራ ባህሪን የሚጋሩ ቢሆንም በበርካታ ጉዳዮች የአገሪቱ ፖለቲካ ሲያስነጥሰው የሚያስነጥሳቸው መሆኑ ደግሞ በተቃራኒው የእውቀት አውድነታቸውን ይቀንሰዋል። ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነው ያሳለፍነው 2011 ዓ.ም ዩኒቨርሲቲዎቹ የነበራቸው ገሀድ የወጣ ባህሪያቸው ነው።
በዚህም የተነሳ በአገራችን የከፍተኛ ትምህርት ታሪክ እንደ 2011 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ከውጭም ሆነ ከውስጥ በሚነሱ ውሀ የማይቋጥሩ ምክንያቶች የሚቀሰቀሱ ግጭቶች ለበርካታ ውድመት ዳርገውናል፤ የትምህርት ጊዜም እንዲባክን ሆኗል። ይህ ወቅት ልጆቻችንን ያጣንበት ዓመት የተለየ ጥቁር ጠባሳ አስቀምጦብናል። የዚህ ውድመት ዋናው ገፊ ምክንያት የአንዳንድ ተማሪዎች የስነምግባር ውድቀት፣ አንዳንድ መምህራን እና የዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ አባላት ከሙያዊ ስነምግባር ባፈነገጠ መልኩ ፖለቲካውን ከትምህርቱ ጋር በማደባለቅ ሁኔታውን ማጦዝ፣ ወዘተ በመሆኑ ብዙ አስተዛዝቦ አልፏል።
ትምህርት ሚኒስቴርም ሆነ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ችግሩን ለመፍታት ጥረት ቢያደርጉም ሙሉ ለሙሉ መፍታት አልቻሉም። ይሁን እንጂ እነዚህ ተቋማት ከዚህ መጥፎ ክስተት የወሰዱት ትምህርት እና ለ2012 ዓ.ም ሁኔታውን ለመቆጣጠር ያደረጉት ጥረት በሌላ ጎኑ የሚመሰገን ነው። በመሆኑም ዘንድሮ በዩኒቨርሲቲዎች ሰላማዊ መማር ማስተማርን እውን ለማድረግ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር በጥብቅ ሁኔታ ሊተገበር የሚገባው የስነምግባር መመሪያና ደንብ አዘጋጅቷል።
ዩኒቨርሲቲዎች ባለፈው የትምህርት ዘመን በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ማለፋቸው ከተማረ ሀይል የማይጠበቅ እና ተማሪዎች በሐሳብ ልዕልና በመከራከር መተማመን ሲችሉ ከውጭ የሚነሱ ፖለቲካዊ ሁኔታዎችን ምክንያት በማድረግ ሲከሰቱ በነበሩ ሳንካዎች ትምህርታቸውን የማስተጓጎል፣ በቡድን መደባደብና መገዳደል አሳዛኝ ክስተቶች እንደነበሩ የማንደብቃቸው ተግባራት ናቸው።
በመሆኑም የተዘጋጀው መመሪያና ደንብ ከላይ የተጠቀሰውን አይነት ህግና ሥርዓትን ተከትለው በማይንቀሳቀሱ የዩኒቨርሲቲ መምህራን፣ ተማሪዎች እና የትምህርት ማህበረሰብ ላይ ጠበቅ ያለ እርምጃ የሚወሰድ መሆኑን ሚኒስቴሩ አሳስቧል። ዩኒቨርሲቲዎችም ለዚህ ዝግጁ ናቸው። ካለፉት ዓመታት ችግሮች በመማር፣ የመማር ማስተማሩ ሂደት ሰላማዊ እንዲሆን ለማድረግ እንዲሁም ከህግና ሥርዓት ውጪ የሆኑ ነገሮችን የማረም ሥራ በ2012 የትምህርት ዘመን መስራት ወሳኝ ጉዳይ መሆኑ ከዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንቶች ጋር መግባባትና የጋራ አቋም ተይዟል።
ከዚህ ጋር ተያይዞ በተቋማቱ ውስጥ የሚታዩ የአሰራርና የአመራር ችግሮችንም መለየትና መፍታት ይገባል። በዩኒቨርሲቲ ውስጥ ያለ ተማሪም ሆነ መምህር አለባበስ፣ የጸጉር አቆራረጥ እና ሌላውም ሥርዓት ያለው ሊሆን እንደሚገባም መመሪያው ቢያስገነዝብም ሁሉም ሊገነዘበውና ሊተገብረው ግድ ነው። አሁን በአንዳንድ ተቋማት ውስጥ የሚታየው መምህሩ ከተማሪው የማይለይበት ሁኔታ፣ መምህር እንደ ቀለም አባትነቱ በአለባበሱ፣ በጸጉር አቆራረጡም ሆነ በሌላውም አርአያ ሊሆን ሲገባ ከዚህ በተቃራኒ መገኘቱ ብቻ ሳይሆን በዚህ ዙሪያ የተልፈሰፈሱ ቁጥጥሮች ዘንድሮ ሊደገሙ አይገባም።
በተቋማቱ ሌሎች ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞችም ተማሪውን ብስጭት ውስጥ የሚከቱ፣ የራሳቸው አጀንዳ እንዲፈጸምላቸው የሚፈልጉ አሉ። ለእነዚህ አካላት ከዚህ በኋላ እድል ሊሰጣቸው አይገባም። ከግቢ ጥበቃ ጀምሮ በመታወቂያ ከሚነሱ አተካራዎች እስከ መኝታ ክፍል ድረስ እንዲሁም በካፍቴሪያ፣ ቤተመጽሐፍት፣ ላብራቶሪ፣ ሬጅስትራር ያሉ ሠራተኞች ተማሪዎቻቸውን የሚይዙበት አግባብ ሊፈተሽ ይገባል። ለዚህም ችግር መመሪያውን በሚገባ መተግበር የሁሉም ተቋማት ድርሻ ነው።
በዩኒቨርሲቲዎች ዙሪያ የሚገኙና የተማሪውን ስነምግባር የሚያበላሹ አንዳንድ የንግድ ተግባራትም ሊፈተሹና በህጉ መሰረት የሚሰሩበት መንገድ ተግባራዊ ሊሆን ይገባል። በተለይ ከመጠጥና አደንዛዥ እፆች ጋር ተያይዞ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ዙሪያ የሚታዩ አዋኪ ነገሮች ጥብቅ ቁጥጥርና እርምጃ ሊወሰድባቸው ይገባል። ተማሪዎች፣ መምህራን እና ሌሎች የዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ አባላትም ስርዓት አልበኝነት ከትምህርት ገበታ የሚያስባርርና እርምጃ የሚያስወስድ መሆኑን ሊገነዘቡ ይገባል።
በአጠቃላይ ዩኒቨርሲቲዎቻችን በ2012 ዓ.ም የውስጥ ክፍተቶቻቸውን አርመው፣ የውጭ ግፊትን ተቋቁመው የመማር ማስተማር ሂደቱን የተሳካ የሚያደርጉበት ዘመን እንዲሆን በመንግሥት በኩል የተጀመረው እርምጃ የሚበረታታ በመሆኑ በሁሉም የትምህርት ማህበረሰብ ሊደገፍና ተግባራዊ ሊሆን ይገባል። እያንዳንዱ ወላጅ፣ ተማሪ እና በየደረጃው ያለው አስተዳደርም ለሰላማዊ የመማር ማስተማሩ ስኬታማነት የበኩላቸውን ድርሻ ሊወጡ ይገባል።
አዲስ ዘመን መስከረም 8/ 2012