ወጣቶችን በተለያዩ የክህሎት ስልጠና በመደገፍ ከተረጂነት ማውጣት ተገቢ ነው። በመሆኑም የራሳቸውን ስራ መፍጠር የሚችሉበትን ሀሳብ ከማቀንቀን ባለፈ በአንድ በማሰባሰብና በማደራጀት በተግባር ስራ ላይ እንዲሰማሩ ማድረግ ደግሞ ያስፈልጋል። ይህ ሲሆን በሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ተሳትፎዎችን በመምራትና በማጎልበት በኩል የወጣቶች ሚና የላቀ እየሆነ ይሄዳል።
በዚህ ረገድ በርካታ ተግባራት በማከናወን ላይ የሚገኘውና በመጪዋ ኢትዮጵያ የወጣቱን የአመራርነት ተሳትፎ ማላቅ (Empowering Next Generation of Ethiopia) የሚል የበጎ አድራጎት ማህበር መስርቶ በሥራ አስኪያጅነት የሚሰራው ወጣት አልአዛር ዘላለም ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ቆይታ አድርጓል። ሙሉ ቃለ ምልልሱን እነሆ።
አዲስ ዘመን፡- ወጣት አልአዛር የት ተወለደ?
ወጣት አልአዛር፡- መልካም። ተወልጄ ያደግኩት ጅማ ከተማ ነው። በኮምፒውተር ሳይንስ የመጀመሪያ ዲግሪ አለኝ።
አዲስ ዘመን፡- የበጎ አድራጎት ማህበሩን መቼና በማን ተመሰረተ?
ወጣት አልአዛር፡- ነሐሴ 24፣ 2011 ዓ.ም ድርጅታችን በይፋ ምስረታውን፣ በፃፍኩት ‹‹የአለም እሽት›› የተሰኘ መጽሐፍ ሚኒስትሮችና የዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንቶች በተገኙበት ተመርቋል። እንደ መጀመሪያ ደመወዜ ሁሉ ከመጽሐፉ ሽያጭ የሚገኘው ገቢ ሙሉ በሙሉ ለበጎ ሥራው የሚውል ነው። የበጎ አድራጎት ማህበሩን የመሰረትነው ገመቹ ታዬ፣ አርዕስት ዐብይ እና አይዛክ በዛብህ የሚባሉ የለውጥ አቀንቃኝ ወጣቶች ተሰባስበን ነው።
አዲስ ዘመን፡- ድርጅቱ የተመሰረተበት ዋና አላማ ምንድን ነው? ከምን አስተሳሰብ ተነስታችሁ ነው በዚህ ላይ መስራት የጀመራ ችሁት?
ወጣት አልአዛር፡- ሰው ተረድቶ አይለወጥም። ሰውን ረድቶ እስከተወሰነ መንገድ ድረስ መውሰድ ይቻላል፤ ሰው ተደግፎ የሆነ የሕይወት አቅጣጫ እንዲይዝ ማድረግ ይቻላል። ነገር ግን በሕይወቱ ደረጃ ለውጥ የሚኖረው በመረዳቱ ሳይሆን ሰውየውን ከሆነ እውቀት ጋር ማገናኘት ሲቻል ነው ከሚል እምነት ተነስተን ነው። በአንድ ሰው ሕይወት ደረጃ ተጽዕኖ ማምጣት የሚችለው በመረዳት አይደለም የሚል እምነት አለን።
አዲስ ዘመን፡- የምትከተሉት መርህ ሰው መረዳት የለበትም የሚል ነው?
ወጣት አልአዛር፡- እኔም ይሄን ጉዳይ አስምሬ መናገር እፈልጋለሁ። ልብ የሌለኝና የማላዝን፣ ሰው ተቸግሮ እያየሁ ከመርዳት ይልቅ አስተያየት መስጠት የሚመቸኝ ሆኜ አይደለም። እንደውም በችግራቸው ወቅት ሳያቸው መንፈሴ ይረበሻል። በዚህ የተነሳ ከዚህ በፊት ብዙ ጣጣ ውስጥ ገብቼ አውቃለሁ። ለብዙ ሰዎች ገንዘብ በጥሬው አንሰጥም። ሰዎች አቅም ያጡበትን መንገድ ለይተን እንጠይቃለን። ምንድን ነው መስራት የምትፈልጉት ብለን እናማክራቸዋለን። ክፍተቱ በተገቢው ተለይቶ ነው ሰው ሊደገፍ የሚገባው የሚል አቋም አለን።
አዲስ ዘመን፡- ’’ሰው ተረድቶ አይለወጥም‘ የሚለው ከምን አንጻር ነው?
ወጣት አልአዛር፡- ሕይወቱን በሙሉ አንድ ሰው እየተረዳ መኖር የለበትም። ስንፈጠር አንዳችን ረጂ አንዳችን ተረጂ ሆነን ለመኖር አልተፈጠርንም። በረጂና በተረጂ ዘርፍ እንዲኖር ፈጣሪ ሰውን አልፈጠረም። ነገር ግን በሕይወት አጋጣሚ ሁሉም ሰው ቸግሮት ተረድቶ ሊያውቅ ይችላል። ስለዚህ ሁሉም ሰው በእርዳታ ውስጥ ያልፋል።
ማወቅና ለይተን መገንዘብ ያለብን በእርዳታ ውስጥ ማለፍ ማለት በእርዳታ ውስጥ መኖር ማለት አለመሆኑን ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ እየኖርን አይነቱ ይለያይ እንጂ መረዳታችን የማይቀር ነው። ስለዚህ ሰው ተረድቶ አይለወጥም የሚለው ራሱን ለመረዳት አሳልፎ የሰጠን ሰው የሚመለከት ነው። በፈጣሪ እኩል የተፈጠረ ሰው ሙሉ ዘመኑን ተረጂ ሆኖ አፈር መቅመስ አለበት ብዬ አላምንም።
አዲስ ዘመን፡-ተጨባጭ ተሞክሮ ላይ መነሻ አድርገህ ነው ይሄን ለማለት የበቃኸው?
ወጣት አልአዛር፡- አዎ ሁለት ነገር ነው መነሻዬ። አንደኛው በስራ ዓለም የረዳናቸው ሰዎች መልሰው ተረጂ ሆነው አይቻለሁ። ዓመት አልፎ ዓመት ሲተካ በየዓመቱ ተረጂዎች አሉ። እኛ ስትራቴጂ እየቀያየርን እንረዳለን እነሱም ስትራቴጂ እየቀያየሩ ይረዳሉ። ይሄ ጉዳይ በእውነት ልብ የሚነካ ነው። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ሁላችን አፈር ውስጥ እንገባለን እኛ ረጂ እነሱ ተረጂ እንደሆኑ።
ስለዚህ ይሄ ለኔ ቁስል ሆኖብኝ ነበር። መረዳቱን እንደ ማለፊያ መንገድ ከመጠቀም ይልቅ እንደመኖሪያቸው ሲቆጥሩት ታያለህ። ለሆዳቸው ምግብ እየሰጠን ሕሊናቸው ሲሞት፣ ሲጎዱ፣ አልሰማቸው ሲል ብዙ ሰዎችን አየሁ። በተለይ ሕጻናት የጎዳና ተዳዳሪዎች አካባቢ ችግሩ የከፋ ነው። ሕጻናቱን በጎዳና እንዳሉ ይወልዷቸዋል፤ እዚያው እያሉ ሕጻናቱ መለመን ይጀምራሉ። እነዚህ ልጆች ሲለምኑ የሞራል ምንም ችግር የለባቸውም። በተፈጥሮ መለመን እጣቸው የሆነ መስሏቸው ይሆን እንዴ ብዬ ራሴን እጠይቃለሁ። ምክንያቱም እንደተወለድክ ያየኸው ነገር ተፈጥሮህ ነው የሚመስልህ። በዚህ ደረጃ ልመና ሕይወታቸውን ሳይለውጥ ተጽዕኖ ሲፈጥር ማየቴ አንዱ ምክንያቴ ነው።
ሁለተኛው ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ በተለያየ ማህበረሰብ ውስጥ ስትኖር የተለያዩ የእርዳታ ድርጅቶች እያየህና እየሰማህ ታድጋለህ። ከውጪ የመጣ የሆነ ድርጅት እረድቶ ያልፋል። አሁንም ሌላ ድርጅት ይመጣል ሰዎች ተጠራርተው ይረዳል። ሌላም ይመጣል ይረዳል፤ ይረዳሉ፣ ይቀጥላል። ይሄ ጤናማ ነገር አይደለም።
አዲስ ዘመን፡- ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ የተለየ ገጠመኝ ይኖርሃል?
ወጣት አልአዛር፡- አንድ ገጠመኝ ልንገርህ። ሰዎችን እረድተናቸው፣ አሰልጥነናቸው፤ መንገድ አሳይተናቸው፣ጥሩ ሥራ አስጀምረናቸው፣ በጥሩ ደረጃ ይሠራሉ። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ትልቅ ደረጃ ላይ ደርሰው እናገኛቸዋለን ብለን ስንመኝ አሁንም ቀይ መብራት ካስቆመው መኪና ስር ቆመው ሲለምኑ ስታይ ልብህ ያዝናል። እነዚህን ሰዎች ገንዘብ ብቻ ነው የሰጠናቸው ማለት ነው? እንድትል ያደርግሃል። ከሪፖርት የዘለለ ለውጥ በሕይወታቸው ካላየህ ልብህ ይሰበራል።
አዲስ ዘመን፡- ችግሩ የማን ነው?
ወጣት አልአዛር፡- ችግሩ የማን ነው የሚለውን አንባቢዎች እንዲያስቡበት እተወዋለሁ። በርካታ ነገር ኢንቨስት ያደረግክበት ሰው አሁንም ተመልሶ እዛው ቦታ ሲገኝ ስታየው ያማል፤ ያሳዝናም። በነገርህ ላይ እኛ አገር ሆኖ ነው እንጂ ሰው በተፈጥሮው ነው መብላት ያለበት፤ ማንም ሊያበላው አይገባም። ምግብ፣ መጠለያ እና ልብስ ሰው በተፈጥሮው ማግኘት ያለበት ጉዳይ ነው። ሰውን ስላበላኸውም አይለወጥም።
አዲስ ዘመን፡- ምን መሰራት አለበት? እነዚህ ሰዎች ምንድን ነው የጎደላቸው?
ወጣት አልአዛር፡- በዚህ ጉዳይ ላይ ሚዛናዊ መሆን ያስፈልጋል። ምሳ ለቸገረው ሰው፤ ምሳ ማብላት እንጂ ምክር አያስፈልገውም። እኔ በሚዲያ አውርቼው ሲያበቃ መሬት ላይ የምታየው የተለየ ከሆነ ችግር ነው። የታዘብኩት የብዙ ሰዎች ችግርም እንዲህ አይነት ነው። መድረክ ላይ ቆመህ የምታወራውና መሬት ላይ ቆመህ የምትኖረው የተለያየ እየሆነ ነው። መሬት ላይ ሊገኝ የሚችል እውነት የሆነ ነገር ነው ማንሳትና ማውራት የምፈልገው። የተቸገረ ሰው መታገዝ፣ መረዳትና መደገፍ አለበት። ይሄን ማድረግ ግዴታ ነው በፈጣሪም ትባረክበታለህ፤ ሰው ስትሆን የሕይወትን ትርጉም ታገኝበታለህ። እኔ በመኖሬ እገሌ ተጠቀመ እንድትል ያደርግሃል።
ይሄ እውነት እንደተጠበቀ ሆኖ በተመጣጣኝ ደረጃ በሰዎች አዕምሮ ላይ መሰራት አለበት። በሰዎች አስተሳሰብ ላይ ሊሰራ ይገባል። እርዳታ የተወሰነ ጊዜ ማለፊያ እንጂ የሕይወት ዘመን ገጽታቸው እንዳልሆነ ሊነገራቸው ይገባል። የተለያዩ ሰዎች እንዳለፉበት እነሱም የሚያልፉበት መንገድ እንደሆነ ማወቅ አለባቸው።
እየረዳናችሁ አይደለም እየደገፍናችሁ ነው እንድትቆሙ ብለን በግልጽ አስምረን ልንነግራቸው ይገባል። እኔ በብዙ ነገር ጉዳት በደረሰበት ሰው ላይም ተስፋ አያለሁ። እንደምንም ብሎ የሆነ ሥራ ጀምሮ ቢለወጥ ምን ያህል ሰዎች ላይ ተጽዕኖ መፍጠር እንደሚችል መገመት አይከብድም። ተመሳሳይ መንገድ እየሄዱ አዲስ ነገር መጠበቅ ይቸግራል። ሰውን መንግስት ሲያታልለው አደገኛ ነው። ጓደኛም ሲያታልለው እንዲሁ። የመጨረሻው አስፈሪ ግን ሰው ራሱን ማታለል ሲጀምር ነው።
ዘመኑን በሙሉ በጀት ሳያስፈልገው በከንቱ ያሳልፋል። አታላይ አያስፈልገውም። በእርዳታ ውስጥ ለውጥ አለ የሚል ራስን ማታለል ይቅር። አንድ ባዶ ዝግ ቤት ውስጥ መቶ ብር ቢኖርና አንተ ለኔ፣ እኔ ለእሷ ስናቀብል ብንውል ያው መቶ ብር ነው። እዚህ አገር ውስጥ ማን ማንን ነው የሚረዳው እንደው መንገድ ለማሳየት ያህል ካልሆነ በስተቀር። ስለዚህ አዲስ ነገር ይፈጠር የሚል ጩኸት ነው የምናሰማው።
አዲስ ዘመን፡- ስልጠናውን በእድሜ ለይታችሁ በተግባር ምን እየሰራችሁ ነው?
ወጣት አልአዛር፡- እኛ ቅድም እንደነገርኩህ ብዙ ነገር እየሰራን ነው። ያለንን ሰጥተን ሰዎች እንዲለወጡ እንጥራለን። አሁን እንደአገር በየአካባቢዎች ጉዞ እናደርጋለን። በዚህ ጊዜ አስተሳሰብን ሊለውጡ የሚ ችሉ የተለያዩ አስተማሪ ዝግጅቶች እናቀርባለን። ከ6ኛ ክፍል እስከ 12ኛ ክፍል ላሉ ወጣቶች የሕይወት ክህሎት ስልጠና መድረኮች፣ ፊስቲቫሎች፣ ስልጠናዎች እያመቻቸን እንሰጣለን። አስተሳሰብና በተግባር የተለወጡ ሰዎችን በመጋበዝ የልምድ ለውውጥ ይካሄዳል። የደብተር፣ የደንብ ልብስና የተለያዩ ቁሳቁሶች ድጋፍ እናደርጋለን።
በምንሄድበት አገር ሁሉ የከፋ ቆሻሻ ያለበትን ጠይቀን እናጸዳለን የእኛን ተሞክሮ የሚቀበሉ የአካባቢው ወጣቶች ተግባሩን እንዲያስቀጥሉም ድጋፍ እናደርጋለን፤ ሀረርና ጅማን በምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል። ሰው ልጅ አስተሳሰብ እንዲጸዳ በመስራት ላይ ነን። በቋሚነት ደም የመለገስና ችግኝ የመትከል እቅድ አለን።
አዲስ ዘመን፡- የምትሰጧቸው ስልጠናዎች ይዘት ምንድን ነው?
ወጣት አልአዛር፡- 16 አካባቢ የሚሆኑ የሕይወት ክህሎት ስልጠናዎች አሉ። የመጀመሪያ የህክምና እርዳታ አስጣጥ፣ የሥራ ፈጠራ ፅንሰ ሀሳብ እና ሌሎች ጉዳዮችን ወጣቶች በትምህርት ቤት ላይ እንዳሉ እንዲያውቁ እናስተምራለን። ራስን መቀበል፣ ማንነትን መቀበል ሥልጠና ይሰጣል። ሱስ አልባ ሕይወትን መምራት ለየትኛውም ቅጠል፣ እንጨትና ሌላ ነገር ወጣቶች ተገዥ ሳይሆኑ ማደግና ሕይወታቸውን መምራት እንዲችሉ ስልጠናዎች ይሰጣሉ። ተሰጥኦን ተንከባክቦ ማሳደግ በትኩረት እየሰራን ነው።
አዲስ ዘመን፡- የአስተሳሰብ ንጽህናን የመፍጠርና መልካም ወጣት የመገንባት ተግባር እየተሰራበት ነው። በእናንተ በኩል ምን ትኩረት ተሰጥቶታል?
ወጣት አልአዛር፡- ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር ዐብይ ናቸው ሀሳቡን ያመነጩት። ለዚች አገር በጣም ብዙ መልካም ነገሮች ይዘው መጥተዋል። የአስተሳሰብ ንጽህና አንዱ ነው። ሁሉም ሰው የራሱን አስተያየት መስጠት መብቱ ነው። ለምሳሌ እኔ ሰማይ ከምድር እሩቅ ነው ስልህ አይ እኔ በዚህ አላምንም ማለት መብትህ ነው። ግን አሳዛኙ እውነት ማመንም ሆነ አለማመን አይጠበቅም። ሰማይ እሩቅ ነው። በዚህ ደረጃ የአስተሳሰብ ነጻነትን ይዘው መጥተዋል።
ኢትዮጵያውያን በዚህ ሰዓት ምግብ እንጂ ምክር ምን ያደርግላቸዋል ብዬ እንደ ብዙው ሰው እኔም አምን ነበር። ግን አሁን ከዶሮና ከእንቁላል የቱ ይቀድማል በሚል አስተሳሰብ ውስጥ ነኝ ያለሁት። የምግቡ ችግር ከአስተሳሰብ የሚጀምር መሆኑን ተረድቻለሁ። በአስተሳሰብ ዙሪያ ሰፊ ክፍተት ይስተዋላል። ስለዚህ እሱን በሽታ ነቅሎ ማከም ከተቻለ መራመድ ያስችላል። ስለዚህ ጠቅላይ ሚንስትሩ በአስተሳሰብ ላይ የጀመሩት ትክክለኛ ተግባር ነው እላለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ለሰጡን አስተያየት እናመሰግ ናለን።
ወጣት አልአዛር ፡- እኔም አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን መስከረም 8 / 2012
ሙሐመድ ሁሴን