
ጅማ፡- የታቀደለት የጥገና ሥራ ሳይሳካ ከአንድ ዓመት በላይ ያስቆጠረው የአባ ጅፋር ቤተ- መንግሥት በሃያ ወራት ለማጠናቀቅ የጥገናው ሥራ መጀመሩን የጅማ ከተማ ባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ አብዱልመሊክ ሙሳ የቤተ መንግሥቱ ጥገና ከአሜሪካ በመጡና በአገር ወስጥ ባለሙያዎች ጳጉሜን ሁለት ቀን 2011 ዓ.ም መጀመሩን ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ የተናገሩ ሲሆን፤ ለጥገናው የሚያስፈልጉ ግብዓቶች ማዘጋጃ ክፍል እየተሰራና ለአገር ውስጥ ባለሙያዎች ስልጠና እየተሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።
በጥገናው ቤተ መንግሥቱ የተሰራበትን የእንጨት መዋቅር ጠንካራውን የማደስና የተበላሸውን የመቀየር ሥራ ይሰራል ያሉት አቶ አብዱልመሊክ፤ ለጥገናው የሚሆን እንጨት፣ ለግድግዳው የሚሆን ድንጋይ፣ለግንቡ ጭቃና ሌሎች ቁሶች ከአካባቢው መገኘታቸው በባለሙያዎች መረጋገጡን ገልጸዋል።
እንደ ኃላፊው ማብራሪያ ጥገናው በልዩ ባለሙያዎችና በጥንቃቄ የሚሰራ በመሆኑ የእንጨት፣ የድንጋይ፣ የጭቃና ሌሎች ሥራዎችን የሚመሩ አራት ዓለም አቀፍ የጥገና ፍቃድ ያላቸው ባለሙያዎች ከአሜሪካ፣ ከአገር ወስጥ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን ባለሙያዎች፣ ከጅማ አምስት የሰለጠኑ የእንጨት ባለሙያዎችና ስለቅርሱ እውቀት ያላቸው የአካባቢው የልምድ አዋቂዎች በሥራው ይሳተፋሉ።
ሥራውን የሚቆጣጠር ድርጅት መቀጠሩን የተናገሩት ኃላፊው፤ በተለይም በእንጨት ጥገና ስልጠና የወሰዱት ባለሙያዎች አሁን ለሚካሄደው ጥገና ብቻ ሳይሆን በቀጣይ በአገሪቱ በእንጨት ለሚካሄዱ የቅርስ ጥገናዎች ደጋፊ እንደሚሆኑ አስረድተዋል።
ኃላፊው ለቅርስ ጥገናው ከወርልድ ሞንመንት ለሚመጡት ባለሙያዎች ክፍያ ከሰባት እስከ ስምንት ሚሊዮን ብር ድጋፍ መደረጉን ፣ የቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን የጥገናውንና የአገር ውስጥ ባለሙያዎች ወጪ መሸፈኑንና የኦሮሚያ ክልል ለጥገናው የሚሆኑ ማሽነሪዎች መለገሱን ጠቁመው፤ የጥገናው ሂደት ከከተማ አስተዳደሩ ጋር ክትትል እንደሚደረግበት ገልጸዋል።
የአባ ጅፋር ቤተ መንግሥት ባለፉት ዓመታት ቀደም ሲል ከነበረው ይዞታ በነዋሪዎች ተገፍቶ የጠበበ ሲሆን፤ ቤተ መንግሥቱን ወደ ነባሩ ይዞታው የመመለስና ሌሎች በከተማዋ ለሚገኙ ቅርሶች የይዞታ ካርታ መሰራቱን አስረድተዋል።
ቤተ መንግሥቱ የመፍረስ አደጋ ተጋርጦበት ይጠገናል ከተባለ ከአንድ ዓመት በላይ ማስቆጠሩን የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ‹‹ከእጃችን ሊያመልጥ ጥቂት የቀረው የአባጅፋር ቤተ መንግሥት›› በሚል በሐምሌ 3 ቀን 2011 ዓ.ም የረቡዕ ዕትም ማስነበቡ ይታወሳል።
አዲስ ዘመን መስከረም 7/2012
አጎናፍር ገዛኸኝ