
አዲስ አበባ፦ በሦስተኛው ዙር የምግብ ዋስትና መርሐ ግብር በታቀፉ ስድስት ከተሞች 141 ሺ115 የሚሆኑ ዜጎች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ የፌዴራል የከተሞች የሥራ ዕድል ፈጠራና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ ገለፀ ።
የኤጀንሲው የኮሙዩኒኬሽን ቡድን መሪ ወይዘሮ አቦዘነች ነጋሽ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለፁት፣ ከሐምሌ 1 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ መሆን በጀመረው ሦስተኛው ዙር የምግብ ዋስትና ፕሮግራም ተጠቃሚ የሚሆኑት ከአዲስ አበባ 92 ሺ 5፣ ከአዳማ 9 ሺ 771፣ ከድሬዳዋ 15 ሺ 610፣ ከሀዋሳ 11 ሺ 940 ፣ ከመቀሌ 4 ሺ 986 እና ከደሴ 6 ሺ 804 ዜጎች ናቸው።
በምግብ ዋስትና የታቀፉት ዜጎች በደረቅ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ፣ በአካባቢ ፅዳት፣ በዕፅዋትና ተክሎች ማሳመር፣ በተቀናጀ የተፋሰስ ልማት፣በወንዝ ዳርቻዎች ማስዋብና በእርከን ሥራዎች ላይ እንደሚሳተፉ የቡድን መሪዋ ጠቁመዋል፡፡
እንደ ወይዘሮ አቦዘነች ገለፃ በምግብ ዋስትና ፕሮግራሙ ላይ የሚሳተፉት ዜጎች በቀን ለአራት ሰዓት የሚሰሩ ሲሆን በሳምንት ለአምስት ቀናት እንደሚሰሩም ጠቁመዋል፡፡ በስራቸውም በሰአት 80 ብር የሚከፈላቸው ሲሆን ከዚህ ውስጥ 20 ከመቶ ይቆጥባሉ፡፡
በምግብ ዋስትና የታቀፉ ዜጎች በአካባቢ ልማት እና በቀጥታ ድጋፍ ንዑስ ፕሮግራም ተጠቃሚ ናቸው ያሉት ወይዘሮ አቦዘነች በቀጥታ ድጋፍ በዕድሜ እና በተደራራቢ አካል ጉዳት ምክንያት በአንደኛውና ሁለተኛው ዙር ወደ 70 ሺ 542 ዜጎች ተጠቃሚ እንደነበሩም ጠቁመዋል ።
በዘላቂ የኑሮ ማሻሻያ ድጋፍ ለማግኘት በ2009 በጀት ዓመት 50 ሺ108 እና በ2010 63 ሺ178 በድምሩ 113,286 ተጠቃሚዎች 20 በመቶ እንዲቆጥቡ ታቅዶ 228 ሚሊዮን ብር መቆጠባቸውንና ዕቅዱ ሙሉ ለሙሉ መከናወኑንም ተናግረዋል ፡፡
የምግብ ዋስትና ፕሮግራሙ በ2009 ስትራቴጂ ተረቆለት ከድህነት ወለል በታች የሚገኙ የከተማ ነዋሪዎችን በአካባቢ ልማትና በቀጥታ ድጋፍ ላይ ተመሥርቶ እየሠሩና ገቢ እያገኙ የምግብ ዋስትናቸውን እንዲያረጋግጡ ለማድረግ የሚያስችል መሆኑን ወይዘሮ አቦዘነች አስረድተዋል።
ፕሮግራሙ ሲጠናቀቅ በዘላቂ የኑሮ ማሻሻያ ፕሮግራም ሥልጠናዎች እየወሰዱ በሚፈልጉበት የሥራ መስኮች ላይ ለመሰማራት የሚያስችላቸውን እቅዶች አዘጋጅተው ወደ መደበኛ የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት እንደሚገቡ ቡድን መሪዋ አስታውቀዋል።
አዲስ ዘመን መስከረም 7/2012
ኃይለማርያም ወንድሙ