
አዲስ አበባ፡- በአዲስ አበባ የካንሰር ልህቀት ማእከል በ450 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር እንደሚገነባ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት /ኢጋድ/ አስታወቀ፡፡
ኢጋድ በቀጠናዊ የካንሰር ኢኒሺዬቲቭ ዙሪያ ትናንት በሂልተን ሆቴል ባካሄደው የሃብት ማሰባሰብና የፓናል ውይይት ላይ የተገኙት የጤና ሚኒስትርና የወቅቱ የኢጋድ ጤና ሚኒስትሮች ኮሚቴ ሊቀመንበር ዶክተር አሚር አማን ለጋዜጠኞች እንደገለፁት፤ በቀጠናው የሚገነባው ይህ የካንሰር ልህቀት ማእከል በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ግንባታው ይጠናቀቃል ተብሎ ይታሰባል፡፡
የማእከሉ ግንባታ ከተጠናቀቀ በኋላ የተለያዩ ስልጠናዎችን ለመስጠት፣ ምርምሮችን ለማካሄድ፣በዘርፉ የሰለጠኑ ባለሙያዎችን ለማፍራትና በቀጠናው ባልተቀናጀ መልኩ ሲሰጥ የነበረውን የካንሰር ህክምና አገልግሎት ወጥነት ባለው መልኩ ለመስጠት እንደሚያስችልም ሊቀመንበሩ ገልፀዋል፡፡
እንደ ሊቀመንበሩ ገለጻ፤የማእከሉ ግንባታ በመጪው ጥር ወር 2012 ዓ.ም የሚጀመር ሲሆን፣የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለዚሁ ግንባታ የሚያስፈልገውን መሬት አዘጋጅቷል፡፡ለግንባታ የሚያስፈልገውን ወጪ በዋናነት ኢትዮጵያ ለመሸፈን ተነሳሽነቱን ያሳየች ስትሆን፣መንግሥትም ለዚህ ቁርጠኛ ሆኗል፡፡
በአባል ሀገራት በኩልም ግንባታውን ለማከናወን ቁርጠኝነቱ እንዳለ ጠቅሰው፣ በተለይም የሳዑዲ አረቢያ መንግሥት ለግንባታው ድጋፍ እንደሚያደርግና በቀጣይም የግል ባለሃብቶችንና አባል አገራትን በማካተት የማእከሉ ግንባታ የሚከናወን መሆኑንም ሊቀመንበሩ አመልክተዋል፡፡
አብዛኛዎቹ ለጋሽ ሀገራት ለግንባታው ድጋፍ ለማድረግ ቁርጠኛ ናቸው ያሉት ዶክተር አሚን፣ የዓለም ጤና ድርጅት የፖለቲካና የቴክኒክ አጋር በመሆኑ በማእከሉ ግንባታ በአብዛኛው የሚሳተፉት የአገር ውስጥና የውጭ የግል ባለሃብቶች መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡ በዋናነትም የሳዑዲ አረቢያ መንግሥት ከሶስት ሳምንት በኋላ ትልልቅ የቢዝነስ ኢንቨስተሮችን ይዘው እንደሚመጡና የአፍሪካ ልማት ባንክም ለግንባታው ፍላጎት እንዳሳየ ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል፡፡
በኢትዮጵያ ከሚከሰተው ሞት አምስት በመቶው በካንሰር ህመም እንደሚከሰት መረጃዎች የሚያሳዩ ሲሆን፣ የካንሰር ልህቀት ማእከል ግንባታው ሲጠናቀቅ በተለይ በቀጠናው ትልቁ የካንሰር ምርምር ማእከል በመሆን ወጥነት ያለው የካንሰር ህክምና አገልግሎት ለመስጠት ያስችላል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
አዲስ ዘመን መስከረም 6/2012
አስናቀ ፀጋዬ