
አዲስ አበባ፡- የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን በአዲስ አበባ ከሰባት እስከ አስር ፎቅ የሚደርሱ አምስት ትልልቅ ህንጻዎችን በ1ነጥብ 8ቢሊዮን ብር ወጪ ማስገንባት መጀመሩን አስታወቀ።የኪራይ ማሻሻያ ተመን ከተደረገ በኋላ በገቢው ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ ብልጫ መገኘቱን ገለጹ፡፡
የኮርፖሬሽኑ የኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ክብሮም ገብረመድህን በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ አምስቱ ህንጻዎች እያንዳንዳቸው 435 የሚሆኑ የንግድና የመኖሪያ ቤቶች የሚኖራቸው ሲሆን፣ ህንጻዎቹ 1ነጥብ 9 ሄክታር መሬት ላይ የሚያርፉም ናቸው።
ህንጻዎቹ ለተለያዩ አምስት ድርጅቶች ተሰጥተው በግንባታ ሂደት ላይ እንደሚገኙ የጠቆሙት አቶ ክብሮም፣ ለብዙ ዜጎች የሥራ ዕድል መገኘቱንና የሕንጻው ግንባታ እየጨመረ በሄደ ቁጥር በሺዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞች የሥራ ዕድል እንደሚያገኙም አስታውቀዋል።
ቤቶች ኮርፖሬሽን ካለፈው የካቲት ወር ወዲህ ያደረገው የንግድ ቤቶች ኪራይ ተመን ማሻሻያ ገቢ ወዲያውኑ ለሌሎች ነጋዴዎች ለንግድ የሚከራዩበትን ቤት እንዲያገኙ የሚደግፍና እንዲሁም ለመኖሪያ ቤቶችም የሚሆኑ ቅይጥ ህንጻዎች ግንባታ ለማከናወን ምቹ ሁኔታን መፈጥሩንም ገልጸዋል።
እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ ፤ህንጻዎቹ ከመጀመሪያው ወለል እስከ ሶስተኛ ወይም አራተኛ ፎቅ ለንግድ አገልግሎት ምቹ ተደርገው ይገነባሉ፡፡ከአራተኛ ፎቅ በላይ ያሉት ደግሞ ለመኖሪያነት የሚያገለግሉ ይሆናል፡፡
‹‹ህንጻዎቹ በአዲስ አበባ ከተማ የተለያዩ አካባቢዎች ማለትም በቦሌ ፍሬንድሺፕ ፣ አዋሬ ፣ከጦር ኃይሎች ወረድ ብሎ ቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ በመሳሰሉ አካባቢዎች እየተገነቡ ይገኛሉ ››ያሉት አቶ ክብሮም ፣ይህም ከመኖሪያነት ባሻገር የንግዱን እንቅስቃሴ የተሳለጠ እንዲሆን ከፍተኛ አስተዋፆኦ እንደሚኖረው አስገንዝበዋል፡፡
የኪራይ ማሻሻያ ተመን ከተደረገ በኋላ የኮርፖሬሽኑን ገቢ በማጎልበት ረገድ ለውጦች መታየታቸውን ጠቅሰው፣በገቢውም ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ ብልጫ መገኘቱን ተናግረዋል፡፡ ይህም ለቤተክህነት ተመላሽ የተደረጉትንና በልማት ምክንያት የፈረሱ ህንጻዎች ሳያካትት መሆኑንም አስታውቀዋል።ከኪራይ ማሻሻያው የተገኘው ጭማሪ ገቢም ለቤቶቹ ግንባታ መጀመር አስተዋፆኦ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡
ኮርፖሬሽኑ ከመደበኛ ወርሃዊ ኪራይ፣ ከውዝፍ ኪራይ፣ ከውል ዕድሳት ፣ከፈረሱ ቤቶች ካሳ ክፍያ፣ ከብሎኬትና ጠጠር ሽያጭ፣ ከመጋዘን ኪራይና ከመሳሰሉት በ2011 በጀት ዓመት 818 ነጥብ 76 ሚሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱ ታውቋል፡፡ይህም የዕቅዱን 99ነጥብ 8 በመቶ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
አዲስ ዘመን መስከረም 6/2012
ኃይለማርያም ወንድሙ