የማህፀን በር ጫፍ ካንሰር ከጡት ካንሰር ቀጥሎ በሴቶች ላይ የሚከሰት ሁለተኛው ገዳይ በሽታ መሆኑ ይታወቃል። በየዓመቱም በዓለም አቀፍ ደረጃ 530ሺ የሚጠጉ ሴቶች በማህፀን በር ጫፍ ካንሰር እንደሚያዙ ይገመታል። በዚህ አይነቱ የካንሰር ህመም የሚጠቁ ሴቶች በአብዛኛው የሚገኙትም በታዳጊ ሀገራት መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ።
በኢትዮጵያም በቅርቡ የወጡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፤ በየዓመቱ 7ሺ 500 የሚጠጉ ሴቶች በማህፀን በር ጫፍ ካንሰር የሚያዙ ሲሆን፣ ከነዚህ ውስጥ 500 ያህሉ በዚሁ ካንሰር ምክንያት ይሞታሉ።
የማህፀን በር ጫፍ ካንሰር ‹‹ሂውማን ፓፒሎማ›› /human papiloma virus/ በተሰኘ ቫይረስ በግብረስጋ ግንኙነት አማካኝነት በአብዛኛው በሴቶች ላይ የሚከሰት ሲሆን፣ ቫይረሱ ወንዶችንም ለጉሮሮና የአፍ ውስጥ ካንሰር ያጋልጣል።
የማህፀን በር ጫፍ ካንሰር ክትባት በዓለም አቀፍ ደረጃ እ.ኤ.አ በ2012 የተዋወቀ ሲሆን፣ በኢትዮጵያም በህዳር ወር 2011 ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ ከመደበኛው የክትባት መርሐግብር ጋር ተሰጥቷል። በመጀመሪያው ዙር የክትባቱ መርሐግብርም ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ እድሜያቸው አስራሁለት ዓመት የሞላቸው ልጅአገረዶች ተከትበዋል። ሁለተኛው የክትባት መርሐግብርም ባለፈው ግንቦት ወር ተሰጥቷል።
የማህፀን በር ጫፍ ካንሰር በገብረስጋ ግንኙነት አማካኝነት ከሰው ወደሰው የሚተላለፍ መሆኑ የሚታወቅ ቢሆንም፣ ቫይረሱ በሌላ መንገድ የሚተላለፍበት አድል ሊኖር እንደሚችል ኒውስ ሜዲካል ከሰሞኑ በአሜሪካ የፔንሰልቫኒያ ተመራማሪዎችን ጥናት ዋቢ በማድረግ ይዞት የወጣው መረጃ ያመለክታል።
የተመራማሪዎቹ ጥናት እንደሚያሳየው ቫይረሱ እንዲኖርባቸው የተደረጉ ጥንቸሎችና አይጦች በደም አማካኝነት ወደሌሎች ጥንቸሎችና አይጦች የማስተላለፍ አቅም እንዳላቸው አሳይቷል። በፔንሰልቫንያ ግዛት በሁለት የእንስሳት ሞዴሊች አማካኝነት የተሰራው ይህ ጥናት ተመራማሪዎች የፓፒሎማ ቫይረስ በደም አማካኝነት ሊተላለፍ እንደሚችልና በደም ተቀባዩ ላይም ኢንፌክሽን ሊፈጥር አንደሚችል አረጋግጠዋል።
ጥናቱ ምን አልባትም ሂዩማን ፓፒሎማ ቫይረስ ከሰው ወደሰው በደም አማካኝነት ሊተላለፍ እንደሚችል ያለውን ግምት ለማረጋገጥ እንደመነሻ ሆኖ ሊያገለግል እንደሚችል አጥኚዎቹ አስጠንቅቀዋል።
በፔንሰልቫንያ ግዛት የህክምና ኮሌጅ የፓቶሎጂና ላብራቶሪ ሜዲስን ረዳት ፕሮፌሰርና የጥናቱ መሪ ጃይፈን ሁ ቫይረሱ በደም አማካኝነት ከሰው ወደሰው የሚተላለፍበትን እድል ለመቀነስ በተለይም ደም ከአንድ ሰው በሚቀዳበት ወቅት ለማረጋገጥ ተጨማሪ ጥናት ማካሄድ ያስፈልጋል ብለዋል። በትክክል እውነት መሆኑን ለማረጋገጥም ለመቀበል የተዘጋጀው ደም የኤች ፒ ቪ ልየታ ሊደርለለት ይገባል።
ፕሮፌሰር ሁ ደም ተቀባዮች ሁልጊዜ በተሻለ መልኩ ሊሰራ የሚችል በሽታን የመከላከል አቅም ሊኖራቸው ስለማይችል ለቫይረሱ ሊጋለጡ እንደሚችሉ ጠቅሰው፣ኤች ፒ ቪን በተለገሱ ደሞች የተለዩ የቫይረስ ዝርዝሮች ውስጥ ለመጨመርና በሰውነት ደም ውስጥ ሊኖር የሚችለውን ትክክለኛውን የኤች ፒ ቪ ጫናና በበቂ ሁኔታ ሊያስከትል የሚችለውን ኢንፌክሽን ልናጠና እንችላለን ሲሉ ያስገነዝባሉ።
ፕሮፌሰር ሁ እንዳሉት፤የጥናት ቡድኑ በ 2005 በተመሳሳይ ቫይረሱ የሚተላለፍበትን መንገድ የማጥናት አድል ገጥሞት ነበር። ከተወሰኑ ዓመታት በፊት የጥናት ቡድኑ ኤች አይ ቪ ኤድስ ከያዛቸው ልጆች የደም ናሙናዎችን በመወስድ ለማየት ሞክሮ የነበረ ሲሆን፣ ናሙናዎቹን ከመረመሩ በኋላ ጥቂቶቹ የፓፒሎማ ቫይረስ እንዳለባቸው ለማረጋገጥ ችለዋል። ቫይረሱ በደም ልገሳ ወቅት ይዟቸው ይሆን የሚል ጥያቄም በወቅቱ አስነስቶ ነበር።
በእንስሳት ሞዴሎች ላይ ኤች.ፒ.ቪን ለመመርመር አስቸጋሪ ስለሆነ የጥናት ቡድኑ በሌሎች የፓፒሎማ ቫይረስ ዓይነቶች ላይ ሙከራዎችን ለማከናወን መወሰኑን ፕሮፌሰር ሁ የገለፁ ሲሆን ኤች ፒ ቪ ዝርያ ተኮር በመሆኑ በእንስሶች ውስጥ በቀጥታ ማጥናት እንደማይቻል ጠቁመዋል።
የጥናት ቡድኑ በቤተ-ሙከራ ውስጥ በተፈጥሯዊ ፓፒሎማ ቫይረሶች የተያዙ ሁለት ትክክለኛ የእንስሳት ሞዴሎች ያዘጋጀ ሲሆን፣ ይህም ከሂዩማን ፓፒሎማ ቫይረስ ጋር ተመሳሳይነት ያለው በመሆኑ በሰዎች ላይ የሚከሰተውን የፓፒሎማ ቫይረስ ኢንፌክሽን ለመመርመር በብዛት ጥቅም ለይ የሚወለውን /Cottontail Rabbit Papillomavirus/ ምርምር ሂደት ተከትሏል።
የጥናቱ ቡድን ለሙከራው በመጀመሪያ ፓፒሎማ ቫይረስ እንዲኖርባት ከተደረገችው ጥንቸል ደም በመውሰድ ቫይረሱ ወደሌለባቸው ጥንቸሎች በላብራቶሪ እንዲገባባቸው አድርገዋል። ከዚህ በኋላም ጥንቸሎች ላይ ዕጢ አድጎ አስጊገኝባቸው ድረስ ለአራት ሳምንታት ክትትል ተደርጎባቸዋል። በዚህም ሂደት ቫይረሱ በጥንቸሎቹ ደም ውስጥ በመሰራጨት እጢ እንዲፈጠር ምክንያት መሆኑ ማረጋገጥ ተችሏል ሲሉ ፕሮፌሰር ሁ ግልፀዋል።
ቡድኑ በእውነተኛው የፆታ ግንኙነት ከሚፈጠሩ የቫይረሱ ዕጢዎች ጋር ተመሳሳይነት ባላቸው በእነዚህ ጥንቸሎች ዕጢዎች ውስጥ በርካታ የዘረ- መል መግለጫዎች የመገኘታቸው ሁኔታ ዝቅተኛ መሆኑን ፕሮፌሰር ሁ አመልክተዋል። በዚህ ሙከራ ከፍተኛ መጠን ያለው ቫይረስ ወደ ጥንቸሎቹ በመርፌ አማካኝነት እንዲገባ ተደርጓል።
በዚህ መልኩ በጥንቸሎቹ ውስጥ የሚፈጠረው ኢንፌክሽን የሚፈጠረው በቫይረሱ ከፍተኛ ጫና ሊሆን ይችላል ብለዋል ፕሮፌሰር ሁ። ይሁንና በተለመደው ሁኔታ በደም ንክኪ የሚፈጠር ኢንፌክሽን ሲሆን የቫይረሱ መጠን በከፍተኛ ሁኔታ ሊቀንስ ይችላል ብለዋል።
ከዚህ በኋላም የጥናት ቡድኑ በመርፌ የሚሰጠውን የቫይረሱን ጫና በአምስት እጥፍ የቀነሰ ሲሆን፣ በዚህ ጊዜ ዕጢዎቹ አሁንም ከ 32 ጥንቸሎች ውስጥ በ18ቱ መታየታቸውን ፕሮፌሰሩ አብራርተዋል። በምርምሩ በደም ውስጥ ያለው ቫይረስ ዕጢዎችን ያስከተለ መሆኑን ለማሳየት ችለናል ያሉት ፕሮፌሰር ሁ፤ ይሁንና ‹‹ደም ስለመውሰድስ?›› ሲሉ ጥያቄ ያነሳሉ።
ደም የሚሰጡ ሰዎች ቫይረሱን የሚወስዱት በጣም በአነስተኛ መጠን ነው ያሉት ፕሮፌሰር ሁ፤ ይህንን ለማረጋገጥ ቫይረሱ ወደአንድ ጥንቸል ውስጥ እንዲጋባ በማድረግ አስር ሚሊ ሊትር ደም ተወስዶ ወደሁለተኛው ጥንቸል እንዲገባ ቢደረግም አሁንም በጥንቸሉ ላይ እጢው መታየቱን የጥናት ቡድኑ አረጋግጧል ብለዋል።
ተመራማሪዎቹ ሌላው ያነሱት ጥያቄ በግብረ ሥጋ ግንኙነት የሚተላለፈው የቫይረሱ ኢንፌክሽን አቅም ያለው ከሆነ በማህፀን ውስጥ ዕጢ እና የካንሰር ለውጦች ሊያስከትል ይችላል ወይ? የሚል እንደነበር ፕሮፌሰሩ ጠቅሰው፣ አሁንም የአይጥ ሞዴልን በመጠቀም ቡድኑ ሙከራውን ደግሟል። በላብራቶሪ ውስጥ አይጦች የፓፒሎማ ቫይረስ ሲወጉ ኪንታሮትና ዕጢዎች በብልታቸው ላይ አግኝተዋል። እንዲሁም ቫይረሱን በአይጦቹ ሆድ ውስጥ ማገኘታቸውን አረጋግጠዋል። ይህም ቫይረሱ ከደም ወደ አፍ፣ ብልትና የሆድ እቃ ውስጥ በፍጥነት የመጓዝ ችሎታ የነበረው መሆኑን ያረጋግጣል ሲሉ ፕሮፌሰሩ ገልፀዋል።
ፕሮፌሰሩ በ ኤች ፒ ቪ ኢንፌክሽን የሚያዙ ሁሉም ሰዎች በካንሰር የሚያዙ አይደሉም ይላሉ። የተወሰኑ ግለሰቦች ላይ ግን ሊከሰት እንደሚችል ያመለክታሉ። ኤች.ፒ.ቪ የተለመደ ቫይረስ ቢሆንም በቫይረሱ የተያዙ ሁሉ ካንሰር አለባቸው ማለት አይደለም። ይሁንና እጅግ በጣም አስቸጋሪው ነገር የኤች.ፒ.ቪ ቫይረስ ያለባቸው ሰዎች አሁንም ቫይረሱን የማሰራጨት አቅም ያላቸው መሆኑ ነው ብለዋል። በዚህም ምክንያት አንድ ሰው በጤና ችግር ምክንያት ደም ከሌላው ሰው አንዴ ቢቀበል በአጋጣሚ ከዚያ በላይ ሌላ ማከል እንደማይፈልግ ፕሮፌሰሩ ጠቁመዋል።
የምርምሩ መሪ በማጠቃለያቸው “ደም በመስጠትና እና በበሽታ ወይም በካንሰር መካከል ያለውን ትስስር ኋላ ላይ መለየት ቀላል እንዳልሆነ የገለፁ ሲሆን፣ በምርምሩ ከተጠቀሱት ውጤቶች አንፃር የደም አቅርቦትን ደህንነት ለማረጋገጥ በየጊዜው ምርመራ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ለማረጋገጥ በሰዎች የደም ናሙናዎች ላይ ሁሌም ጥናት ማካሄድ ብልህነት ነው ብለዋል።
አዲስ ዘመን መስከረም 6 / 2012
አስናቀ ፀጋዬ