ዓለማችን የስልጣኔ ካባ የተከናነበችው ከግብርና መሰረታዊ የኢኮኖሚ ምንጭ ወደ ኢንዱስትሪ ስትሸጋገር ነው። በእጅ ከሚሰሩ የዕድ ጥበብ ውጤቶች በፋብሪካ የተመረቱ ምርቶች ሲተኩና በገጠር ከሚኖር አብዛኛው ህዝብ ወደ ከተሜነት ሲሸጋገር እንደሆነ የአደባባይ ሚስጥር ነው።
እኤእ በ18ኛው ክፍለ ዘመን በእንግሊዝ አገር የተቀጣጠለው የኢንዱስትሪ አብዮት እንደ ሰደድ እሳት በአውሮፓና ሰሜን አሜሪካ ሊስፋፋ ችሏል። በዘመኑም አዳዲስ መሳሪያዎች፣ የኃይል አማራጮችና ዘመናዊ ማሽኖች ጥቅም ላይ መዋል በመጀመራቸው የህብረተሰቡን የአኗኗር ዘይቤ መቀየር እንደተቻለ መፃህፍት ይጠቅሳሉ። ለዚህ ስኬትም የብረታ ብረትና ኢንጅነሪንግ ዘርፉ ዕድገት ለሁለተናዊ ለውጥ መሰረት እንደሆነ ይነገራል።
ይህን ተከትሎ የትራስፖርት፣ የኮሙኒኬሽንና የባንኮች ዕድገት እንዲሁም የሸቀጦች ምርታማነትና ትርፋማነት ኢንዱስትሪ አብዮቱን ሊያፋጥኑት ችለዋል። ሁለተኛው የኢንዱስትሪ አብዮት ደግሞ እኤእ በ19ኛውና እና በ20ኛው ክፍለ ዘመን ማብቂያ ላይ ብዙ ሳይንሳዊ ግኝቶችን ይዞ የመጣበት ጊዜ ነበር። በዚህ ዘመን ሳይንስ የፈጠራቸው አዳዲስ ግኝቶች ተግባራዊ የተደረጉበት ነው።
የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ሀብቶች በአግባቡ እሴት ተጨምሮባቸው ጥቅም ላይ የዋሉበት ጭምርም ነው። ኮምፒውተር ጥቅም ላይ መዋሉን ተከትሎም በሰው ኃይል ይንቀሳቀሱ የነበሩ ማሽኖች ወደ ዲጂታል ቴክኖሎጂ የተቀየሩበት እንደሆነ የሚታወስ ይሆናል። ለዚህ ሁሉ የኢንዱስትሪ አብዮት መሳካት የብረታብረት ዘርፉ መሰረት እንደሆነ ይነገራል። ምዕራባውያንም ሆኑ እንደ ቻይና ያሉ በማደግ ላይ ያሉ አገራት በብረታብረትና ኢንጅነሪንግ መስክ ፈጣን ለውጥ ማምጣታቸው ዛሬ ለደረሱበት ብልፅግና አሸጋግሯቸዋል።
ለእነዚህ አገራት ኢንዱስትሪ የኢኮኖሚያቸው የደም ስር ሆኖ እስካሁን ድረስ ዘልቋል።እንደ ቻይና፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ታይዋንና ኢንዶኖዢያ ላሉ አገራት ደግሞ አሁንም የብረታ ብረት ኢንዱስትሪ ልማት ለኢኮኖሚያቸው የብረት ምሶሶ ሆኖላቸዋል። በአብዛኛው በዓለማችን የሰለጠኑ አገራት ዛሬ ለሚያመርቷቸው ተሽርካሪዎች እና አውሮፕላኖች፣ ለሚገነቧቸው መንገዶችና ህንጻዎች እንዲሁም ለሚዘረጓቸው የባቡር ሀዲዶችና ቴክኖሎጂዎች ከብረታብረት ዘርፉ የተገኙ መሆናቸው ይታወቃል።
የዘርፉ ዕድገት የኢኮኖሚ ዕድገት መለኪያ ከመሆኑም ባሻገር ሁለተናዊ እድገትን ለማሳለጥ ምሶሶም ነው። ኢትዮጵያ ቀደም ሲል ጀምሮ ብረትን ተጠቅማ ማረሻ፣ማጭድና ቢላዋ፣መጥረቢያና ሌሎች መገልገያዎችን መስራት ብትችልም ቀደም ሲል ዘርፉን የሚያበረታታ ሁኔታ አልነበረም።
በተለይ ቀደም ሲል በነበረው የፊውዳል ስርአት በዚህ ሙያ የተሰማሩ ባለሙያዎች በህብረተሰቡ ዘንድ የተሰጣቸው ስያሜና ተቀባይነት አነስተኛ በመሆኑ ተገቢው ለውጥ ማምጣት አልተቻለም። በተለይ በብረታብረት ስራ ላይ የተሰማሩ ሰዎች አንጥረኛ፣ ቀጥቃጭ ወዘተ የሚሉ ስያሜዎች እየተሰጣቸው ሙያው በህብረተሰቡ ዘንድ ዘልቆ እንዳይገባና እንዳያድግ ትልቅ እንቅፋት ተፈጥሮ ቆይቷል።
በአንጻሩ ከፊውዳሉ ስርዓት ውድቀት በኋላ ለዘርፉ የሚሰጠው ትኩረት በመጠኑም ቢሆን የተለወጠበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ያም ሆኖ ግን ዘርፉን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ከመደገፍና ከማሳደግ አንጻር የሚፈለገውን ያህል እርምጃ መራመድ አልተቻለም። በዚህ የተነሳ አገራችን በዘርፉ በቂ ጥሬ ሃብት ቢኖራትም የሚገባውን ያህል ልትጠቀም አልቻለችም።
የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉሙሩክ ባለስልጣን መረጃ እንደሚያመለክተው ኢትዮጵያ እኤእ 2008 እስ 2012 ድረስ በአማካይ 564 ሺ 457 ቶን የብረት ጥሬ ዕቃዎችንና ውጤቶችን ከቱርክ፣ ከዩክሪን፣ ከሩሲያ፣ ከቻይና ከጃፓን አገሮች አስገብታለች።ለዚህ የብረት ጥሬ ዕቃና ውጤቶችን አራት ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ዶላር ወጪ አድርጋለች።ይህ የሚያሳየው ዘርፉ ምን ያህል ተቃሚና ተፈላጊ መሆኑን ነው። ምክንያቱም ያለ ብረት ውጤቶች ዕድገትና ቴክኖሎጂ አይታሰብም።
ኢትዮጵያም የብረታ ብረት ኢንዱስትሪው ለኢኮኖሚ ዕድገትና ብልፅግና የስሙን ያህል ጥንካሬ እንዲሆን በግል ባለሃብቶች የተለያዩ የብረታ ብረት ፋብሪካዎች ተገንብተዋል፤ እየተገነቡ ናቸው። ከእነዚህ መካከል አንዱ ባለቤትነቱ የኮሪያ ባለሀብቶች የሆነው ኢኮስ (ECOS)ብረታ ብረት ፋብሪካ ይገኝበታል። ይህ ፋብሪካ በኦሮሚያ ክልል በዱከም ከተማ በ30 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ነው የተገነባው።
በመጀመሪያና በሁለተኛው ምዕራፍ ግንባታው 300 ሺ ቶን የተለያዩ ብረታ ብረት ውጤቶችን የማምረት አቅም አለው። ለቴክኖሎጂ ሽግግር፣ ለስራ እድል ፈጠራ፣ ለውጭ ምንዛሬ ማግኛና በጥቅሉም ለአገሪቱ እድገት የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ መሆኑን የሚናገሩት በኢኮስ(Ekos) ብረታ ብረት ፋብሪካ የማስታወቂያና የትምህርት ክፍል ኃላፊ ሚስተር ሊ ሂንግ ኢትዮጵያና ኮሪያ በደም የተሳሰረ ግንኙነት እንዳላቸው ይገልፃሉ።
ፋብሪካው የኢትዮጵያና የኮሪያ ረጅም ግንኙነት መገለጫዎች አንዱ መሆኑን የሚጠቅሱት ሚስተር ሊ ወደፊትም ከአካባቢው ህብረተሰብ ጋር አብሮ ለማደግ በማህበራዊ አገልግሎት ላይ አተኮሮ የሚሰራ መሆኑን ጠቁመዋል። ፋብሪካው ከዋና ስራው ጎን ለጎንም ማህበራዊ ኃላፊነቶችን ለመወጣት እየሰራ ይገኛል።
ለአብነት ያህልም በዱከም አካባቢ የኤሌክትሪክ ሀይል የማያገኙ 38 አርሶ አደሮች የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚዎች ለማድረግ ዕቅድ እንዳለው ተናግረዋል። እንዲሁም ለአካባቢው ህብረተሰብ የውሃ አቅርቦት ለማሟላት ዕቅድ መያዛቸውን ገልጸዋል።
እንደ ኃላፊው ገለጻ፤ ብረት ለኢኮኖሚ ዕድገትና ኢንዱስትሪን ለማስፋፋት የጀርባ አጥነት ነው። ለህንጻ፣ ለባቡር ሀዲድ፣ ለኢንዱስትሪ ፓርኮችና በጥቅሉ ለሁለተናዊ የኢኮኖሚ ዕድገት የብረታ ብረት ውጤቶች ትልቅ ፋይዳ አላቸው። ፋብሪካው በብረታ ብረት ፋብሪካ የካበተ ልምዱንና እውቀትን ለኢትዮጵያን ባለሙያዎች ለማሸጋጋር ጉልህ ድርሻ አለው። ኢትዮጵያ ከውጭ ታስመጣ የነበረውን የብረት ምርትም በአገር ውስጥ በማምረት የውጭ ምንዛሬ ማዳንም ችሏል።
ፋብሪካው ዘመናዊ ማሽኑን ለማንቀሳቀስ የሚጠቀምበት ሀይል ከአየር ብክለት ነጻ ሲሆን 500 ሰዎች በላይ ሰዎች የስራ ዕድል ፈጥሯል። በአሁኑ ጊዜም በዓመት 60 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ የሚያድን ምርት እያመረተ ይገኛል። ተጨማሪ የብረት ማቅለጫና ማመረቻ ፋብሪካ ለመገንባት ዕቅድ መኖሩንም ነግረውናል። ይህም ፋብሪካው አሁን እያመረተ ከሚገኘው 300ሺ ሜትሪክ ቶን ብረት የማምረት አቅም ወደ 500ሺ ሜትሪክ ቶን ማሳደግ ያስችለዋል። ይህም በጥቅሉ ፋብሪካው በዓመት ከውጭ የሚመጣውን የብረት ብረት ምርትን በአገር ውስጥ በመተካት 90 ሚሊዮን ዶላር ማዳን የሚያስችል ይሆናል።
የፋብሪካው ዋና ስራ አስፈጻሚ ሚስትር ሼል ሀቺኦ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ ኢኮስ ብረታ ብረት ፋብሪካ እኤአ በ1914 በደቡብ ኮሪያ የተመሰረተ ድርጅት ሲሆን በኦሮሚያ ክልል ዱከም ከተማ ያስገነባው የብረታ ብረት ፋብሪካም ባለፈው ዓመት ጥቅምት ወር ላይ ነው ተመርቆ ስራ የጀመረው። በ30ሚሊዮን ዶላር የተገነባው ፋብሪካው በኢትዮጵያ እየተስፋፋ ለመጣው ግንባታ የተለያዩ የብረታ ብረት ምርቶችን ያቀርባል ።
የፋብሪካ ስራ የሙያ ስነ ምግባር ይጠይቃል የሚሉት ዋና ስራ አስፈጻሚው ምርቶችን በጥራት አምርቶ ለደንበኞች በተመጣጣኝ ዋጋ ማቅረብ የረጅም ጊዜና ታማኝ ደበኞችን ለማፍራት ያስችላል ባይ ናቸው። በኢትዮጵያ ያላውን ከፍተኛ በብረታ ብረት ምርት ፍላጎት ለማርካትም ፋብሪካውን የማስፋፋት ስራዎች ለመስራት ዕቅድ መያዙን ጠቅሰዋል። እስካሁንም በሁለት ምዕራፍ የማስፋፋት ስራዎችን መስራቱን አውስተዋል።
ፋብሪካው ጥሬ ዕቃ ከዩክሪን፣ፖላንድና ደቡብ ኮሪያ የሚያስመጣ ሲሆን በኢትዮጵያ ያለውን ከፍተኛ የብረታብረት ፍላጎት ለማርካት እየሰራ ይገኛል። ፋብሪካው እያመረታቸው ከሚገኙ የብረታ ብረት ምርቶች መካከል ፌሮ፣ የኤሌክትሪክ ሽቦ፣ የብረት ቱቦና የማዕዘን ብረት እንደሚገኙበት ይጠቅሳሉ። ፋብሪካው በግንባታው ላይ የሚታየውን የብረት እጥረት በማቃለልና ግንባታ እንዲፋጠን የበኩሉን ሚና መወጣቱን ነው የነገሩን።
መንግስት የግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ ለተሰማራባቸው ለኮንስትራክሽን ግብአት የሚሆኑ የብረታ ብረት ውጤቶችን ማምረት የሚችሉ ኢንዱስትሪዎች እንዲቋቋሙ ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ነው። በዚህም የአርማታ ብረትን በ2003 ዓ.ም 454 ሺህ ቶን የነበረው የማምረት አቅም በአሁኑ ጊዜ ሁለት ሚሊዮን ቶን የሚጠጋ ምርት እንደሚመረት መረጃዎች ያሳያሉ።
በሀገሪቱ እየተስፋፋ የመጣውን የኮንስትራክሽን እንቅስቃሴ ተከተሎ የአርማታ ብረት ፍላጎት ከቀን ወደቀን እየጨመረ ነው። በመንግሥትና በግለሰቦች ከሚከናወኑ ግዙፍ ፕሮጀክቶች በተጨማሪ በግለሰብ ደረጃ ለሚሠሩ ቀላል የግንባታ ሥራዎች ጭምር የአርማታ ብረትን የመጠቀም ፍላጎቱ ከፍ ብሏል።
የግሉን ባለሀብት በብረታብረትና ኢንጅነሪንግ መስክ የበኩሉን ድርሻ እንዲያበረክት የሚስችሉ ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ። የነባር ኢንዱስትሪዎችን አቅም የማሳደግና ወደ አዳዲስ ኢንቨስትመንቶች በስፋት እንዲገቡ ለማድረግ በመንግስት በኩል ለልማቱ የተመቻቻ ሁኔታ ተፈጥሯል። የፋይናንስ ድጋፍ እንዲያገኙና የመሰረተ ልማት አቅርቦትን ፣የሰው ኃይል ስልጠና በብቃት ለመፈፀም ቀልጣፋና ልማትን የሚደግፍ አስተዳደር ለመፍጠርም መንግስት የበኩሉን ጥረት እያደረገ ነው ያለው።
የብረታብረት ፋብሪካዎች መስፋፋት የቴክኖሎጂ ሽግግርን ከማፋጠን ባሻገር ለኢኮኖሚ ዕድገት ቁልፍ ሚና ያላቸውን የልማት ፕሮጀክቶችን ለመገንባት ሚናው ከፍተኛ ነው። መንግስት በግሉ ዘርፍ ያለውን የመካከለኛና ከፍተኛ የብረታ ብረትና ኢንጅነሪንግ ኢንዱስትሪዎች አቅም መገንባት ያስፈልጋል።
በሌላ በኩል ዘርፉ የመሰረት ልማት ግንባታውን ከማገዝ አንፃር የኮንስትራክሽን ግብአቶችን የተለያዩ የኢንዱስትሪ ማሽነሪዎችንና መለዋወጫ እቃዎችን በሀገር ውስጥ በማምረት ገቢ ምርቶችን ለመተካት እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ ዕድገት ቢታይበትም አሁንም ትኩረት የሚሻ ዘርፍ ነው። ስለዚህ መንግስት በኢንዱስትሪ ለመበልጸግና ኢንዱስትሪን ለማስፋፋት ብረታ ብረትና ኢንጅነሪንግ ዘርፉ ማዘመን ለነገ የሚባል ጉዳይ አይደለም።
አዲስ ዘመን መስከረም 5/2012
ጌትነት ምህረቴ