
አዲስ አበባ:- የዘንድሮውን አለም አቀፍ የቱሪዝም በአል በድምቀት ለማክበር እንዲቻል ሁኔታዎችን የማመቻቸት ተግባራት በመከናወን ላይ መሆናቸው ተገለፀ።
“ቱሪዝም ለስራ እድል ፈጠራና ለተሻለ ህይወት” በሚል መሪ ቃል የሚከበረው የዘንድሮው የአለም ቱሪዝም ቀን በአገራችን በድሬዳዋ ከተማ የሚከበር ሲሆን በክብረ በአሉ ላይም የተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚቀርቡ ተገልጿል።
በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የአገር ውስጥ ቱሪዝም ማስፋፊያ ጊዜያዊ አስተባባሪ አቶ ቴዎድሮስ ሀብታሙ ለአዲስ ዘመን እንደገለፁት፤ የዘንድሮው አለም አቀፍ የቱሪዝም ቀን በአለም አቀፍ ደረጃ ለ40ኛ፣ በሀገራችን ደግሞ ለ32ኛ ጊዜ መስከረም 17 የሚከበር ሲሆን፤ በበአሉ ላይም ባህላዊ እሴቶችን የሚያሳዩ በርካታ ሁነቶች እንደሚቀርቡ ታውቋል።
ባህላዊ ሁነቶቹ የአገራችንን ባህላዊ እሴቶች በሚያስተዋውቅና በሚያበለፅግ መልኩ ለእይታ ይቀርባሉ የሚሉት አቶ ቴዎድሮስ፤ ባህላዊ ሲምፖዚየም፣ ኤግዚቢሽን፣ ፋሽን ትርኢት፣ የጥናትና ምርምር ስራዎች፣ ውይይቶች፣ የድሬዳዋን ልዩ ባህሪ፣ አብሮ መኖርና መቻቻልን የሚያስተጋቡ ሁነቶች፣ ምስራቅ ኢትዮጵያን የሚገልፁ ማሳያዎች፤ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች፣ የግመል ውድድር፣ ባህላዊ ምግቦች አሰራርና አመጋገብ እና ሌሎች ፓኬጆችም ይቀርባሉ። የድሬዳዋ አጎራባች ክልሎችም ባህላዊ እሴቶችና ሌሎች ተግባራትም በበአሉ ላይ ሰፊ ቦታን ይይዛሉ ሲሉም ተናግረዋል።
በአሉ “በአጠቃላይ የምስራቅ ኮኮቦች የሚታዩበት፤ የአገራችን ቱሪዝም በስፋት የሚተዋወቅበት፤ ዘርፉን ለማበልፀግ ሰፊ ስራ የሚሰራበት፣ በዘርፉ ለመሰማራት የሚፈልጉ ባለሀብቶች የሚበረታቱበት፤ የቱሪስት ፍሰትን ለመጨመር ቃል የሚገባበት፣ የአገራችን ህዝቦች ከተለያዩ የአገራችን ባህላዊ እሴቶች ልምድ የሚካፈሉበት” እንደሚሆንም ጊዜያዊ አስተባባሪው አቶ ቴዎድሮስ ተናግረዋል።
“የበአሉ አከባበር በ2012 የስራ እድል ፈጠራ የሚለው ጎልቶ የሚወጣበት ነው” የሚሉት አቶ ቴዎድሮስ በቱሪዝሙ ዘርፍ ከፍተኛ የስራ እድል ለወጣቱ የሚፈጠርበትና ዜጎች፤ በተለይም ወጣቱ ተጠቃሚ የሚሆንበት የስራ ዘመን እንደሚሆንም ተናግረዋል። ይህ ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ በቅርቡ ያስተላለፉትን መልእክትና ያስቀመጡትን አቅጣጫ ተከትሎ የተያዘ እቅድ መሆኑንም አቶ ቴዎድሮስ ተናግረዋል።
በአሉ የቱሪዝምን ምንነት ከማስገንዘብ ባሻገር አገራችን በዘርፉ ያላትን አቅም የምንለይበት በመሆኑ የጎብኚዎችን ቁጥር፤ በተለይም ያገር ውስጥ ጎብኚዎችን ለማበረታታትና ቁጥራቸውን ለማሳደግ ከፍተኛ ፋይዳ እንደሚኖረው አቶ ቴዎድሮስ ጠቁመዋል፡፡
110 ሚሊዮን ህዝብ ባላት አገራችን ያገር ውስጥ ቱሪስት ቁጥር ገና ከ23 ሚሊዮን አልዘለለም ያሉት አቶ ቴዎድሮስ ይህንን ችግር ለመቅረፍ በዓሉ ከፍተኛ እድል እንደሚፈጥርም ይገልፃሉ።
በአብዛኛው ክልሎች ትልቁን ኃላፊነትና ድርሻ የሚይዙበትና የሚሳተፉበት ይህ በአል ሁሉም ክልል እራሱን የሚያስተዋውቅበት፣ ያለውን የተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ ሀብቱን ለይቶ የሚያውቅበት፣ አውቆም ለሌላው የሚያሳውቅበት፣ የአገሪቱን የቱሪዝም ዘርፍ ከማሳደግ አኳያ ሁሉም የየድርሻውን እንዲወጣ የሚያደርግበት፣ በየአካባቢው የአገር ውስጥ ቱሪስት ቁጥርን ለማሳደግ እድል የሚሰጥበት፣ በዘርፉ ለመሰማራት የሚፈልጉ ባለሀብቶችን ለመሳብ አመቺ ሁኔታ የሚፈጠርበት መሆኑንም ኃላፊው ጠቁመዋል።
አዲስ ዘመን መስከረም 5/2012
ግርማ መንግሥቴ