
አዲስ አበባ ፡- የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ጤናማ ያልሆነ የዋጋ ውድድር ውስጥ መግባታችን ለዘርፉ ዕድገት መሰናክል እንደሆነባቸው ገለጹ፡፡ ውድድሩ ለአደጋ ስጋቶች የሚመጣጠን የአረቦን ክፍያዎችን እንዳናስከፍል አድርጎናልም ይላሉ፡፡
የንብ ኢንሹራንስ ኩባንያ የቢዝነስ ዴቨሎፕመንትና ፕላኒግ ክፍል ኃላፊ አቶ ዮናስ በላይ ለአዲስ ዘመን እንደገለፁት፤ በኢንሹራንስ ኩባንያዎች መካከል የሚታየው ጤናማ ያልሆነ ውድድር ለአደጋ ስጋቶች የምናስከፍለው የአረቦን ገቢ ተመጣጣኝ እንዳይሆን ያደረገ ሲሆን ይህ ለዘርፉ ዕድገትና ለኩባንያዎቹ ህልውና መሰናክል ሆኖባቸዋል፡፡
ኩባንያዎቹ ለአደጋ ስጋቶች በጣም ዝቅተኛ የአረቦን ክፍያ የሚያስከፍሉ መሆኑን አውስተው ለአብነትም አንድ የኢንሹራንስ ኩባንያ የ100ሺ ብር አደጋ ስጋት ዋስትና ቢወስድ የአረቦን ክፍያው አንድ ሺህ ብር መሆን ቢኖርበትም ኢንሹራስ ኩባንያዎች ግን በጣም ቀንሰው 100 ብር የአረቦን ክፍያ የሚያስከፍሉበት ሁኔታ መኖሩን ጠቅሰዋል፡፡
ጤናማ ያልሆነው ውድድርም የኢንሹራንስ ኩባንያዎቹ በሚፈለገው ፍጥነት እንዳያድጉ ማድረጉን አመልክተው፤ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በአጠቃላይ አገራዊ ምርት(ጂዲፒ) ያላቸው ድርሻም ዜሮ ነጥብ ሁለት በመቶ ብቻ መሆኑ የዘርፉ ዕድገት የሚጠበቀውን ያህል አለመሆኑን ያሳያል ብለዋል፡፡
ኢንሹራንስ ኩባንያዎቹ ለሚወስዱት የአደጋ ስጋት ዋስትና ተገቢውን የአረቦን ክፍያ ቢያስከፍሉና አዳዲስ የመድን ዋስትናዎችን ቢሰጡ ኩባንያዎቹ ተደራሽነታቸውን በማስፋት፣ የስራ ዕድል በመፍጠር ረገድ በኢኮኖሚው ላይ የሚኖራቸውን ድርሻ ከፍ የሚያደርገው መሆኑን አቶ ዮናስ ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ነጻነት ለሜሳ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች የአደጋ ካሳ ክፍያ ምጣኔ እየጨመረ ቢሄድም ኢንሹራንስ ኩባንያዎች የምናስከፍለው የአረቦን ክፍያ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መምጣቱ ጤናማ ውድድር መኖሩን ማሳያ ነው፡፡
ለአብነትም ብዙ ካሳ የሚያስከፍል ደንበኛ የአረቦን ክፍያ በአደጋው መጠን ልክ ሲጨመርበት ወደ ሌሎች የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በመሄድ አነስተኛ የአረቦን ክፍያ የሚከፍልበት ሁኔታ ይታያል፡፡ይህም ኢንሹራንስ ኩባንያዎች በሚፈለገው መጠን እድገትና ትርፍ እንዳያስመዘግቡ አድርጓቸዋል፡ ፡
በኢንሹራንስ ኩባንያዎች መካከል ጤናማ ያልሆነ ውድድር መኖሩን በማንሳት በማህበር ደረጃ ውይይት ማድረጋቸውን ያነሱት አቶ ነፃነት፤ በህግ የተወሰነ የአደጋ ስጋት ዋስትና ዝቅተኛ የአረቦን ክፍያ መጠን አለመኖሩ ጤናማ ያልሆነ ውድድር እንዲፈጠር ምክንያት በመሆኑ በጥናት ለመፍታት እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
አቶ ነፃነት ብሄራዊ ባንክ የኢንሹራንስ ኩባንያዎችን ችግር ሊፈታ የሚችል የመድን ስራ ረቂቅ አዋጅ ማዘጋጀቱን ገልጸው፤ የባንክ አነስተኛው የወለድ ክፍያ በህግ እንደተወሰነው ሁሉ ለኢንሹራንስ ኩባንያዎች ደግሞ ተመጣጣኝ በሆነ መልኩ ዝቅተኛ የአረቦን ክፍያ መጠን የሚወስን እንደሚሆን ተናግረ ዋል፡፡
ከአደጋ ተጋላጭነት አንጻር የኢንሹራንስ ኩባንያዎች የሚያስከፍሉት የአረቦን ክፍያ መጠን ከዓመት ዓመት እየቀነሰ መሆኑን የገለጹት የኢትዮጵያ መድን ሰጪዎች ማህበር ዋና ጸሀፊ አቶ ሀዱሽ ህንጻይ ለአደጋ ስጋት የሚያስከፍሉት የአረቦን ክፍያም ከሌሎች ጎረቤት አገራት ጋር ሲነፃፀር አነስተኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ውድድሩን ጤናማ ለማድረግም ማህበሩ ጥናት እያስጠና መሆኑን ገልጸው ጥናቱን መሰረት በማድ ረግም መፍትሄ የሚሰጠው መሆኑን ተናግረዋል፡፡
አዲስ ዘመን መስከረም 5/2012
ጌትነት ምህረቴ