በሠላም አውለን ብሎ መስቀለኛ እያማተበ ግማሹ ሲገባ ግማሹ ይወጣል። አካባቢው ወጪ ወራጁ የበዛበት ይመስላል። ከፊት ለፊት ደግሞ ለወትሮ እንግዳ የማይጠፋው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት (ፓርላማ) ይታያል። ከበሩ ላይ የሚገኙት የፌዴራል ፖሊሶች ጠበቅ ያለ ፍትሻ ካደረጉ በኋላ እንግዶች መታወቂያቸውን በር ላይ ለሚገኙ አስተናባሪዎች እየሰጡ ይገባሉ።
ወዲህ ደግሞ አንገቱን ወደ ፓርላማው ግቢ ሻገር አድርጎ ለተመለከተ የቁጥሮች ድርድር እንጂ ጊዜን የማይናገረው የፓርላማ ሰዓት ፀጥ ብሎ በትንሹ እና በትልቁ ቆጣሪው ከሁለት ቁጥሮች ላይ ተገትሮ ሥራ እንዳጣ ተሽከርካሪ ከአንድ ሥፍራ ተገትሯል።
ሰዓቱ ጊዜን በትክክል ባይጠቆምም ሰዎች እየተጠቋቆሙበት ማለፋቸው አይቀሬ እንደሆነ መናገሩ ነው። አራት ኪሎ ትችትና አድናቆት ያስተናገዱ ህጎች የረቀቁበትና የፀደቁበት፣ ከሞት እስከ ሕይወት ታላላቅ ሁነቶች የተከናወኑበት ይህ ስፍራ የነባሮችና አዳዲሶች እንግዳ መንደር ነው። ወዲህ ለነብሳቸው አብዝተው በሚጨነቁ ሰዎች የተከበበው የቅድስት ስላሴ ካቴድራል ቤተክርስቲያን ጊቢ ውስጥ የሚስተዋለው የሰዎች እንቅስቃሴ ሥፍራውን እረፍት አልባ አድርገውታል። አራት ኪሎ ላይ ከፓርላማው ሠዓት በቀር ሁሉ በጥድፊያና በተጠንቀቅ ላይ ነው። ወጪና ወራጁ አዲስ በሆነበት በዚህ አካባቢ እንቅስቃሴውም በዚያው ልክ ነው።
አቶ ህዝቂያስ ብሩክ ላለፉት ሦስት አስርት ዓመታት አራት ኪሎ ላይ ከትሞ ወጪ ወራጁን እየተመለከተ፤ ለእለት ጉርሱም የሚሆነውን እያሰሰ 28 ዓመታትን አስቆጥሯል። ‹‹49 ዓመት ሳያልፈኝ አይቀርም›› ይላል። በአሁኑ ወቅት አራት ኪሎ ከቅድስተ ሥላሴ ካቴድራል ቤተክርስቲያን ዋናው በር በስተግራ ሸራ ወጥሮ ጫማ በመስፋና በማፅዳት በ‹‹ሊስትሮ›› ሥራ ይተዳደራል።
መሬት ለመሬት እየንፏቀቀ ካልሆነ እንደማንኛውም ሰው ቁጭ ብድግ ማለት አይቻለውም። ገና በአምስት ዓመቱ ሳለ ነበር የአካል ጉዳት ያጋጠመው። ልጅ ሆኖ እየተጫወተ ሳለ ወደቀ። ከዚያም ቀጥ ብሎ መቆም አቃተው። በጉዳቱ ሳቢያ እንደ ጓደኞቹ ቦርቆ ለመጫወት እንቅፋት ሆነበት። ዳሩ ግን በተቻለውና አቅሙ በፈቀደ መጠን ከአብሮ አደጎቹ ጋር እየተጫወተ ለቤተሰብም እያገለገለ አደገ።
ከአዲስ አበባ በቅርብ ርቀት ላይ በምትገኘው መናገሻ ‹‹ሱባ›› የምትባል መንደር ነው የተወለደው። ህዝቂያስ ከዚህ የተወለደበት ሰፈር፤ ዕትብቱ የተቀበረበት መንደር፣ የልጅነት ጊዜውን ካሳለፈበት ከዚህ ሰፈር ዛሬም ትዝታው በአዕምሮው ሽው እልም እያለ ያስቸግረዋል። ምንም እንኳን የአካል ጉዳት ቢደርስበትም በወጣትነት ዘመኑ እርሻ ያርስ ነበር። ግን በሂደት ደግሞ በፈተና ላይ ሌላ ፈተና ገጠመው።
በ1997 ዓ.ም ከፓርላማው ፊት ለፊት ወደሚገኘው አርበኞች ህንፃ ለመሻገር ሲል አደጋ ደረሰበት። ቀድሞ ተጎድቶ በነበረው እግሩ ለይ ድጋሚ ‹‹ላዳ ታክሲ›› ገጨው። ታዲያ ከዚህ ጊዜ በኋላ ነገሮች እየተወሳሰቡ በክራንችም እንደልቡ ቀጥ ብሎ መንቀሳቀስ ከበደው። ብቻ ግን እንደምንም ብሎ ሕይወቱን ይመራ ጀመር። ደግሞ ላዳ ሹፌር ከሶ ማሰቃየቱን አልወደደምና ነገሩን ተውኩት ይላል። በአጋጣሚ ችግሩን የተገነዘበ አንድ ውጭ የሚኖር ሰው ዘመናዊ ‹‹ዊልቸር›› ገዝቶ ሰጠው። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ወደ ተለያዩ አካባቢዎች ሲንቀሳቀስ በፍጥነት በዊልቸሯ ይከንፋል፤ ያንን ሰው አግዚአብሔር ይስጠው እያለ።
ፖለቲካን በሩቁ
ህዝቂያስ በትምህርቱ እስከ ስምንተኛ ክፍል ገፍቷል። ከዚያን በኋላ ግን አቋረጠ ዛሬ ሲያስበው ያንገበግበዋል። የሆነው ሆኖ ከአራት ኪሎ አድባር ስር ቁጭ ብሎ ብዙ ነገሮችን ይታዘባል፤ ምንም እንኳን በብዕር ባይከትበውም በአዕምሮው ይከትበዋል።
ሃይማነተኞች ቅድስተ ሥላሴ ካቴድራል ቤተክርስቲያን ገብተው ተሳለምው ሲውጡ፤ ወዲህ ደግሞ የአገሪቱ ጉምቱ ፖለቲከኞች ወደ ፓርላማው ለመግባት በሱፍ ሲገማሸሩ እየተመለከተ ዓለማዊነትንና መንፈሳዊነትን እያነጻፀረ ወቸ ጉድ! እያለ ሕይወት በየፈርጇ እንዴት እንደሆነ ይቃኛታል። ምንም እንኳን ኑሮውን ከፓርላማው አጠገብ ቢያደርግም ፖለቲካን በሩቁ የሚል አቋም አለው። ‹‹እኔ ምስኪን ድሃ ሆኜ›› ስለፖለቲካ ምን አገባኝ የሚል ሃሳብ አለው። የዕለት ጉርሱን ተንፏቆ ያልቻለውን ፖለቲካ በእንፉቅቅ መምራት ከባድ እንደሆነበት ተገንዝቦታል። ግን ፓርላማ እና ፓርላመኞችን በቅርበት እየተመለከተ ፖለቲካን ደግሞ በርቀት ብሎ የሚኖር ሰው ነው።
የጠጅ ፍቅር
በቀን ስንት ብር እንደሚያገኝ አሊያም ደግሞ ወጪና ገቢውን በትክክል አያውቅም። የዕለት ጉርሱን ስለመሸፈኑ ብቻ ነው የሚጨነቀው። ከዚህ በተረፈ ጠጅ አፍቃሪ ስለሆነ እርሷን ለመቅመስ ካገኘ ደስተኛ ነው። ህዝቂያስ ከመጠጦች ሁሉ ጠጅ አብልጦ ይወዳል። ጠጅ በንጉስ አዳራሽ ለተከበረ ሰው የሚቀርብ እንጂ እንዲሁ ተገኘ ተብሎ የሚጠጣ አሊያም ደግሞ የሚንቆረቆር ተራ መጠጥ አይደለም ሲል ያንቆለጳጵሰዋል። ጠጅ የሚጠጡትም የጨዋታ አዋቂዎች፣ ነገር አሳማሪዎች፣ ሰው አስታራቂዎችና የተከበሩ ናቸው። ቀደም ባሉት ዘመናትም የኢትዮጵያ ነገስታት እንግዳ ወደ እልፍኛቸው ሲመጣ የሚያቀርቡት፣ በአዳራሽ የተከበሩት ሹማምንቶችን ተጠርተው ፍሪዳ ተጥሎ ጮማ ተቆርጦ ካበሉ በኋላ በማር ጠጅ እንዲያወራርዱ የሚያቀርቡላቸው የጨዋ መጠጥ ነው ሲል ያሞካሸዋል።
እርሱ በአሁኑ ወቅትም ጠጅ በፍቅር ይወዳል። በአዲስ አበባ አራቱንም ማዕዘን ከንፎ ሸጋ ጠጅ ካለበት ቤት አነፍንፎ አጣጥሟል። አሁንም ቆንጆ ጠጅ ካለበት ስፍራ እንድምን ሄዶ ያጣጥማል። ከዚህ በዘለለ ሌሎች መጠጦችን አይወድም።
ትዝብት
ምንም እንኳን የጠጅ ወዳጅ ቢሆንም በሌሎች መጠጥ ቤቶች ስለገጠመው ትዝብት ብዙ ገጠመኞች አሉት። ለአብነት ደንበኛ ንጉስ ነው ከሚል ጥቅስ አጠገብ የእንስሳ ምስል ያለበትን ቢራ አስቀምጠው ግራ እንደሚጋቡት ይናገራል። ለመሆኑ ‹‹ደንበኛ ንጉስ›› ነው የሚለው ለቢራው ወይስ ለእንስሳው ሲል ይጠይቃል። አንዳንድ መጠጥ ቤቶች የሚሰቅሏቸው ጥቅሶች ደግሞ እውን ጥቅስ ወይስ ንባብ ነው ሲል ይታዘባል በጣም ከመርዘማቸው የተነሳ።
አንዳንዴ ደንበኛን ለመሳብ ታስበው ከሚሰቀሉ ፅሁፎች በርካቶች ከሞራል አኳያ የማይመጥኑ መሆናቸው ታዝቧል። ከምንም በላይ በርካታ ማስታወቂያዎች ግላዊነትን እንጂ ማህበራዊ ሕይወትን አያጠናክሩም ሲል ትዝብቱን ይገልፃል። እንደ ጠጅ ያሉ መጠጦች ከአቀራረባቸው እስከ አሰራራቸው የበርካታ ሰዎችን ጥረት የሚፈልግ ሲሆን፤ ለጨወታም ድምቀት ወደር የለሽ መጠጥ እንደሆነ አድናቆትን ይናገራል።
አንዳንድ መጠጥ ቤቶች ደግሞ ከዚህ በላይ አትጠጣ ብለው እልክ የሚያስይዝ ማስታወቂያ ለጥፈው ሰውን በእልህ ከአቅሙ በላይ ያስጠጣሉ ይላል። ለአብነት እርሱ የሚጠቀምበት አንድ 22 አካባቢ የሚገኝ ቤት ከሁለት ጠጅ በላይ እንዳይጠጣ ስለሚከለክሉት ሁለት ከጠጣ በኋላ በድብብቆሽ ዓይነት ሌላ ለመጠጣት እንደሚጥር ይናገራል። በእርሱ የአራዳ አባባል ‹‹በሽሉ›› ይጠጣል። እናም እንዲህ ዓይነት ማስታወቂያዎች ከእውቀት ማነስ የሚመነጩ ወይስ እኛን ከማኮሰስ የመጡ ናቸው ሲልም በአግራሞት ይጠይቃል።
ቤት ፍለጋ
ይህ ሰው በአሁኑ ወቅት ቀን ሥራውን እየሰራ ይውልና ማታ እዚያው ቅድስት ስላሴ ካቴድራል ቤተክርስቲያን አካባቢ ወደምትገኝ መጠለያ ይገባል። ቁርስና ምሳውን ለመሸፈን ብዙ ጥረት ያደርጋል እንጂ ሰማይ ለነካው ኑሮ እጅ መስጠት አይሻም። አንዳንድ መልካም ሰዎች ደግሞ አልፎ አልፎ ቁርስ ብስኩት ነገር ከሻይ ጋር ይጋብዙታል።
‹‹በጨወታ አዋቂነቴ ሰው ይወደኛል›› የሚለው ህዝቂያስ ይኸው ዛሬ ደረስኩ ሲል ያመሰግናል። አሁን ተስፋ የሚያደርገው ነገር አለ። ቤት ማግኘት ወይንም ቤት መሥራት። እንደ እውነቱ ከሆነ ቤት መስራት የሚለው ሃሳብ ሰው ስለሆነ የሚያስበው እንጂ ሠዎች ቤት ሰርተው ካልሰጡት በራሱ ወጪ የሚገነባው ሆነ የሚያድሰው ቤት እንደሌለ እርግጠኛ ሆኖ ይናገራል።
እርሱ እንደሚለው ለበርካታ ዓመታት አቅመ ደካማ ነን፤ በዚህ ላይ አካል ጉዳተኛ ስለዚህ ቤት ስጡኝ ሲል የመንግስት አካላትን ተማፅኗል። ግን የእርሱን ህምም የሚታመምለት፤ የእርሱን ስቃይ የሚጋራው ሰው አላገኘም። እንዲሁ ዛሬ ነገ ሲሉት ዓመታት መንጎዳቸውን ያስታውሳል። የሚገርመው ግን ዛሬም ቢሆን ቅን አሳቢዎች ካሉ መልካም ነገር ይኖራል የሚል ሃሳብ አለው። ከሁሉም በላይ ግን አንድ ቀን ነገሮች ተለውጠው የተሻለ ህይወት እንደሚኖረው ተስፋ ያደርጋል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ መስከረም 3/2012
ክፍለዮሐንስ አንበርብር