በዚህ ርእስ ስር መጻፍ ስፈልግ በርካታ ሃሳቦች በልቤ ውስጥ ተመላልሰዋል። እነዚህን የተመላለሱ ሃሳቦች ሁሉ ለማስፈር መድረኩም ዓምዱም አይፈቅዱልኝምና መቆጠብን መረጥኩ። ግን ብዙ ጊዜ ምርመራ የሚለውን ቃል የሚጠቀሙ ሰዎች ስለቃሉ ያላቸው ግንዛቤ አንድም ከህክምና ጋር አለዚያም ከወንጀል ፍተሻ ጋር በቢሮ አካባቢ ያሉ ሰዎች ደግሞ የተጠቀሰውን ሃሳብ ከማጣቀሻነት፤ ጋር ያያይዙታል፤ ምርመራን።
ታዲያ ዋነኛው ነገር ምንን እንዴት እንመርምር የሚለው ነው። በዚህ ትውልድ ውስጥ ችግሮች እንዳሉ እያየን ነው። እነዚህን ፣ ችግሮች ለመፍታት ምርመራውን ከየት እንጀምር? ይህ ዋነኛው ጥያቄ ነው። የትውልዱን ችግር ምንጭ የት እንፈልገው? የአስተሳሰቡን ግድፈት ምንጭ የት እናግኘው? ለዚህስ ግኝትስ ምን መልስ እንስጥ ? ዋነኛውና መልስ የሚያስፈልገው ጥያቄ ነው።
አሁን ወጣቶቻችን ፣ በማዕበል ውስጥ የሚንዠዋዠው ጀልባን የመሰሉበት ጊዜ ነው። አንዳንዴም ይህች ጀልባ በውሃው እየተሸፈነች ውሃው ነው፤ የሚናወጠው ወይስ ጀልባዋ ናት? ብለን እንድንጠይቅ እስክንገደድ ድረስ በሚያሳስት ወጀብ ውስጥ ናቸው። ለነገሩ ለባህሩ መናወጥ ምንጩ፣ ንፋሱ መሆኑ የምናውቀው ቢሆንም ለመለወጣችን አልጨበጥ ባይነትና ህይወትንም በጨለማው በኩል ብቻ የማየት አባዜያችን ምክንያት ነው ማለትም ይቻላል ፤ ከዚሁ ጋር ተያይዞም መፍትሔውን ውጭ ውጭውን በማየት ለመፍታት የመሞከር ልማዳችንም ከምን ይሆን? ስንል መጠየቅም ይገባናል።
እኔ፣ እንደሚመስለኝ፣ እናም እንደማምንበት፣ አንደኛው ችግር፣ የብዙ ችግሮቻችንን፣ ምክንያት ከውስጥ ሳይሆን ከደጅ መፈለጋችን ነው።
ተማሪዎች፣ ትምህርታቸውን ላለመከታተላቸው ምክንያት፣ የራሳቸውን ድርሻ ከማየት ይልቅ፤ ወላጆቻቸውን፣ ወንድምና እህቶቻቸውን ወይም ጓደኛቸ ውን ሰበብ ማድረግ ይቀናቸዋል። አለፍ ሲልም መምህራኖችን ፤ የክፍል ተማሪ ዎችን አንዳንዴም ጥበቃዎችን፣ ርእሰ መምህ ሮችን እና መንግስትን መውቀስ ቀላሉ ማምለ ጫቸው ነው።
ለህይወት ችግሮች ሌላን ሰው ተጠያቂ ማድረግ፣ እጅግ ቀላሉ ማምለጫና ማቋረጫ መንገድ ነው። ግን እውነት ነው ወይ? ስንል መልሱ እሱ ሆኖ አይገኝም፤ ችግርን ማየት መጀመር ያለበት ከውስጥ ነው፤ ከራስ።
እንደ ምሳሌ ላንሳላችሁና፣ አንድ ወጣት ሲናገር፣ “ሲጋራ ማጨስ የጀመርኩት…. አለ፤ …. ጓደኞቼን ለመምሰል ብዬ ነው። እነርሱ ሲጫጫሱና ሲያወሩ ራሴን ዝቅ አድርጌ እንዳላይ ጥሩው መንገድ እነርሱን መምሰል ነበርና አደረግኩት፤” ሲል ነው፤ የተናገረው። እንደ እውነቱ ከሆነ፣ ጓደኞቹ ይህን እንዲያደርግ እጁን አልጠመዘዙትም፤ ግን ልቡን እንዲጠመዝዙት ፈቅዶላቸዋል። “ሌላው ሰው፣ እንዲወጣብህ እስካላጎነበስክ በስተቀር ማንም እዘለኝ ብሎ ሊያዝዝህ አይችልም።” በእግሩ መራመድ እየቻለ፣ አካሉ ላይ የደረሰ ጉዳት ሳይኖር ፣ ተሸከመኝ ፤ ስላለህ ብቻ ከተሸከምከው አጥፊው አንተ እንጂ፤ እርሱ አይደለም። እዚህ ላይ የጓደኛነት ተጽእኖ የለም፤ እያልኩ ግን አይደለም።
ከክፍል “ፎርፌ” ለመስጠትና ላለመማር የጓደኛህ ይሁንታና ፣ የምትወዳት ልጅ ስልክ ምክንያት አይሆንም። እነርሱ፣ በአስማት ይዘውህ ከምትማርበት ክፍል አልወጡም ፤ “ስልክ ያነሳህ አንተው፣ የተስማማህ አንተው ፤ የተራመድከው በአንተ እግር፣ በር የከፈተው ያንተ እጅ፣ ደብተር የተሸከመው ያንተ ትከሻ….” ሆኖ ሳለ ጓደኛዬ ገፋፍቶኝ እኮ ነው ፤ ብሎ ሰው ላይ ማላከክ አይቻልም ። ለጥሪው “የእሽታ “ መልስ የሰጠኸው አንተ ነህ። ለመከራውና ለውጤቱም ዋናው ተጠያቂ ራስህ ነህ። ማንም ላይ ማላከክ አይቻልም ። የችግርህን ምንጭ ደጅ ለደጅ መፈለግ አንድም የዋህነት ነው፤ አለዚያም ሰበበኛነት ነው።
ከዚህ ምሳሌ የምንረዳውም ዋነኛ ነገር፣ ሱስ በሚያሲዝ ዓመልም ይሁን ባልተገባ ባህሪ ውስጥ ለመመላለስ የራሳችን ድርሻ ዋናው ሲሆን ሌሎች ሰዎችና ሁኔታዎች አጋዥ ናቸው።
አንድ ጊዜ ነው አሉ። በሃገራችን አንድ የገጠር አካባቢ አንድ ሽመል (ዱላ ) የያዘ ሰው አንዱን መሳሪያ የያዘ ሰው በዱላ ሊመታው ይሞክረዋል። ጠመንጃ የያዘው ሰው ሸሸት እያለ ሰዎች መሃል ይገባና “ኧረ ይህን ሟች አንድ በሉት ፤ በዱላ ሊሞክረኝ ይከጅለዋል፤” አለ፤ አሉ። “ገዳይ ቢዘገይም ሟች ይገስግሳል።” የሚሉት ብሒል የሚሰራው ይሄኔ ነው። በሌላ ችግር የተያዘ ሰው ጉዳዩን ካልተያያዘ ሌላ ስፍራ መፍትሔ ለማምጣት ከሞከረ ፍጻሜው አያምርም። የችግራችንን መፍትሔ ውስጣችን መፈለግ ልንጀምር ይገባናል።
በሀገራችን ልዩ ልዩ ስፍራዎች የተነሱትን ችግሮች መንስኤ ልብ ብለን በመፈተሽ መፍትሔውን መፈለግ የተገባ ነው። እኔ እንደ ችግሩ ዋነኛ መንስኤ ያልኩት የችግሩን መነሻ ሌላ ቦታ በመፈለግ መፍትሔ ማምጣት ስላለመቻሉ ያነሳሁት ነጥብ እንደተጠበቀ ሆኖ ሌሎች ነገሮችንም አብረን መፈተሽ ይገባል፤ ብዬ አምናለሁ።
ወጣቱና ትምህርቱን ስናይ ደግሞ፣ የተለየ ምስል እናገኛለን። ትምህርት ብለን ስንል የትምህርቱ አዘገጃጀት፣ ካሪኩለሙ፣ የመማር ማስተማር ድባቡ፣ ማለትም የክፍል መምህር ጥመርታው ፣ የመጽሐፍና ተማሪው ምጣኔ ፣መጠነ ማቋረጡን ለመቀነስ እየተደረገ ያለው ጥረትና ስልቱ…. ትምህርቱ የሚቀርብበት መንገድና አሰረጫጨቱን የሚመለከት ነው። በዚህም መሰረት፣ ለወጣቶቻችን የምንሰጣቸው የትምህርት አዘገጃጀቶች ለመሆኑ ምን መልክ አላቸው፣ ማለት ይገባናል። በእውኑ፣ አሳታፊ፣ መከባበርን የሚሰብክ ፣ አድማሱ የሰፋ፣ አንድነትን የሚያሳይና የሚያፋቅር ነው ? ወይንስ ተንኳሽ ፣ ልዩነትን አራጋቢ፣ ቂምና ቁርሾ አነሳሽ፣ በመካከላቸው አጥር አጣሪ እና የከረመ ለቅሶን እያጣቀሰ፣ በደል እየደረደረ፣ ሙሾ የሚያወርድ ነው? ብለን መጠየቅ አለብን።
ባለፉት ሶስት አሰርት ዓመታት በሚገባ ሲጋቱና ሲራገብ የቆየውን፣ መማር ለልዩነት፣ መማር ለመወነጃጀል፣ መማር ለመነቋቆር እንዲሆን ሲደረግ ብዙዎቻችን ቃል አልተነፈስንም። በእኩልነት ስም አለቅጥ ልዩነት ሲራገብ አብረን “ባንስማማም የተስማማን” ደፍረን ያልተናገርን ብዙዎች ነበርን። ሰዎችን “በማንነታቸው አይፈሩ” የተባለውን ክቡር ሃሳብ በመለወጥ ፣ “በልዩነታቸው ይኩሩ“ “ልዩነታቸውን ይደስ ኩሩ፤” መርጠው ባልተወለዱበት” ማንነት ያቅራሩ”፣ በሚል እኩይ ሐረግ በመለወጥ ሐገር በልጆቿ የደም አበላ እንድትነከር ሲደረግ ነበረ።
ከዚሁ ጋር መልካም የነበሩና አንድነትን ይሰብኩ የነበሩ እሴቶቻችን እየተነወሩና ልዩ ቅጽል እየተለጠፈላቸው፣ ከፋፋይ ጽንሰ ሃሳቦች አየሩን እንዲሞሉትና ወጣቶቻችን በዚህ አስተሳሰብ እንዲመረዙ ከመዋእለ ህጻናት እስከ ከፍተኛ ትምህርት ቤቶች ድረስ ያለማቋረጥ ተሰርቷል።
ትምህርት አካባቢን ለመመርመር፤ ሀገርን ለመቃኘት፣ አህጉርን ለመመልከት እና ዓለምን ለማነጻጸር ማገልገል ሲገባው ሰው በሰፈሩ ታጥሮ ፣ በመንደሩ ታስሮ ወንድሙንና የወንድሙን ባህል አስነውሮ እንዲያስብ ሲደረግ ቆይቷል። የራስን ማክበርስ ባልከፋ፣ የራስን ከፍታ ለማሳየት ሌላውን ማሳነስ እንደ አሰራር ታቅዶበት መስራት ግን መለወጥ አለበት።
የሚገርመው በከፍተኛ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ወጣቶች በጋራ በሃገራዊና በአህጉራዊ ጉዳዮች ላይ እንዳይወያዩ፣ በብሔራቸው ታጥረው፣ እንዲቀሩ ማድረግ ብቻ ሳይሆን የእግዚአብሔር የሆኑት ወገኖች እንኳን በአምልኮ ህብረት ደረጃ የአማራ ህብረት፣ የሲዳማ ህብረት፣ የካምባታ ወይም የእንትን ህብረት ብለው የጸሎት ጊዜያቸውን በብሔር ከፍለውት ማየት እንዴት ያሳምማል። ሲጣሉማ አይነሳ…በደብተር የተጣሉ ልጆች ጠባቸው ወዲያውኑ ወደወራሪና ተወራሪ ብሔሮች ፀብ ተለውጦ፤ ብረት መወራወር በሴንጢ መሳነጥ፣ በጩቤ መቧጨቅ ይቀጥላል። ተማሪዎቹ፣ ፣ “ምንህን አመመህ ሲባሉ?” ………. ሳይሉት የቀራቸው ነገር ቢኖር፣ ” ጨጓራዬን እንደ አማራ አቃጠለኝ” ና ”ስኳሩ እንደ ኦሮሞ ከፍ አለብኝ” መባባል ነበር ።
ልዩነታቸው እስከዚህ እንዲዘቅጥ ሥራቸውን የሰሩት አካላት ውጤታቸው ያስከተለውን ድንቁርናና መዘዝ እያዩ፣ ማታ ማታ በ”የዳንስ ወለሉ” ጮቤ እንደሚረግጡ የታመነ ነው። ደግሞ ይህንን የሻገተ አስተሳሰብ፣ በ”ልዩነት እኩልነት” ይሉት ይሆናል፤ አንድም እኩልነት ግን እንደሌለበት ያጤኗል። “ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ” ነውና። ስለዚህ ይህንን የተጠናገረ አስተሳሰብ ከትምህርት ተቋማት ማስወገድና የተስተካከለ እይታ በልጆቻችን ልብ ውስጥ ማስረጽ ጊዜ የማይሰጠው ሥራ ነው።
አንድ ነገር፣ እዚህ ላይ ልጨምር። ታስታውሱ እንደሆነ በየዘመኑ ትምህርት መጀመሪያ ላይ የታሰበባቸውና ከፖለቲካ ጽህፈት ቤቶች እየተዘጋጀ ለአንድ ሳምንት ያህል “የ10ዓመቱ የኢኮኖሚ ስትራቴጂ፣ የአሰራርና አመራር ለውጥና አካሄድ፣ ግብርና መር የኢኮኖሚ ስልት፣ የኢትዮጵያ የቀደሙ የአገዛዝ ዘይቤዎችና የወደፊት ስትራቴጂ….” ተብለው የሚቀርቡ ወረቀቶች እንደ አዝማሪ ግጥም ፣በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉትን አንዳንድ ወገኖች ትምክህተኛ፣ ሌላውን ጠባብ ብሔረተኛ ፣ የተቀረውን ደግሞ ተቸካይና ተራማጅ እያሰኙና ስም እየለጠፉ በማቅረብ ተማሪውም መምህሩም በተባለው መሰረት እንዲሄድ አጋዥና ተወጋዥ ሲያሰባስቡበት እንደነበር ትዝ ይላችኋል።
እነዚህ በመንግስት ወጭ ይቀርቡ የነበሩ የጥላቻ አዋጅ ትርክቶች ህዝቡን ከፋፋይ እንጂ ሰብሳቢ አልነበሩም ፤ የሚያስፈራሩ እንጂ የሚያስተባብሩ መልዕክቶች አልነበራ ቸውም። እኛ የምናስበው እንዲህ ነውና፤ እናንተም እንደ እኛ አስቡ፤ አድምጡና ፈጽሙ፣ የሚባልበት አበል የሚያስገኙ ክፉ አዋጆች ነበሩ። እናም እነዚህን መሰል ነገሮች ከትምህርት ዓምባ መጥፋትና ለነጻ ሃሳብ ማንሸራሸሪያና መነጋገሪያነት መዋል አለባቸው።
በአጠቃላይ የትምህርት ፖሊሲያችን ተመርምሮ ከመዋዕለ ህጻናት እስከ ከፍተኛ ትምህርት ቤቶች ያለው ሥርዓተ ትምህርት፣ በጥንቃቄ በማዘጋጀት ልጆች ፣ ሃገራዊ፣ አህጉራዊና ዓለምአቀፋዊ ሰብእና ተላብሰው የሚወጡባቸው ዓምባዎች እንዲሆኑ መሰራት አለበት።
ሌላው ወጣቶች የክፉ ፖለቲካ (ወገን- ጠል የሆነና ባይተዋር ተጋፊ Zenophobic ይሉታል ፈረንጆቹ) አራጋቢዎችና የ”ሞላቸው የሚነዳቸው” ሃይል ፣ ከመሆን ወደ ኢኮኖሚ አርበኛነትና ፍቅር አብሳሪነት ማደግ የሚችሉበትን ዓውድ ሊመቻች ይገባዋል። የሥራ ሃሳቦቻቸውን ማሳደጊያ ስልት መፍጠር፣ የሥራ እድሎችን ቦታም ፣ ነገድ፣ ዘርና ብሔር ሳይለዩ መስራት የሚችሉበትን አጋጣሚ ሁሉ ማመቻቸትና አሳታፊ ማድረግ እንዲሁም በምክርና በፋይናንስ በመደገፍ ለተሻለ ደረጃ እንዲበቁ ማገዝ ተገቢ ነው።
ከሁሉም በላይ ወጣቶቻችን ምን ፣ መቼ ፣ እንዴት ለመሆን፣ ምን ለመሆን እና የት ለመስራት እንዳሰቡ አውቀው እንዲሰሩ በማድረግና እርምጃቸውን በመገምገም እንዲጓዙ በመደገፍ፣ ታላላቆች ለታናናሾች፣ የቀደሙት ለኋለኞቹ ልምድ እንዲያካፍሏቸው ዕድል ማመቻቸት ተገቢ ነው።
እንኳንስ ግለሰብ፣ “ህዝብ እንኳን ራዕይ ከሌለው ይጠፋል”ና ፤ በራዕይ መመላለስ የሚችሉበትን እድል በመፍጠር መጓዝ አስፈላጊ ነው ። ያለራዕይ ጉዞ የዕውር ድንብር እርምጃ ነውና ። ፈረንጆችም “Clarity to eliminate ambiguity” ይላሉና ለነገሮቻችን፣ ለመፍትሔዎቻችንና ለግንኙነቶቻችንም ጥርት ያለ ምስል መፍጠር የተገባ ነው። ስለዚህ የራስን ችግር ማወቅ፣ ተነሳሽነትን መመርመርና በጽናት መጓዝ ከሚፈለገው ግብ ያደርሳል።
ዓለምን ለማሾር የሚነሳ ዓላማ የሚጀምረው በጥቂት እርምጃ ነው፤ ሁሉ በተሟላበት ዓለም ለመነሳት የቻለ ጉዞ በየትኛውም የዓለም ክፍልና ባለራዕይ የለም። ከላይ እንደተገለጠው ራስን መርምሮ ማነሳሳትና በጽናት መሄድ ያስፈልጋል።
ስለዚህ በትምህርታችንም ዕውቀት ለመጨበጥና በቴክኖሎጂ ምጡቅ የሆነች ሀገር ለመፍጠርም እንዲሁም የኢኮኖሚ ትንሳኤያችንን ለማብሰር ቀድመን፣ የምንፈልገውን ግብ ማወቅ፣ በተፈጥሮ የተቀበልነውን ተሰጥኦዋችንን መጠቀም፣ ከሌሎች ልምድ መካፈልና ማዳበር፣ በተገቢ ዕውቀት ማሸት ፣ ለዚህም በትኩረት መነሳት ቀጠሮ የሚሰጠው ጉዳይ አይደለም።
በመሆኑም፣ ራሳችንን እንመርምር፤ ዙሪያ ገባችንን እንመርምር፣ ማህበረሰባችንን እንመርምር፤ ለሀገራችን የተሻለ ነገ ለመፍጠር እንነሳ። ለዚህም ከመጻህፍት ንባብ ልምድ እንቅሰም፤ ከአረጋውያን የህይወት ልምድ የምንካፈልበትን እድል እንፍጠር፤ ያኔም ምንን ለምን እንደምናደርግ ይገባናል።
ከዚህ ሌላም በርካታ ችግር አባባሽና ነገር አመቻች ውጫዊ ሁኔታዎች እንደሚኖሩ ትረዳላችሁ ብዬ አስባለሁ። ሰው በተፈጥሮው ከሥጋ፣ ነፍስና መንፈስ ውሁድ ነውና ህይወቱ መንፈሳዊም ስለሆነ ስለመንፈሳዊ ህይወቱ ምግብና ሥራ (አኗኗር) መመርመርም ይገባዋል ። ለዚህ ጥያቄ መልስ ለመስጠት በተመስጥኦ ተቀምጦ ማብሰልሰል እና እየሆንኩ ያለሁት ነገር የተገባ ነውን? ያዋጣኛል ወይ? ሊል ይገባዋል። እንዲህ ካልሆነ ፣ መንፈስ በረሃብ ይሞታል። ያኔም ነፍስ የራሷን ምርጫ ትወስዳለች። ሥጋም እንዲሁ ያንን ፈለግ ይከተላል።
አንድ ተከታታይ የሆነ ፊልም (‹The Last man on Earth› የሚል) አንድ ሰሞን ወጥቶ በመገረም ለማየት ሞክሬ ነበር ። የፊልሙ ዋነኛ ገጸ ባህሪ ፣ በዓለም ላይ ያለ ሰው ሁሉ በአንድ ቫይረስ ጥቃት ሳቢያ ጠፍቶ በፈራረሰ ከተማ ውስጥ ራሱን ለብቻው ተርፎ ያገኘ ሰው ነው። ይህ ሰው ታዲያ ከፈራረሰው ከተማ ውጭ በሞላው ሀገር ውስጥ አንድ ሌላ ነፍስ ፍለጋ ሲንከራተት ይታያል። ሁሉም ነገር እንኳን የራስ ሆኖ ሌላ ሰው ከሌለበት ያለን ነገር ሁሉ የለንም ወይም ከንቱ ነው። የፊልሙ ጭብጥ ሲጠቃለል ሰው ዓለምን ሁሉ በእጁ ጨብጦ እንኳን ሰው ካላገኘበት የያዘው ሁሉ ምንም መሆኑን የሚያሳይ አንድምታ ያለው፣ ነው።
ሁሉም ነገር ያለሰው ምንም ነው። ስለዚህ የምናደርገው ነገር ሁሉ፣ በምድር ከሰው ጋር፣ ለሰው ልጅ ልዕልናና በሰው ልጅ መስተጋብር ሲሆን ነው፤ የሚያምረው። እርስ በእርሳችን የጉድለታችን ሙላቶች እንጂ፤ የሙላታችን ጉድለቶች አይደለንም ።
ስለዚህ ስንመረምር የምንመረምረው ከሰው ልጅ ጥቅም ደስታና ትፍስህት፣ ከልባዊ እውነት ጋር በማስተያየት ይጠቅማልን? እውነት ነውን? በሌላው ሀዘን አይፈጥርምን? ህሊናን ያረካልን፤ ያስደስታልን ? ብለን በመመርመር ካደረግነው ውጤታማነታችን አያጠያይቅም።
የምርመራችን ሁሉ ግብም መሆን ያለበት ይኼው ነው። ራስን በመመርመር ለማህበረሰብ ደህንነት፣ ለሀገር ጥቅምና ለሰው ልጅ በረከትነት በመልካምነት መኖርን ማወቅ መቻል ነው። መልካም ራስን የመመርመር ሳምንት እንዲሆንላችሁ እመኛለሁ!!
አዲስ ዘመን ቅዳሜ መስከረም 3/2012
በአገልጋይ ዮናታን አክሊሉ