የ2008 ዓም አዲስ ዓመት ክረምቱን ገፎ ብቷል። የአደይ አበባ ሽታና የአዲስ ጀንበር ብርሃን ምድሪቱን እያደመቀ ነው። የልጃገረዶች ጭፈራ በአቻ ወንዶች ሆታ ታጅቦ መስከረምን አጥብቷል። ይህ ወቅት ሁሌም ለፍጥረታት አዲስ እንደሆነ ነው። አሮጌው ዘመን ተሽሮ፣ ተተኪው ይሞሸርበታል። ብሩህ ተስፋ ተነድፎ፤ መልካም ምኞት ይበሰርበታል።
በዓል በመጣ ቁጥር በየመንገዱ የሚኖር ግርግር ከወትሮው በእጥፍ ይጨምራል። የጎዳናው ንግድ፤ የገበያው ትርምስና የእግረኞች ብዛትም በቀላሉ አይ ቀን ስም ። ከዋዜማው እስከ ማግስቱ ከነድምቀቱ ይቀጥላል።
በነዋሪ ብዛት የሚታወቀው የጀሞና አካባቢው በተለይ በእንዲህ አይነቱ አጋጣሚ በድምቀት ውሎ ይመሻል። በዚህ ወቅት እግረኞች ከጎዳና ነጋዴዎች እየተጋፉ፣ መንገዱን ያጠብባሉ። ታክሲዎችና፣ ባጃ ጆችም ያዩትን ሁሉ ለመሻማት በየራሳቸው ይዋክባሉ።
ዙሪያ ገባውን ያሉ የንግድ ቤቶች ጦማቸውን ውለው አያውቁም። መዝናናትን የሚሹ ሁሉ ከሳሎናቸው ውለው ያመሻሉ። ጭፈራ ቤቶችና የመጠጥ ግሮሰሪዎች ይህን ጊዜ ተጠ ቅመው በሙዚቃና በልዩ መስተንግዶ እንግዶችን ለመሳብ መጣራቸው ተለምዷል። በጋራ መኖሪያ ቤቶች የታነፀው ይህ ሰፈር ዕድገቱ ከሌላው አካባቢ ቀድሞ የፈጠነ መሆኑ ይነገርለታል።
ነጋዴዎችና ሠርተው መለወጥ የሚሹ ታታሪዎች፣ ኪስ ዳባሾችና ማጅራት መቺዎች፣ መንተፈው ሯጮችና በርከት ያሉ ነዋሪዎች በዚህ ጎዳና በእኩል ይመላለሳሉ። ሁሌም ጀሞና አካባቢው በመልከ ብዙ ገጽዎች ተከቦ ክፉና ደግ ወሬዎች ይሰሙበታል።
መስከረም 3 ቀን
2008 ዓ.ም
እነሆ! ከአዲሱ ዓመት ላይ ሦስት ቀናት ተነስተዋል። የመስከረም አየር በጠራው ሰማይ ውሎ የወሩ መጀመሪያን አንድ ሲል መቁጠር ይዟል። አሁንም የአውደ ዓመቱ ጠረን ስፍራውን እንዳወደው ነው። የዕንቁጣጣሽ ዜማና የአገር ልብሱ ድምቀት አልደበዘዘም። የልጆች ጭፈራና የዓመት በዓሉ ምርቃት ከጆሮ አልጠፋም።
ጀሞ ቁጥር አንድ ከአስፓልቱ ዳርቻ ከአንዱ የጋራ መኖሪያ ሕንፃ ሥር ያለውን የጭፈራ ቤት ብዙዎች ያውቁታል። አንዳንዶች ለመዝናናት በዚህ ስፍራ ማምሸትን ይመርጣሉ። በርካቶች ሰዓቱ ሲገፋ የሚኖረው ድምቀትና ነፃነት ይመቻቸዋል። በሙዚቃ እየጨፈሩና በመጠጥ እየተዝናኑ ጊዜን የሚገፉ ደንበኞች ጥቂት አይደሉም።
የዛን ቀን ምሽት ከወትሮው የተለየ ሆኗል። የአውደ ዓመቱ ድባብ የፈጠረው ድምቀትም ብዙዎችን የሳባቸው ይመስላል። ጓደኛሞች፣ ፍቅረኞች፣ ብቸኞችና ሌሎችም በየ ጥጉ ተቀምጠው በራሳቸው ዓለም ይዝ ናናሉ። አስተናጋጆች የሚታዘዙትን ለማድረስ ከወዲያ ወዲህ ይላሉ። የመጠጥ ጠርሙሶችና ብርጭቆዎች ሥራ አልፈቱም። ከፍ ብሎ የተከፈተው ሙዚቃም ከቤቱ ልዩ መብራት ጋር ተዛምዶ ጥቂቶች እንዳሻቸው ይሆኑበት ይዘዋል።
በስፍራው የቆዩና መዝናናቱ የበ ቃቸው አንዳንዶች ሰዓታቸውን አይተው መነሳት ጀምረዋል። ሌሎች ከሌላ ስፍራ የቆዩ ደግሞ ቤቱን መርጠው ወደ ውስጥ ማምራት ይዘዋል። ሰዓቱ በገፋ ቁጥር ገበያው የሚደራው መጠጥ ቤት አሁን በሰዎች ሙላት እየተጨናነቀ ነው።
ምሽት 4፡ ሰዓት ከ30 ድንገት ወደስፍራው ብቅ ያሉት ሁለት ወንዶች ከኋላቸው ሁለት ሴቶችን አስከትለው ወደወስጥ ዘለቁ። ማንነታቸውን የሚያውቁ አስተናጋጆችም ፈጠን ብለው ወንበር ጠቆሟቸው። ሙዚቃው ከጣራ በላይ እየተሰማ ነው። ሰዎቹ የፈለጉትን አዘው ጨዋታቸውን ቀጥለዋል።
ትዕግስትና ሜሮን ባልንጀሮች ናቸው። ከሁለቱ ወንዶች አንደኛው ደግሞ የጭፈራ ቤቱ ባለቤት ተሾመ ሲሆን አብሯቸው ያለው መኮንንም የጓደኛ ያህል የሚቀርበው ደንበኛው ነው።
ተሾመ ሜሮን የመኮንን ፍቅረኛ መሆኗን ያውቃል። አንዳንዴ ምሽት የሱን ቤት ማዘውተራቸው ደግሞ ቀረቤታቸውን የተለየ አድርጎታል። ሰሞኑን በመኮንን ህመም ምክንያት ተጠፋፍተው ቢቆዩም የምሸቱ አጋጣሚ ዳግም አገናኝቶ ወጋቸውን ቀጥለዋል።
መኮንን የታሸገ ውሃውን አየተጎነጨ ሁለቱ ሴቶች የተከፈተላቸውን ቢራ እንዲጠጡ ይጋብዛል። የቤቱ ባለቤት ተሾመም ከውስጥና ከውጭ ያሉ ደንበኞችን በዓይኑ እያማተረ ከጨዋታው ይሳተፋል። ውሏቸውን በመኮንን ቤት ያደረጉት ሁለቱ ሴቶች አመሻሹን ዘና ለማለት በመፈለጋቸው ምርጫቸው በጭፈራ ቤቱ ሆኗል።
ሁለቱ ወንዶች በራሳቸው ጨዋታ ተጠምደው እየተወያዩ ነው። ሴቶቹም ከቢራቸው እየተጎነጩ መዝናናት ቀጥ ለዋል። ከውስጥና ከውጭ ያሉ ደንበኞችን በማስተናገድ ያልቦዘኑት ሠራተኞች ሩጫ ላይ ናቸው። ሁሉን እንደየጠባዩ ተቀብለው በትዕግስት ይሸኛሉ።
ትግስትና ሜሮን ከጨዋታውና ከቢራው አንድ እያሉ ነው። በመሐል ደግሞ ወደ መፀዳጃ እየሄዱ ይመለሳሉ። ተመልሰውም የጀመሩትን ቢራ በሳቅ እያዋዙ ይጎነጫሉ። ሴቶቹ በመ ፀዳጃ ምልልሳቸው አንድን ሰው አስተውለዋል። ይህ ሰው ከቀናት በፊት ሜሮንን ሊተናኮላት የሞከረው ‹‹ቾምቤ›› የተባለው ወጣት ነው።
በወቅቱ ሜሮን ልክ እንደዛሬው በአንድ መዝናኛ ውስጥ ነበረች። ፍቅረኛዋ መኮንንና ትዕግስትም አብ ረዋት ነበሩ። በዕለቱ ቾምቤ በስካር ናውዞ እየተንገላወደ ቀረባት። ክፉ ቃላት እየሰነዘረም ሊያዋርዳት ሞከረ። በዚህ ብቻ አላበቃም። ቀረብ ብሎ ሊመታት ተገለገለ።
ሜሮንን ጨምሮ ጓደኟዋ መኮንን የቾምቤን ድርጊት ከስካር ቆጥረው ሊታገሱት ሞከሩ። በስፍራው የነበሩ ሌሎችም ከአካባቢው እንዲርቅ ደልለው አስወጡት፤ ዛሬ ሜሮን ይህን ሰው በዚህ ስፍራ ዳግም ማግኘቷ አስገርሟታል። ከሩቁም ለጓደኛዋ አሳይታ በትውስታ አውርተውታል።
ቾምቤም ቢሆን ሴቶቹን በሩቁ አይቶ ለይቷቸዋል። አብሮት ለተቀመጠው የፌዴራል ፖሊስም በእጁ እየጠቆመ የሆነ ቃል ሹክ ብሎታል። ከእጆቹ ጥቁር የሹራብ ጓንት ያጠላቀው ፖሊስ ክላሽ መሣሪያውን ከጉልበቱ አጋድሞ ቾምቤ የሚለውን ሁሉ በትኩረት አዳም ጧል። ግንባሩን እየቋጠረና እየፈታ፣ ባሻገር እያየና እየገላመጠ ካለበት ሆኖ ተቁነጥንጧል። ከቤቱ ውጭ ተቀምጠው ድራፍት ከሚጎነጩት ሦስት ሰዎች መሐል የእሱ ስሜት የተለየ መሆኑ በግልጽ ያስታውቃል።
ፖሊሱ አስተናጋጇን ጠርቶ አንድ ቢራ አዘዘ። የታዘዘቸውን ይዛ ከመምጣቷ በፊትም ከመቀመጫው ተነስቶ ወድወጭ ቃኘ። በረንዳውን አልፎ መራመድ ሲጀምር እነሜሮን ዳግም ወደ መፀዳጃው ለመሄድ እየተያዩ ነበር። ፖሊሱ ከእነሱ ቀድሞ ወደ መፀዳጃው አለፈ። ወዲያው ከኋላው የደረሱት ጓደኛሞች እየተሳሳቁ ወደ በሩ ተቃረቡ።
ሜሮን በቅርበት ተጠግታ ገረበብ ብሎ የተዘጋውን በር አንኳኳች። ውስጥ ሰው መኖሩን ስታውቅ ግን በድንጋጤ መለስ ብላ ይቅርታ ጠየቀች። ፖሊሱ የእነሱን መነሳት በማየቱ በፈጣን እርምጃው ቀድሟቸው ነበር። አሁን ከበሩ ቆማ ይቅርታ ያለቸው ሴት ሜሮን ስለመሆኗ እርግጠኛ ሆኗል።
በሩን ከፍቶ ሲወጣ ሁለቱም ከመተ ላለፊያው ቆመው ነበር። የመፀዳጃውን መለቀቅ አይተው ወደውስጥ ሲያመሩም እሱ በአጭር ርቀት ሆኖ ከጀርባቸው ለማየት አመችቶታል።
ሁለቱ ሴቶች ከመፀዳጃው ቆይተው ወደ ወንበራቸው ሲያመሩ ፖሊሱ ከመተ ላለፊው መቆሙን አስተውለው ተያዩ። ከደቂቃዎች በፊት ‹‹ቾምቤ›› ከተባለው ወጣት ጋር አፍ ለአፍ ገጥሞ ሲያወራ ነበር። እንዲህ ከሆነ ደግሞ እነሱ ባሉበት አካባቢ መገኘቱ አጋጣሚ ላይሆን ይችላል።
አሁን ብቻውን ቢሆንም መንገዱን ዘግቶ መቆሙ አስደንጋጭ ነው። ከትከሻው የዋለው ክላሽ ደግሞ ከምንም በላይ ያስፈራል። የፊቱ መኮሳተርና የአስተያየቱ ክፋትም የጤና አይመስልም።
ወታደሩ ድንገት ጀርባውን አዙሮ ፊቱን ወደእነሱ መለሰ። ይህኔ ሁለቱም ከዚህ ቀድሞ አይተውት እንደማያውቁ እርግጠኞች ሆኑ። እሱ ግን ጣቱን ወደ ሜሮን እየጠቆመ ‹‹ምን አባሽ ስለሆንሽ ነው ሰው የማታናግሪው›› ሲል አፈጠጠባት። ንግግሩ የቀልድ የመሰላት ሜሮን ጓደኛዋን በፈገግታ እያስተዋለች ዝም አለችው።
ከሜሮን ምንም ምላሽ ያላገኘው ወታደር ፊቱ ላይ ንዴት ታየበት። ጥርሱን ነክሶ ተጠጋትና አንድ ጥፊ ፊቷ ላይ አሳረፈባት። አስከትሎም በቦክስ ያጣድፋት ጀመር። ምቱን መቋቋም የተሳናት ወጣት ራሷን መከላከል አልተ ቻላትም። ዕንባዋን እያዘራችና እየጮኸች ከመሬቱ ተዘረረች።
የሆነውን ሁሉ ማመን ያቃታት ትዕግስት የጓደኛዋን ሁኔታ አስተውላ ለግልገል መሐል ገባች። ይህኔ ወታደሩ በንዴት እንደጋመ ፊቱን ወደ እሷ መለሰ። የተቀባበለውን መሣሪያ ከትከሻው አውርዶም በቀጥታ ተኮሰባት። ጥይቱ አቅጣጫውን ቀይሮ ሳያገኛት ቀረ። እሷ በጥይቱ ስለመሳቷ እያመነች አይደለም። የሆነውን ሁሉ መቀበል ተስኗታል። በድንጋጤ እየሮጠች ወደ መፀዳጃው ገብታ ስትደበቅም በፍርሐት እንደራደች ነበር።
ፖሊሱ በንዴት የሚንቀጠቀውን እጁን ዳግም ከመሣሪያው አዋለ። አይኖቹን ጣል ሲያደርግም ሜሮን ከወደ ቀችበት ለመነሳት አቅም እንዳጣች አስተዋለ። ጊዜ አላጠፋም። እንደ ጓደኛዋ ሮጣ ከማምለጧ በፊት ቃታውን ስቦ አፈሙዙን ወደእሷ አዞረ። አልሳታትም። ጥይቱ የግራ ጡቷን ቦጭቆ ወደጀርባዋ ሲያልፍ አስተዋለ። ዳግመኛ መሣሪያውን አመቻቸቶ ተኮሰ። ጥይቱ አሁንም የግራ እግሯንና ጎኗን በስቶ በርቀት ተሸቀነጠረ። ወዲያው ስፍራው በደም ጎርፍ ተጥለ ቀለቀ።
ወታደሩ ያሻውን የፈፀመ ይመስላል። እንደ አዳኝ አውሬ አይኖቹ እየቃበዙ መላ ሰውነቱ ይንቀጠቀጣል። በዚህ ስሜቱ እምብዛም አልቆየም። መሣሪያውን አንስቶ አፈሙዙን ወደጭንቅላቱ አዞረ። አሁንም ከክላሹ ሆድ የተተፋው ጥይት በፍጥነት አምባረቀ። ቅንድቡን ገምሶም ደም እንደጎረሰ እሱን ጥሎ ወደቀ።
አሁን ሁለቱም በደም ተበክለው ጎን ለጎን ወድቀዋል። የትዕግስትን ጩህትና የከባድ መሣሪያውን ድምጽ የሰሙም በድንጋጤ ተሯሩጠው ደርሰዋል። ሜሮን በመጠኑ ትንፋሽዋ ይሰማል። በከባድ ስቃይ ውስጥ ሆና እየቃተተች ነው። በመኪና የፈጠኑ ቁስለኛዋን ይዘው ጤና ጣቢያ ደጃፍ ደርሰዋል። ያም ሆኖ ህይወቷን ማትረፍ አልተቻላቸውም። ባለጠመንጃው ወታደር ግን ጉዳቱ ለሞት የሚያበቃው ባለመሆኑ በቂ ህክምና አግኝቶ ህይወቱ ተርፏል።
የፖሊስ ምርመራ
ከስፍራው የደረሱ ፖሊሶች ሙያዊ ምርመራቸውን ጀምረዋል። በምሽት ቤቱ ለተፈፀመው ወንጀል ምክንያት ነበር የተባለው ‹‹ቾምቤ›› ከስፍራው ከራቀ ቆይቷል፡ ሟች፣ እጮኛዋና የሴት ጓደኛዋ ከዚህ በፊት ከወታደሩ ጋር ትውውቅ ቀርቶ ተያይተው ያለማወቃቸው ለብዙዎች መነጋገሪያ ሆኗል። ወታደሩ ሟችን በፍቅረኛው ፊት መግደሉም አሳዛኝ ዜና ሆኖ ሰንብቷል። ተጠርጣሪው በበኩሉ ድርጊቱን ሲፈፅም ምንም የሚያስተውሰው ነገር እንደሌለ ለፖሊስ በሰጠው ቃል አረጋግጧል።
በፖሊስ በመዝገብ ቁጥር 298/08 የተከፈተው ፋይል በመርማሪ ሳጂን አማረ ቢተው መሪነት በየዕለቱ መረጃዎች እየተመዘገቡበት ነው። ተጠርጣሪው በዕለቱ ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት ወደ ቡና ቤቱ ለመምጣት ምክንያት የሆነው ራት ለመብላት የመፈለጉ እውነት ነበር። ይህንንም አብሮት ሲጠብቅ የነበረው ጓደኛው በሰጠው ምስክርነት አረጋግጧል።
ፖሊስ የውግ ቁጥሩ 9560 የሆነውንና ወንጀሉ የተፈፀመበትን ክላሽንኮፕ መሣሪያ ሲያነሳ ከነበሩት 150 ጥይቶች መሐል ሰላሳ ያህሉ መጉደላቸውን አውቋል። የፌዴራል ፖሊሱ በሟቿ ላይ ድረጊቱን ሲፈፅም ያለምንም የቂም በቀል መነሻና ያለአንዳች ትውውቅ ስለመሆኑም ከበርካታ እማኞች ጠይቆ ለማወቅ ችሏል።
ፖሊስ በተለያዩ ማሳያዎች የሰነዳ ቸውንና ተጠርጣሪውን ለክስ ያበቃሉ ያላችውን ማስረጃዎች በጠንካራ መረጃዎች አያይዞ አጠናቋል። ጉዳዩን ወደ ዓቃቤ ሕግ በማሳለፍም የጊዜ ቀጠሮ አስይዞ በመጠባበቅ ላይ ነው።
ውሳኔ
ጥቅምት 2 ቀን 2010 ዓ.ም የተሰየመው የአራዳ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የተከሳሽ ፖሊስ ሙሉ አበበን የመጨረሻ የፍርድ ውሳኔ ለማሳለፍ በቀጠሮ ተገናኝቷል። ፍርድቤቱ ከፖሊስና ከዓቃቤ ሕግ የደረሰውን የምርመራ ውጤት አገናዝቦም ከውሳኔ ላይ ደርሷል። በዕለቱም ተከሳሹ ሆን ብሎ በፈፀመው የከባድ ሰው መግደል ወንጀል ጥፋተኛ ሆኖ በመገኘቱ እጁ ከተያዘበት ጊዜ በሚታሰብ የአስራ ስምንት ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ሲል ወስኖበታል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ መስከረም 3/2012
መልካምሥራ አፈወርቅ