
– አገልግሎቱ ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ይገመታል
አዲስ አበባ፦ በ2011 የበጀት አመት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በወጣቶች የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከአንድ ሚሊዮን በላይ የበጎ ፈቃደኞች መሳተፋቸውንና ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የጉልበት አስተዋጽኦ መደረጉ ተገለጸ፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የወጣቶችና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ቢሮ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ማስተባበሪያ ዳይሬክተር አቶ አክሊሉ ትዕዛዙ ለአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል እንደገለጹት፤ አገልግሎቱ የተከናወነው በወጣቶች የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ነው፡፡
እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ፤ በበጀት አመቱ በስምንት የበጎ ፈቃድ አይነቶች አገልግሎቱ ሲሰጥ የቆየ ሲሆን በዋንኛነትም በተለያዩ ትምህርት ቤቶች ሲካሄድ የቆየው የማጠናከሪያ ትምህርት የተለየ ትኩረት ነበረው ብለዋል።በዚህ መርሀግብር በ114 ጣቢያዎች ለሚገኙ ከ13ሺ በላይ ተማሪዎች የማጠናከሪያ ትምህርት የተሰጠ ሲሆን 16ሺ የሚሆኑት ደግሞ መሰረታዊ የኮምፒውተር ስልጠናን አግኝተዋል፡፡
ስልጠናው ሲሰጥ የቆየው ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ከመጡና ቁጥራቸው 2ሺ800 በሚሆኑ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መሆኑን የጠቀሱት አቶ አክሊሉ፤ ከዚህ ጋር ተያይዞም መስማትና ማየት ለተሳናቸው 280 ተማሪዎች በተደረገው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በሶስት የተለያዩ ጣቢያዎች ስልጠናው ተሰጥቷል፡፡
በጀት ዓመቱ በትምህርት ዘርፍ ለ64ሺ 883 እገዛ ለሚያስፈልጋቸው ተማሪዎች አገልግሎት ሲሰጥ የቆየ ሲሆን ሁሉም እንቅስቃሴ የተከናወነውም በበጎ ፈቃደኝነት በነበረ መነሳሳት ነው፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ በተመረጡ 131 አደባባዮችና መስቀለኛ መንገዶች ላይ በነበረው ተሳትፎም ከ3ሺ100 በላይ የሚሆኑ በጎ ፈቃደኞች የመንገድ የትራፊክ ደህንነቱን ሲያስተባብሩና ለህብረተሰቡ ግንዛቤ ሲሰጡ ቆይተዋል።በበጀት አመቱ በነበረው የደም ልገሳ አገልግሎት በበጎ ፈቃደኛ ወጣቶቹ አማካኝነት ከ20ሺ ሊትር በላይ ዩኒት ደም ከህብረተሰቡ ተለግሷል፡፡
እንደ አቶ አክሊሉ አገላለጽ፤ በበጀት አመቱ ለአቅመ ደካማና ረዳት ለሌላቸው አረጋውያንና አካል ጉዳተኞች ቤት ለማደስ የተያዘው ዕቅድ አንድ ሺህ ቢሆንም በከተማ አስተዳደሩ በነበረው የስራ ተነሳሽነት ጭምር የ 1ሺ441 አረጋውያንና አካል ጉዳተኞች ቤት ታድሷል፡፡
ጥገና የሚያስፈልጋቸው የተለያዩ ተቋማትን ለማደስ በተደረገው እንቅስቃሴም 488 ትምህርትቤቶችና አምስት ሆስፒታሎች የታደሱ ሲሆን በተመረጡ 459 ቦታዎች ላይ በነበረው የጽዳት ዘመቻም 7ሺ869 ሜትር ኩፕ ቆሻሻን በማንሳትና አካባቢውን መልሶ በማጽዳት አረንጓዴ ቦታዎችን ለህብረተሰቡ ማስረከብ ተችሏል፡፡
በሰብዓዊ አገልግሎት በየሆስፒታል የሚገኙ ህሙማንን የመንከባከብና ሌሎች ግልጋሎቶችን የማበርከት ፓኬጅ በአዲስ መልክ የተጀመረ ሲሆን በ10 ሆስፒታሎች ላይ አንድ ሺህ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ተሰማርተው ቆይተዋል፡፡
የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጻር የተሻለ ነበር ያሉት አቶ አክሊሉ በ2010 ዓ.ም በነበረው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በ880ሺ የበጎ ፈቃድ አገልጋዮች 56 ሚሊዮን ብር የሚገመት የጉልበት አስተዋጽኦ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
በ2011 ዓ.ም በከተማዋ በነበረው የበገ ፈቃድ አገልግሎት ህብረተሰቡን ጨምሮ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሰዎች የተሳተፉ ሲሆን የመርሀግብሩ እንቅስቃሴ በገንዘብ ሲተመንም ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ ይገመታል፡፡
አዲስ ዘመን መስከረም 3/2012
መልካምስራ አፈወርቅ