አቶ አብዱልፈታህ አብደላ የሀገረሰብ ጥናት ተመራማሪ ናቸው። በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ወደ 57 የሚደርሱ ጥናቶችን አድርገዋል። ከዚህ ውስጥ 10 የሚደርሱትን በመጽሐፍ መልክ አዘጋጅተው ለአንባቢያን አቅርበዋል። መጽሐፎቹ በሀገረሰብ አስተዳደር፤ ታሪክና የህግና ፍትህ ስርዓቶች ላይ የሚያተኩሩ ናቸው። ከነዚህም ውስጥ ዋና ዋናዎቹ፤ የወለኔ ሕዝበ ታሪክ፤ የወለኔ ሕዝብ ባህላዊ ህግ፤ የኮንሶ ብሔረሰብ ባህል የህግ ሥርዓት፤ የኮሬ ብሔረሰብ ባህል የህግ ሥርዓት፤ የቡርጂ ብሔረሰብ ባህል ህግ ሥርዓት፤ የደራሼ የሞሊዬ፤ የማሾሌና የኩስሜ ብሔረሰቦች የባህል ህግ ሥርዓት፤ የአፋር ሕዝብ ባህል ህግ ሥርዓት፤ የሀገረሰብ አስተዳደር፤ የህግና የፍትህ ሥርዓቶች በኢትዮጵያ የሚሉት ዋና ዋናዎቹ ናቸው። በአሁኑ ወቅት የሀገር በቀል ዕውቀቶች ጥናትና ምርምር ተቋምን መስርተው ልዩ ልዩ ምርምሮችን በማድረግ ላይ ይገኛሉ።
የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍልም ከእኒህ የሀገረሰብ ጥናት ተመራማሪ ጋር ቆይታ አድርጓል፤ መልካም ንባብ።
አዲስ ዘመን፡- የሀገር በቀል ዕውቀቶች ላይ እንዲያተኩሩ ያደረገዎት ምክንያት ምንድን ነው?
አቶ አብዱልፈታህ፡- እኔ ተወልጄ ያደኩት ከአዲስ አበባ 120 ኪሎ ሜትር ወለኔ ውስጥ ነው። እስከ 16 ዓመቴ ድረስ የተወለድኩበት አካባቢ ነው ያደኩት። እኔ ሳድግ ማህበረሰቡ የራሱ የሆኑ ባህሎች፤ እሴቶችና አስተዳደር ዘይቤዎች ነበሩት። የመንግሥት ጣልቃ ገብነት እምብዛም ነበር። ሕዝቡ በራሱ ሥርዓቶች ሲተዳደር ነበር የቆየው። የራሱ ማንነት ነበረው። ችግሮቹን በራሱ ይፈታል። በዳይና ተበዳይ እኩል ቆም ተበዳይ በፍትህ ይዳኛል፤ በዳይም ይክሳል። ግጭቶች ሳይካረሩና ሁከት ሳይፈጥሩ በማህበረሰቡ ወግና ልማድ ይፈታሉ። በአጠቃላይ የተረጋጋ የማህበረሰብ ሥርዓት ነበር። እኔም የዚሁ ማህበረሰብ አካል ስለነበርኩ ስብእናዬ የተረጋጋ እና የራሴ ማንነት የነበረኝ ሰው ነበርኩ። ይሁን እንጂ ትምህርቴን ለመቀጠል በ16 ዓመቴ ወደ አዲስ አበባ መጣሁ። ትምህርቴንም ቀጥዬ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገባሁ። በመጀመሪያ የጋዜጠኝነት ትምህርት፤ ቀጥሎም የህግ ትምህርት አጠናሁ። እነዚህን ትምህርቶች ሳጠና ፍጹም ኢትዮጵያዊነት አጣሁባቸው። አኗኗራችንን፤ እኛነታችንን የሚገልጽ አንድም ነገር ላገኝ አልቻልኩም። በሙሉ ከነጮቹ የተገለበጠ ፍጹም ኢትዮጵያዊነት የሌለው የትምህርት ሥርዓት እየተገበርን መሆኑን ደረስኩበት።
ከትምህርቱም ባሻገር አኗኗራችን፣ አለባበሳችን፣ አነጋገራችን በአጠቃላይ የኑሮ ሥርዓታችን በሙሉ ከኢትዮጵያዊ የአኗኗር ሥርዓት እያፈነገጠ የአውሮፓያኑን መስሏል። እኔ ያደኩት ደግሞ ፍጹም ኢትዮጵያ በሆነ የራሱ ባህል፤ ወግና ሥርዓት ባለው ሕዝብ በመሆኑ የማንነት ቀውስ ገጠመኝ። እራሴን አጣሁት። በሀገሬ ውስጥ እየኖርኩኝ ማንነቴን አጣሁት። ሰው በሰው ሀገር እየኖረ ማንነቱን ቢያጣ የሚገርም አይደለም እንዴት ሰው በሀገሩ እየኖረ ማንነቱን ያጣል። የማየው፣የምሰማው፣የምኖረው ሁሉ የእኔ አልመስልህ አለኝ። በመጨረሻም ታመምኩ። የደረሰብኝን ችግርም ለታዋቂው የታሪክ ምሁር ለፕሮፌሰር ላጲሶ ጌዴሌቦ አማከርኳቸው። የሰጡኝን ምክር እስካሁን አልረሳውም። «በዚህ ሀገር የማንነት ቀውስ ያልወደቀ የለም። ሁላችንም ቀውስ ውስጥ ነን። ነገር ግን ከቀውሱ መውጣት ይቻላል። ኢትዮጵያን እራስህ ፈልጋት፤ እራስህ አጽናት፤ እራስህ መርምራት፤ እራስህ ትርጉም ስጣት፤ በዚህ መልኩ ችግሩን ተሻገረው» የሚል ምክር ለገሱኝ። እኔም የተረዳሁት ነገር ቢኖር ሁላችንም በማንነት ቀውስ ውስጥ መውደቃችንን ነው። ስለዚህም ከዚህ ማንነት ቀውስ ውስጥ ለመውጣትና እራሴንም ለማግኘት ወደ ማህበረሰብ ዕውቀቶች ጥናት ለመግባት ወሰንኩ።
አዲስ ዘመን፡- ወደ ማህበረሰብ ጥናት መግባትዎ ለገቡበት የማንነት ቀውስ መድኃኒት ሆኖዎታል?
አቶ አብዱልፈታህ፡- አዎ በደንብ አድርጎ ።
አዲስ ዘመን ፡- እንዴት እስኪ ያብራሩልኝ?
አቶ አብዱልፈታህ፡- እንዴት መሰለህ ወደ ማህበረሰብ ጥናት መግባቴ ከእኔ በፊት ኢትዮጵያን እንዳገኛት አድርጎኛል።
እራሴን ፍለጋ የገባበሁበት ጥናት ኢትዮጵያን እንዳገኛት አድርጎኛል። ያደረግኳቸው ጥናቶች እንዳረጋገጡልኝ ብናውቀውም
ባናውቀውም ሁላችንም ከማንነታችን ተፈናቅለናል። በርካታ ሕዝብ ችግሩን ሳይረዳው ከበሽታው ጋር አብሮ እየኖረ ነው ያለው። ብዙ ሰው አያውቀውም ፤ አይረዳውም።
አዲስ ዘመን፡- ለማንነት ቀውስ የዳረገን ምንድን ነው?
አቶ አብዱልፈታህ፡- የመጀመሪያው የትምህርት ሥርዓታችን ነው። የትምህርት ሥርዓታችን እኛን አይመስልም፤ በ1930ቹ መጀመሪያ አካባቢ ከውጭ እንዳለ ተገልብጦ የመጣ ነው። ለነጮች ሥነ ልቦና እና የአኗኗር ሥርዓት የተዘጋጀ የትምህርት ሥርዓት ፍጹም የተለየ ሥነ ልቦናና የአኗኗር ዘይቤ ላለው ሕዝብ ያለልኩ እንዲለብሰው የተሰፋ ብልኮ ነው። ለዚህ ነው የትምህርት ሥርዓቱ ለዘመናት ቢሞከርም የሀገሪቱን ዘርፈ ብዙ ችግሮች ሊቀርፍ ያልቻለው።
በሌላም በኩል የፍትህ ሥርዓታችንም የእኛ አይደለም። ኢትዮጵያውያን በርካታ የሆነ የፍትህና የአስተዳደር ሥርዓት በየአካባቢው እያላቸው የራስን በመናቅና በማንቋሸሽ ነጮቹ የሚገለገሉበትን ፍትህ ሥርዓት አምጥተን ሕዝቡ ላይ በመጫናችን በሀገሪቱ ውስጥ ፍትህ እንዲጠፋና ኅብረተሰቡም በፍትህ ሥርዓቱ ላይ እምነት እንዲያጣ ምክንያት ሆኗል።
የአስተዳደር ሥርዓታችንም የእኛ አይደለም። ኢትዮጵያ የቀደምት ሥልጣኔ ባለቤትና ረጅም ዘመናትን ያስቆጠረ ለሌላውም የሚተርፍ በርካታ አስተዳደር ሥርዓት ያላት ሀገር ሆና ሳለች የአስተዳደር ሥርዓታችንም ከውጭ ኢምፖርት የተደረገ ነው። መግቢያዬ ላይ እንዳነሳሁት ኅብረተሰቡ የመንግሥትን ጣልቃ ገብነት ብዙም ሳይፈልግ እራሱን በራሱ ሲያስተዳደር የኖረ ሕዝብ ነው። በዚህም የተረጋጋ፤ ችግሮቹን በራሱ መፍታት የሚችል፤ግፍና በደልን የሚጠየፍ ሕዝብ ነበር። ከውጭ የተቀዳው የአስተዳደር ሥርዓት ሕዝቡ ላይ በግድ ሲጫንበት እነዚህ ማህበራዊ ሀብቶች እየተደፈጠጡ ሄዱ።
ሚዲያዎቻችንም ቢሆኑ ኢትዮጵያዊ ማንነት የላቸውም። በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ልዩ ልዩ ዕሴቶች ላይ ትኩረት አድርጎ የሚዘግብ አንድም ሚዲያ አታገኝም። ይልቁንም የውጭውን ማህበረሰብ አኗኗር የሚያንቆለጳጵሱ፤መጤ ባህሎችን የሚያስፋፉና ወጣቱን ፈረንጅ አምላኪ የሚያደርጉ ዘገባዎችን ያለመታከት ሲያቀርቡ ለተመለከተ ኢትዮጵያዊ ሚዲያዎች ናቸው ብሎ ለመገመት ይቸገራል። እና ለማንነት ቀውስ የዳረጉን በርካታ ችግሮች ናቸው።
የተፈጥሮ ሀብቶቻችንም ከውጭ በመጡ ዝርያዎች ተተክተዋል። ከሚተከሉት ዕጽዋቶች የሀገር በቀል ዝርያ ያላቸው ከአንድ በመቶ አይበልጡም። ሕዝቡን የማይመስሉ የውጭ ዝርያዎች ስለሚተከሉ ከማህበረሰቡ ጋር ያላቸው ተፈጥሯዊ መስተጋብር እጅግ ደካማ ነው።ጽድ ስንል፤ኮሽም ስንል፤ብሳና ስንል፤ወይራ ስንል፤ዝግባ ስንል የእኛ ስለሆኑ ከእኛ ጋር ሥነ ልቦናዊ ቁርኝት አላቸው።
በሌላም በኩል ከቀዳማዊ ኃ/ስላሴ አሁን እስካለንበት ድረስ የምንመራባቸው የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለሞች ኢትዮጵያዊ እርሾ የሌላቸው ናቸው። ያለ በቂ ጥናትና ምርምር ሁሉም የመሰለውን ርዕዮተ ዓለም እየቀዳ ሕዝቡ ላይ ይጭናል። በአጠቃላይ ኢትዮጵያውያንን ከማንነታቸው እያፈናቀሉ ያሉት፤ የትምህርት ሥርዓቱ፤ የፍትህና አስተዳደር ሥርዓቱና ርዕዮተ ዓለማዊ የፖለቲካ ሥርዓቱ ናቸው።ኒዮ ሊብራሊዝም፣ሶሻሊዝም፣ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ብለህ ኢትዮጵያን ልታለማ አትችልም። ርዕዮተ ዓለም አስተሳሰብ ነው። ከውጭ ሀገራት በመጣ አስተሳሰብ ደግሞ የኢትዮጵያን ችግር ልንፈታ አንችልም።
አዲስ ዘመን፡- እንደኛ ላሉ ድሃ ሀገራት ርዕዮተ ዓለም መቅረጽ እንዲህ ቀላል ነው እንዴ?
አቶ አብዱልፈታህ፡- በጣም ቀላል ነው።
አዲስ ዘመን፡- እንዴት ነው ቀላል የሆነው?
አቶ አብዱልፈታህ፡- አየህ፤ እንደ ኢትዮጵያ የዘመናት ሥልጣኔ፤ የሀገረሰብ አስተዳደር፤ የህግና የፍትህ ሥርዓቶች ባለቤት ለሆነች ሀገር ከአንድም በላይ በርካታ ርዕዮተ ዓለሞች ሊፈልቁባት የሚችል ሀገር ነች። ኢትዮጵያ እኮ የርዕዮተ ዓለም መሰረት መሆን የምትችል ሀገር ነች። ርዕዮተ ዓለም ማለት አንድ ሀገር፣ አንድ ሕዝብ፣ አንድ ጥንታዊ መንግሥት ሲኖርበት፣ ሲያስተዳደርበት፣ሲገዛበት የነበረ ሥርዓት ማለት ነው። በዚህ ደረጃ ደግሞ ቀደም ብዬ እንደነገርኩህ ኢትዮጵያውያን ከ130 በላይ ርዕዮተ ዓለም ሊሆኑ የሚችሉ አስተሳሰቦችና ሥርዓቶች አሉን። ደግሞም በሳይንስ መነጽር ብትፈትሻቸው እንኳን ሁሉም ሊባል በሚችል መልኩ የርዕዮተ ዓለምን ዕሳቤ የሚያሟሉ ናቸው።
አዲስ ዘመን፡- ለማንነት ቀውስ መዳረጋችን በተጨባጭ ያመጣብን ችግር ምንድን ነው?
አቶ አብዱልፈታህ፡-ቀደም ብዬ እንደገለጽኩልህ ማህበረሰባዊ ዕውቀቶቻችን ኢትዮጵያና ሕዝቦቿን ለበርካታ ዘመናት በጽኑ መሠረት ላይ ያቆሙ የሕዝቦች መስተጋብር ሰላማዊና በመከባበር ላይ የተመሰረተ እንዲሆን ያስቻሉ፤ ዜጎች ያለ አድልኦና ልዩነት እንዲኖሩና የጋራ ሥነ ልቦና እንዲያዳብሩ ያስቻሉ የእኛነታችን መሠረቶች ናቸው። እኒህ መሠረቶች እየተናዱ ሲመጡ የመከባበር፣የመቻቻል፣ አብሮ የመኖርና የመደማመጥ ባህላችን አብረው ተሸረሸሩ። መሰረታቸው ተናጋ። ከመከባበርና ከመቻቻል ይልቅ መጠራጠር፤አብሮ ከመኖር ይልቅ መጤና ነባር በሚል አትድረስብኝ መባባል፣መፈናቀል፣መጋጨት መጎዳዳትና መገዳደል ደረጃ ላይ ደርሰናል። ይህ ደግሞ ለበርካታ ማህበራዊ እና ሥነልቦና ቀውሶች እየዳረገን ይገኛል። ሰዎች እርስ በእርሳቸው እንዳይተማመኑ ብሎም የሀገር ፍቅር ስሜታቸውን እንዲያጡ አድርጓቸዋል። በቅርቡ የወጣውን መረጃ እንደሰማነውም ኢትዮጵያ በሀገር ውስጥ መፈናቀል በዓለም ሁለተኛ ደረጃ የደረሰችውም ከዚህ የመነጨ ነው። እናም ጉዳቱ በቃላት ከሚገለጸው በላይ የሆነና ቶሎ ወደ ማህበረሰባዊ ዕውቀቶቻችን ካልተመለስንም እንደ ሀገር እና እንደ ሕዝብ ለመቀጠል ከማንችልበት ደረጃ ላይ እንደርሰለን። ስለዚህም ወደ እራሳችን እሴቶች መመለስ አለብን። ወደ እራሳችን ስንመለስ ሰላማችን ይመለሳል። አብሮነታችን ይቀጥላል፤ የቀድሞ ገናናነታችን ስፍራውን ይይዛል።
አዲስ ዘመን፡- አሁን እንደሀገር ያጋጠሙንን ችግሮችን በሀገር በቀል እውቀቶች መፍታት እንችላለን ነው የሚሉኝ?
አቶ አብዱልፈታህ፡- ምን ጥርጥር አለው። በኢትዮጵያ በአራቱም ማዕዘናት ወደ 130 የሚጠጉ የዕውቀት ተቋማት አሉ። ልክ እንደ ገዳ ሥርዓት ያሉ። እነዚህ ተቋማት የአስተዳደር፤ የህግና የፍትህና ሥርዓቶች ናቸው። እነዚህ ተቋማት ኢትዮጵያ እንደ ሀገር እንድትቆም ያደረጓትና የሁሉም ዕውቀቶች ምንጭ ናቸው። በማህበራዊውም፤ በኢኮኖሚውም ሆነ በፖለቲካው መስክ ችግር ቢያጋጥመን እነዚህ ሀገራዊ ዕውቀቶች ፍቱን መፍትሄ አላቸው። ሰላም ከፈለግን ሰላም የምናመጣባቸው፤ አንድነት ከፈልግን አንድነት የምናመጣባቸው፤ ፍትህ ከፈለግን ፍትህ የምናመጣባቸው ሀገራዊ ሀብቶቻችን ናቸው።
ሕዝብን የመሰረቱት እነዚህ ተቋማት ናቸው። ኢትዮጵያም የተመሰረተችው በእነዚህ ተቋማት ነው። እስከ 19 ኛው ክፍለ ዘመን ኢትዮጵያ ስትተዳደር የኖረችው በእነዚህ ሥርዓቶች ነበር። በእነዚህ ሥርዓቶች ስንተዳደርም እንዳሁኑ በድህነትና በኋላ ቀርነት ውስጥ አልነበረም የኖርነው። ዛሬ ድረስ የምንኮራባቸው ተፈጥሯዊና ሰው
ሰራሽ ሀብቶች እኮ የፈለቁት ከእነዚህ ሀገር በቀል ዕውቀቶች ነው። የላሊበላ፣ የአክሱም፣ የጎንደር ሥልጣኔ የተገኙት ከእነዚህ ማህበረሰባዊ ዕውቀቶች ነው። የኮንሶ የእርከን አሰራር ጥበብ፣ የደራሼ የግብርና ጥበብ መገኛቸው ሌላ እኮ አይደለም፤ ሕዝቡ በዘመናት ሂደት ያዳበራቸውና ፍጹም ኢትዮጵያዊ የሆኑ ሀገራዊ ሀብቶች ናቸው። በየትኛውም የሀገሪቱ አካባቢዎች ብትዘዋወር አስደናቂ ሆኑ ሀገረሰብ የዕውቀት ሀብቶችን ታገኛለህ።
ከ19ኛው ክፍለ ዘመን በኋላ እነዚህ ተቋማት ቀስ በቀስ መዳከም ጀመሩ። እነዚህ ተቋማት ስለተዳከሙም ኢትዮጵያ ቀስ በቀስ እየተዳከመች ሄደች። እነዚህ ተቋማት ከጠፉ ኢትዮጵያም ትጠፋለች። በሳይንሳዊ ትርጉሙ ሕዝብ ጠፋ የሚባለው መዋለድ ስላቆመ አይደለም። ማንቱ ሲጠፋ፤ ታሪኩና ባህሉ በሌላ ሲቀየር ነው ሕዝብ ጠፋ የሚባለው። አሁን እኛ እዚህ ደረጃ ላይ ባንደርስም ክፉኛ በሆነ መልኩ እነዚህ ማህበራዊ ሀብቶቻችን ተዳክመዋል። በጽኑ መሠረት ላይ መቆም አቅቷቸዋል። አሁን ኢትዮጵያም የተንገዳገደችው እነዚህ ተቋማት ስለተንገዳገዱ ነው። እራሳችንን ጠልተን እና ከራሳችንን ሸሽተን ሀገር እንገነባል ማለት ከተረትነት የዘለለ ፋይዳ የለውም።
አዲስ ዘመን፡- እስቲ ጉዳዩን ተጨባጭ ያድርጉልኝ፤ እነዚህ ሥርዓቶች አሁን ያለውን ሀገራዊ ችግር እንዴት ሊፈቱት ይችላሉ ?
አቶ አብዱል ፈታህ፡- ኢትዮጵያ አሁን ከገጠሙን በላይ ውስብስብ ችግሮችን አልፋለች። እነዚህን ችግሮች ያለፈችባቸው መሣሪያዎችም አሏት። ከላይ እንዳነሳሁልህ ኢትዮጵያ የራሷ የሆኑ የአስተዳደር፣ የህግና ፍትህ ሥርዓቶች አሏት። በአደረግነው ጥናት መሠረትም ከሀገር አልፈው ዓለምን ሊያስተዳድሩ የሚችሉ ገዳን የመሰሉ ሀገራዊ ሥርዓቶችና ተቋማት አሉን። በወለኔና ክስታኔ ማህበረሰብ ዘንድ የጎርደነ ሴረ፤ በጉራጌ ቅጫ፤ በአገው ወይት ሽምርነ፤ ቀንጪ በዋጅራት፤ መድኣ በአፋር፤ ሄራ በሶማሌ እና የመሳሰሉት የእኛ የሆኑ ማህበረሰባዊ ተቋሞቻችን ናቸው። ተቋማት ስልህ የመንግሥት ተቋም ማለቴ ሳይሆን ማህበረሰቡ በዘመናት ሂደት የፈጠራቸውና ተንከባክቦ ዛሬ ላይ ያደረሳቸው ሥርዓቶች ማለቴ ነው። እነዚህ ተቋማት በራሳቸው ሙሉ ናቸው። ፍትህ ሳይጓደል፤ ግጭቶች ስር ሳይሰዱ፤ፍቅርና ማቻቻል ሳይበረዝ እንዲቀጥል የሚያደርጉ ሁነኛ መድኃኒቶች ናቸው። እነዚህን ሥርዓቶች ሕዝቡ የእኔ ናቸው ብሎ የሚቀበላቸውና የማንነቱም መገለጫዎቹ ናቸው። ለእነዚህ ሥርዓቶች ይገዛል፤ በእነዚህ ሥርዓቶች ይዳኛል። ምንም ይሁን ምን ኦሮሞ ከገዳ ሥርዓት አይወጣም። አፋርም ከመድኣ፤ ሶማሌ ከሄራ፤ ወለኔ ከጎርደነ ሴረ አይወጣም። ሌሎችም እንዲሁ።
በቅርቡ ያየነው የጋሞ አባቶች ድርጊት እኮ ሌላ ሳይሆን የሀገረሰብ ባህላችን የፈጠረው አስደናቂ ተግባር ነው። እሳት ለብሰው እሳት ጎርሰው የመጡት ወጣቶች የጋሞ አባቶች ባህሉንና ወጉን ጠብቀው ባደረጉት ተግባር ሊከሰት ይችል የነበረውን ጥፋት መታደግ ችለዋል። በየትኛውም ኃይልና ጉልበት ልታቆመው የማትችለውን አፍጥጦ የመጣን ቁጣ የጋሞ ማህበረሰብ ለዘመናት ባካበተው የግጭት አፈታት ሥርዓት ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ችሏል። ከሁሉም በላይ የሚገርመው ደግሞ እሳት ጎርሰው እሳት ለብሰው የመጡት እነዚህ ወጣቶች ያለምንም ማንገራገር የጋሞ አባቶች ያደረጉትን ተማጽኖ ተቀብለው ወደ መጡበት በሰላም መመለሳቸው ነው። ይህ ከአስተሳሰብ ጋር፤ ባህልን ከማክበር ጋር፤ ከእኔነት ጋር የተያያዘ ነው እንጂ ዝም ብሎ በድንገት የተከሰተ ፊልም የሚመስል ድርጊት አይደለም። መንግሥትና ሕዝብ እነዚህን ማህበረሰባዊ ሀብቶች ጥለዋቸው፤ ዘንግተዋቸው፤ ወጣቱ በአግባቡ እንዲያውቃቸው ሳይደረጉና በትምህርት ሥርዓቱ ውስጥ ሳይካተቱ እንኳን ምን ያህል ችግሮቻችንን የመፍታት አቅም እንዳላቸው ማሳያ ናቸው። ትኩረት ቢሰጣቸው ደግሞ ምን ያህል ተዓምር ሊሰሩ እንደሚችሉ መገንዘብ አያዳግትም። በተመሳሳይ መልኩ በመላው ኢትዮጵያ ተመሳሳይ የሆኑ የእኛነታችን መገለጫ የሆኑ የግጭት አፈታት ሥርዓቶች አሉን። ግጭትን መፈቻዎች ብቻም ሳይሆኑ የልማት መሣሪያዎች፤ የመቻቻልና መከባበር መሠረቶች የሆኑ ሀብቶች በኢትዮጵያ በየትኛውም አካባቢ አሉ። እናም አሁን እንደ ሀገር ያጋጠሙንን ችግሮች መፍታት የምንችለው እነዚህን ሀገረሰባዊ ዕውቀቶች በመጠቀም ብቻ ነው። ከዚህ ውጪ የሚደረጉ ሙከራዎች ጊዜያዊ መፍትሄ ከማምጣት ውጪ ዘላቂ መፍትሄ ሊሆኑ አይችሉም።
አዲስ ዘመን፡- ይህን ያህል አቅም ካላቸው ለምንድን ነው ችላ ያልናቸው?
አቶ አብዱልፈታህ፡- ችግሮቹ ሁለት ናቸው። የአመለካከትና የዕውቀት ችግሮች ናቸው። በመጀመሪያ ደረጃ እነዚህ ሀገረሰባዊ የአስተዳደር ሥርዓቶቻችን እኛን እንዳያገለግሉና ጥቅም ላይ እንዳይውሉ በህግ ተሸረዋል። በ1952 በወጣው የፍትሐብሔር ህግ አንቀጽ 33/47 እነዚህ ሀገር በቀል ዕውቀቶች ጥቅም ላይ እንዳይውሉ ተሽረዋል። እስካሁንም እንደተሻሩ ናቸው። መቼም ለክፋት ነው ብዬ አልልም። ምናልባት ካለማወቅ የመነጨ ነው ብዬ አስባለሁ። እነዚህ ሀገረሰባዊ የአስተዳደር፤የህግና ፍትህ ሥርዓቶቻችን የሚሰጡትን ፋይዳ ካለመረዳት የመነጨ ነው ብዬ አስባለሁ።
በሌላም በኩል ደግሞ ሀገረሰባዊ ዕውቀቶችን አሳንሶ የመመልከት ችግር አለብን። ለችግሮቻችን መፍትሄ ከአውሮፓ የመጣ ሸቀጥና ሀሳብ ብቻ ይመስለናል። በተለይም ተማረ የምንለው ዜጋ ጋር ይህ አስተሳሰብ በእጅጉ ጎልቶ ይታያል። የትምህርት ሥርዓታችን በፈጠረብን ችግር ለቅኝ ገዢ ሥርዓት በእጅጉ ተጋልጠናል። በቅርቡ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያመለክቱትም ኢትዮጵያ ከየትኛውም የአፍሪካ ሀገር በባሰ መልኩ ለቅኝ ገዢዎች አስተሳሰብ የተጋለጠች ሆና ተገኝታለች።
አዲስ ዘመን፡- ቅኝ ሳንገዛ እንዴት ከአፍሪካ ሀገሮች በባሰ መልኩ ለቅኝ ገዢዎች አስተሳሰብ ተጋላጭ ልንሆን እንችላለን?
አቶ አብዱልፈታህ፡- እውነት ነው ቅኝ አልተገዛንም። ይህም የምንኮራበት የጀግንነት ተጋድሏችን ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ከየትኛውም ሀገር በከፋ መልኩ የቅኝ ገዢዎችን ሀሳብ ተቀባይና ተግባሪዎች ነን። ለዚህ ደግሞ ችግር የዳረገን ከላይ ለማንሳት እንደሞከርኩት ከውጭ የቀዳናቸው የትምህርት፤ የአስተዳደርና ርዕዮተ ዓለም ሥርዓቶቻችን ናቸው። ሌሎች ሀገራት በቅኝ ግዛት ውስጥ እያሉ እኛ ነፃ ብንሆንም የትምህርት ሥርዓታችንን ግን በእኛው አምሳል መቅረጽ አልቻልንም። ቀጥታ ከቀኝ ገዢዎች ቀድተን ነው ያመጣነው። የአስተዳደርና የፍትህ ሥርዓቶቻችንም በተመሳሳይ መልኩ ከዘመኑ ቅኝ ገዢዎች የተወሰዱ ናቸው። በየዘመናቱ ሲፈራረቁ ቆዩትም ርዕዮተ ዓለሞች ተመሳሳይ ገጽታ ያላቸው ናቸው። ታዲያ እንዴት ብለን ከአስተሳሰቡ ልንርቅ እንችላለን።
ጎረቤታችን ኬንያ እንኳን የትምህርትም ሆነ የፍትህና አስተዳደር ሥርዓቶቿ ከፊል አፍሪካዊ ገጽታን የተላበሰ ነው። ናይጄሪያን፣ ማሊን፣ ጋናንና የመሳሰሉትን ብንወሰድ የራሳቸውን ባህል ጠብቀው ለመሄድ ሲሞክሩ እናያለን። አለባበሳቸው እንኳን አፍሪካዊ ገጽታ አለው። የእኛን አለባበስ እኮ ብትመለከተው ፍጹም ኢትዮጵያዊነት የጎደለው ሆኖ ታገኘዋለህ። ባህላዊ መጠጦችና ምግቦቻችን በነጮች የአመጋገብ ሥርዓት እየተተኩ ነው። አሁን አሁን አፍሪካውያንም ይህንን የኢትዮጵያ ለውጭ አስተሳሰብ ተጋላጭነት ጥያቄ ውስጥ እየከተቱት መጥተዋል። ስለዚህ አኩሪ ባህሎቻችንን እያጣን እንዳንመጣ አሁን የተጋረጡብንን ችግሮች አልፈን መሄድ እንድንችል ለሀገረሰብ የአስተዳደር፤ የህግና የፍትህ ሥርዓቶቻችን ተገቢውን ቦታና ክብር ልንሰጥ ይገባል።
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ አመሰግናለሁ።
አቶ አብዱልፈታህ፡- አኔም በጣም አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ መስከረም 3/2012
እስማኤል አረቦ