ሁለተኛው የዓለም ጦርነት (1939–1945) የ80 ሚሊዮን ህዝብ እልቂት አስከተለ፡፡ እልቂቱም በዘግናኝነቱ እስካሁን ተጠቃሽ ነው፡፡ ይህ እልቂት እንዳይደገም አንድ ነገር ማድረግ እንደሚያስፈልግ ስምምነት ላይ ተደረሰ፡፡ ኃላፊነቱንም 48 አገራት ወሰዱ፡፡
በተወካዮቻቸው አማካኝነትም አንድ ገዢ ሰነድ ተዘጋጀ፡፡ በተባበሩት መንግሥታት አማካኝነት በ1948 ተዘጋጅቶ የፀደቀው ይህ ዓለም አቀፍ ሰነድ፤ ሰዎች ሰው በመሆናቸው ብቻ ሁለንተናዊ መብቶቻቸው ይከበሩላቸው ዘንድ ታስቦ የተዘጋጀ ነው፡፡ 30 መሰረታዊ የሰው ልጅ መብቶችን ያካተቱ አንቀጾችን የያዘው ሰነድ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት በማግኘቱ ሀገራት በመተዳደሪያ ሰነዶቻቸው አሰፈሩት፤ ኢትዮጵያም እንደዛው፤ መንግሥታት ሰነዱን ይቀበሉና ያጽድቁት እንጂ፤ ዓለማችን እየተመራች፤ ህዝቦች እየተስተዳደሩ ያሉት ግን ከሰነዱ በተቃራኒው ይመስላል፡፡ ለዚህም ታሪክ በጥቁር መዝገቡ ከትቦ ያስቀመጣቸው የዓለማችን ግፈኞችና ያደረሱት በደል የግፍ ጥግ ሁነኛ ማስረጃዎች ናቸው፡፡
አዶልፍ ሂትለር በጀርመን፤ ሞሶሎኒ በጣሊያን፤ ፒኖቼ በቺሊ፤ ፓልፓት በካምቦዲያ፤ ጄነራል ፍራንኮ በስፔን ያደረሱት እልቂትና ውድመት ከዚህ በመለስ የሚባል አይደለም፡፡ የኢንዶኖዥያው ስኋርቶ፤ የኡጋንዳው ኢድ አሚን ዳዳ፤ የማዕከላዊ አፍሪካዋ ቦካሳ፤ የሀይቲው ፍራንኮስ ዱዋልየር እና መሰሎቻቸው ያፈሰሱት የንጹሀን ደም እስካሁን ይጣራል፡፡
ምን ዋጋ አለው! እነዚህንና እነዚህን መሰል አረመኔዎች የፈጸሙት ኢ-ሰብዓዊ ተግባር በአስተማሪነቱ ሲወሰድ፤ የንጹሃን ሰብዓዊ መብቶች ሲከበሩ፤ ዓለም በሰላም ውላ ስታድር አይታይም፡፡ ጭራሹንም የዘመኑ መሪዎች የነሂትለርን ተግባር በመልካም ምሳሌነቱ የወሰዱት ይመስል ግፉን አጠናክረው ቀጥለውበታል፡፡ እስከጥግ ድረስ፤
የሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ በተለይ በአገራችን፣ ገና ጥልቅ ጥናት ያልተደረገበት ቢሆንም፤ የበርካታ መገናኛ ብዙሀንና ተንታኞች ትኩረት ግን አልተነፈገውም፡፡ ርዕሰ ጉዳዩ የዕለት ተዕለት ቀዳሚ ተረክ ከመሆን ዘልሎ አያውቅም፡፡ ሰሚ ኖረም አልኖረ ይዘገባል፤ ይተነተናል፤ ይብጠለጠላል፡፡ «ንክች ያባ ቢላዎ ልጅ» ባዩ የመብት ጣሽ ቡድንም እልህ የተጋባ ይመስል ግፉን እየገፋበት እዚህ ደርሷል፡፡
በአሁኑ ሰዓት በየአካባቢው፤ ስምምነቱን በተቀበሉ አገራት ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ስምምነት ሰነድ የጸደቀበት 70ኛ ዓመት እየተከበረ ይገኛል፡፡ የሀገራችን የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ታህሳስ 2 ቀን 2011 ዓ.ም ማታ «የፍትህ ሰቆቃ» በሚል ርዕስ ያቀረቡትና ለማመን የሚያስቸግር፤ ዘግናኝ የሰብዓዊ መብት ጥሰት መፈጸሙን የሚያሳየው ዘጋቢ ፊልምም የዚሁ አካል ነው፡፡
የሰዎችን ሰብዓዊ መብት የተመለከተውና «Universal Declaration of Human Rights» በሚል የሚታወቀው ሰነድ ከጸደቀና ሥራ ላይ ከዋለ እነሆ 70ኛ ዓመቱ የደፈነ ሲሆን፤ በዓለም አቀፍ ደረጃም እየተከበረ ይገኛል፡፡ ሰነዱን በመጀመሪያ ካጸደቁት ሦስት የአፍሪካ አገራት አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያም ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በመሆን ባለፈው ሳምንት በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አዳራሽ አክብራዋለች፡፡
ሰሞኑን ኢኮኖሚክ ታይምስ ዶትኮም እንዳስነበበው የአሜሪካን መንግሥት በንጹሃን ወገኖች ላይ አሰቃቂ የሰብዓዊ መብት ጥሰትና ግድያ በፈጸሙ ከፍተኛ የሰሜን ኮሪያ ባለስልጣናት ላይ ሁለ-ገብ እገዳ ጥሏል፡፡ የአሜሪካ ባለስልጣናት እንደገለጹት፤ የእገዳው አስፈላጊነት በመገናኛ ብዙሀን ላይ አፋኝ ቅድመ ምርመራን ከማስቆም፤ የሰብዓዊ መብቶችን ጥሰት ከመግታት አኳያ ድርጊቱን በመቃወም የህዝቡን ትኩረት መሳብ ነው፡፡ ድረ-ገጹ የአሜሪካንን የገንዘብ ግምጃ ቤት ጠቅሶ እንደዘገበው፤ እነዚህ ባለስልጣናት በተግባሩ ቁልፍ ሚና የነበራቸው ናቸው፡፡
በመሆኑም ይላል ዘገባው፤ እነዚህ ግለሰቦች በአሜሪካ ውስጥ ያላቸው ማንኛውም ዓይነት ሀብት ህገወጥ ነው፡፡ ስለዚህ፤ ማንኛውም የገንዘብ ተቋም ወይም የገንዘብ ዝውውር የሚያከናውን አካል የነዚህ ባለስልጣናት ገንዘብ ህገ ወጥ መሆኑን አውቆ ከማንቀሳቀስ እንዲቆጠብ ሲል ውሳኔ አስተላልፏል፡፡
እገዳው የተጣለባቸው ሦስቱ ባለስልጣናት የሰሜን ኮሪያ ደህንነት ሚኒስትር፤ የመስሪያ ቤቱ የምክር አገልግሎት ክፍል ኃላፊ፤ እንዲሁም የፕሮፖጋንዳና ቅስቀሳ ክፍል ዳይሬክተር መሆናቸው በመግለጫው ተመልክቷል፡፡
ይህ ከብዙዎቹ ለማሳያ ያህል የጠቀስነው ክስተት፤ የዜጎቻቸውን ሰብዓዊ መብቶች የጣሱ ባለስልጣናትና የአሜሪካ መንግሥት የወሰደው እርምጃ የሚያሳየው ነገር አለ፡፡ እሱም በንጹሃን ላይ አሰቃቂ ወንጀል ፈጽሞ የትም ማምለጥ፤ መሰወር የሚቻል አለመሆኑንና የሰዎች መሰረታዊ ሰብዓዊ መብቶች፤ ሰው በመሆናቸው ብቻ የትም ሆነ የት ሊከበሩ የሚገባቸው መሆኑን ነው፡፡
በኦፍሻየር ካምፕ ውስጥ የሚገኙ ስደተኞች ያለአግባብ በመያዝ ሰብዓዊ መብታቸውን ጥሰሀል በሚል ከተባበሩት መንግሥታት ጀምሮ የሌሎች ተቋማትና መንግሥታት ወቀሳና ተጽዕኖ እየደረሰበት ያለው የአውስትራሊያ መንግሥት እንደ መንግሥት ተጠያቂ እየሆነ ይገኛል፡፡
ፓምቡዛ ኩም ዶት ኮም ድረ-ገጽ እንዳስነበበው ደግሞ፤ የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ጃኮብ ዙማ በሳድክ ትሪቢዩናል (SADC Tribunal) በተባለ የፍትህ ተቋም ላይ የወሰዱት እርምጃ ህገመንግሥቱ ከሰጣቸው ስልጣን፤ ከፍትሃዊ አሰራር ውጭ እና ኢ-ምክንያታዊ ነው በሚል ለፍርድ እንዲቀርቡ የአገሪቱ መንግሥት መወሰኑን አስታውቋል፡፡ ይህም ከህግ ውጭ መሆን የማይቻልና ወንጀለኞችም መጠየቅ ያለባቸው ስለመሆኑ ሌላው ጉልህ ማስረጃ ነው፡፡
የንጹሃን ዜጎችን ሰብዓዊ መብት በመጣስ፤ በአሰቃቂ ሁኔታ በማሰቃየት፤ በመግደል፤ ተገቢ ባልሆነ መንገድ በመያዝ የትም ሀገር ሄጄ እኖራለሁ ይሉ ፈሊጥ፤ የሀገርን ሀብትና ንብረት በመዝረፍ ወደፈለኩበት ሀገር ባንክ ልኬ አስቀምጣለሁ ይሉት ቋንቋ በዚህ በ21ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ላይ ያረጀ ያፈጀ ብቻ ሳይሆን፤ የሻገተ እንስሳዊ አስተሳሰብ ለመሆኑ ጥሩ ማሳያ ነው፡፡ ይህም ብቻ አይደለም፤ ዕድሉም ከነጭራሹ የተዘጋ ስለመሆኑም ይናገራል፡፡
ሰሞኑን ዩዝ ፎር ሂዩማን ራይትስ ዶት ኮም የዩኒሴፍን፣ የተባበሩት መንግሥ ታትን፣ የዓለም የሥራ ድርጅትንና ሌሎች መረጃዎችን ጠቅሶ እንደዘገበው 286 ሚሊዮን ህጻናት ሰብዓዊ መብታቸው ተገፍፎ ለስቃይና ለመከራ፤ 300 ሺህ የሚሆኑት ደግሞ በእርስ በርስ ጦርነትና ግጭት ምክንያት ለጉልበት ብዝበዛ፣ ከ600 – 800 ሺህ የሚደርሱ ሰዎች ለስደት ተዳርገዋል፡፡ የህዝብ ቁጥራቸው 250 ሺህ በሆኑ ከተሞች 100 በመቶ የዘረፋ ተግባራት ይካሄዳል፡፡ የነዋሪዎች መብት ያለማቋረጥ ይጣሳል፡፡ የአሁኑ ዘመን የዓለማችን ገጽታ ይህን ይመስላል፡፡
እነዚህ አካላት ሰነዱን በፊርማቸው ያጽድቁ፣ ይቀበሉት፤ የሰነዳቸውም አካል ያድርጉት እንጂ ላለፉት ሰባት አሥርት ዓመታት በሰነዱ ላይ የሰፈሩት አንቀጾች ከመሰረታቸው ሲናዱ፣ ሲደለዙና በነጭ ሲሰረዙ፤ የሰዎች፤ በተለይም የንጹሀን ዜጎች ሰብዓዊ መብቶችና ነጻነቶች ሲዳጡና ሲጨፈለቁ ነው የኖሩት፤ አድልኦ፣ ግድያ፣ ማሰቃየትና ጭካኔያዊ ተግባራት፣ አዋራጅ ኢ-ሰብአዊ አያያዝ፤ የዘር፣ የቀለም፣ የጾታ፣ የእድሜ፣ የሀብት ፣ የፖለቲካ . . . ልዩነቶችን መሰረት ያደረገ አድልኦ ሁሉ ከመቼውም በላይ ባለፉት 70 ዓመታት የተፈጸሙ ግፎችና ንጹሀን የተጋፈጧቸው መከራና ስቃዮች ናቸው፡፡ እነዚህ ሁሉ ተዳምረው የሰውን ልጅ ለተለያዩ መከራዎች እየዳረጉት ሲሆን አንዱም ስደት ነው፡፡
የተባበሩት መንግሥታት (2015) ባወጣው ዘገባ እንደገለጸው፤ በዓለማችን የሰዎች ሰብዓዊ መብቶች በከፍተኛ ደረጃ እየተጣሱ ነው፡፡ ይህም ተበዳዮች አገር ጥለው እንዲሰደዱ ምክንያት ሆኗል፡፡ በዘገባው እንደተመለከተው፤ በ2013 51.2፤ በ2014 59.5 ሚሊዮን ዜጎች አገራቸውን ጥለው ተሰደዋል፡፡ በ2015 በዓለማችን ከሚገኙ 122 ሰዎች መካከል አንዱ ተሰድዷል፡፡ ከዚህ መረጃም የሰብዓዊ መብት ጥሰቱና ረገጣው የት እንደደረሰና የቁጥሩን እያሻቀበ መሄድ ልብ ይሏል፡፡
ምን ይደረግ?
ሁሉም በሚባል ደረጃ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ተቋማት የሚስማሙበት አንድ ነገር ቢኖር፤ ሰዎች ሰው በመሆናቸው ብቻ፤ ያለምንም የዘር፣ የቀለም፣ የጾታ፣ የሃይማኖት፣ የዕድሜ፣ የሀብት፣ የፖለቲካ ልዩነት፣ የቋንቋ ወዘተ. ልዩነት መብቶቻቸው ይከበሩ፤ የህግ የበላይነት በዓለም ይሰፍን ዘንድ የፍትህና የዴሞክራሲ ተቋማትን ማቋቋምና ማጠናከር ተገቢ መሆኑን ነው፡፡ ይህ ሲሆን ብቻ ነው በሰነዱ ላይ የሰፈሩት መሰረታዊ የሰብዓዊ መብት መርሆዎች እውን የሚሆኑት፤
ሰሞኑን በኢትዮጵያ፤ 70ኛው የሰብዓዊ መብቶች ቀን በዓል ሲከበር የአገራትና ተቋማት፤ ጥናት አቅራቢዎችና ተወያዮች ከስምምነት ላይ የደረሱበት አቢይ ቁም ነገር ቢኖር፤ «ለሰዎች ሰብዓዊ መብት መከበርም ሆነ መጣስ ተጠያቂዎቹም ሆኑ ተመስጋኞቹ የዴሞክራሲና የፍትህ ተቋማት ናቸው» የሚለው ነው፡፡
ሰብዓዊ መብቶችን ከጥሰት መከላከል፣ ማክበር፣ ማስከበርና መጠበቅ የሁሉም ሰው ጉዳይ መሆኑ እውነት ነው፡፡ ይሁን እንጂ፤ በመንግሥታትና ጉዳዩን ጉዳዬ ብለው በባለቤትነት በያዙ አገር እና ዓለም አቀፍ ተቋማት እጅ ላይ የወደቀ ነው፡፡ ሰነዱን በፊርማቸው ያጸደቁ፣ የተቀበሉና የህጐቻቸው አካል ያደረጉ፤ ተጠያቂም ሆነ ተመስጋኝ እነሱ ናቸው፡፡
ሀገራት፣ በተለይም ችግሩ ሥርዓታዊ የሆነባቸውና ስር የሰደደባቸው አገራት አሜሪካ በኦባማ የአስተዳደር ዘመን ያጸደቀችውን Magnitsky Act (2012) ህግ ለራሳቸው በሚያመቻቸው መንገድ መውሰድና ተግባራዊ ማድረግ የሚበጃቸው ይመስላል፡፡
በአሁኑ ሰዓት አሜሪካ ይህንን ህግ Global Magnitsky Act በሚል ስያሜ ወደ ዓለም አቀፍ ህግነት የቀየረችው ሲሆን ዓለም ተቀብሎላታል፡፡ እንግሊዝ፣ ኦስትሪያ እና የመሳሰሉትም ተቀብለውት የአገራቸው ህግ አካል አድርገው እየሰሩበት ይገኛሉ፡፡ የአሁኑ የኢትዮጵያ ተጨባጭ እውነታም የሚያስገነዝበው ነገር ቢኖር ይህንኑ ነው፡፡ ይህንኑ ህግ ከህጓ ጋር በማጣጣም በሥራ ላይ ማዋል፤
በተለይ አሜሪካ ህጉን እየተጠቀመችበት ሲሆን፤ ሰሞኑንም በከፍተኛ ሙስናና አሰቃቂ ሰብዓዊ መብት ረገጣ ተግባር ላይ ተሰማርተው የተገኙ የሰሜን ኮሪያ የደህንነት ባለስልጣናትን ካገር አገር እንቅስቃሴ ማገድና በዘረፋ ካገራቸው ውጪ ያስቀመጡት ገንዘብ በህገወጥነት እንዲመዘገብና እንዳይንቀሳቀስ ለማድረግ የወሰነችውም ይህንኑ ህግ ተጠቅማ መሆኑ ነው በተለያዩ መገናኛ ብዙሀን የተዘገበው፤ ይህ ተለያዩ አገራት ልምድ የሚያሳየው ነገር ቢኖር፤ ወንጀለኞች የትም ሆነ የት በሰሩት ግፍና ወንጀል ሊጠየቁ የሚገባ መሆኑን ነው፡፡
በቅርቡ በኢትዮጵያ የተፈጸመውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት አስመልክተው ለጋዜጠኞች መግለጫ የሰጡት ዓቃቢ ህግ ብርሀኑ ጸጋዬ፤ ድርጊቱ በተባበሩት መንግሥታት ኮሚሽን የሰፈረውን «አንቀጽ 7»ን የጣሰ፣ በዓለም አቀፍ የወንጀል ፍርድ ቤት (ICC) የሚያስጠይቅ፤ በሰው ዘር ላይ የተፈጸመ አሰቃቂ ወንጀል (Crime Against Humanity) መሆኑን መግለጻቸው ይታወሳል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 10/2011
ግርማ መንግሥቴ