ወጣት ወለላ ናስር የሀረር ከተማ ነዋሪ ነው፡፡ ለስራ ጉዳይ ወደ ጅማ ከአቀና ሁለት ዓመታት ሆኖታል፡፡ በጅማ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ በመካኒክነት ሙያ እየሰራ ነው ያገኘነው፡፡ ኢንዱስትሪ ፓርኩ በግንባታ ወቅትም ሆነ ከተጠናቀቀ በኋላ ለብዙ ወጣቶች የስራ እድል እንደፈጠረና እንደሚፈጥርም ራሱን በአብነት በመጥቀስ ይናገራል፡፡
ኢንዱስትሪ ፓርክ ለወጣቶች ብዙ የስራ ዕድል ይፈጥራል የሚለው ወጣቱ፣ ፓርኩ ሙሉ በሙሉ ስራ ሲጀምር በጅማና አካባቢው ስራ አጥ ወጣቶች አይኖሩም የሚል እምነት አለው፡፡ እኔም ሆንኩ ሌሎች ወጣቶች በኢንዱስትሪው ፓርክ የመጀመሪያ ምዕራፍ የስራ ዕድል ተጠቃሚ ሆነናል የሚለው ይህ ወጣት፣ ኢንዱስትሪ ፓርኩ የስራ ዕድል ከመፍጠር ባሻገርም የከተማዋን ዕድገት ያፋጥናል ሲል ይገልጻል፡፡
ለአብነትም በኢንዱስትሪ ፓርኩ አካባቢ ብዙ ወጣቶች የተለያዩ ንግዶችን በመክፈት ተጠቃሚ እየሆኑ ናቸው፡፡ ይህም ህብረተሰቡ የተሻለ ገቢ እንዲያገኝ ያደርጋል፡፡ ስለዚህ ኢንዱስትሪ ለልማትም ሆነ ለወጣቱ ዘላቂ የስራ ዕድል ለመፍጠር ትልቅ ጠቀሜታ አለው፡፡ እናም ወጣቱ ፓርኩን እንደ ግል ንብረቱ ሊጠብቀውና ድጋፍ ሊያደርግለት ይገባል ባይ ነው፡፡
በጅማ ከተማ ነዋሪ የሆነው ሙህዲን ሁሴን ወጣት ወለላ የኢንዱስትሪ ፓርኩ ፈርጀ ብዙ ጥቅም አለው የሚለውን ሀሳብ ይጋራል፡፡ በከተማዋ የኢንዱስትሪ ፓርክ በመገንባቱ እሱም ሆነ የአካባቢው ወጣቶች ደስተኛ መሆናቸውን ይገልጻል፣ ምክንያቱም ለብዙ ወጣቶች የስራ ዕድል ይፈጥራል፡፡ የከተማዋ ዕድገት እንዲነቃቃ ያደርጋል ብሏል፡፡
‹‹ከእኛ ከወጣቶች የሚጠበቀው የአካባቢውን ሰላም መጠበቅ ነው›› የሚለው ወጣቱ፣ ኢንዱስትሪ ፓርኩ ስራውን በአግባቡ እንዲሰራ ማድረግ ጥቅሙ በኢንዱስትሪ ፓርኩ ውስጥ ተቀጥረው ለሚሰሩት ወጣቶች ብቻ ሳይሆን በአካባቢው በንግድ ስራ ለተሰማሩትም ጭምር ነው፡፡ ስለዚህ ለጥቅማችን ስንል ባለሀብቶችና ባለሙያዎችን መንከባከብና የአካባቢው ሰላም መጠበቅ ቀዳሚ ተግባራችን ሊሆን ይገባል›› ሲል ተናግሯል፡፡
በአሁኑ ጊዜ የጅማ ዞን ብዙ የተማረ የሰው ሀይል በስፋት የሚገኝበት አካባቢ ነው፡፡ ኢንዱስትሪ ፓርኩ ለዚህ ወጣት የተማረ የሰው ሀይል ሰፊ የስራ ዕድል ይፈጥራል፡፡ በሌላ በኩል፣ ደግሞ በጅማ ዞንና በአካባቢው ያሉ አርሶ አደሮች የተለያዩ የግብርና ምርቶች በስፋት ያመርታሉ፡፡ በፓርኩ ውስጥ የግብርና ምርቶችን አቀናብረው ለገበያ የሚያቀርቡ ፋብሪካዎች ወደስራ የሚገቡ በመሆኑ ለአርሶ አደሩ የገበያ ትስስር ለመፍጠር ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል የሚሉት ደግሞ የጅማ ዞን የከተማ ልማትና ቤቶች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መሰረት ሀይሉ ናቸው፡፡ ይህም የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ያሳድገዋል፡፡ የቴክኖሎጂ ሽግግርንም የሚያመጣ ጭምር ነው፡፡
እንደ ኃላፊው ገለጻ፣ ለጅማ አካባቢ ብቻ ሳይሆን ለደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ጭምር የኢንዱስትሪ ማዕከል ሆኖ ያገለግላል፡፡ በጥቅሉ ኢንዱስትሪ ፓርኩ ለአገሪቱ ኢኮኖሚ ዕድገት የበኩሉን ድርሻ ይጫወታል፡፡ የወጪ ንግድ ገቢም ማሳደግ ያስችላል፡፡
‹‹ጅማ በፍቅርና በአብሮ መኖር እሴት የሚታወቅ አካባቢ ነው›› የሚሉት አቶ መሰረት፣ ወደ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ የሚገቡ ባለሀብቶችም በዞኑ አንድ ችግር የሆነውን ስራ አጥነት ለመፍታት ጭምር የሚመጡ በመሆኑ በሰላም ጉዳይ ስጋት ሊያድርባቸው አይገባም፡፡ ምክንያቱም ህብረተሰቡ ለራሱ ሲል ሰላሙን የሚጠብቅበት ሁኔታ አለ፡፡ በተለይ ፓርኩ መጥፎ አጋጣሚን ሳይሆን መልካም ዕድልን ነው ይዞ የመጣ በመሆኑ ህብረተሰቡ ለራሱ ኢኮኖሚ ዕድገትና ለልጆቹ የስራ ዕድል ተጠቃሚነት ሲል እንደ አይኑ ብሌን ይንከባከበዋል ብለዋል፡፡
ብዙ ጊዜ ለኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ ሲባል ከአካባቢው የሚነሱ አርሶ አደሮች ተገቢው ካሳ አልተከፈለንም የሚል ቅሬታ ያነሳሉ፡፡ በጅማስ ይህ ቅሬታ አለ ወይ? ብለናቸው አቶ መሰረት ሲመልሱ ከቦታው ለተነሱ አርሶ አደሮች ተገቢው ካሳ ተከፍሏቸዋል፡፡ በዚህ ረገድ የሚነሳ ቅሬታ የለም የሚል ምላሽ ሰጥተውናል፡፡
ኢንዱስትሪ ፓርኩ ውስጥ የጨርቃ ጨርቅ፣ የአልባሳትና የተለያዩ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች የሚገቡበት በመሆኑ በአካባቢው ያለውን የግብርና ምርት እሴት ጨምሮ ለገበያ ማቅረብ እንደሚያስችል የገለጹት የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳ፣ ፓርኩ የጅማ ከተማን ዕድገት ለማፋጠንና ለወጣቶች የስራ ዕድል ለመፍጠር ያስችላል፡፡ እንዲሁም በቀጥታና በተዘዋዋሪ መልኩ ፈርጀ ብዙ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያለው ነው፡፡
እንደ አቶ ለማ ገለጻ የጅማ ኢንዱስትሪ ፓርክ ለክልሉና ለመላ አገሪቱ የኢንዱስትሪ ልማት መፋጠን ያለው ድርሻ በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ ስለዚህ የኢንዱስትሪ ፓርኩ በጅማ ከተማ መገንባቱ የሚፈጥረውን ምቹ ሁኔታ ለመጠቀም ህዝቡ ከወዲሁ መዘጋጀት ይኖርበታል፡፡ የከተማውና የአካባቢው ህዝብ፣ በተለይም ወጣቶች የፓርኩን ሁለተናዊ ጠቀሜታ በመገንዘብ ለስራ ወደ ጅማ የመጡ ባለሀብቶችንና ባለሙያዎችን በፍቅር ማቀፍና ማስተናገድ አለባቸው፡፡ ለልማት ጥረታቸው መቀናት ብሎም ለኢንዱስትሪ ፓርኩ ዓላማ መሳካት በኃላፊነት ስሜት የድርሻቸውን መወጣት አለባቸው፡፡
‹‹የአገር ዕድገትና የህዝብ ኑሮ መሻሻል መሰረቱ ስራ ነው፡፡ የስራ የዕድገትና የተመቻቸ የኑሮ መሰረት ደግሞ ሰላም ነው›› ያሉት አቶ ለማ፣ የአገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶች በጅማና በሌሎች የኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ለመሳተፍና የድርሻቸውን ለማበርከት በጉጉት እንዲመጡ የሚያደርጋቸው ትልቁ ጉዳይ እምቅ የተፈጥሮ ሀብትና የእንግዳ ተቀባይነት ባህላችን ቢሆንም ይህ ብቻ በቂ አይደለም፡፡ ባለሀብቶች ሀብታቸውን አፍስሰው ኢንቨስት ማድረግ የሚችሉት የክልላችን ሰላም ሲረጋገጥ ነው፡፡ እንዲሁም፣ ኢንቨስተሮችን የሚስብ ፈጣን የአገልጋይነት መንፈሳችን እየጎለበተ ሲሄድና የህግ የበላይነት ተረጋግጦ ህግን ተከትሎ ሰርቶ የማደር ዋስትና ሲኖር ነው፡፡ በመሆኑም ህዝቡ ይህንን በመረዳት ከወትሮው በተሻለ ደረጃ ለህግ የበላይነት መረጋገጥና ለዘላቂ ሰላም መስፈን ዘብ ሊቆም ይገባል ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የጅማ ኢንዱስትሪ ፓርክ አስፈላጊ መሰረተ ልማቶች የተሟሉለት፣ ለጥሬ ዕቃነት ሊውሉ የሚችሉ የግብርና ግብዓቶች ከደጃፉ የሚጠብቁት፣ ሰፊ የሰራተኛ ሀይልም ያለበት አካባቢ ነው፡፡ እንዲሁም፣ ለስራና ለኑሮ የሚመች አካባቢም ነው፡፡ ስለዚህ ለአልሚ ባለሀብቶች የተመቸ አካባቢ ስለሆነ የአገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶች ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኩ ፈጥነው በመግባት የልማቱ አጋር እንዲሆኑ ጠይቀዋል፡፡
የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስትም በዚህም ሆነ በሌሎች የኢንዱስትሪ ፓርኮች ላይ ተሰማርተው አገርንና ህዝብን እየጠቀሙ ራሳቸውን ለማሳደግ ለሚንቀሳቀሱ ባለሀብቶች ያልተቆጠበ ድጋፍ ያደርጋል ሲሉ አቶ ለማ አረጋግጠዋል፡፡
ኢትዮጵያ በ2018 ዓ.ም የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ቁጥር 30 በማድረስ ኢንዱስትሪው ከወጪ ንግድ ገቢ ያለውን ድርሻ 50 በመቶ ለማሳደግ ግብ ይዛለች፡፡ በተመሳሳይ፣ ማኑፋክቸሪንግ ከአጠቃላይ ምርት ዕድገት (ጂዲፒ) 25 በመቶ ድርሻ እንዲኖረው አቅዳ እየሰራች ነው፡፡ በዚህም ከ200 ሺህ በላይ ዜጎች የስራ ዕድል ለመፍጠር ዕቅድ ተይዟል፡፡
በአገሪቱ በግንባታ ላይ ያሉትንና ስራ የጀመሩትን ጨምሮ 11 ኢንዱስትሪ ፓርኮች ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህ መካካል በቅርቡ ግንባታው ተጠናቅቆ የተመረቀው የጅማ ኢንዱስትሪ ፓርክ ይገኘበታል፡፡ የጅማ ኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ 61 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ተደርጎበታል፡፡ ግንባታውን ያካሄደው ቻይና ኮሙኒኬሽን ኮንስትራክሽን የተባለ ኩባንያ ሲሆን የግብርና ውጤቶችን በማቀነባባር ለውጭና ለአገር ውስጥ ገበያ የሚያቀርብ ይሆናል፡፡ ኢንዱስትሪ ፓርኩ የሚያርፈው በ300 ሄክታር መሬት ላይ ሲሆን፣ የመጀመሪያው ምዕራፍ ግንባታ 75 ሄክታር ላይ አርፎአል፡፡
ኢንቨስትመንት ለአገራት የዕደገትና ለዜጎች ደግሞ የዳቦ ማግኛ ምንጭ በመሆኑ ከልዕለ ሀያሏ አሜሪካ ጀምሮ እስከ ታዳጊ አገራት ድረስ ለመሳብ ብዙዎች ላይ ታች ይላሉ፡፡ ለኢንቨስትመንት ምቹ የሆነ ህግ ያወጣሉ፤ ማበረታቻዎች ይሰጣሉ፤ መሰረተ ልማቶችን ያሟላሉ፡፡ አስፈላጊውን ድጋፍም ያደርጋሉ፡፡ በተለይ እንደ አፍሪካ በርካታ ስራ አጥ ዜጎች ባሉባቸው አገራት ደግሞ ኢንቨስትመንትን መሳብ ከድህነት ለመውጣት አማራጭ የሌለው መንገድ ነው፡፡
ለዚህም ነው ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዕድገቷን ለማፋጠንና ለዜጎቿ የስራ ዕድል ለመፍጠር ኢንቨስትመንት በመሳብ ረገድ ታትራ እየሰራች ያለችው፣ ለዚህ ማሳያ የሚሆነን በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ለመሳብ ብዙ ስራዎች እንደሚሰሩ ይፋ ማድረጋቸው ነው፡፡ ከተለያዩ አገራት ባለሀብቶች በተገናኙበት ወቅት ሁሉ በኢትዮጵያ ኢንቨስት ቢያደርጉ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ እየገለጹ ናቸው፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 10/2011
ጌትነት ምህረቴ