ለ2012 ዓ.ም እንኳን በሰላምና በጤና አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
አዲሱ ዓመት የጤና የሰላም የብልፅግና እንዲሁም ኢትዮጵያዊ አንድነታችንን እንደ ሀገር በስኬት የምንረማመድበት እንዲሆንልን መልካም ምኞቴን ለማስተላለፍ እወዳለሁ። ከአንዱ ዘመን ወደ ሌላኛው ዘመን የሚደረገው ሽግግር ቀን ቆጥሮ አሮጌውን ከመሸኘትና አዲሱን ዓመት ከመቀበል ያለፈ አንድምታ አለው።አዲስ አመት ተስፋን ሰንቀን ወደ ተሻለ ህይወት ራሳችንን የምናዘጋጅበት ነው። በተጨማሪም አዲስ አመት ወደፊት አሻግረን ለምናየው ህልማችን የብርሃን ወጋገን የሚሰጥልን የጥንካሬያችን ምንጭ ነው።
እየተሰናበትነው ያለው 2011 ዓ.ም በብዙ መለኪያዎች የተለየ አመት ነበር ለማለት ይቻላል። ችግሮቻችንን እንዳሉ ሆነው ለሀገራችን በርካታ በጎ ነገሮችን ይዞ የመጣ ዓመት ነበር።ሁሉም ዜጋ በሀገሩ ጉዳይ ተሳታፊ እንዲሆን መንገዱን የሚጠርጉና በፖለቲካ፣ ኢኮኖሚና ማህበራዊ መስኮች መሰረት የጣሉ ስራዎች ተከናውነዋል።ዛሬ እኔ እናንተ ፊት መቅረቤ በራሱ ከጥቂት ወራት በፊት ማንም ይሆናል ብሎ የማይገምተውና ለሴቶች እህቶቻችን የ‹‹ይቻላልን›› ጠንካራ መልዕክት ያስተላለፈ ነው።የሴቶችን እኩልነት ለማረጋገጥ በሩ ተከፍቷል።እንዳይዘጋና ብሎም በርካታ ሴቶች እንዳያልፉበት ለማድረግ ሁላችንም ልንረባረብበት ይገባል።
በአመለካከታቸው የተነሳ ተራርቀው የቆዩ ወገኖች በሀገር ጉዳይ ላይ በጠረጴዛ ዙሪያ ለመቀመጥና ለመወያየት በቅተዋል።በአመለካከትና በዕምነት መለያየት የጋራ ጉዳይን መሳት ሊሆን አይገባውምና። የሚያስተሳስረን አንዱና ብቸኛው ገመድ ኢትዮጵያዊነት ነውና።ዛሬ ሀገራችን ባለችበት ሁኔታ ሊያግባባንና ሊያስተሳስረን የሚገባው ጉዳይ ወገኖቻችንን ከድህነት ሰንሰለት ማላቀቅ፣ መሰረታዊ ፍላጎታችንና መብቶቻችንን ማስከበር ነው ብዬ በጽኑ አምናለሁ።
መጪውን ዓመት ስንቀበል የመጣንበትን በመዘንጋት አይደለም። ባለፉት ዓመታት የሀገራችንን ህልውና ሳይቀር የተፈታተኑ ሁኔታዎችን አሳልፈናል። በታሪካችን አይተነው የማናውቀው የውስጥ መፈናቀልና ግጭት በጎ ተግባሮቻችንን
ጥላሸት ቀብቶታል። ያለንን የምንለካውና የምናከብረው ለነገም ትክክለኛ ህልም የምናልመው መነሻችንን ካልዘነጋን ነው።
ሀገራችን የተያያዘችው የለውጥ ሂደት ካለፉት ብዙ የተለየ የሚያደርገው የነበረውን ጠራርጎ ‹‹ሀ›› ብሎ የጀመረ ሳይሆን ለዚህች ሀገር እድገትና ብልጽግና እሰለፋለሁ የሚለውን ሁሉ አስተባብሮ ለመጓዝ የተነሳ ነው። ይህ ደግሞ የራሱ የሆኑ አዳዲስ መሰናክሎችን ይዞ መጥቷል። በአጠቃላይ እንደዚህ ያለ መሰረታዊ ለውጥ አልጋ በአልጋ ይሆናል ብሎ ማሰብም ከእውነታው መራቅ ነው።
ባለፉት ጊዜያት ያየናቸው አስከፊ ሁኔታዎች በሀገራችን እንዳይከሰቱ የማድረግ ሃላፊነት በመንግስት ወይም በተወሰኑ አካላት ላይ ብቻ የሚተው አይደለም።የሁላችንም ኢትዮጵያውያን የአንድ ጊዜ ሳይሆን የምን ግዜም ተግባር መሆን አለበት። የሀገር ሰላምና መረጋጋት እንዲሁም የልማት ጉዳይ ለይደር የሚተው አይደለም።
ከሁሉም በላይ ደግሞ ማንኛውም ነገር ወሰንና ልከት እንዳለው ለአንድ አፍታ አንዘንጋ። ውሃ ሞልቶ ከፈሰሰ ሊመለስ እንደማይችል ሁሉ አስቀድመን መከላከልና ማስቀረት እየቻልን ለግል፣ ወይንም ለቡድን ፍላጎት ብቻ ብሎም ለአንድ ወቅት የፖለቲካ ጥቅም የሚደረጉ፣ ሊኖረን የሚገባንን ቀይ መስመር ያለፉ ተግባራት በስተመጨረሻ ልንመልሰው ወደማንችል መቀመቅ እንዳይከቱን ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ አለብን።
አዲስ አመት በአንድ መጽሐፍ ውስጥ በተከታታይ የተለያዩ ጉዳዮች እንደሚጻፍባቸው አዳዲስ ምዕራፎች ሊመሰል ይችላል።
የኢትዮጵያችን መጽሐፍ ውስጥ የ2012 አገርን ጽኑ መሰረት ላይ ያሥቀመጥንበት ተቋሞቻችንንና ተቋማዊ አሰራርንና አንድነታችንን የምናጠናክርበት ምዕራፍ እናድርገው።
ኢትዮጵያችን ከእኛ የምትፈልገው ከአቅማችን በላይ የሆነ ነገር አይደለም። ሁላችንም ልጆቿ የትም እንሁን የትም የምንችለውን በጎ ተግባር ማበርከት ከቻልን ችግሮቻችን ሁሉ የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ቀስ በቀስ እየተቃለሉ መምጣታቸው እርግጥ ነው።አንዳችን ለሌላችን መሆን ከቻልን ያኔ የኢትዮጵያችን መልካም ዘመን እውን ይሆናሉ።
አንድነታችንን ካጠናከርን መሰናክሎቻችንን ሁሉ አራግፈን ወደ ማማው መውጣታችን አይቀሬ ነው። አባቶቻችንና እናቶቻችን በተግባር ያሳዩን በችግሮቻችን ተውጠን ከስመን መቅረት ሳይሆን ከችግሮቻችን መካከልም የማይደበዝዙ ድንቅ ተግባራን በመፈጸም በሁለት እግር መቆም እንደሚቻልም ጭምር ነው። በመጪው አመት ሰላሟና ደህንነቷ የተረጋገጠ ኢትዮጵያን እውን እንደምናደርግ ለዚህም አንድነታችን የማዕዘን ድንጋይ መሆኑ ሙሉ እምነት አለኝ።
ከክረምት በኋላ የደፈረሱ ወንዞች እንደሚጠሩት ሁሉ ፤መሬቱ እንደሚለመልመው፤ አበቦች በአዲስ ተስፋ ሰጪነት እንደሚያብቡት ሁሉ እኛም ሌላ ክረምት ሳንጠብቅ ራሳችንን ለማጥራት እንጀምር።
በድጋሚ አዲሱ አመት የጤና፣ የሰላም፣ የፍቅር እና የብልጽግና እንዲሆንልን እመኛለሁ።
መልካም አዲስ አመት
አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን መስከረም 1ቀን 2012 ዓ.ም