-ጀነራል ብርሀኑ ጁላ
የጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኤታማዦር ሹምና የዘመቻ መምሪያ ኃላፊ
የሀገር መከላከያ ሚኒስቴር አዲሱን ዓመት በሕብረብሔራዊ ስሜት ያከብራል ፡፡ ከዚህ በዓል ጎን ለጎንም አገራዊ ኃላፊነቱን በተለይ ደግሞ የአገር ሉዓላዊነትን የማስከበር ተልዕኮውን ለመወጣት ከመቼውም ጊዜ በላቀ ዝግጁ ነው ሲሉ የመከላከያ ሚኒስቴር ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹምና የዘመቻ መምሪያው ኃላፊ ጀነራል ብርሃኑ ጁላ ይናገራሉ፡፡ አዲሱን ዓመት አስመልክተን ከጀነራሉ ጋር ያደረግነውን ልዩ ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡
አዲስ ዘመን፡- መከላከያ አዲሱን አመት እንዴት ሊቀበለው ተዘጋጅቷል ?
ጀነራል ብርሃኑ፡- መከላከያ አዲሱን አመት የሚቀበለው የሀገሪቱን ሰላምና ደሕንነት ካለፈው አመት በተሻለ ሁኔታ የማረጋገጥ ስራ በመስራት ነው። የጀመረውን የሪፎርም ስራ አጠናክሮ ይቀጥላል። 13 ግቦች 6 ፕሮግራሞች አሉት። የአምስትና የስድስት አመት ፕሮግራም ነው። ይህንን ተግባራዊ እናደርጋለን። አሁን እየሰራን ያለነው ለአጠቃላይ ሪፎርሙ ተግባራዊነት የሚያግዙ መሰረቶችን ነው፡፡ በያዝነው አዲስ አመት አጠናክረን እንቀጥላለን፡፡
አመራሩ በዚህች ሀገር ውስጥ የነበረውን የውስጥ ቅራኔ አቻችሎ ወደ አንድነት ወደ ጋራ ብልጽግና እንድትሸጋገር ለማድረግ የሚያስችል ጥረት እያደረገ ነው፡፡ ጥረቱ መደገፍ አለበት፡፡ የለውጡን በጎ ጥረት የማይቀበል ለማደናቀፍ የሚሰራ ኃይል አለ፡፡ መንግስት የፈረሰ መስሎት ራሱ የፈለገውን ለመውሰድ የሚሰራ ኃይል አለ፡፡ ስልጣን በአቋራጭ ለመያዝ የሚፈልግ ኃይል አለ። ይሄ ሁሉ ተደማምሮ የአለፈው አመት በጣም አስቸጋሪ አመት ነበር፡፡ በዚህ አመት ያለፈው አመት ስህተትና ችግር በሌላ መልኩ እንዳይከሰት መከላከያ ጠንክሮ ይሰራል፡፡
በጣም ከፍተኛ ትእግስት አሳይተናል፡፡ መከላከያ ከቦታ ቦታ ሲንቀሳቀስ መንገድ እየተዘጋበት ጥሰን ማለፍ እርምጃም መውሰድ እየቻልን የለውጥ ጊዜ ነው መታገስ አለብን በሚል ጉዳት እየደረሰብንም አሳልፈናል፡፡ የመከላከያ ኮንቮይ(ቅልፈት) እንዳይሄድ እየተደረገም ታግሰናል፡፡ መከላከያ ላይ ድንጋይ እየተወረወረ ዝምታን የመረጥንበት ሁኔታም ነበር። እንዲህ አይነት የወንጀል ድርጊት በየትኛውም ሀገር መከላከያ ኃይል ላይ አይፈጸምም፡፡ ከአሁን በኋላ በየትኛውም ቦታ እንዲህ አይነቱን ነውረኛ ድርጊት አንታገስም፡፡
በሀገሪቱ ከመጣው ለውጥና የዴሞክራሲ ምሕዳር መስፋት ጋር ተያይዞ የሀገሪቱን የመከላከያ ኃይል የሚፈታተኑ ተደጋጋሚ ችግሮች አጋጥመውታል፡፡ ኃይል መጠቀም የለብንም ችግሮች በዚህ አይፈቱም በሚል ነበር መታገስን የመረጥነው፡፡ በአዲሱ ዓመት ይህ በምንም መልኩ አይደገምም፡፡ ከሕግ ውጭ የሆነ ማንኛውም እንቅስቃሴ ሕገወጥና ስርአት አልበኝነት ይስተካከላል፡፡
አዲስ ዘመን፡- በአዲሱ አመት ሠራዊቱ ሕገመንግስታዊ ተልእኮውን ለመወጣት ያለው ዝግጁነት ምን ይመስላል?
ጀነራል ብርሃኑ፡- በዚህ አመት ብዙ ለውጦች ይኖራሉ፡፡ የክልል ጸጥታ ኃይሎች ይጠናከራሉ። ጠንካራ የክልል የጸጥታ ኃይሎች እንዲሆኑ እናደርጋለን፡፡ አሁንም ስራውን ጀምረን እየሰራን እያገዝናቸው ነው፡፡ የመከላከያን ጫናና ሸክም በከፍተኛ ደረጃ እንዲካፈሉ እናደርጋለን፡፡ በሁለተኛ ደረጃ የመከላከያ ሠራዊታችን አደረጃጀት ተቀይሮአል። አደረጃጀቱ ኃይል የሚያባዛ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- እንዴት ?
ጀነራል ብርሃኑ፡- ይህ ማለት በጣም በርካታ ኃይል በእጃችን ይኖረናል፡፡ አደረጃጀቱ የሚፈጥረው የመንቀሳቀስ አቅም አለ፡፡ ለምሳሌ በፊት ከሪፎርሙ በፊት በነበረው አደረጃጀት ብርጌድ የሚባል አልነበረንም፡፡ ሬጅመንት ከሬጅመንት ክፍለጦር ከክፍለ ጦር እዝ ነው የነበረው፡፡ አሁን በአዲሱ አደረጃጀት ብርጌድ ተፈጥሮአል፡፡ አንድ ብርጌድ ሠራዊት አንድ ቦታ ላይ ከሰፈረ ትልቅ ኃይል ነው። አካባቢውን መቆጣጠር ቀጠናውን ማስፋት ይችላል፡፡ የመንቀሳቀስ አቅማችን ይጨምራል፡
ንቅናቄው በትራንስፖርት አቅም ይደገፋል (ሞተር ኬድ ሞቢሊቲው) ፈጣን ይሆናል፡፡ የተደራጀው ኃይል እዛው እያለ በትጥቅ በፈጣን ተነቃናቂነት በትራንስፖርት አቅም እንዲጠናከር ይደረጋል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ይሄ የሚሆነው መከላከያ ራሱን ችሎ ነው ወይስ ከክልል ያለውን ኃይል በመጨመር ?
ጀነራል ብርሃኑ፡- የክልል ኃይልን በማሰልጠን በማስታጠቅ የመደበኛውን ሠራዊት አሰራሮች፤ ግዳጅ አፈጻጸሞች፤ መመሪያና ደንቦች፤ ዲሲፕሊኖችን እንዲላበስ በማድረግ ራሱን እንዲችል ማድረግ ነው። አደረጃጀት ንቅናቄ የትጥቅ ጉዳይ ደግሞ የመከላከያ ስራ ነው፡፡ ይሄን በማድረግ ኃይላችንን በማባዛት ለማንኛውም ስምሪትና ግዳጅ አፈጻጸም ዝግጁ እንዲሆን ይደረጋል፡፡ በየቦታው ከሚከሰቱት የጸጥታ ችግሮች አንጻር መከላከያ ከጎኑ እያለ ራሱን ችሎ የሚሰጠውን ግዳጅ ስለሚወጣ የመከላከያን ሸክም ያቃልላል፡፡
ኃይላችንን ዝግጁ ስናደርግ ትልቁ የሀገራችንም ሆነ የአካባቢያችን ወቅታዊ ስጋት አሸባሪነት መሆኑ ተለይቶ የተቀመጠ ነው፡፡ በቅርብ ቀን ይወረናል ብለን የምንሰጋው አደጋ አለ ብለን አናስብም፡፡ ከታክቲክና ከስትራቴጂ አኳያ ምናልባታዊ የሆኑ የጠላት ወረራዎች ቢከሰቱስ የሚለው ወሳኝ ጉዳይ ሁልጊዜ አብሮ ታሳቢ ተደርጎ ስለሚወሰድ በሀገር ደረጃ በሁሉም አቅጣጫ የማያቋርጥ ቋሚ ዝግጁነት አለን፡፡ በጦርነት ሕግጋት ውስጥ ዋናው መርህ በሰላም ጊዜ ለጦርነት ተዘጋጅ የሚለው ነው። ልንወረርም እንችላለን የሚል የሁልጊዜም የላቀ ዝግጁነት አለን፡፡ ከዚህ በተረፈ አሸባሪነት ፊታችን ላይ የተደቀነ ትልቁ አደጋ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- አሸባሪነት የውጊያ ባሕርይው የተለየ ስለሆነ መደበኛ የውጊያ ስልት አይከተልም፡፡ ይሄን በቅርብ ርቀት የተደቀነ አደጋ ለማስወገድ ምን ያህል ተዘጋጅተናል ?
ጀነራል ብርሃኑ፡- አሸባሪነት ሀገራዊ፣ አህጉራዊ፣ ዓለም አቀፋዊ አደጋ ነው፡፡ የሰላም የሀገር የሕዝብ የልማትና የእድገት ጠንቅና ጠላት ነው፡፡ ስለ አሸባሪነት ስናነሳ በአጥፍቶ ጠፊነት ፤ በሕዝብ ውስጥ ተመሳስሎና ተደብቆ እየተሽሎከሎከ ጥፋትና አደጋ ለማድረስ በነፍስ ወከፍና በአነስተኛ ቡድን የሚንቀሳቀሰውን ኃይል የመከታተል የማደንና አደጋው ከመድረሱ በፊት የማምከን ስራው ባለቤት አለው፡፡ የመከላከያ ስራ አይደለም። ይሄ የብሔራዊ ደህንነትና የፌዴራል ፖሊስ ስራ ነው፡፡
አሁን ባለው ዓለም አቀፍ እውነት በተጨባጭ በታየውም መሰረት አሸባሪነት በመደበኛ ሠራዊት ቅርጽ ሻለቃና ብርጌድ ሠራዊት አደራጅቶም ይዋጋል፡፡ በሶሪያ በሶማሊያ በአፍጋኒስታን ታይቷል፡፡ አልሻባብና አይሲስ በዚህ መንገድ ሲዋጉ ቆይተዋል፡፡ እየተዋጉም ነው፡፡ ይሄ ኃይል በኢትዮጵያ ምድር ምንም አይነት ይሁን ምን አደረጃጀትና ቅርጽ ይዞ ጥቃት እንዳያደርስ ድል እንዳያገኝ የሚያግድ ስራ ስንሰራ ቆይተናል፡፡ አሁንም በበለጠ መልኩ እንሰራለን፡፡ እየተሽሎከለከ ሕዝብ ላይ ጅምላ ጨራሽ ጥፋት ለማድረስ የሚንቀሳቀሰውን ደግሞ ከሚመለከታቸው የጸጥታ ኃይሎች ጋር በመሆን ባለን ፈጣን የመረጃ ልውውጥ በታየበት ቦታ ሁሉ ፈጥነን በመድረስ የማያዳግም እርምጃ እንወስዳለን፡፡
አዲስ ዘመን፡- መከላከያ ሕብረ ብሔራዊና የሕዝብ ወገንተኛ ነው ሲባል በምን መልኩ ይገለጻል ?
ጀነራል ብርሃኑ፡- ሕብረ ብሔራዊ ማለት የኢትዮጵያን ሕዝብ በሙሉ የመሰለ የሚወክል ማለት
ነው፡፡ የብሔረሰቦች ተዋጽኦ ያለው ነው፡፡ ይህ ኃይል ዋናው ስራው የመላ ሀገሪቱን ሉአላዊነት፤ የግዛት አንድነት ከየትኛውም አይነት የውጭም ሆነ የውስጥ ጥቃት ነቅቶ መጠበቅና መከላከል ነው፡፡ መከላከያ የሀገራዊ አጀንዳ ባለቤት ነው፡፡ ለኢትዮጵያ ሰላም መከበር ዘብ ሆኖ የቆመ ኃይል ነው፡፡
መከላከያ የጎጥና የመንደር እሳቤ የለውም፡፡ ሕብረ ብሔራዊ ሠራዊት ነው ሲባል ሁሉም ዜጋ የእኔ ነው የሚለው፤ የሚኮራበት የሚተማመንበት ለሁሉም ደህንነት የሚሰራ ግዙፍና በዘመናዊ አደረጃጀት የተዋቀረ የታጠቀ ሀገራዊ ተቋም ነው፡፡ የሚወክለው ኢትዮጵያን ነው፡፡ እዚህ ላይ አንዳንድ ሀገር የማፍረስ አላማና ግብ ይዘው የሚንቀሳቀሱ ክፍሎች ሆን ብለው በታቀደና በተጠና ሁኔታ በመከላከያ ላይ በሚከፍቱት የሐሰት ፕሮፓጋንዳና ስም የማጠልሸት ዘመቻ ብዥታ ሊኖር አይገባም።
መከላከያ ብቸኛ ብርቅዬ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሀብትና የክፉ ቀን ደራሽ ብርቱ ክንዱ ነው፡፡ ይሄንን እውነት በተደጋጋሚ አሳይቷል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ይሄ ተቋም ከሌለ በሰላም ተኝቶ ማደር አይችልም፡፡ ሕልውናም የለውም፡፡ የሆነውን ሁሉ በአለፉት ዓመታት በተጨባጭ አይቷል፡፡ የታደገው የመከላከያ ሠራዊት ነው፡፡ ይህንን እውነት በሚገባ እያወቁ ተቋሙን ለማፍረስ የሚሰሩ አሉ፡፡
መከላከያ የጎጥና የመንደር እሳቤ የለውም፡፡ ሕብረ ብሔራዊ ሠራዊት ነው ሲባል ሁሉም ዜጋ የእኔ ነው የሚለው፤ የሚኮራበት የሚተማመንበት ለሁሉም ደህንነት የሚሰራ ግዙፍና በዘመናዊ አደረጃጀት የተዋቀረ የታጠቀ ሀገራዊ ተቋም ነው፡፡ የሚወክለው ኢትዮጵያን ነው፡፡ እዚህ ላይ አንዳንድ ሀገር የማፍረስ አላማና ግብ ይዘው የሚንቀሳቀሱ ክፍሎች ሆን ብለው በታቀደና በተጠና ሁኔታ በመከላከያ ላይ በሚከፍቱት የሐሰት ፕሮፓጋንዳና ስም የማጠልሸት ዘመቻ ብዥታ ሊኖር አይገባም።
መከላከያ ብቸኛ ብርቅዬ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሀብትና የክፉ ቀን ደራሽ ብርቱ ክንዱ ነው፡፡ ይሄንን እውነት በተደጋጋሚ አሳይቷል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ይሄ ተቋም ከሌለ በሰላም ተኝቶ ማደር አይችልም፡፡ ሕልውናም የለውም፡፡ የሆነውን ሁሉ በአለፉት ዓመታት በተጨባጭ አይቷል፡፡ የታደገው የመከላከያ ሠራዊት ነው፡፡ ይህንን እውነት በሚገባ እያወቁ ተቋሙን ለማፍረስ የሚሰሩ አሉ፡፡
እንደ ተቋም የመክሰስም የመከሰስም መብት ስላለን በሕግ እንጠይቃለን፡፡ ከሕግ ውጭ የምንወስደው እርምጃ የለም፡፡ እንከሳለን፡፡ እናስታግሳቸዋለን፡፡ በቂ መረጃ አሰባስበን ሰላዮች መሆናቸውን ካረጋገጥን በሀገር ክህደት ወንጀል ከሰን ለፍርድ እናቀርባቸዋለን፡፡
አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ወቅት ሀገራዊ ሰላማችን በምን ደረጃ ላይ ይገኛል?
ጀነራል ብርሃኑ፡- በአንጻራዊነት ሀገራዊ ሰላማችን እስከ ዛሬ ከነበሩት ሁሉ በእጅጉ የተሻለ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ከምስራቅ እስከ ምዕራብ ከሰሜን እስከ ደቡብ ብዙ የሚታይ የተከሰተ መከላከያን በግዳጅ የሚወጥር ችግር የለም። ፖሊስን የሚመለከቱ የወንጀል ችግሮች ግን አሉ። እንደ ሀገር ወንጀልን አስቀድሞ የመከላከል ስራ ቢሰራም አይነትና ቅርጻቸውን እየለዋወጡ የሚከሰቱ ወንጀሎች አሉ፡፡ በንጉሱም በደርግም ጊዜ ነበር፡፡ አሁንም አለ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ፌዴራል ፖሊስ ከመከላከያ ጋር ቅንጅት አለው ተናቦ ይሰራል ?
ጀነራል ብርሃኑ፡- የሀገሪቱ የጸጥታ ኃይል በጠቅላላ አብሮ ነው የሚሰራው፡፡ የጋራ ምክርቤት አለው፡፡ መከላከያ፣ የፌዴራል ፖሊስ፣ አዲስ አበባ ፖሊስ፣ ብሔራዊ ደህንነት፣ ክልሎች ሁሉ በጋራ ነው የሚሰሩት፡፡ የጋራ እቅድ ፣ ግምገማ ፣ የጋራ ውሳኔ ፣ የጋራ ስምሪት አለ፡፡ በዚህ መልክ ነው የሚሰራው፡፡ የተደራጀ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- መከላከያ ጠቅላይ ኤታማዦር ሹሙን ጀነራል ሰአረ መኮንን አጥቷል፡፡ በሠራዊቱ ውስጥ የተፈጠረው ስሜት ምን ነበር ?
ጀነራል ብርሃኑ፡- መሪው የተገደለበት ሠራዊት ምንም አይሰማውም ማለት አይቻልም፡፡ ምን ተፈጠረ ? ሀገራችን ላይ ምንድነው የሆነው? ማነው ያደረገው? ለምንስ ተደረገ? የሚል ከፍተኛ የሆነ ጥያቄ አለ፡፡ በሀገራችን እንዲህ አይነቱ ነገር የመጀመሪያ ነው፡፡ በደርግ ጊዜ በነበረው የጀነራሎቹ መፈንቅለ መንግስት እርስ በእርስ የተጠፋፉበት ሁኔታ ካልሆነ በስተቀር እንዲህ አይነት አደጋ አጋጥሞን አያውቅም፡፡ ሠራዊታችን እንዲህ አይነት ልምድ የለውም፡፡
የተረጋጋው መንግስት ማን እንዳደረገው ለምን እንዳደረገው ይፋ ያደርጋል፤ በአደረገውም ላይ እርምጃ ይወስዳል፤ እኛ ስራችንን እንስራ ፤ስራችንን በመስራት ነው የጀነራል ሰአረን ግድያ የምንበቀለው፡፡ የምንክሰው በሚል ሠራዊቱ ተወያይቶ፤ ተግባብቶ ወደ መደበኛ ስራው ገብቷል፡፡ የመጨረሻውን የግድያውን ዝርዝር መንስኤና ምክንያት ገዳዩ ማን ምን እንደሆነ ግን ማወቅ ይፈልጋል፡፡ መንግስት በዚህ ላይ እየሰራ ነው፡፡ ጥሩ ፍንጭዎችም አሉ። አንድ መሪ ወይንም አዛዥ ችግር ቢገጥመው ቢሞት፣ ቢቆስል፣ ቢታመም ወዲያው ሌላው ተተክቶ ስራውን ይሰራል፡፡ ግዳጁን ይወጣል፡፡ የሆነውም እንደዚሁ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- የአመራር ክፍተቱ የተሞላበት ሁኔታ እንዴት ነው ?
ጀነራል ብርሃኑ፡- ሠራዊቱ የመንግስትን ውሳኔ ይቀበላል፤ ያከብራል፡፡ የጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹም ምደባ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ውሳኔ ነው፡፡ ይሄ ደግሞ ሕገመንግስታዊ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- በአንድ ወቅት ኢትዮጵያ መልሳ ባሕር ኃይሏን እንደምታቋቁም ለዚህም ስራዎች መጀመራቸውን ገልጸው ነበር፡፡ የተጀመረው ስራ ከምን ደረሰ ቢገልጹልኝ ?
ጀነራል ብርሃኑ፡- ባሕር ኃይላችንን አደ ራጅተናል። መዋቅሩ አልቋል፡፡ አመራርና ስታፍ ተመድቧል፡፡ ሰዎች ወደ ውጭ ሀገራት ለስልጠና ሄደዋል፡፡ የባህር ኃይል አካዳሚ እየከፈትን ነው። ከዜሮ ስለጀመርን ጊዜ ይወስዳል፡፡ ዋናው የሰው
ኃይል ማዘጋጀት ነው፡፡ ብዙ መኮንኖች ወደራሽያ ወደ ፈረንሳይ የተለያዩ ሀገሮች ልከናል፡፡ ሀገር ውስጥም የምናሰለጥናቸው ይኖራሉ፡፡ ዝግጅት ላይ ነን፡፡ ሰው ሳትፈጥር ጀልባ መርከብ ብታመጣ ዋጋ የለውም። ሰው ነው እያዘጋጀን ያለነው፡፡ ዘመናዊ የሆኑ የጦር መርከቦች መሳሪያዎች ጀልባዎች እንገዛለን፡፡ የባሕር ኃይሉ ካምፕ ያስፈልገናል። የባሕር ኃይል መደቦች ይኖሩናል፡፡ እያስፋፋን እንሄዳለን፡፡
አዲስ ዘመን፡- በአማራ ክልል በቅርቡ ከሜቴክ የሄዱ የጦር መሳሪያ ቀለብ (ጥይቶች) የጫኑ 5 የጭነት መኪናዎች በወጣቶች ተይዘው ውዝግብ ተፈጥሮ ነበር፡፡ ይህ እንዴት ሊከሰት ቻለ? ቢያስረዱን?
ጀነራል ብርሃኑ፡- መከላከያ ይህን ጉዳይ በተመለከተ ዝምታን ነው የመረጠው፡፡ ዝም ያልንበት ምክንያት የተሰራው ስራ እጅግ አሳፋሪና ሕገወጥ ስለሆነ ነው፡፡ ትጥቁ የሜቴክ ነው፡፡ የመከላከያ አይደለም፡፡ ዞሮ ዞሮ የሀገር ሀብት ነው፡፡ በመከላከያ ላይ የስም ማጥፋት የከፈቱ ኃይሎች የመከላከያ ንብረት ነው፤ ትግራይን ሊያስታጥቅ ነው ብለው ነው ዘመቻ የከፈቱት፡፡ መንገዱ ዓለምአቀፍ መንገድ ነው፡፡ ከኢትዮጵያ ተነስቶ ካርቱም ከሰላ ይገባል፡፡ የፌዴራል መንገድ ነው፡፡ የፌዴራል መንግስት በዚህ መንገድ ላይ የሚያመላልሰውን እያንዳንዱን መኪና ሪፖርት እያደረገ አያሰማራም። የመሳሪያ ቀለቡ ሕጋዊ ነው፡፡ የሚመለከታቸው መንግስታዊ አካላት ሁሉ ያውቁታል፡፡
ሱዳኖች ትጥቁን የገዙት በኢትዮጰያ ለውጥ ከመምጣቱ በፊት ነው፡፡ ገንዘብ ከፍለዋል፡፡ ሜቴክ ሻጭ ነው፡፡ ሸጦላቸዋል፡፡ በስምምነታቸው መሰረት ዴሊቨር አድርጉልን (አስረክቡን) አሉ፡፡ ሜቴክ ልልክላቸው ነው አለ፡፡ ጦር መሳሪያ ስለሆነ ወደ ሁለተኛ ሀገርም ስለሚሄድ መንገድ ላይ የጉምሩክ ሰዎች ፖሊሶች እንዳያስቆሙት ስለሚመለከተን እኛ ደብዳቤ ጻፍን፡፡ ስንጽፍ ሱዳንና ሜቴክ ያደረጉትን ስምምነት ተመልክተን፤ ምን ያህል እንደሆነ አውቀን፤ ስንት ገንዘብ እንደከፈሉ አይተን፤ ሕጋዊ መሆኑን አረጋግጠን ማለፍ አለበት ብለን ለጉምሩክና ለሚመለከታቸው ደብዳቤ ጽፈናል፡፡ ጉምሩክ ደግሞ መተማ ላለው እንዲናገር ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- አይኤስ ኤስ (አለም አቀፉ እስላማዊ አክራሪ ቡድን) ያለውን ትርምስ በመጠቀም ኢትዮጵያ ውስጥ ገብቻለሁ ሲል በድረገጹ ገልጿል፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት ዝምታን መርጧል የሚል ድምጽ ይሰማል፡፡ እርስዎ ምን ይላሉ?
ጀነራል ብርሃኑ፡- ነገሩ አዲስ አይደለም፡፡ በአይሲስ የተመለመሉ ስልጠና የወሰዱ የተጠመቁ ሰዎች እንዳሉ መንግስት በሚገባ ያውቃል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በተለያየ ቦታ ለመንቀሳቀስ በተደጋጋሚ ጥረት አድርገው መክኖባቸዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ምን እያደረጉ እንዳሉ፤ የት የት ቦታ በመንቀሳቀስ ላይ እንደሆኑ፤ ከእነማን ጋር ግንኙነት እንዳላቸው፤ በከተሞች ውስጥ ያሉት ሰዎቻቸው እነማን እንደሆኑ፤ ማን ከማን ጋር እንደሚገናኝ፤ ምን እየሰሩ እንዳሉና እቅዳቸው ምን እንደሆነ ሌላም መግለጽ የማያስፈልጉ ጉዳዮችም ጭምር እጅግ ከፍተኛ በሆነ የቅርብ ክትትል ስር ናቸው፡፡
ከሰሞኑ የተያዙ በቁጥጥር ስር የዋሉ አሉ። መከላከያ በጥንቃቄ በከፍተኛ ሀገራዊ የኃላፊነት ስሜት ሀገርና ሕዝብን ከአደጋ ለመጠበቅ ቀን ከሌት እየሰራን ነው፡፡ ሀገራችንንና ሕዝባችንን ከየትኛውም አደጋ ለመጠበቅና ለመከላከል ባለብን አደራና ከባድ ኃላፊነት የተነሳ አንተኛም፡፡ አናንቀላፋም፡፡ ቀን ከሌት በበዓላትም ጭምር ስራ ላይ ነን፡፡
እረፍት የሚባል ነገር አናውቅም፡፡ ያረፍንበት ጊዜም የለም፡፡ መንግስት ጠንቅቆ ያውቃቸዋል። አንዳንድ ጊዜ የሆነ ሰው እንደተገኘ ሄዶ መያዝ መቆጣጠር ልክ አይሆንም፡፡ ልክ የማይሆነው ብዙ ነገር ሊያመልጥ ስለሚችል ነው፡፡ ብዙ ነገር እንዳያመልጥ ተደርጎ በሕግ አግባብ መቆጣጠር ይቻላል፡፡ ግለሰቦች አሉ፡፡ የት እንዳሉ ይታወቃል፡፡
ክትትል ሲደረግባቸው የነበሩ በቅርብ ቀን የተያዙ አሉ፡፡ ያልተያዙ በጥብቅ በአይነቁራኛ ክትትል ውስጥ ያሉ አሉ፡፡ አይ ኤስ ኢትዮጵያ ገብቻለሁ የሚለው በሕዝቡ ውስጥ ሽብር ለመልቀቅ በማሰብ የተጠቀመበት የሥነልቦና ጦርነት (ሳይኮሎጂካል ዋርፌር) ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ በዚህ የሚፈራ የሚደናገጥ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ገብቶ የአይሲስን ኦፕሬሽን የማካሄድ አቅም የለውም፡፡
አዲስ ዘመን፡- ሠራዊቱ ከመደበኛ ግዳጁ ውጪ የሕይወት መስዋዕትነት እየከፈለ ነው ?
ጀነራል ብርሃኑ ጁላ፡- ሠራዊታችንን በተመለከተ በእውነት ለመናገር በጀግንነት በብቃት በከፍተኛ ወታደራዊ ዲስፕሊን ሕገመንግስቱን ሀገሩን ሕዝቡን ጠብቋል፡፡ ወደፊትም ይጠብቃል፡፡ ሠራዊታችን እየተገደለ፣ እየሞተ፣ ድንጋይ እየተወረወረበት፣ በድንጋይ እየተወገረ ፣ እየተተፋበት፣ ቃልኪዳን የገባበት ሀገርና ሕዝብን የመጠበቅ ተልእኮ ስላለው ጥርሱን ነክሶ ግዳጁን ፈጽሟል፡፡
በተለይ ሕዝብ ውስጥ የሚደረጉ ግጭቶች በጣም ከባድ ናቸው፡፡ ጦርነት ቢሆንማ ኖሮ በየትኛውም የመሬት ገጽ ላይ ልክ ማስገባት እናውቅበታለን፡፡ ሕዝባችን ውስጥ ግን በጣም ጥንቃቄ ይጠይቃል፡፡ ጥንቃቄ ለማድረግ ሲል ነው ሠራዊቱ እየሞተ ያለው። ሠራዊታችን አፋርና ኢሳ ሲዋጋ ለሁለቱም ጥንቃቄ ለማድረግ መሀል እየገባ እየሞተ ነው ያሳለፈው፡፡
እጅግ የሚያሳዝነን ጉዳይ ሠራዊቱ ለሀገርና ለሕዝብ ሲል በሚከፍለው መስዋእትነት ለእኛ ሲል ነው የሞተው የሚል ምስጋና የለውም፡፡ አፋር ለእኔ አላገዝክም ይላል ኢሳ ለእኔ አላገዝክም ይላል። ቤኒሻንጉልና ኦሮሚያ መሀል እንደዛ፡፡ ገሪና ቦረና መሀል እንደዛ፡፡ ቅማንትና አማራ መሀል እንደዛ። ምንም ምስጋና ሳይኖረው በከፍተኛ ደረጃ ሕዝብ እንዳያልቅ የሕይወት ዋጋ እየከፈለ የጠበቀ ሀገሪቱን ከትርምስ ከጥፋት ሕዝባችንን ከእልቂት ያዳነ የታደገ ነው የመከላከያ ሠራዊታችን፡፡ በ2012 ዓ.ም ሠራዊታችን ሕዝብ ውስጥ በሚፈፀሙ ግጭቶች የሚከፍለው መስዋዕትነት መቆም አለበት፡፡
ሽኔ ኦነግ በሶስት ወር ውስጥ መንግስታዊ ስልጣን እይዛለሁ ብሎ ጦርነት አውጆ ሕዝባችን ላይ መንገድ ዘግቶ፤ የሕዝብ ልጆች ትምህርት ቤት እንዳይማሩ አድርጎ ፤ እጅግ ከፍተኛ የሆነ ማህበራዊ ቀውስ ፈጥሮ በሚፈነጭበት ወቅት ሠራዊታችን በለመደው የግዳጅ አፈጻጸም ስርአት ግዳጁን ተወጥቶ ምእራብ ቀጠናን ከባኮ እስከ አሶሳ ነጻ አውጥቶታል፡፡ አሁን አለን ለማለት ብቻ የሚወራጩ ጫካ ውስጥ የተደበቁ ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ተደራጅቶ የሚንቀሳቀስ ለሕዝብና ለመንግስት ስጋት የሚሆን ኃይል ግን የለም፡፡ ይሄ ሠራዊታችን የሰራው ስራ ነው፡፡
በደቡብም እንደዚህ አይነት ችግር አጋጥሞን ነበር። እዛም ሰብሳቢው የፈጠረው ግጭት ነበር። በአዲስ አበባ የተፈጠረውን ሁኔታ እናስታውስ፡፡ አዲስ አበባን ከቡራዩ ጋር አያይዞ ጠቅላላ የጦርነት ቀጠና ለማድረግ ፕላን (እቅድ) አውጥተው ሰርተው ነበር፡፡ በአንድ ቀን ውስጥ ወደነበረበት እንዲመለስ ያደረገው ሠራዊቱ ነው፡፡ በቅርቡ በአማራ ክልል በአመራሮች ላይ በተፈጸመው ግድያና መፈንቅለ መንግስት ሠራዊታችን ነው ሕግና ስርአት እንዲይዝ ያደረገው፡፡
በሶማሌ የአብዲ ኢሌን አመጽ ሠራዊታችን ነው ያስታገሰው፡፡ ሶማሊያ ክልልን ለመገንጠል የነበረውን የአብዲ ኢሌ ፕሮጀክት ያከሸፈው ሠራዊታችን ነው። የወላይታና የሲዳማን ግጭት ሠራዊታችን በጥበብ ነው የፈታው፡፡ በሁለቱ ሕዝቦች መካከል ምንም አይነት የጥቅም ግጭት ሳይኖር ሆን ብሎ ኪራይ ሰብሳቢው ኃይል የፈጠረው ግጭት ነበር፡፡ አንድ ሰው ሳይገድል ከክልሉ የጸጥታ ኃይል ጋር ሆኖ ሕዝቡ ወደ መደበኛ ሰላሙ እንዲመለስ ያደረገው ሠራዊቱ ነው። ሠራዊታችን ባይኖር ኖሮ አማራ ክልል ይነድ ፤እርስ በእርስ መጫረስም ይመጣ ይኖር ነበር፡፡ እነዚህን የመሳሰሉ በርካታ አደጋዎችን እየተጋፈጠ እየተከላከለ መስዋእትነት እየከፈለ ሲሰራ ነው አመቱን ሙሉ ያሳለፈው፡፡
ከመደበኛ ግዳጁ ውጭ ይሄን ሁሉ የሚያደርገው የሀገርና የሕዝብን ደሕንነትና ሰላም ለመጠበቅ ሀገሪቷ በውስጥና በውጭ ሴረኞች እንዳትፈርስ ነው። ሕገመንግስቱ ነው የሚያስተሳስረን ብሎ ነው። የመከላከያ ሠራዊታችን በእጅጉ ሊመሰገን ሊወደድ ሊወደስ ሊከበር ይገባዋል፡፡ ይሄንን የሀገር መከላከያ ኃይል የማያመሰግን ካለ የለየለት የሀገር ጠላት ብቻ ነው የሚሆነው፡፡ የኢትዮጵያ ጠላት፡፡
ሕዝባችን ልጁም ስለሆነ ለሠራዊታችን ትልቅ አክብሮት እንዳለው እናውቃለን፡፡ ችግር በተፈጠረበት ቦታ ሁሉ በየቦታው ሠራዊቱ ለምን እኔ ጋር አይመጣም ነው የሚለው፡፡ ሠራዊቱ በተሰማራበት የትም ቦታ ቢሆን ሕዝቡ ከቤቱ ያለውን ምግብ ውሃ እየወሰደ እየሰጠ ቡና እያፈላ መረጃም እያቀበለ በደስታ ነው የሚቀበለው። አማራ፣ ኦሮሚያ፣ ቤኒሻንጉል፣ትግራይ ሶማሌ፣ ደቡብ በሁሉም የሀገሪቱ ክልል ያለው ሕዝብ ለሠራዊቱ ጥልቅ ፍቅር ያለው ነው፡፡
ሕዝቡ በሠራዊቱ እንደሚኮራ ሁሉ እኛም በሕዝባችን በእጅጉ እንኮራለን፡፡ ሕዝቡ ሠራዊቱን በዚህ መልክ ነው የሚያየው፡፡ ሠራዊቱ ወገኑ ወንድሙ የሕዝብ ልጅ እንጂ ጠላት አይደለም፡፡ ሀገሬን ወገኔን ሰላምና መረጋጋቷን እወዳለሁ የሚል ዜጋ ሁሉ ሀገር በሴረኞች እንዳትፈርስ ከተለያዩ አደገኛ ትርምሶችና አደጋዎች ጋር እየተጋፈጠ ሕይወቱን እየከፈለ በየቦታው እየተንከራተተ የጠበቃትን የታደጋትን የሀገር መከላከያ ሠራዊት ሊያከብረው ሊኮራበት ሊመካበት ይገባል። ይሄ ሠራዊት ሊከበር እንጂ ሊሰደብ ሊዘለፍ አይገባውም፡፡ ይሄ ሠራዊት ባይኖር እስከአሁን ምን ሊፈጠር ይችል ነበር ብሎ ማሰብ ተገቢ ነው። ዛሬም ነገም የሀገራችንና የሕዝባችን ጠንካራውና ብርቱው ክንድ ከአደጋና ከማንኛውም ጥቃት የሚከላከለው የመከላከያ ኃይሉ ነው፡፡ በድጋሚ ሊከበር ሊመሰገን ይገባዋል፡፡
አዲስ ዘመን፡- በአዲሱ አመት ለኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊትና ለኢትዮጵያ ሕዝብ የሚያስተላልፉት መልዕክት ካለ?
ጀነራል ብርሃኑ፡- ለኢትዮጵያ ሕዝብና ለመከላከያ ሠራዊታችን እንኳን ለአዲሱ አመት በሰላም አደረሳችሁ ለማለት እወዳለሁ፡፡ የአምናን ከባድ ሀገራዊ ችግር በጋራ አልፈን ወደ አዲስ አመት በመሸጋገራችሁ እንኳን ደስ አላችሁ እላለሁ፡፡ ዘመኑ የሰላም የፍቅር የመግባባት እንዲሆንልን እየተመኘሁ ሁላችንም የሀገራችንን ሰላም፤ መረጋጋት፤ ደህንነት በጋራ ቆመን እንድንጠብቅ አደራ ለማለት እወዳለሁ፡፡
ምርጫም ሆነ ፖለቲካና ፖለቲከኞች የሚኖሩት በመጀመሪያ ሰላሟ የተጠበቀና የተረጋጋች ሀገር ስትኖር ነው፡፡ ሕዝባችን መንቃት ማወቅ መጠንቀቅ አለበት፡፡ ሕዝባችን የራሳቸውን የፖለቲካ ፍላጎት ለማሟላት ሲሉ ሆን ብለው መርዝ የሚረጩ ኃይሎች በሚያስተጋቡት የሀሰት ፕሮፓጋንዳና ወሬ መዋከብ መረበሽ መደናገጥ የለበትም፡፡
ሁለተኛው ነገር በመንግስት መዋቅር ውስጥም ይሁን ከመንግስት መዋቅር ውጭ ባለው ጥገኛ ኃይል መነዳት የለበትም፡፡ በደምብ አርቆ ማስተዋል ማሰብ ከሽማግሌዎች ከኃይማኖት መሪዎች ከምሁራን ጋር መነጋገር መወያየት ያስፈልጋል፡፡ ሕዝቡ ሁከትና ረብሻ የሚያነሱትን እኛ መብታችንን በሕጋዊና በሰላማዊ መንገድ እናገኛለን፡፡ እናንተ ማንንም አትወክሉም፤ እናውቅላችኃለን ልትሉን አይገባም። በጉልበት የምታመጡልን ነገር የለም፡፡ አትችሉም ማለት መቻል አለበት፡፡
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ አመሰ ግናለሁ፡፡
ጀነራል ብርሃኑ፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡
አዲስ ዘመን መስከረም 1 /2012
ወንድወሰን መኮንን