‹‹በመጀመሪያ እንኳን ለ2012 ዓ.ም በሰላምና በጤና አደረሰን ፤አደረሳችሁ። እግዚአብሔር አምላክ ጊዜያትንና ወቅቶችን እያፈራረቀ ዓለምን ይመግባል፤ያስተዳድራል›› ሲሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትሪያሪክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ ምኞታቸውን ገልፀዋል። ፈጣሪ የሚፈልገው በሰላም እንድንኖር፣ እንድንረዳዳ፣ እንድንደጋገፍ፣ እንድንተጋገዝ፣ በአንድነትና በሕብረት እንድንኖር ነው። ያለፈውን 2011ዓ.ም በሰላም አስፈጽሞ ለሚቀጥለው 2012 ዓ.ም በሰላም አድርሶናል ብለዋል።
አዲሱን አመት ልብሳችን ብቻ ሳይሆን ልባችንንም አንጽተን ልንቀበለው ይገባል። አለበለዚያ ትርጉም ሊኖረው አይችልም። አዲስ አመትን ስንቀበል በአዲስ መንፈስ ፣በአዲስ አስተሳሰብ፣ በሰላምና በፍቅር፣ በአንድነት ሕብረ ብሔራዊነታችንንና፣ አንድነታችንን የሰመረና ያማረ አድርገን ነው ሲሉም ተናግረዋል።
‹‹እግዚአብሔር አምላክ ይችን ምድር የሰጠን በሰላምና በፍቅር፣በወንድማማችነት እና በእህትማማችነት እንድንኖርባት ነው። ይህ አለም እኛ ካላወቅንበት ምን አልባትም ብዙ ችግር ሊኖረው ይችላል። እኛ ካላወቅንበት ዘመኑ የሚለዋወጥ እና ሰውን የሚለውጥ ችግሮችን ሁሉ የሚፈጥር ሊሆን ይችላል። እኛ ካሳመርነውና እኛ ከነቃንበት ደግሞ መልካም ምድር ሊሆን ይችላል። ›› ብለዋል አቡነ ማቲያስ።
እግዚአብሔር የባረከው የዘሩበትን የሚያበቅል የተከሉበትን የሚያጸድቅ ዓለም ወይም ሀገር ሊሆን ይችላል። አባቶቻችንንና እናቶቻችን ሰላማዊያን ሆነው ይህችን ሀገር ለእኛ ለአሁኑ ትውልድ አስረክበዋል። እኛ ደግሞ አባቶቻችንና እናቶቻችን ያደረጉትን ሁሉ እያስታወስን ስለሀገር ሰላም ስለሀገር ፍቅር ስለሀገር አንድነት ስለህዝብ አንድነት በጠቅላላ ኢትዮጵያውያን ይህንን ሁሉ በመንፈሳዊ ህይወት እንድንጓዝ አዟል ባይ ናቸው።
‹‹እብለ እክሙ ሑሩ በመንፈስ›› በመንፈሳዊ መንገድ ሂዱ ተጓዙ ስጋዊ ምኞትን ግን አትፈጽሙ ምክንያቱም ሥጋዊ ምኞት የሚያሳስበው ሥጋዊ የሆነ ነገርን ነው። መንፈሳዊ ህይወት ደግሞ መንፈሳዊ ነገርን ያሳስባል ወደ መንፈሳዊ ህይወት እንድንሄድ ያደርገናል። ህሊናችን መንፈሳዊ የሆነውን ነገር ትወዳለች። ስጋችን ደግሞ ግዙፍ እንደመሆኑ መጠን ልዩ ልዩ ሀጥያትን እንድንሰራ ይገፋፋናል። ይህ ስጋዊ ባህሪያችንን ተከታትለን በመንፈሳዊ ህይወት እንድንኖር ነው መጽሀፍት የሚያዙት፣ የሚመክሩትና የሚያስተምሩትም ብለዋል።
እናም መጪው ዓመት የተባረከ የተቀደሰ የሰላም የፍቅር የአንድነት የምህረት የረድኤት የቸርነት ዓመት እንዲሆንልን ሁላችንም አስተሳሰባችንንና ጸሎታችንን አንድ እንዲሆን። የሐይማኖት አባቶች እንደመሆናችን መጠን እኛ ሁልጊዜም ስለሰላም ስለአንድነት ስለፍቅር ስለህብረት ነው ስንለምን የምንኖረው። እና ይህንንም ሁኔታ ሁላችንም እንድንከተለው አሳስባለሁ። ኢትዮጵያዊ የሆንን ሁሉ ለሀገር ለትውልድ ማሰብ ይኖርብናል። ለሰላማችንና ለአንድነታችን አጥብቀን እንድናስብ አሳስባለሁ።
እግዚአብሔር አምላክ አዲሱን ዘመን የተባረከና የተቀደሰ ያድርግልን የስራ፣ የእድገት፣የልማት የጤና፣የፍቅርና የአንድነት ዘመን ያድርግልን ብለዋል።
ከጠቅላይ ሚንስትሩ ጀምሮ ለተሰበሰቡ ባለስልጣናት ዱአ(ጸሎት) ያሥፈልገናል ሲሉ ሙፍቲ ሐጅ ኡመር ኢድሪስ በቤተ መንግስት ተገኝተው መልዕክት አስተላልፈዋል።
‹‹ዛሬ እዚህ የተሰባሰብነው 2011 ዓ.ም አልፎ 2012 ዓ.ም እየተሸጋገርን በመሆኑ ነው።በአልነቱ ምንድን ነው? ጥቅምና ጉዳቱ ምንድን ነው? በአል ማለት ቀኑን ማክበር ማለት አይደለም። ሥራ መፍታት አይደለም። ራስን መገምገሚያ ነው። ባሳለፍነው አመት ምን ሰርተናል፣ ምን መልካም ነገር አሳልፈናል፣ ምንስ መጥፎ ነገር ገጥሞናል፣ ምን ጥቅም ሰርተናል በሚል የምናይበት ነው።
አስተማሪዎች፣ ተማሪዎች፣ ወላጆች፣ ልጆች፣ ሙስሊሞች፣ክርስቲያኖች ሁላችንም በአጠቃላይ ራሳችንን የምንገመግምበት ነው። ምን አሳልፈናል፤ ለሀገራችን ምን ሰርተናል ብለን ልንጠይቅ ይገባል። የሰው ልጅ ቀን ሲሰራ የዋለውን ማታ መገምገም ይገባዋል፤›› ብለዋል።
በእምነት ‹‹ታላቁ ነብይ በሰው ከመገምገማችሁ በፊት ራሳችሁን ገምግሙ›› ብለው መልዕክት አስተላልፈዋል። ሥለዚህ ቀን ሲሰራ የዋለውን ማታ መገምገም አለበት፤ማታ ሲሰራ ያደረውን ጧት መገምገም አለበት። ወራቱ ባለቀ ጊዜ ያሳለፈውን መገምገም ይኖርበታል። አመት ሲሆን ደግሞ በአመቱ ያሳለፈውን መገምገም አለበት። የሚሉት ሐጂ ሙፍቲ ያሳለፈው መጥፎ እንደሆነ መጸጸት፣መመለስ፣ማስተካከል የሚስተካከለውን ማስተካከል አለበት። በማይስተካከለው መጸጸት አለበት። ለሚቀጥለው አመት ደግሞ መጥፎውን መሰረዝ፣ ጥሩውን አጠናክሮ ማስቀጠል፤ ያልተስተካከለውን ማስተካከል፤አመጸኛው ወደ ሰላም መምጣት ፤መጥፎ ሐሳብ ያለው ወደ ጥሩው መምጣት ይኖርበታል። በአል ማለት የምንማርበት እንጂ ሥራ ልንፈታ፣ ልናከብረው፣ቀኑን ልንገዛው አይደለም ባይ ናቸው።
ወደ አንድነትና ወደ ሰላም ስንመጣ በጣም አስገራሚ ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ ዛሬ በአብዛኛው እየተማረ ነው።ሁሉም ያወቀ ነው። ሁሉም አዕምሮ ያለው ነው። ከሐይማኖት አባቶች ጀምሮ እያንዳንዱ፣በአስተዳደር አካባቢ ያለው፣ ሙስሊሙም ክርስቲያኑም፣ ወንዱም ሴቱም፣ ሥለ አንድነት ሊጠየቅ ግድ ነው። አስፈላጊ ነው፤ ጠቃሚ ነው።
ሥለሰላም ብንጠየቅ አንገብጋቢ ነው፤አገራዊ ነው ፤ መንግስታዊ ተግባር ነው፤ሕዝባዊ ተግባር ነው፡ በእውነተኛ ተግባሩ ላይ ምንድን ነው የከለከለን? መሞኛኘቱ ፋይዳ የለውም።ተንኮል ከየት ነው የሚነሳው? ችግር ከየት ነው የሚነሳው? አደጋ ከየት ነው የሚከሰተው? እኛ እንደ እስልምና ሐይማኖት አስተምህሮት ‹‹ሰዎች ካልተስማሙ ፣ሰዎች አንድ ካልሆኑ፣ሕዝብና መንግስት አንድ ካልሆኑ፣ ካልተዛዘን፣ ባልና ሚስት ካልተስማሙ፣ጎረቤትና ጎረቤት ካልተስማሙ፣ሙስሊምና ክርስቲያን ካልተስማሙ የአደጋ ሰዎች ትሆናላችሁ›› ይላል።
ለእናንተ የተወሰነውን ክብር ፣ጤና ስጦታ(አርዛቅ) እቀይረዋለሁ ብሏል። ሰላም እንድታገኙ አደርጋችኋለሁ።በረከት እንዳታገኙ አደርጋችኋለሁ፤ ጸጋችሁን እቀማችኋለሁ፤ በችግር አሰቃያችኋለሁ፤ በበሽታ አሰቃያችኋለሁ ብሏል።
አሁን እየሆነ ያለውን እያንዳንዳችሁ ታውቃላችሁ። የእህል መወደድ፣የእቃ መወደድ እና ማንኛውም ነገር መወደድ ከየት መጣ? ሀገራችን ሰፊ ነው? መሬታችን ለም ነው። እየጨመረ ነው ታዲያ እርዚቁን ምን አሳነሰው? ምን አስወደደው? የእኛ አንድ አለመሆን ነው፤ የኛ ሰላም አለመሆን ነው።ለመሆኑ ችግሩ ምንድን ነው? አንዱ አንዱን ይገድላል።
አንዱ አንዱን ያደማል፤ያፈናቅላል፤መሪዎች ከጠቅላይ ሚንስትር ጀምሮ እስከ ቀበሌ ድረስ አሉ። ፖሊሶች ፣ደህንነቶች አሉ፤ እርስ በእርሳችን አለን፤ ችግር ከየት ነው የሚመጣው? ምን ይጠብቃሉ። ችግር ከየት ነው የተነሳው? ሳንሞኛኝ ለአንድነት መዘጋጀት አለብን በሚመጣው አዲስ አመት። ሳንታለል ለአንድነት መዘጋጀት አለብን። ለሠላም ዝግጁ መሆን አለብን።ሀገራዊ አመለካከትም ሊኖረን ይገባል። ሕዝባዊ አመለካከት ሊኖረን ይገባል። መንግስታዊ አመለካከት ሊኖረን ይገባል።
አላህ የሠውን ልጅ በአጠቃላይ ሲፈጥር ሁሉም በስልጣን ላይ ሊቀመጥ አይደለም። ሁሉም ባለስልጣን ከሆነ ማን ታዛዥ ይሆናል።ሁሉም ሀብታም ከሆነ ማን ደሃ ይሆናል። እኩሉ መሪ፤ እኩሉ ተመሪ ፤እኩሉ ሀብታም እኩሉ ደሃ ልንሆን ነው አላህ የፈጠረን። ለድህነት የተፈጠረው ሰው ካከበርኩ ብሎ ሌላ ችግር የፈጠረ እንደሆነ እንደገና ችግሩ ይከፋል። ለሀብታምነት የተፈጠረ ሰው ከማግኘት በፍጹም የሚቀር አይደለም።
አላህ ለሥልጣን የፈጠረው ሰው ሥልጣን ከማግኘት የሚቀር አይደለም። ፈጣሪ ጌታችን አላህ ያለው ‹‹እኔ በስልጣን ላይ ሳስቀምጥላችሁ አክብሩት፣ውደዱት፣ምከሩት፣እገዙት ነው›› ያለው፤ አውግዙት አላለም። አሁን ከለውጡ ወዲህ ያለው እና የምንሰማው ጉድ ነው። ባለስልጣን ይሠደባል። ሀብታም ይሰደባል፤ምሁር አዋቂ ይሰደባል ይሄ ጉድ ምንድን ነው።ከየት መጣ? ማን አመጣው? እኛው አመጣነው።
የሐይማኖት አባቶች እየተናገሩ እና እየመከሩ ነው።እውነተኛ የሐይማኖት አባት ከሆን፣ አቋማችን የተስተካከለ ከሆን፣በሥልጣንና በጥቅም የማንሞኝ ከሆነ ሕዝብ ይሠማናል።
አሁን እኔ ማስተላለፍ የምፈልገው መልዕክት የመንግስት አካላት ከታች እስከ ላይ ድረስ አገራዊ ልትሆኑ ይገባል።ሕዝባዊ አመለካከት ያለው መሆን አለበት፤ለሀገር የሚያስብ መሆን አለበት፤ለሕዝብ የሚያሥብ መሆን አለበት።
የሐይማኖት አባቶች እውነተኛ የእምነት አባቶች ሊሆኑ ይገባል። አስተማሪዎች ትክክኛ አስተማሪ ሊሆኑ ይገባል። ተማሪዎቻቸው ትክክለኛ እንዲሆኑ። ወላጆች ትክክለኛ ሊሆኑ ይገባል፤ልጆቻቸው ትክክለኛ እንዲሆኑ። ችግር ብንፈጥረው ተመልሶ እኛው ላይ ነው የሚሆነው። ችግር ፈጣሪውም አብሮ ይቸገራል ሲሉ አፅንኦት ሰጥተዋል።
‹‹ሥለዚህ መልዕክቴ እውነተኛ እናስተካክል የሚል ነው፤ሕጋዊ በሆነ ሥልጣን ሕዝቡን በሕግ እንምራ፤ ሌሎቻችን ባለስልጣኖቻችንን እናክብር፤ሀብታሞችን እናክብር፤እርስ በእርሳችን እንከባበር፤ ወላጆችን እናክብር፤ጓደኛ ለጓደኛ እንከባበር፤እንመካከር፤እንተዛዘን፤እንተባበር፤ እንቀራረብ እላለሁ። ዝም ብለን እየተሰባሰብን ከአንገት በላይ ብናወራው ከምላስ ይቀራል እንጂ ከልብ አይደርስም። ከልብ የወጣ ቃል ነው ከልብ የሚደርሰው።ፈጣሪ ለሰላምና ለከይር ሥራ የምንሰባሰብ ያድርገን፤አገራችን አማን ያድርግልን። ሰላሙ ከእናንተው ነው የሚፈልቀው። መዋደዱም ከእኛው ነው የሚገኘው። መተባበሩም ከእኛው ነው የሚገኘው።››
አዲስ ዘመን መስከረም 1 /2012
መሐመድ ሁሴን እና ኢያሱ መሰለ