ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በሀገራችን የተከሰተው አለመረጋጋት የተለያዩ ጉዳቶችን እያደረሰ እንዳለ ይታያል። ዜጎችን ለሞት፣ ለመፈናቀልና ለተለያዩ ችግሮች ዳርጓል። ለዘመናት የቆዩት የአንድነት እሴቶች ተሸርሽረው ሰዎች በጥርጣሬ እንዲተያዩና በመካከላቸው መተማመን እንዲጠፋ አድርጓል። እያደገ በነበረው የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ተጽዕኖ በማሳረፍም የሀገሪቱና የህዝቦቿ ብልጽግና በፍጥነት እንዳይረጋገጥ መሰናክል ፈጥሯል።
መንግሥት በአዲሱ ዓመት ለሀገሪቱ ሰላምና መረጋጋት ልዩ ትኩረት በመስጠት በህዝቦች መካከል ሰላም ፍቅርና አንድነት ጠንክሮ የተጀመረውን ልማት በማስቀጠል ብልጽግናችንን ማረጋገጥ እንዲቻል መልካም ጅምሮችን እያደረገ ይገኛል። ይህን አስመልክቶም ምሁራን የሰጡትን ሀሳብ እንደሚከተለው ለማቅረብ ተሞክሯል።
ሀገራችን የሁላችንም መኖሪያ እንደመሆኗ ስልጣን ላይ ያለው አመራርም ይሁን ተፎካካሪ ፓርቲዎች፤ የተማረውም ይሁን ያልተማረው፤ ወጣቱም ሆነ አዛውንቱ፤ ህዝቡ በአጠቃላይ በባለቤትነት ለአንድነቷ ለክብሯና ለብልጽግናዋ መረባረብ ይኖርበታል ይላሉ የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ገብሬ ይቲንሶ።
እርሳቸው እንደሚሉት ሀገራዊ አንድነት የብሄራዊ መግባባት መገለጫ ነው። ብሄራዊ መግባባት ማለት ደግሞ በአንድ ሀገር ውስጥ የሚኖሩ አብዛኛዎቹ የህብረተሰብ ክፍሎች በዋና ዋና ጉዳች ላይ የጋራ የሆነ ስምምነት ሲኖራቸውና መግባባት ሲፈጥሩ ነው። ይህ ስምምነትና መግባባትም የህዝቦችን ፍላጎትና ጥቅም የሚያስከብር የውስጥ ልዩነቶችን የሚያጠብና መቀራረብን የሚፈጥር በመሆኑ አገራዊ አንድነትን ይበልጥ ያጠናክራል።
ህዝቦች በዋና ዋና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ መግባባት ላይ ካልደረሱ አሁን እንደሚታየው በሚመቻቸው መንገድ ብቻ ሀገሪቱን ወደ ራሳቸው ሃሳብ በመጎተት በመካከላቸው ልዩነቶችን በመፍጠር በሀገሪቱ ሰላምና ደህንነት ላይ ሥጋት በመፍጠር አገራዊ አንድነት ላይ አሉታዊ ተፅእኖ ይፈጥራል።
የተከሰተውን የአገራዊ አንድነት መቀዛቀዝ አሁን ካለንበት ሁኔታ አንጻር ብቻ መመልከት ተገቢ አይደለም የሚሉት ፕሮፌሰር ገብሬ ይቺ ሀገር ምን አይነት ሁኔታዎችን አልፋ ነው የመጣችው? እንዴትስ በተለያዩ ጊዜያት የተለያዩ ችግሮችን እያለፈች መጣች የሚለውን ማስታወስ ካልተቻለ ችግሩን ለመፍታት አዳጋች ነው።
በአሁኑ ወቅት አገራዊ አንድነትን በሚመለከት ሁለት ዋልታ ረገጥ አስተሳሰቦች እንዳሉ የሚናገሩት ምሁሩ አንደኛው ኢትዮጵያዊነትን ብቻውን ወይም ሀገራዊ አንድነትን ነጥለው የሚያራምዱና ሌሎች ደግሞ ህብረ ብሄራዊነትን እንደዚሁ አጥብቀው የሚያራምዱ መሆናቸው ነው።
አገራዊ አንድነትን ስናነሳ እነዚህን ሁለት ሃሳቦች የምርጫ ጉዳይ አድርገን ከሁለቱ አንዱን እንመርጥ ከተባለም ልንሳሳት እንችላለን። ዓምና ስህተት ተፈጽሞ ከሆነ ዘንድሮ መድገም የለብንምና ጉዳዮቹን በአስተውሎት መመልከት እንደሚያሥፈልግ ይመክራሉ።
ሕብረ ብሄራዊነትና አገራዊ አንድነት
በዚህም መሰረት ወደ ኋላ ሄደን የሀገራችንን ታሪክ ስንመለከት ኢትዮጵያ ውስጥ ምናልባትም ከአጼ ቴዎድሮስ ዘመነ መንግስት ጀምሮ እስከ ደርግ መጨረሻ የነበሩት መንግስታዊ ሥርዓቶች በሀገራዊ አንድነት የሚያምኑና ሀገሪቱን አንድ አድርገው ለማስተዳደር የሞከሩ ነበሩ ሲሉ ይዘክራሉ።
ነገር ግን ይህ ሀገራዊ አንድነት ላይ የተሰጠው ልዩ ትኩረት በጊዜ ሂደት ያስቆጣቸው ወገኖች ስለነበሩ የትግል እንቅስቃሴ አድርገው በተለይም የደርግ ሥርዓት ከተወገደ በኋላ የኢህአዴግ መንግስት ወደ ስልጣን መጥቶ ህብረ ብሄራዊ አንድነት በአገሪቱ ላይ እንዲመሰረት ተደርጓል። በዚህም ወቅት ነገሮች የተገላቢጦሽ ሆኑና ሀገራዊ አንድነቱ ትኩረት ተነፍጎት ስለነበር ሀገሪቱ የመበታተን አደጋ ተጋረጠባት።
እንደእርሳቸው አባባል ወደፊት እና ወደ ኋላ የምናይበት ምክንያት ሀገራዊ አንድነት ላይ የተደረገው ትኩረት ወደትግል ወስዶን ህብረ ብሄራዊነት እንደ አማራጭ መምጣቱን እና አሁንም ህብረ ብሄራዊነት ብቻ ትኩረት በማግኘቱ ሌላ ችግር መከሰቱን እንድናስታውስ ነው። ይህም ስለሆነ ህብረ ብሄራዊነትን ያልተቀበለ ሀገራዊ አንድነት ወይም ኢትዮጵያዊነት እንዲሁም ኢትዮጵያን ወይም አንድነትን ያልተቀበለ ህብረ ብሄራዊነት ለዚች ሀገር አይጠቅምም ሲሉ ይሞግታሉ።
በዚህም መሰረት ኢትዮጵያ እንድ አይነትን ሳይሆን አንድነትን መለያየትን ሳይሆን ልዩነቶችን ማክበር እንዳለባትና ሁለቱም እንደሚያስፈልጓት ምሁሩ ይገልጻሉ። ህብረ ብሄራዊነት መሬት ላይ የሚታይ እውነታ ነው የሚሉት ፕሮፌሰር ገብሬ የአማራ ፣ የጉራጌ ፣ የኦሮሞና ሌሎች ብሄረሰቦች የሉም ማለት እንደማይቻልና ለመኖራቸው እውቅና ሰጥቶ የኢትዮጵያን አንድነትን የማጠናከር ሥራ መሠራት እንዳለበት አፅንኦት ሰጥተው መክረዋል።
ሁለቱንም አስተሳሰቦች አቻችሎ መሄድ ለሀገር አንድነት ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር የገለጹት ምሁሩ ብሄር ብሄረሰቦች የሀገሪቱ ባለቤቶች ሲሆኑ ለህልውናቸው መረጋገጥም የሀገር አነድነትና ሰላም ወሳኝ መሆኑን አስረድተዋል። ስለሆነም የሀገር አንድነት ከሌለ የብሄረሰብ ማንነትና መብት አደጋ ውስጥ ሊገባ ይችላል ብለዋል።
እንደ ኢትዮጵያ ባሉና በርካታ ብሄር ብሄረሰቦች ባሉባት ሀገር የብሄረሰቦች መብትና ብዝሀነት ሳይከበር ሀገር እንገነባለን ማለትም ሌላ ችግር ሊያሥከትል እንደሚችል ይገልፃሉ። በአዲሱ ዓመት ህብረተሰቡ እራሱን ለሀገራዊ አንድነትና ብልጽግና እንዲያዘጋጅ እየተደረገ ያለው ጥረትም ከላይ ባለው አስተሳሰብ ቢቃኝ ውጤታማ መሆን እንደሚቻል አስረድተዋል።
አሁን ለአንድነትና መግባባት የተሰጠው ትኩረት በእጅጉ የሚያበረታታ መሆኑን የገለጹት ፕሮፌሰሩ አሁንም አንድነት ላይ ብቻ ትኩረት ሰጥተን በአንድ ጉዳይ ላይ ብቻ መንጠልጠልን ከመረጥን ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ደግሞ ወደ ኋላ የሚመልሰን ነገር እንዳይፈጠር መጠንቀቅ ያስፈልጋል ይላሉ። በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ህዝብ በመደማመጥና በመከባበር አንድነቱን በማጠናከር ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነቱንና የሀገሩን ብልፅግና ማረጋገጥ እንዲገባው አስገንዝበዋል።
በአዲሱ ዓመት ሰው በእውቀት ላይ በመመስረትና ሰከን ብሎ በመነጋገር በሐሳብ ልዕልና አሸንፎ ወይም ተሸንፎ የህዝቦቹን ሰላምና አንድነትንም ሆነ የሀገሩን ደህንነት ማስጠበቅ ሀገራዊ ግዴታው መሆኑን መረዳት ይኖርበታል።
የመንግስት አካላት ውሳኔ፣ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች አቋም፣ የዜጎች በተለይም የወጣቶች ሃሳብ በሙሉ በመነጋገርና እርስ በእርስ በመወያየት ላይ የተመሰረተ መሆን ይኖርበታል። ጉዳዮቹንም ለይቶ ለውይይት ማቅረብ ያስፈልጋል። ለምሳሌ ብሄራዊ አንድነት ላይ ምን ምን ጉዳዮች ይታዩ በፖቲካ፣ በኢኮኖሚና ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ኢትዮጵያ ስታራምድ የነበረው ስትራቴጂ ምን ይመስላል? ከኢትዮጵያ አውድ አንጻር የመንግስት አካሄድ ተገቢነው በሚሉት ላይ መነጋገር ይገባል። ዞሮ ዞሮ ጉዳዮች የሚፈቱት በንግግር እስከሆነ ድረስ አላስስፈላጊ የሀሳብ መከፋፈልና ሌሎች ጉዳዮች ከመከሰታቸው በፊት ቁጭ ብሎ መነጋገር ወደ አገራዊ አንድነት የሚያመጣን የስልጣኔ በር ነው።
ችግሮችን በመነጋገር መፍታት ከተቻለ ህዝቦች አንድነታቸው ይጠነክራል፤ የህዝቦች አንድነትና የሀገር ብልጽግና ደግሞ ተመጋጋቢ ናቸው። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ሀገራዊ አንድነቱ እየተቀዛቀዘ በመምጣቱ ምክንያት በሀገራችን ኢኮኖሚያዊ እድገትና ብልጽግናችን ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል። ምናልባት ዛሬ ላይታየን ይችል ይሆናል እንጂ እያንዳንዷ ያልተጠቀምንባት አንድ ደቂቃ ነገ በሳምንት የሚገመት ዋጋ ልታስከፍለን ትችላለች። እያንዳንዷ ያባከንናት አንድ ሳምት ነገ በወራትና በዓመታት የሚገመት ዋጋ ልታስከፍለን ትችላለች። ይህን ሁሉ ጉዳት የምንረዳው ግን ከእንቅልፋችን ስንነቃና የኑሮ ውድነት ሲገጥመን ሊሆን ይችላል ሲሉም ስጋታቸውን አስቀምጠዋል።
በእኛ ሀገር ባለፉት ሶስትና አራት ዓመታት እዚህ ግባ የሚባል የልማት እንቅስቃሴ እንዳልነበር የሚናገሩት ምሁሩ ኢንቨስትመንትን ጨምሮ የነበሩት ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች በሙሉ በተፈጠረው የሰላም ችግር ምክንያት መቋረጣቸውን አንዳንዶችም በተፅእኖ ውስጥ እንደ ነበሩ ገልጸዋል። ይህም ለሀገራችን ብልጽግና አሉታዊ ክስተት እንደነበር አስታውሰዋል።
የዚህን ኪሳራ ወደ ፊት የምንከፍለው እኛው እንደሆንና ችግሩ ከእኛም አልፎ ለሚቀጥለው ትውልድ ድህነትን እንድናሻግርለት የሚያደርግ ተግባር ነው ብለዋል። ብሄራዊ መግባባት ያለበት አንድነት ልዩነቶችንና ግጭቶችን አስወግዶ ልማትን በማሳደግ ሀገራችን ብልጽግናን እንድትጎናጸፍ የሚያስችል ቀና መንገድ እንደሆነም አስረድተዋል።
መለያየት፣ መበታተንና መጋጨት ልማት ላይ እንዳናተኩር የሚያደርግና ያለንንም ሀብት የተፈናቀሉና የተጎዱ ሰዎችን በመርዳትና በማቋቋም ልናወጣ እንደምንችል ከቅርብ ጊዜ ተሞክሯችን ያየነው እውነታ እንደሆነም አስረድተዋል።
የሀገር አንድነትና ብልጽግና ጉዳይ የሁሉም ዜጎች ጉዳይ እንደመሆኑ በአዲሱ ዓመት በእያንዳንዱ ዜጋ አዕምሮ ውስጥ ኢትዮጵያን እንዴት ልካሳት ምን አስተዋጽኦ አበርክቼ አንድነቷን፣ ሰላሟንና ብልጽግናዋን ላጠናክር የሚሉ አስተሳሰቦች ማበብ ይኖርባቸዋል። እያንዳንዱ ዜጋ እራሱን በዚህ መልክ ከቃኘ ኢትዮጵያን ማሳደግ ይቻላል።
ችግርንም፣ ሰላምንም፣ ልማትንም አጣጥመን የምናውቅ ህዝቦች እንደመሆናችን ማናችንም ብንሆን ችግርና ውድቀትን ስለማንፈልግ ያለፉትን ስህተቶች ላለመድገም 2012 ዓ.ም የፍቅር፣ የአንድነት፣ የሰላም የብልጽግና እንዲሆን የድርሻችንን አስተዋጽኦ ማድረግ እንደሚገባን አሳስበዋል።
በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ተባባሪ ፕሮፌሰር ውሂብእግዜር ፈረደ በበኩላቸው አንድነት በህዝቦች መካከል የጋራ መግባባትና ራዕይ መያዝ እንደሆነ እንዲሁም በሀገረ መንግስት ጉዳይ ብዙ ሰዎች የሚኖራቸው የጋራ አስተሳሰብ መሆኑን ይገልጻሉ።
አገራዊ አንድነት ልዩነትን መሰረት ያደረገ ነውም ይላሉ ሰዎች በሃይማኖት ሊለያዩ ይችላሉ። ይህን ልዩነት ቀይሮ አንድ መሆን አይቻልም ስለዚህ ልዩነቱ ለዘልዓለም የሚኖር የተፈጥሮ ጸጋ ነው። ህዝቦችን አንድ አድርጎ የሚገምዳቸው ራዕያቸውና መድረሻቸው ነው። ስለዚህ የጋራ ራዕይ የያዘ ህዝብ አንድ ህዝብ ሊሆን ይችላል ይላሉ። በዚህ እሳቤ የኢትዮጵያ ህዝቦች አንድነታቸውን በማጎልበት ሀገሪቱ ላይ የተጋረጠውን የመከፋፈል አደጋ መታደግ እንደሚችሉም ይመክራሉ።
አገራዊ ብልፅግና
የአንድን ሀገር ብልጽግና ከሚያረጋግጡት ዋና ጉዳዮች ውስጥ የህዝቦች አንድነት ግንባር ቀደም ሚና እንዳለው የተናገሩት ምሁሩ ህዝቦች ሲተባበሩ ከፍርሀትና ከፍላጎት ባርነት ነጻ በመውጣት ብልጽግናን ሊያረጋግጡ እንደሚችሉ አስረድተዋል።
ብልጽግና ከፍላጎት ባርነት ነጻ መውጣት ነው ሲባልም ለምሳሌ ሰዎች የምግብ ፍላጎታቸውንና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በሀገር ደረጃ ይንቀሳቀሳሉ። ያላቸውን የእርሻ አቅም ፣ የሰው ሃይል ፣የቴክኖሎጂ አቅምና ገንዘብ በማንቀሳቀስ አንዱ ከአንዱ ጋር ተመጋጋቢና ተደጋጋፊ ስራዎችን በመሥራት ውጤታማ መሆን ይችላል። በዚህ ሂደትም በተለያየ ቦታ ያሉትን ሀብቶችና ጸጋዎች ማንቀሳቀስ ይቻላል።
ለምሳሌ አፋር ያለው ጨው ሶማሊያ ላይ አገልግሎት እንዲሰጥ ፣ ሶማሊያ ላይ ያለው አንድ ምርት አፋር ላይ ጥቅም እንዲሰጥ ሲደረግና ልክ እንደዚህ በሀገሪቱ ያሉ ምርቶች ሲለወዋወጡና ሰዎችም ሲተባበሩ ብልጽግና ይመጣል። አንዱ ሌላውን የማይበድል ሲሆን፣ ፍትህ፣ አኩልነት ነጻነትና ዴሞክራሲ ሲረጋገጡና ሰው ከፍርሀት ነጻ ሲወጣ ሀገር ይበለጽጋል።
‹‹በአሁኑ ወቅት የችግሮቻችን ምንጮች እኛው እራሳችን ነን›› የሚሉት ተባባሪ ፕሮፌሰሩ መንግስት ማህበራዊ መስተጋብሩን ሰላማዊና ህዝብ የሚተማመንበት ማድረግ ከቻለና አቃፊ የሆነ የፖለቲካ ሥርዓት መገንባት ከቻለ ወደ ብልጽግና የሚደረገው ጉዞ የተሳካ እንደሚሆን ያስረዳሉ። አሳሪ የሚባሉ ባህሎችንና ወጎችንም የሚሰብሩ ፋና ወጊ ምሁራንም ከመሀል ፈንቅለው በመውጣት ሀገሪቱን ሊያሻግሩ ይችላሉ ብለዋል። ካረጀና ከወደቀ አስተሳሰብ ነጻ ወጥቶ ተራማጅ ማሕበረሰብ የሚፈጠረውና ሀገሪቱ ወደ ብልጽግና ጎዳና እንድትሄድ የሚያደርጋት የጋራ ራዕይ ያለው አንድ ህዝብ ሲፈጠር ነው።
የጋራ ራዕይ ያለው ህዝብ ከየት ተነስተን ወደየት እየሄድን ነው ምን ዓይነት የዴሞክራሲ ሥርዓት እየተከተልን ነው ኢትዮጵያ የምትለማው? እንዴት ነው እድገታችን ብልጽግናችን? እንዴት ከራሳችን ጸጋ መመንጨት ይችላል። የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታችን ካለፍንባቸው ተሞክሯችን እንዴት ሊቀዳ ይችላል የሚለውን ሁሉ የሚቀምር ይሆናል።
በአዲስ ዓመት የኢትዮጵያ አንድነትና ብልጽግና ይረጋገጣል የሚል መፈክር ከማሰማት በፊት መንግስት መሬት ላይ የሚወርዱ ተጨባጭ አሰራሮችን መዘርጋትና ለህዝቡም ማስተዋወቅ ይኖርበታል ይላሉ ተባባሪ ፕሮፌሰሩ። መጀመሪያ ሀገሪቱን እንደ ጅማት ሰፍተው የያዙ እሴቶችና ማህበራዊ መስተጋብሮች እንዳይፈራርሱ መጠንቀቅ ያሥፈልጋል። እንደ እርሳቸው አባባል ይህ ካልሆነ ግን አጠቃላይ የሀገሪቱን ሁኔታ የሚፈታተንና የሚያናውጥ አንድነት የሚባለውን አብይ ጉዳይ የባሰ ስጋት ላይ የሚጥል ክስተት ይፈጠራል። ከማንነት ፖለቲካ ወደ ሃይማታዊ ፖለቲካ እየተገባ መመጣቱም አንድነታችን ምን ያህል አደጋ ላይ እንዳለ ማሳያ ነው ብለዋል።
ቀደምሲል በሀገሪቱ ላዕላይ መዋቅር እየታየ የነበረው ፖለቲካዊ ችግር አሁን ላይ ማህበራዊ ችግር ሆኖ ህዝቦች አንድነታቸውን አጠናክረው ብልጽግናቸውን እንዳያረጋግጡ እንቅፋት መሆኑን ይገልጻሉ። እንደእርሳቸው አባባል መጪውን ዘመን የይቅርታ የፍቅርና የሰላም እንዲሆን ከመመኘት በዘለለ ለምንድነው ወደ ግጭት የሄድነው? ለምንድነው እስከመገዳደል የደረስነው? የሚለውንም መፈተሽ ጠቃሚ ነው።
የፖለቲካ ሥርዓቱ በሚፈለገው መንገድ ሲገነባ ህዝቡ በራሱ ጊዜ ሊስማማ ይችላል። ሥርዓቱ ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ ሲሆን ሰዎች በልቦናቸው ያለውን ቂም ይተዉታል። ሥርዓቱ እራሱ ሲስተካከል አስታራቂ ይሆናል ፤ ሥርዓቱ ፍታዊ ሲሆን ውስጣዊ እርካታ ስለሚሰጥ ሰዎች ኑ ታረቁ ሳይባሉ በሃሳብ መቀራረባቸው ብቻ ያስታርቃቸዋል ይላሉ ተባባሪ ፕሮፌሰር ውሂብእግዜር ፈረደ።
መምህር ባምላኩ ማናየ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በድህረ ምረቃ መርሀ ግብር የሁለተኛ ዓመት የጂኦግራፊ ተማሪ ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት በአዲሱ ዓመት አንድነትና ብልጽግና በሀገሪቱ እንዲሰፍን ህብረተሰቡ መጀመሪያ የሚቀርቡለትን የሰላም ጥሪዎች ከልብ በመቀበል የራሱንም ሆነ የሌሎችን በሰላም የመኖር ህልውና ማረጋገጥ እንዳለበት ይመክራሉ። መንግስት ከምንም ነገር በላይ የላላውን የህዝቦች አንድነት ወደ ነበረበት ለመመለስ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንዳለበት የሚናገሩት አቶ ባምላኩ አሁን እያደረገ ያለው እንቅስቃሴም የሚበረታታ ነው ብለዋል።
በመጀመሪያ በመንግስት ፣ በተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎችም ሆነ በህብተሰቡ መካከል ተቀራራቢ ሀገራዊ እይታ ሊኖር ይገባል የሚሉት መምህሩ ብዙ ህዝብን በሚመሩ የየክልልና የፌዴራል ባለስልጣናት መካከልም ሰላማዊ ግንኙነት ተፈጥሮ የህዝቦችን ማህበራዊ ትስስር በማጎልበትና የጋራ ተጠቃሚነታቸውን በማረጋገጥ የተጀመረውን ሀገራዊ እድገት ማጠናከር እንደሚቻልም ይመክራሉ።
ከአፍሪካ ሀገራት በቀዳሚነት የተሻለ ኢኮኖሚያዊ እድገት ሲያስመዘግቡ ከነበሩት ሀገራት ውስጥ ኢትዮጵያ አንዷ እንደነበረች በመግለጽም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የህዝቦች ሰላማዊ ግንኙነትና አንድነት በመታወኩ በሀገሪቱም ሆነ በህዝቦቿ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ላይ ስጋት መፈጠሩን አስታውሰዋል። ሌላው ቀርቶ በክልሎች መካከል የነበረውም የገበያ ትስስር ሳይቀር እንደተገታ በመጥቀስ በዚህ ሂደት የሀገርን ብልጽግና ማምጣት እንደማይቻል ተናግረዋል። ሃሳብ የብዙ ጉዳዮች መፈጠሪያ ነው ያሉት መምህር ባምላኩ ሰዎች ቅን ሃሳቦችን በማመንጨት በርካታ ማህበራዊና ሀገራዊ ጥቅሞቻቸውን ማስከበር እንደሚችሉም ጠቅሰዋል።
በአንድ ሀገር ላይ ፖለቲካን መነሻ ያደረገ ማህበራዊ ቀውስ ሲፈጠር ኢኮኖሚያዊ ቀውስን ማስከተሉ አዲስ ነገር አይደለም ያሉት መምህሩ ዛሬ በሀገራችን እየከፋ ለመጣው የኑሮ ውድነትም አንዱ ምክንያት የሰላም እና የአንድነት አለመኖር የወለደው የገበያ አሻጥርና ሥርዓተ አልበኝነት ነው። በርካታ ቁጥር ያለው ስራአጥ ባለባት በዚች ሀገር የተለያዩ የሥራ እድሎችን መፍጠር ሲገባን የተፈጠረውንም የምንዘጋ ከሆነ ሀገራዊ ብልጽግናን ማምጣት ይቅርና የዕለት ገቢን ማግኘት እንደሚያዳግት ይናገራሉ።
ሀገር የብዙዎች እስከሆነች ድረስ በጋራ አስተሳሰብ ላይ የተመሰረተ አቅጣጫን መከተል ግድ ይላል። ህብረተሰቡ ተሰሚነት አለን በሚሉ አካላት በሚዘወረው የፖለቲካ መንገድ ለመጓዝ ከመሞከሩ በፊት የመንገዱን ቀናነት መመልከትና ነገሮችን መመዘን እንደሚያስፈልገውም መምህሩ ይመክራሉ።
የሀገር ብልጽግናን ለማረጋገጥ አስተማማኝ ሰላም ያስፈልጋል፣ አስተማማኝ ሰላምን ለማምጣት ደግሞ ህዝቦች የጋራ መግባባት ላይ ደርሰው የተጠናከረ አንድነት ሊኖራቸው ይገባል። ይህ ሲሆን ሰዎች ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሰው የመሥራት ዕድል ያገኛሉ ፤ ግጭትና መፈናቀል ይወገድና ልማት ይስፋፋል ፤ የሰው ልጆች ተስፋ ይለመልማል፤ ኢኮኖሚ ያድጋል፤ ሀገርም ይበለጽጋል ይላሉ።
ኢትዮጵያውያን በደም ፣ በቋንቋና በባሕል የተሳሰርን ከመሆናችንም ባሻገር እንድነታችንን የበለጠ ለማጠናከር እንደ የጡት ልጅ ፣ አበልጅ፣ ጉዲፈቻ የመሳሰሉ ጠንካራ ማህበራዊ መስተጋብሮች ያሉን መሆኑን መምህር ባምላኩ ይገልጻሉ። በእነዚህ ማህበራዊ ተራክቦዎቻቸው ፍቅራቸውን ሲያጎለበቱ የኖሩ ህዝቦች እንደመሆናቸው ዛሬም ወደ አንድነታቸው ለመምጣት አያስቸግራቸውም ይላሉ።
ሰዎች ዛሬን በሰላም ኖረው ነገን ለትውልድ ማስተላለፍ የሚችሉት በመካከላቸው ያሉ አለመግባባቶችን በመነጋገር መፍታት ሲችሉና በአንድ ላይ ለሚያኖሯቸው እሴቶቻቸውም ዋጋ ሲሰጡ ነው። ይህ ሲሆን ደግሞ ተ ደምረናል ማለት ነው።
እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የሀገሪቱን አንድነት ከሚጎዱ ድርጊቶች ተቆጥቦ በተባበረ ክንዱ ለመበልጸግ መትጋት እንደሚገባው ያላቸውን አስተያየት ሰጥተዋል። ያለፉትን ጥፋቶች በመርሳትም መጪውን አዲስ ዘመን በአዲስ አስተሳሰብ እና በመደመር መቀበል እንደሚያስፈልግ መክረዋል። ይህ ሲሆን ለሁሉም ነገር ቀና ይሆናል፤ ለአንድነቱም ለብልፅግናውም።
በአጠቃላይ እንደ ምሁራኑ አስተያየት መንግስት የያዛቸውን የልማት አጀንዳዎች ከዳር ለማድረስ መጀመሪያ በመደመር ፍልስፍና ህዝቦችን ማቀራረብና አንድ የጋራ መግባባት ላይ የተመሰረተ ሀገራዊ ራዕይ እንዲኖራቸው ማድረግ ይኖርበታል። ህዝብ ለአንድ ዓላማ በጋራ ሲቆም ውጤታማ ስራ መስራት ይቻላል። እንደተባለውም አንድነት ይጠነክራል ፤ ሀገርም ይበለጽጋል። አሁን በሀገሪቱ ያለውን የተለያየ አስተሳሰብ ወደ አንድ ለማምጣትም ሰዎች ሁሉ ይቅርባይና ቅን ልብ በመያዝ ቁጭ ብለው መነጋገር ይገባቸዋል። ይህ ሲሆን አዲሱ ዓመት ወደፊት የሚያራምዱ አዳዲስ አስተሳሰቦችን በመያዝ ከችግሮቻችን የምንላቀቅበት እና የምንበለፅግበት ይሆናል።
አዲስ ዘመን መስከረም 1 /2012
ኢያሱ መሰለ