ብሄራዊ እርቅ ሰፊ ፅንሰ ሀሳብ የያዘ ነው። በአንድ ሀገር ወይም ህዝብ ውስጥ የቆዩ አሉታዊ አሊያም የከረሙ ቁስሎች ዙሪያ ያለ አለመግባባት የሚመሰረት ነው። ይህ ህዝብ ወይም ማህበረሰብን እየከፋፈለ በሂደትም ወደ መጥፎ ደረጃ በማድረስ ችግሩ አመርቅዞ ለሌላ ችግር ዋና መንስኤ እየሆነ በአጠቃላይ ማህበረሰባዊ መዋቅርን እያበላሸ የሚሄድን ችግር የመፍቻ መንገድ ነው፤ እርቅ።
በአንድ አገር ታሪካዊና ፖለቲካዊ ሁኔታዎች ይኖራሉ፤ እነዚህ በማህበረሰቡ ችግር የሆኑ ጉዳዮች ዛሬያችንን አሊያም ነጋችንን እያበላሹ እንዳይሄዱ እንደ አገር ወይም እንደ ህዝብ ጉዳዮቹን የመፍታት ሂደት በእርቅ፣ በወንድማማችነት፣ በመቻቻልና በፍቅር አንድ የነበረን አስቸጋሪ ምዕራፍ ዘግቶ አዲስ ሌላ ምዕራፍ ስለመክፈት እና አዲስ አገር ስለመውለድ የሚሰብክ ትልቅ ጉዳይ ነው። በዚህም በአገሪቱ አዲስ የፖለቲካ አስተሳሰብ ስለመጀመር ነው ብሄራዊ እርቅ የሚሰብከው፡፡
ምንነት?
ብሔራዊ መግባባት የተለያዩ ወገኖች በአንድ ወይም በተለያዩ ፅንሰ ሃሳቦች፣ ፖሊሲዎችና እምነቶችን በመያዝ ለአገር ወይም ለህዝብ ይጠቅማሉ ብለው የሚሞግቱበት ነው።ሌሎች ደግሞ እንዲሁ ለአገር እና ለህዝብ ይጠቅማል በማለት የተለየ ሃሳብ በመያዝ ይቀርባሉ። እነዚህ ያለ ውይይት እና ያለመቀራረብ ሳቢያ በመካከላቸው ያለው ክፍተት /Gap/ ከሰፋ ወደ ሌላ ችግር ይወስዳል። ይልቁኑ በአዲሱ ዓመት አንድ አገር ፤ አንድ የጋራ ተስፋ አለን በሚል የምንሰራው እና የምናስበው ስለ አንድ አገር በመሆኑ የተፈጠረው ነገር ከውይይት የጎደለ በመሆኑ በእነዚህ ልዩነቶች ዙሪያ ተግባብተንና ተቀራርበን መፍትሔ እናስይዛቸው የሚል ሃሳብ ያዘለ ነው።
በዚህም የተለያዩ ሃሳቦች ወደ አላስፈላጊ እሰጥ አገባ ውስጥ ከሚያስገቡን በሰከነ ውይይት ወደ አንድ ለመምጣት የሚያሥችል ተመራጭ ዘዴ ነው። በመሆኑም ከውዝግቡና ጭቅጭቁ ይልቅ ወደ ስራ የሚያስገባንን መንገድ የመምረጥ ጉዳይ ይሆናል ማለት ነው ፤ብሔራዊ መግባባት፡፡
እዚሀ ላይ ግን ከእርቅ በፊት መቅደም የሚገባው ብሔራዊ መግባባት ነው ወይስ እርቅ? የሚለው አከራካሪ ቢሆንም ብሔራዊ መግባባቱ ይቅደም የሚለው ሚዛን የደፋ ዓለም አቀፍ ምክረ ሀሳብ ነው። አንድ አገር ወይም ህዝብ የሚፈጠርበት መንገድ ብዙ ነው። አብዛኛው የዓለም አገር የተፈጠረው በሀይል ወይም በጉልበት እንደሆነ ሰነዶች ይዘክራሉ። ነገር ግን አስቦ፤ ዲዛይን አድርጎ አገር የፈጠረ አለ የሚባሉት የአሜሪካኖች አገር አፈጣጠር ነው።ይህም ቢሆን ብዙ ክርክሮችን ያስተናገደ ጉዳይ ነው።
በምንም መንገድ ይሁን አገር አንድ ጊዜ ከተፈጠረች በኋላ ዜጎች አገራቸውን እንደገና በሚበጃቸው ሁኔታ ማስተካከል (Reform) ማድረግ ይችላሉ። ነገር ግን በመጀመሪያም አገር ሲፈጠር አብሮ ለመኖር የሚያስችል መግባባት ወይም ስምምነት (Social contruct) ተፈፅሟል ማለት ነው።
የሰለጠነ አገር እንዲኖር ደግሞ ዜጎች የበለጠ መግባባት ላይ መድረስ ይኖርባቸዋል።እንደ አገር ብሔራዊ መግባባት ሊደረግባቸው የሚገቡት ውስንና መሰረታዊ ጉዳዮች ናቸው።ለአገር አንድነት መግባባት ይገባል። ‹‹አንድ አገር ነን፤ አንድ ዜጋ ነን›› ብሎ ማመን ነው የሚፈለገው።ከዚያ ጋር ተየያዥ የሆኑና በጋራ የሚያኖሩን መርሆች መግባባት ላይ ልንደርስባቸው የሚገቡ ናቸው፤ በተለይ በ2012 ዓ.ም።እነዚህም የህግ በላይነት፣ ዴሞክሲና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ናቸው።
በእነዚህ አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ መለያየት አይቻልም።በእነዚህ ላይ መለያየት ካለ አገር አገር ሆና መቀጠልዋ አጠራጣሪ ነው። ነገር ግን ልዩነቱ እነዚህ ጉዳዮች እንዴት ይፈፀሙ በሚለው ላይ ከሆነ የአካሄድ ልዩነት ሊኖር ይችላል፤ ይህ ደግሞ ተጠባቂና አስፈላጊም ነው። እነዚህ ጉዳዮች በመሰረታዊነት የዜጎችን በህይወት የመኖር፣ ክብር ፣ ነፃነት፣ ደስታን የማግኘት መብት፣ ንብረት የማፍራት መብት እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን ሁል ጊዜ መግባባት የሚያስፈልጋቸው እንደሆኑ እንደ አገር ልንግባባ ይገባል፡፡
እርቅ ሳይኖር መግባባት?
በመጀመሪያ ከእርቅ በፊት ፀብ ወይም የተጋጩ ሀሳቦች/ነገሮች አሉ ማለት ነው።አንድ ማህበረሰብ በሚያልፍበት መንገድ ውስጥ አንደኛው እርከን የግጭት እርከን ነው።በዚህ ብዙ ህይወትና ንብረት ይጠፋል። ማህበረሰቡ ይህን እርከን ጨርሶ ወደ መንቃት (Awakening) ሲመጣ ያ የግጭት እርከን ስህተት እንደነበር ይገነዘባል ማለት ነው። በመሆኑም አንድ ማህበረሰብ እርቅ ደረጃ ላይ ሲደርስ ከአንድ ደረጃ ወደ ሌላ ደረጃ ተሻግሯል ማለት ነው። እዚህ ደረጃ ላይ መድረስ በራሱ ትልቅ ነገር ነገር ነው።
‹‹ከዚህ በፊት የሰራሁት ነገር ግለሰቦችን፣ ብሄርን፣ በጥቅሉ አገርን አስቀይሟል ፤ በድዬም ነበር፤ ስህተት ነው፤ በአገራችን የተፈጠሩት ነገሮች በተለይ ብሄርን ከብሄር፤ ግለሰሰብን ከግለሰብ ማህበረሰብን ከማህበረሰብ አጋጭቷል›› በሚል ተፀፅተን ነገን ለመስራት ደግሞ የተሰራውን ክፉ ስራ አምኖ ለመቀበል ድፍረት ይጠይቃል።ስለዚህ ማህበረሰቡ ይህም ፈተና ሲሻገረው ወደ እርቅ ይገባል ማለት ነው፡፡
ስለዚህ እርቅ ታሪካችን ውስጥ እነዚያ የማንፈልጋቸው ቁስሎች ሁሉ ተለውጠው እንደ አዲስ ለመጀመር ነው። መግባባት ሲባል ደግሞ አዲስ የምንገነባው አገር አንዱ ሌላውን ተጭኖ የሚጓዝበት ሳይሆን ወይም እርቅ እንድንፈፅም ላደረጉን ሁሉ መግባባት ላይ መድረስ አለብን። በመሰረቱ አብረን በጋራ የማንስማማባቸው ጉዳዮች ካሉ ችግር ነው፡፡
በመሆኑም በመሰረታዊ ጉዳዮች ላይ አገራዊ መግባባት ላይ መድረስ ግድ ነው።ለድርድር የሚቀርብ ደግሞ አይሆንም። በእነዚህ ጉዳዮች ላይ መግባባት ሲቻል እርቁም የተሳካና እውን ይሆናል። ለእነዚህ ሁለቱ ግን፤ መግባባት እና እርቅ ከስሜት እና ጥርጣሬ ወጥተን ወደ እውቀትና መብሰል መድረስ አለብን። በመሆኑም ለፍትህ እና ለነፃነት እጅ መስጠት ይገባል።በአገራዊ ጉዳዮች ላይ ተግባብተን እርቅ ደረጃ ላይ መድረስ የአንድ ማህበረሰብም ሆነ ግለሰብ የደረሰበትን የእድገት ደረጃ ያመላክታል። ለዚህም ነው እርቅ በቃል ቀላል ሆኖ በተግባር የሚከብደው፡፡
ብሄራዊ መግባባትና ብሄራዊ እርቅ ወቅታዊና ለአገር አንገብጋቢ ጉዳዮች ወይም አጀንዳዎች ናቸው። በፅንሰ ሀሳብ ደረጃ ስንመለከታቸው የተለያዩ ጉዳዮች ናቸው የሚል እምነት ያላቸው ፀሀፍትም አሉ። ብሔራዊ መግባባት በአንድ ሉዓላዊ አገር ውስጥ የሚኖሩ ህዝቦች በሁሉም ጉዳይ ላይ ላይግባቡ ይችላሉ። ነገር ግን መሰረታዊ በሚባሉ አገራዊ ጉዳዮች መግባባት የሚጠይቁ ነገሮች አሉ ብሎ መውሰድ ይገባል። ነገር ግን የትኛው ጉዳይ ይቀድማል? መግባባቱ ወይስ እርቁ የሚለው ሀሳብ ልዩነት ሊፈጥር ይችላል።
ስለ እርቅ ስናስብ በመጀመሪያ ‹‹በአገር ደረጃ መግባባት የለም›› የሚል መነሻ መኖር የለበትም። በአገር ደረጃ መግባባት አለ፤ እንደ አገር ግን በቂ መግባባት ባለመኖሩ ነው ችግሩ የሰፋው የሚለው አብዛኞቹን ጸሀፍት ያስማማ ጉዳይ ነው። በመሆኑም እንደ ኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ምን ያህል መግባባት አለ የሚለው ጉዳይ እንጂ ‹‹መግባባት የለም›› የሚል መነሻ የለም፤ መኖርም የለበትም። ምክንያቱም 100 ሚሊዮን ህዝብ ኢትዮጵያን ያቆያት በመግባባት ነው። ችግሩ መግባባቱ እየተሸረሸረ በመምጣቱ ጠንካራ አገራዊ አንድነት ለመፍጠር ደግሞ አብዛኞቻችን ልዩነታችንን በማጥበብ ብሔራዊ መግባባት መፍጠር አለብን ነው ቁልፉ ጉዳይ።
ስለዚህ መግባባት እንደ አገር አለ።የትም አገር ግን 100 ፐርሰንት መግባባት የሚባል ነገር አለመኖሩንም ልብ ማለት ይገባል።ለአገር የሚበቃን ያህል ብሔራዊ መግባባት ለእድገትና ከድህነት ለመውጣት የሚያስፈልግና ሁሉንም ዜጎች ደስተኛ ማድረግ በሚችል መልኩ ያስፈልጋል። ስለዚህ የመግባባት እጥረት እንጂ መግባባት ጭራሽ የለም የሚል መነሻ የለም፤ ምክንያቱም መግባባት እንደ አገር የለም የሚለው አስተሳሰብ የተሳሳተ ነው። ብሔራዊ መግባባት ለኢትዮጵያ አዲስ የሚጀመር ፕሮጀክት አይደለም፡፡
ኢትዮጵያ አገር ሆና መኖር ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን መግባባት አለ። በጋራ መኖር ላይ እንደ አገር ተግባብተናል።የህግ የበላይነት ላይ በቂ መግባባት አለን ወይ? አልተግባባንም ይቀረናል። ዴሞክራሲ ላይ በተመሳሳይ በቂ መግባባት ላይ አልደረስንም፤ ይቀረናል። በጥቅሉ መግባባት አለ፤ ነገር ግን በወሳኝ አገራዊ ጉዳዮች ላይ በቂ መግባባት የለም የሚለው መግባባት ላይ መድረስ ይኖርብናል፡፡
እርቅ ለምን ያስፈልገናል?
ብሔራዊ እርቅ ያስፈልጋል አያስፈልግም የሚለው ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት አከራካሪ አጀንዳ ሆኖ ዘልቋል።አስፈላጊነቱ ላይ የተለያዩ አስተሳሰቦች አሉ።በፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ሊህቃን እና ምሁራን ዘንድ የተለያየ አስተሳሰብ አለ።አንዳንድ ወገኖች እንደሚሉት እርቅ የማህበረሰቡ እሴት ነው፤ ስለዚህ ብሔራዊ እርቅ ያስፈልገናል ይላሉ። ሌሎች ወገኖች ደግሞ ብሔራዊ እርቅ አያስፈልግም፤ ምክንያቱም ከህግና ፍትህ ጋር ይቃረናል፤ ተቃርኖ አለው፤ የሚል አመክንዮ አላቸው፡፡
ሌሎች ፀሀፍቶች ደግሞ የሚለግሱት ሀሳብ አለ፤ ‹‹ብሔራዊ እርቅ አያስፈልግም፤ ይሄ ነገር ሞኝነት ነው›› የሚል። ይልቅ በሃይማኖት ውስጥ ያለ አንድ እሴት ነው ሲሉ ሌሎች ደግሞ ‹‹በስልጣን ላይ ያለን አካል እድሜው እንዲራዘም በቆረጣ የሚኬድ አካሄድ ነው›› የሚል የተለያዩ ትርክቶች/ አስተያየቶች አሉ።የሆኖ ሆኖ ግን ዓለም አቀፍ ተሞክሮ እንደሚያስረዳን፤ በተለይ የደቡብ አፍሪካ እና ኡጋንዳ ያለውን ተሞክሮ ስናስታውስ እርቅ ለአንድ አገር ወሳኝ ነው።ህግና ፍትህ በዳይና ተበዳይን እኩል አያስደስትም።እርቅ ግን ዘላቂ ብቻ ሳይሆን ሁለቱንም ወገኖች (በዳይና ተበዳይን) ከልብ አስማምቶ በመመለስ ረገድ የሚታወቅና የሚመረጥ ነው፡፡
በመሆኑም አገራችን አሁን ካለችበት ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር እርቅ የሚያስፈልጉበት ሁኔታዎች ብዙ ናቸው።ከለውጡ በፊት የነበረው ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ነባራዊ ሁኔታ የህዝቡን ፍላጎትና ጥያቄ የሚመልስ አልነበረም።በሌላ በኩል ደግሞ ከዓለም አቀፍ ተጨባጭ ሁኔታው ጋር አብሮ የሚሄድ አይደለም።የቀድሞው መዋቅር ረግጦ ተቀምጧል። ህዝቡም አልተመቸውም፤ ንትርክ ተፈጥሯል ግጭትም እንዲሁ።ይህ ሁሉ ደግሞ አዲስ ምዕራፍ ላይ አድርሶናል።ይህ አሁን ያለንበት እድል ደግሞ በራሱ ብሔራዊ እርቅ እንዲከናወን ብዙ ገፊ ምክንያቶች አሉን፡፡
አስፈላጊ ነው አያስፈልግም የሚለው ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በተለያዩ ጎራዎች ተከፍለው ሲከራከሩና ሲሟገቱ ዛሬ ላይ ተደርሷል። አያስፈልግም ሲል፤ ይህን አቋም በማራመድ ሲሞግት የነበረው ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ ራሱ ነበር። በሌላ ወገን ደግሞ የተለያዩ የፖለቲካ ምሁራን እና ልሂቃን ጭምር ብሔራዊ እርቅ ያስፈልጋል፤ አገራችን ከገባችበት አዘቅጥ ውስጥ ለመውጣት ግድ ነው ሲሉ ሞግተዋል።
ጠቅለል አድርገን ስናየው ግን እርቅ በየትኛውም ብሔር ብሄረሰብ እንዲሁም ሃይማኖቶች ውስጥ ያለ እና የቆየ እሴት ነው። ይህ የማህበረሰቡ ነፀብራቅ ነው። እርቅ መንስኤው ምንም ይሁን ምን የጠብ ግድግዳዎች ተገንብተዋል፤ በፖለቲካ አስተሳሰብ ምክንያት፤ በቋንቋ ምክንያት፤ በዘር ምክንያት የተገነቡ የጠብ ግድግዳዎች አሉ። እነዚህን ለማስተካከል እርቅ ግድ አስፈላጊ ይሆናል። ብሔራዊ እርቅ ሲተገበር ደግሞ እነዚህን አጥሮች ያፈርሳሉ። ለዚህ ደግሞ የተዘጋጀ ልብ ሊኖረን ግድ ነው። የእርቅ አስፈላጊነት ላይ ስናነሳ መንስኤው ምንም ይሁን ምን በተለያዩ ምክንያቶች የተፈጠሩ ግንቦችን ለማፍረስ የራሱ ትልቅ ፋይዳ አለው።
በአሁኑ ወቅት ለአገራችን የእርቅ አስፈላጊነት አከራካሪ አይደለም።ደፋር የሚያከናውነው ተግባር እንጂ ለክርክር አይቀርብም። ከዚህ በፊት በተለያዩ ወቅቶች ብሔራዊ እርቅ ያስፈልጋል የሚል ጥያቄ ሲነሳ ቆይቷል። ‹‹የተጣላ ባልና ሚስት የለም፤ ሂዱና አስታርቁ›› እየተባለ ብዙ ሲሳለቅበት የኖረ ጉዳይ ነው። ይህ ደግሞ አገር ከሚመሩ ሰዎች ሳይቀር ሲገለፅ የቆየ በመሆኑ ጉዳዩን አስገራሚ ያደርገዋል።ዛሬ ያ ሁሉ ተለውጦ ብሔራዊ እርቅ ያስፈልጋል መባሉ በራሱ ትልቅ አገራዊ እመርታ ነው፡፡
በአሁኑ ወቅት ለአገራችን ብሔራዊ እርቅ የሚያስፈልግበት ጉዳይም ሆነ ሁኔታ በጥንቃቄ የሚገለፅ መሆን አለበት። ሕዝብ ከህዝብ ስለተጋጨ የሚፈፀም አይደለም። በሌሎች አገራት ህዝብ ከህዝብ ተጋጭቶ ለእርቅ በቅተዋል፤ እኛ አገር ግን ህዝብ ከህዝብ ስለተጋጨ አይደለም እርቅ አስፈላጊ ሆኖ የቀረበው። በአገራችን በተለያዩ ወቅቶች የነበሩ አገዛዞች/ ስርዓቶች የተለያየ ስም እና ዝና ያላቸው ሆነው በተለያዩ ዘመናት የመጡቱ ቀንበራቸውን ለህዝብ አሸክመው ሲነዱት ዘመናትን ባጅተዋል።በሂደ ትም ብዙ በደል ፈፅመዋል።
በዚህ ሂደት ብዙ ትንተናዎች እየተሰጡ ወደ ህዝብ ሲመጣም ህዝብ ህዝብን እንደ በደለ ተደርጎ ሲሰበክ/ሲተረክ ተቆየ።በመሆኑም እርቁ ዛሬ የሚያስፈልገን በተለያዩ ወቅቶች በነበሩ ስርዓቶች የተፈፀሙ ስህተቶች በመፈፀማቸው መሆኑ መግባባት ያስፈልጋል፤ እነዚህ ጦሳቸው ዛሬም ድረስ ዘልቆ ለግጭት መንስኤ ሆኗል።እነዚህ ነገሮች በአዲስ ዓመት ላይደገሙ መዘጋት አለባቸው።አዲስ ምዕራፍም መጀመር አለብን ነው ቁም ነገሩ።የተሳሳቱና በቀል ያረገዙ ሀሳቦች መታረቅ አለባቸው።ቂም በቀል አርግዘን ወደኋላ እየተመለከትን ወደ ፊት መራመድ አንችልም፤ 2012ንም በዚህ ስሜት መቀበል አይኖርብንም፡፡
ወደ ኋላ እየጎተቱን እና እያጣሉን ያሉ ጉዳዮች በገዥዎቻችን የተፈፀሙ በደሎች ላይ መነጋገር አለብን።በታሪክ ምዕራፍ ጉዳዮቹ ተቀምጦላቸው እነማን በዚህ ሂደትና ታሪክ ይካተቱ ተብሎ የተቋቋመው የእርቀ ሰላም ኮሚሽን ፤ ምንም እንኳ ስራው በጣም እየዘገየ ያለ ቢሆንም፤ በበቂ ሁኔታ ተዘጋጅቶና ተጠንቶ ብሔራዊ እርቁ መከናወን አለበት።
አሁንም ቢሆን ግን አገራችን የሚያስፈልጋት እርቅ የተሳሳተ አተያይ እንዳይኖረው በሚገባ መፈተሽ ይገባናል።ብሔራዊ እርቅ የሚያስፈልገው ህዝብ ከህዝብ ስለተጋጨ አይደለም። ህዝብን ለማጥቃት አልሞ፤ ሆን ተብሎ በሌላ ህዝብ የተሰራ የግጭት መንስኤ የለም።ወደፊትም አይኖርም፡፡
ማን ከማን ይታረቅ
እርቁ እስከ አሁን እንደ አገር የቆሰልንባቸው በርካታ የስርዓት ውልዶች አሉን።አንድን የህብረተሰብ ክፍል በሁለት ከፍለን ማየት እንችላለን። አንዳንድ ማህበረሰብ (Harmony) አንድነትንና ስምምነትን ፈጥሮ ስለራሱ መልካም ታሪክ ያወራል።ምናልባትም ስለሌላ ማህበረሰብ መጥፎ ነገር ሊያወራም ይችላል።ውህደት መፍጠር ያልቻሉ ህዝቦች ግን አንደኛው በሌላው ላይ በጠላትነት አስተሳሰብ ይኖራል። ይህ ግን በህዝብ ደረጃ ላይሆን ይችላል።ነገር ግን መገለጫዎች አሉ።ምሳሌ እናንሳ፤
ሁለት አንድነት/ስምምነት ያልፈጠሩ፤ በአንድነት መኖር ላይ ያልደረሱ ህዝቦች በሁለት ጠላቶች መካከል ያለ የታሪክ አፃፃፍ ስልት ይጠቀማሉ። ታሪክ በባህሪው ስነምግባርን ለመገንባት የሚጠቅም ነው።ታሪክ ማንነትን ለመገንባትም ሆነ ለመናድ መጠቀም ይችላል። አንድ ህዝብ እንደ ህዝብ አንድ አካል ሆኖ ሲቆይ እንድ የሚያደርገውን ታሪክ ይፅፋል።
ይህ መሆን ሲያቅተው ግን ቡድን ይሰራና በሌላ ቡድን ላይ ሌላ ታሪክ ይፅፋል።በፊልሞቻችን፣ በልብ ወለዶቻችን፣ በፎክሎራችን ወዘተ…።ይህ በስነ ጥበብ ባለሙያውም በፊልም ባለሙያውም ጭምር የሚገለፅ ሆኖ ታይቷል። እነዚህ ነገሮች በገሀድ እየታዩ ነው። በመሆኑም ሌላ ስም ሊሰጣቸው አይችልም፤ ተጣልተዋል ማለት ነው። በቃ የሆነው እነዚህ ሃሳቦች መጣላታቸው ነው፡፡
በመሆኑም እርቅ ስንል ሰው የማስታረቅ ጉዳይ አይደለም ማለት ነው። የተጣሉ ሃሳቦች በመኖራቸው እነዚህን ነው የምናስታርቀው። ለሃሳቦቹ መጣላት በርካታ መገለጫዎች ቢቀመጡም እነዚህን መገለጫዎች በሚገባ ለይቶ በማውጣት ማረም ነው ትልቁ የእርቅ ስራ። በቀጣይ ሂደታችን እርቅ ፈፅመናል ስንል አንደኛው ወገን የሌላኛውን ታሪክ በመልካም መልኩ ሲፅፍበት፤ አዲስ ታሪክ እንጀምራለን። በመሆኑም የምንፅፈው ታሪክ ራሱ በሁለት ሶስት ተቧድነን ሳይሆን አንድ አካል አንድ ቡድን ሆነን ነው።
በመሆኑም በአዲሱ ዓመት የሁላችንንም ታላቅነት ሊያጎለብት የሚችል ታሪክ እንፅፋለን ማለት ነው። ታሪካችን አግላይ ሳይሆን ሁሉንም አካታች ማድረግ ይጠይቃል።ተረቶቻችንን ጨምሮ በየቤቱ የምንናገራቸው ጨዋታዎች ሁሉ ልዩነታችንን የሚያሳዩ ናቸው። እያንዳንዱ አካል ከብሄር ወደ ጎሳ የወረደውም ጭምር የፃፈውና የቀለደው ቀልድ አለ፤ እነዚህ ሁሉ ፀብ ናቸው። እናስታርቃቸው ስንል ከሰው በላይ መታረቅ ያለባቸው እነዚህ ሀሳቦች ናቸው። እነዚህን ስናክም ነው የእርቅ ስራ ሰራን የምንለው። ዋናው ጉዳይ በእያንዳንዱ ማህበረሰብ ውስጥ ያሉ፤ አንዱ በሌላው ላይ ያለው የተጣላ አስተሳሰብ ወይም ሃሳብ ነው ከሰዉ በላይ መታረቅ ያለበት። እዚህ ላይ የምንደባበቀው ሀቅ መኖር የለበትም፤ እውነት (Truth) ቦታ ሊኖራት ይገባል። በአንድ ብሔር ውስጥ ይሆንና ስለሌላው ብሔር የሚፅፈው የተሳሳተ ሃሳብ አለ። ያ ነው አሁን አገር እየጎዳ፤ ቂም እና በቀልን እንድናረግዝ ያደረገን።
እነዚህ በሙሉ አንድነታችንን እና ውህደ ታችንን ችግር እንዳለበት የሚያሳዩ በመሆናቸው እነዚህ ተደምረው ነው የአንድን ግለሰብ ወይም ቡድን ስሜትና ቁርሾ የሚፈጥሩትና የሚያንሩት። ከልጅነት ጀምሮ የሁሉንም ሃይማኖት ውስጥ ያሉ አማኞች አንድ የሚያደርጉ እና ብሔር ብሔረሰቦችን አንድነት የሚያጠናክሩ ፊልሞችንና ልብ ወለዶችን መስራትና ማሳየት ስንጀምር በፊት እንዲጣሉ ያደረግናቸውን አስተሳሰቦች እና ሃሳቦች እንዲታረቁ አደረግን ማለት ነው፡፡
ህዝብ እንደ ህዝብ አልተጣላም።ብሔር እንደ ብሔር የተጣላም የለም።ነገር ግን በተለያዩ የርዕዮት ወለድ ፖሊሲዎችን ለማሳካት የሚፈልጉ ግለሰቦች በታሪክ አጋጣሚ ከጥንት ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ያሉ ገዥ መደቦች የሚከተሉትን የራሳቸውን የርዕዮት ዓለም አስተሳሰብ ለማራመድ ሲሉ የሚፈጥሩት የሃሳብ ግጭት ወይም ጦርነት ነው፡፡
እውነት ይቅደም!
በእርቀሰላም ሂደት ውስጥ ዋናው ቀዳሚው ጉዳይ አገሪቱ ያለፈችበት እውነት ነው።እውነቱ ላይ በሚገባ መወያየት ስንችል ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት የጠፋው ጥፋት እውነት (Truth) ላይ መነጋገር አለመቻላችን ነው።ስለዚህ እውነቱ ላይ መወያየት ጭምር ነው ተዘግቶ የቆየው። ይሕ አሁን መድረክ፤ ጠረጴዛ ሊያገኝ ይገባል። እውነቱን ካላወቅን መፍትሄውን ለማበጀት ይቸግራል።ስለዚህ ለእርቅ መጀመሪያ እውነት መቅደም አለበት።ደቡብ አፍሪካውያን እንዳደረጉት ሁሉ እውነትን ማስቀደም ይገባናል።
በአገራችን ባለፉት ሶስት አስርት ዓመታት ውስጥ በርካታ በደሎች ተፈፅመዋል።አካል የጎደለበት፣ ንብረት የጎደለበት፤ የተፈናቀለ… ወዘተ ብዙ ብዙ በደሎች አልፈዋል፤ ተፈፅመዋል። ‹‹ኑ በደል የደረሰባችሁ ተመዝገቡ›› ቢባል ተበደልኩ ብሎ የሚመጣው ህዝብ ብዛት ቤት ይቁጠረው። እነዚህን ጉዳዮች ፍርድ ቤት በማቋቋም የአገሪቱን ችግር መያዝ ይቻል ነበር። በፍትህ ግን ይህን አይችልም። ሰፊና ጥልቅ በደልን ለማፅዳት ተመራጩ እርቅ ነው። የበደሉ መጠን ሰፊ በመሆኑ በፍትህ መድረክ ለመፍታት አይቻልም፤ ዘላቂም አይሆንም። እውነት ፍትህ እና እርቅ ዛሬ ለአገራችን ያስፈልጋል፡፡
ሲጠቃለል
ከዚህ ቀደም በአገራችን ወደ ግጭት የወሰዱን በርካታ መንስኤዎች ውስጥ ጥልቁና ዋናው የተሳሳቱ ትርክቶች ናቸው። አንዱ ስለሌላው ታሪክ ያለው እይታ በጣም የተለየ እና የተዛባ ነው። አንዱ በሌላው ላይ ‹‹የእኔን ታሪክ ለማንቋሸሽ የተሰራ ነው›› ብሎ ያስባል። ብዙዎቻችን ያለብን ችግር የአተያይ ነው። መደማመጡ ሲፈጠር ‹‹እኔ ጋር ያለው እውነት ሌላው ጋር አለ፤ ሲል እውነት ይወጣል፤ ከዚያም አውነት ላይ ተመስርቶ ህዝብ ይዳኛል ማለት ነው። ከተሳከረ ነገር ከመነሳት ይልቅ እውነትን መሰረት አድርጎ የሚነሳ እርቅ ሊኖረን ይገባል። በመሆኑም ያለምንም ገፊ ምክንያት ስንቀራረብ እና ስንነጋገር እውነቱ ይገለፃል።
ለዚህ ደግሞ መልካም ፍቃደኝነት ከእያን ዳንዳችን ይፈለጋል። ስንነጋገር የቱ ጋር ተጠየቃዊ ሁኔታው ይታያል? ብሎ መግባባት ላይ ሲደረስ እውነታው ይታወቃል። በተለያዩ ወቅቶች የተፈጸሙ ችግሮች ግለሰብ እና ቡድን ብቻ ሳይሆን የመገናኛ ብዙሃን ሳይቀሩ የሚያቀርቡት ፕሮግራም ችግሩን እያሰፉት ነው። ይህ በዚህ መልክ ሳይቀር ቀርቧል።
አሁን በተለይ በአዲሱ ዓመት ነገሩ እየተለወጠ ስለሆነ የተለወጠ አቀራረብ እና ፤ ለእርቀ ሰላም አቅም የሚሆን ስራ ማዘጋጀት ይገባል። እነዚህ ተቋማት ሳይቀሩ የእርቀ ሰላሙ አካል መሆን አለባቸው፤ ይገባልም። ይቅርታ ለመስጠትም ለመቀበልም መዘጋጀት የአንድ ማህበረሰብ ከፍታ ልኬት ነው። የአስተሳሰቡ ልዕልና ማሳያውም ይሆናል። አንዱ ሌላውን ስላዋረደ እኔም በተራዬ ማለት አይገባም፤ መሆን የለበትም።
የትናንቱን የችግር ምዕራፍ ዘግተን ወደ ሌላ ምዕራፍ ለመሸጋገር ፍቅር እና ሰላም መሰረት ናቸው። እርቅ ውስጥ ፍትህ አለ፤ በእርቅ ውስጥ ያለው ፍትህ ደግሞ ተመራጭ እና ዘለቂ ነው። በእርቅ ሂደት ግለሰቡ ራሱ አምኖ ምስክር ስለሚሆን እርቁ በአስተማማኝ ሁኔታ የሚቋጭ በመሆኑ ተመራጭ ነው።ይህ ደግሞ የጤነኛ ማህበረሰብ መገለጫ ሆኖ ዘመን ይሻገራል፡፡
አዲስ ዘመን መስከረም 1 /2012
ሀብታሙ ስጦታው