ወታደራዊው ስብስብ ደርግ በአፈሙዝ ኃይል ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ስላሴን ከዙፋናቸው አውርዶ ስልጣን የተቆጣጠረው ከ 45 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት መስከረም ሁለት ቀን 1967 ዓ.ም ነበር፡፡
ንጉሱን ከስልጣን ለማውረድ አስቀድሞ በርካታ ተግባራትን ሲያከናውን የከረመው ደርግ ጳጉሜን አራት ቀን 1966 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ ኢትዮጵያን ከ1909 ዓ.ም እስከ 1923 ዓ.ም በአልጋ ወራሽነት ከ1923 ዓ.ም ውሳኔው እስከተላለፈበት ምሽት በ ንጉሰ- ነገስትነት የመሩትን ቀዳማዊ አፄ ኃይለስላሴን ከዙፋናቸው እንዲወርዱ በአብላጫ ድምፅ ወሰነ፡፡
ንጉሡ መውረዳቸውን ከማወጁ በፊትም ችግሮች እንዳይፈጠሩ ህዝቡን በስነ-ልቦና ለማዘጋጀት ጳጉሜን 5 ቀን 1966 ዓ.ም ምሽት የ1965ቱን የወሎ ህዝብ የረሃብ እልቂት የሚያሳየውን ፊልም ከንጉሠ ነገሥቱ የምቾትና የቅንጦት ኑሮ ጋር እያነፃፀረ አቀነባብሮ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን አቀረበ፡፡ መስከረም ሁለት ቀን 1967 ዓ.ም የደርግ ተወካዮች ብሔራዊ ቤተመንገስት ሄደው ለንጉሡ ከዙፋናቸው እንዲወርዱ መወሰኑን ገልጸውላቸው በቮልክስዋገን መኪና ደርግ ወደተመሰረተበት አራተኛ እግረኛ ክፍለ ጦር ግቢ ወሰዷቸው፡፡ ንጉሡ በደርግ ሃይሎች ተከበው ከቤተ-መንግስት ወደ አራተኛ ክፍለ ጦር ሲወሰዱ ብዙ ህዝብ መንገድ ላይ ወጥቶ ይመለከት ነበር፡፡ ወጣቶችም “ሌባ! ሌባ!” እያሉ ይጮኹ ነበር፡፡ በተለይም ቮልክስዋገኗ መስቀል አደባባይ አካባቢ ስትደርስ ከፍተኛ ፉጨትና ጭብጨባ ነበር፡፡
ደርግ መስከረም ሁለት ከማለዳው አንስቶ በወታደራዊ ማርሽ የታጀበ መግለጫ በራዲዮን ሲያሰማ ዋለ።
በመግለጫው ንጉሱ እርጅና ተጫጭኗቸው አገር መምራት ስላልቻሉ ከስልጣን እንዲወርዱ ተደርጓል ተባለ። የመኮንኖችና አነስተኛ ማዕረግ ያላቸው ሹሞች የሆነው ወታደራዊ ስብስብ ደርግ በሚል ስያሜ በጊዜያዊነት የመንግስት ስልጣን መጨበጡን ገለጸ፡፡ የተለያዩ አደረጃጀቶችና ማህበራትም ለጊዜው ምንም አይነት እንቅስቃሴ ማድረግ መከልከላቸውም ተነገረ፡፡
መስከረም ሶስት ቀን 1967 ዓ.ም የታተመው አዲስ ዘመን ጋዜጣ መስከረም ሁለት ቀን ስለነበረው ሁኔታ “ትናንት ጠዋት” በሚል ርዕስ ተከታዩን ዘገባ አስነብቦ ነበር፡፡
‹‹ቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ ከሥልጣን መውረዳቸው በጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር መታወጁን የአዲስ አበባ ኗሪ ትናንት ጧት በአንድ ሰዓት ተኩል ላይ በኢትዮጵያ ራዲዮ ሲሰማ፣ ምንም አይነት መደናገጥና መሸበር ሳያደርስ እንደተለመደው ወደ ሥራ መስኮቹ ሲሰማራ ታይቷል፤ … የለውጡን ሁኔታ ለመከታተል በብዛት ወደ አደባባዮች እና ዋና መንገዶች የወጣው ሕዝብ ወደ ሥራውና ቤቱ እንዲሄድ ወታደሮች በኩምቢቮክስ ባገን መኪና ውስጥ ሆነው በድምፅ ማጉያ ‹ስለተባበራችሁን ከልብ እናመሰግናለን፤ ሆኖም የእናንተ እዚህ መሰብሰብ አስፈላጊ መስሎ ስላላገኘነው ወደየሥራችሁ እንድትሄዱ እንጠይቃለን› በማለት እየተዘዋወረ አሳስቧል፡፡››
ደርግ “ያለ ምንም ደም ኢትዮጵያ ትቅደም” በሚል ፍልስፍና እመራለሁ ቢልም ብዙም ሳይቆይ አገሪቱ በደም ታጠበች። ደርግ መንበሩን ተቆጣጥሮ መንፈቅ እንኳን ሳይሞላው ንጉሳውያን ቤተሰቦችን ፣ የንጉሱ ዘመን ሹማምንትንና ከራሱም አባላት አንዳንዶቹን ምንም አይነት የፍርድ ሂደት ሳይኖር በመረሸን ወደ ሰፊው ጥፋት ተንደርድሯል፡፡
ቀጥሎም በቀይ ሽብርና በነጭ ሽብር የበርካታ ዜጎች ህይወት በአደባባይ፣ በመንደር ውስጥና በየጥሻው ረገፈ፡፡ ወደስልጣን ሲመጣ ጊዜያዊ የሚል ካባ ደርቦ የነበረው ደርግ ይህን ካባ አውልቆ በቋሚነት መንበሩ ላይ መሰየሙን መረዳት ተቻለ፡፡
ደርግ በዘመኑ ስሙን በበጎ የሚያስነሱ ተግባራትንም አከናውኗል። ማንበብና መጻፍ የማይችለውን አብዛ ኛው ኢትዮጵያዊ ከመሀይምነት ለማው ጣት የዕድገት በህብረት የዕውቀትና የሥራ ዘመቻን አውጇል። ኃይማኖትና መንግስት የተለያዩ መሆናቸውንና ሁሉም ቤተ-እምነቶች በዕኩልነት እንደሚታዩ የሚገልጽ ደንብ አውጥቷል፡፡ ቀደም ሲል በሹማምንትና በባላባት ቁጥጥር ስር የነበረውን የገጠር መሬት ፣ የከተማ ቦታና ትርፍ ቤቶች የመንግስት ስለመሆናቸው ደንግጓል። እስካሁንም ድረስ ለአገር ልማት አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ የሚገኙ የተለያዩ ፋብሪካዎችንም አቋቁሟል። ሶማሊያ ኢትዮጵያን በወረረችበት ወቅትም ወረራውን በመመከት ኃላፊነነቱን በሚገባ ተወጥቷል፡፡ በጦ ርነት የተሰዉ ወታደሮች ልጆችን ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በመሰብሰብ ህጻናት አምባን አቋቁሞ መንግስታዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት ያደረገው ጥረትም የሚያስመሰግን ነው፡፡
ኢትዮጵያ የነበሯትን ዕንቁ ሰዎች በመፍጀቱ ይበልጡኑ በታሪክ የሚታወሰው ደርግ ፣ ከ 17 ዓመታት ቆይታ በኋላ እሱም በተራው በ 1983 ዓ.ም ከሥልጣኑ ተወግዶ በመስከረም ሁለት ፈንታ ግንቦት 20 ቀን መከበር ከጀመረ 28 ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡
አዲስ ዘመን ረቡዕ ጳጉሜ 6/2011
የትናየት ፈሩ