ታዋቂ ጋዜጠኛ አቶ ሙሉጌታ ሉሌ አዘውትረው ≪ ዓይን ውበት ይወድዳል≫ የሚል ብሂል ነበራቸው። እኔም ከእርሳቸው ሐሳብ በመጋራት ስለመስከረም ወር ውበት እንዲህ እላለሁ።
ክረምት እንዳለፈ መስከረም ሲጠባ፤
ለሦስት ወራት እድሜ ውኃ ተቀልባ፤
ለመለመች ጽጌ አበበች አበባ፤
የፀሐይዋን ብርሃን ዐፈር ተመግባ።
ሜዳና ረባዳው የተራራው ግርጌ፤
ዓይን ውበት ይወድዳል ዓይን አይጠግብም ዐይቶ፤
አንቴና ዘርግቶ ) ጆሮ አይሞላም ሰምቶ ፤
የመስከረም ዐደይ አበባ ፈንድቶ።
(ትንቅንቅ 1993፤234)።
ግጥሙ ከወራት ሁሉ መስከረም በመላ አገራችን የተፈጥሮ ውበት የሚፈካበትና የሰው ልጅም በደስታ ስሜት የሚዋጥበት መሆኑን ያመለክታል። በተለይ በገጠር አዝርዕቱ፤ ዕፅዋቱ፤ ሜዳና ረባዳው፤ ጋራው ሸንተረሩ፤ የልምላሜ ካባ ተጎናጽፎ፤ በአደይ አበባ፤ በሶሪ ላባና በልዩ ልዩ ኅብረቀለማት ደምቆ ተንቆጥቁጦ ሲታይ በእጅጉ ደስ ይላል። በዚህ ዓይነት በመስከረም በምሥራቅ ጎጃም ቆላና ደጋ አካባቢ፤ ከጎሐ ጽዮን እስከ ደጀን ያለውን አገር የተመለከተ በተፈጥሮ ውበት ተመስጦና ተማርኮ እንዳይቀር ያሰጋዋል። በአካባቢው የመስከረም ውበት የሚታየው ገና ከአዲሱ ዓመት ዋዜማ ጀምሮ ነው∷ ቀደም ብሎ በነሐሴ 16 ቀን በልጃገረዶች የእንግጫ ማሻ ቀን ይከበራል፤ ይኸውም ልጃገረዶች እጅብ ያለ እንግጫ ይልጉና እቴ አበባሽ አደይ ሆ በማለት እየዘፈኑ ያሹታል። ከጳጉሜን አንድ እስከ ጳጉሜን 5 (6) ወጣት ወንዶችና ልጃገረዶች ሌሊት በ9 ሰዓት እየተነሡና «እቴ አበባሽ አደይ » እያሉ በመዝፈን፤ ወንዶች የዐባይ ዳር አደይ — በማለት የአዲስ ዘመን ብሥራት የሆኑ የጨዋታ ዓይነቶችን በመዝፈን ከአፋፍ ላይ በአሸንዳ ገብቶ ከሚወረወር ፏፏ ውስጥ እየገቡ ይጠመቃሉ። ጳጉሜን 3 ደግሞ በእግር ወይም ዐባይ ወራጅ በሚሉ መኪናዎች እየተሳፈሩ ወደ ዓባይ ወንዝ በመጓዝ ሲጠመቁና ሲጨፍሩ ይውላሉ ።
በአዲሱ ዓመት መባቻ ላይ ልጃገረዶች አዳዲስ የሀገር ባህል ወይም ዘመናዊ ልብስ ለብሰው፣ በምሪ ወገባቸውን አሥረው ታጥቀው አሽንክታብ፣ ጨረቃ ጠልሰም፣ ብርማርዳ፣ ድሪ፣ መስቀል፣ አድርገው፤ ዓይናቸውን ተኳኩለው፣ ፀጉራቸውን ጋሜ ቅርድ በተባለው የፀጉር አሠራር ተሠርተው፣ አደስ ቅቤ ተቀብተው፤ በባውንድ አስብበው፣ የብር ጉትቻ በጆሯቸው አድርገው፣ በብር መስቀላቸው ላይ አሪቲ (ሪያ) ሰክተው፣ እጅና እግራቸውን እንሶስላ ሞቀው፣ በክንዳቸው አምባር አሥረው፣ ብር አልቦ በእግራቸው፣ ብር ቀለበት በጣታቸው አድርገው፣ አስቀድመው ማንም እንዳይነካው ያሹትን እንግጫ ይነቅሉና ከአደይ አበባና ከሶሪ ላባ ጋር ይጎነጉኑታል፤ ከዚያም የአበባውን ጉንጉን በአንገታቸው ላይ አጥልቀው እየዘፈኑ ወደ ቤተ ክርስቲያን በመሄድ «ዓመት ዓመት አድርሰን » እያሉ በቤተ ክርስቲያኑ ግርግም ላይ ለበረከት ያስቀምጡታል።
ከዚያም ለጨዋታ በሚሰበሰቡበት ቦታ ላይ ሎሚ በጉንፋቸው ይዘው፤ ክብ ይሠሩና በእጆቻቸው ጭናቸውንና መሬቱን እየተመተሙ ተንበርክከው (ቁጢጥ) ብለው ድሪያ ይጫወታሉ፤ እንዲህ እያሉ። «እንግጫየ ሰሌን፤ ልደቁሰው ኩሌን፤ እንግጫየ የወሩ፤ ዘረዘረ ዳርዳሩ፤ እንግጫየ ደነፋ፤ ጋሻውም ደፋ። እቴ አበባሽ ዐደይ፤ ዐደይ (ሺህ ዐደይ ወይም ሻደይ የሚለው ከዚህ የተገኘ ይመስላል ) እያሉ ይዘፍናሉ። ዐደይ ፈነዳ፤ መስከረም ነጋ፤ እንግዲህ ልቤ ካንዱ ላይ ርጋ ፤- ልቤን ልቤን፤ ኩላሊቴን፤ እናቴን ጥሯት መድኃኒቴን፤ እርሷን ካጣችሁ መቀነቷን፤ እርሷ ካልመጣች መቼም አልድን። እቴ አበባየ ሆይ፤ አደይ አበሻ ፤ እነራስ ኃይሉ እነመንገሻ። አደይ አበባ ፤ የመስከረሙ፤ እነ ጉብሌ ወዴት ከረሙ።» በአዲሱ ዓመት ቀኑን ሙሉ በሚከናወነው የጨዋታ ሥነ ሥርዓት «ዛጎሌ« የተባለው ጨዋታ በልጃገረዶች ይሰማል። ‘’ዛጐሌ ጌታው ሎሌ፣ እንደኛ ማር ይተኛ፤ በሰውየው መንገድ ሰውየው ዘለቀ፤ ዓይኔ እንደበረዶ ውኃ ሆኖ አለቀ። ቶፋ ቶፍዬ፤ ስንዴ ቀቅዬ ብላ ብለው፤ ዛሬስ ዓመዶ ሊማታ ነው… ተው አትማታ ዛር አለብኝ የዛርም ዛር፤ የብር ጨንገር፤ ያች የብር ጨንገር ወረደች ባሶ፤ ወየው አግኝቸው የልቤ ደርሶ—’’።
ወጣት ወንዶችም ለዕንቁጣጣሽ በዓል የተገዛላቸውን እጀ ጠባብ፣ ኮት፤ ተፈሪ ሱሪ፣ ተነፋነፍ (ባት ለሁለት፣)…ለብሰው፣ ቀጭን ኩታ ደርበው፤ ዱላቸውን አሞግረው፣ ልጃገረዶቹ ወደሚጫወቱበት ቦታ ግር ብለው ይሄዱና የወንዶቹ አቀንቃኝ እንዲህ ይላል።
‘’ እዩት እዚያ ላይ ግራሩ መንታ፣ አይንሽ ያበራል እንደሎሚታ። ተሎሚታውም ያንቺ ዓይን ይበልጣል፣እንደ መስታወት ያጥበረብራል። ዐደይ አበባ የመስከረሙ፣ እነ ቸርጋዴ ወዴት ከረሙ። ዐደይ ዐደይ፣ ተሞናደይ’’ እያለ የሚያፈቅራትን ልጃገረድ በዓይኑ እየቃኘ ሲያሞግሳት የተወደደችዋ ልጃገረድም ከወጣቱ ላይ ቀልቧ ያረፈበት መሆኑን ካረጋገጠች በተራዋ፡-’’ እዩት እዚያ ላይ ከግራሩ ሥር፤ ድስት ተጥዶአል ቋንጣና ምስር። ቋንጣው ይቅርና ይምጣ ምስሩ፤ አንተን አሰገኘኝ የፍቅሬ ዛሬ። ዐደይ ፈነዳ መስከረም ነጋ፣ እንግዲህ ልቤ ባንተ ላይ ይርጋ። ‘’ትለዋለች።
በዚህ የዕንቁጣጣሽ በዓል ልጃገረዶችና ያገቡት ወጣት ሴቶችም (ድኅረ ገቦች – ድረ ገቦች) ተቀላቅለው በኅብረት ይጨፍራሉ፤ ይጫወታሉ። ሴቶች ልጆች ጨዋታውን እያደመቁት ሲሄዱ ወንዶችም በጣም ይቀርቧቸዋል። መጠጋታቸውን ልጃገረዶቹ ሲያውቁ ‘’ኖሩ ‘’ ‘’ ኖሩ’’ ‘’ይሏቸዋል ወንዶችም፣’’ ክበሩ’’’’ ክበሩ’’ይላሉ። ከድኅረገቦች (ካገቡት) ወጣት ሴቶች መኻከል አንደኛዋ ወደምትፈልገው ጎረምሳ ዓይኗን እየወረወረች።’’ ጠላ ጠላ፣ ጠላ ጠጣ፤ የኔ ቀበጥባጣ’’ ትለዋለች።’’ ጠይቻለሁ፤ ላይሽ መጥቻለሁ’’ሲላት’’ ብታየኝ፤ አንድ ጊዜ ሳመኝ’’ ትላለች።’’ ብስምሽ፤ ይቆጣል ባልሽ፤ብሎ ይመልሳታል።ባሉ ባሉ እሱ የት አይቶ፤ ሲቆፍር ተደፍቶ ‘’ትላለች።’’ ሲቆፍር ምቺው (በይው) በድግር።’’ይላታል።’’ ድግር መና፤’’ ያፋታናል ገና’’ ትላለች።’’ ቢያፋታሽ፣ እኔ አለሁልሽ«‘’ ውሽማ ይብላ እንጂ በቅጤ ጠለላ፣ ባልማ ምን ይላል ደረቁን ቢበላ። ያንችማ ወዳጅ የኮራሽበት፤ ከዳገት ቀረ እንደበሬ እበት።’’ሲላት
እርሷ መልሳ ከፈሪ ወዳጅ ይሻላል ዱባ፤ ከአጥር ላይ ዘምቶ ያደምቃል አምባ፤ ከፈሪ ወዳጅ ይሻላል ቅል፤ አጥር ላይ ዘምቶ ያገለግል » ብላ ፈሪ መሆኑን እየገለጸች ትሰድበዋለች። ልጃገረዶቹ መሬቱን እንደከበሮ እየደለቁ ጭፈራቸውን ያደምቁታል።
ባልን ተመስሎ የሚጫወተው ወጣትም ሚስቱ ሌላ ወንድ መውደዷን በማየት እንደዚህ ይላታል።’’ ፍየሌን ነብር በላት፤ ለቅዱስ ዮሐንስ አረዳት፤’’ ለገና ብየ ሳደላድላት።’’ ጨዋታው እየጎላ እየደመቀ ይሄዳል። ‘’ መስከረም ሲጠባ ዓደይ ሲፈነዳ ሰው እንኳን ወዳጁን ይጠይቃል ባዳ። እየተባለ ይዘፈናል። የልጃገረዶች ጨዋታ ይቀጥላል። ‘’ እንግጫዬ ደነፋ፣ጋሻውም ደፋ።’’ እንግጫዬ ሰሌን፤ ልደቁሰው ኩሌን።’’ እንግጫዬ የወሩ ዘረዘረ ዳርዳሩ።’’ አላሊሆይ ቁርቁምባ ገረድ አያችሁ ወይ? ቁርቁምባ ለዳገቴ ሰጠኋት ለመንግሥቴ፤ መንግሥቴና መንግሥቴ ቢናደፉ ወለቃን አሳለፉ።ለወለቃ
ለአጃ ቆሎ አንሺ ቶሎ ቶሎ እመይቴ ቀጠሮ።’’በመስከረም ወር ላይ’’ ልጃገረድ ያላጨ ሰንደዶ ያልቀጨ ዋጋ የለውም’’ ይባላል። ከዚህ ወር ጀምሮ መተጫጨትና ፍቅር መመሥረት የተለመደ ነውና፣ ለታጩ ልጃገረዶች ይዘፈናል።’’ እነ ጉብሌ ሊሄዱ ናቸው፣ ተጫነላቸው ፈረስ በቅሏቸው፣ በኩል ተውቧል ዓይነ ርግባቸው።’’
በዕለቱ በየቤቱ ጨፌና ቄጠማ ይጎዘጎዛል። አበባ በሥርዓቱ እየተዘጋጀ በየቦታው ይቀመጣል። ልጆችና አረጋውያን አዳዲስ ልብሳቸውን ለብሰው በደስታ ይፈነድቃሉ። በአመሻሽ ላይ ወጣቶች ዳቦት አቀጣጥለው ‘’ ኢዮሐ አበባዬ መስከረም ጠባዬ፣ ኢዮሐ የበር በሬ ውኃ። በሸዋ በጎንደር፣ በትግሬ፤ በወሎ፣ በሐረርጌ፣ በሲዳሞ፣ … ያላችሁ እንዴት ከረማችሁ። እንኳን ከዘመን ዘመን ከጨለማ ወደ ብርሃን በሰላም አሸጋገራችሁ። እንጉሮ ገባሽ በያመቱ ያምጣሽ..ያውዳመቱ ችቦ በራ፣ጽልመት ተገፎ ሰማይ ጠራ። ፈነጠቀ ወጋጋኑ፣ የምሥራች ለዘመኑ። ከሰላም ጋር ተበሠረ፣ አዲስ ዓመት ተከበረ። ኢዮሐ መስከረም ጠራ፣ ያውዳመቱ ችቦ በራ፣ እልልታ ሆነ ጭፈራ። ደመራው ተቀጣጠለ፣ እሳቱ ተንቀለቀለ። አድባራት መሥዋዕት አቀረቡ፣ በሰላም ጭስ ተከበቡ፤ እድምተኛው ደመራውን ዞረ፣ የምሥራች ብሎ ጨፈረ። የፍቅር ዓመት ጽጌረዳ፣ አበባው ሁሉ ፈነዳ።
ያውዳመቱ ችቦ በራ፣ደመና ተገፍፎ ሰማይ ጠራ። ‘’እያሉ ያቀጣጠሉትን ችቦ በአየር ላይ እየወረወሩ ሲጨፍሩ፣ ሲዘፍኑ የምሽቱም የችቦ እሳት ርቀት እስከወሰነው አድማስ እስከ ከለለው ድረስ ከቀዬ ቀዬ ከአድባር እስከ አድባር፣ ከመንደር እስከ መንደር፣ … ሲንቀሳቀስና ሲንቦገቦግ መሬት የእሳት ላንቃዋ ተከፍቶ ነበልባል የምትተፋ ትመስላለች። የአየር ላይ ውጋጋኑን ደግሞ ሲመለከቱት እግዚአብሔር ከመንበረ ጸባዖቱ ወርዶ የብርሃን አክሊል ደፍቶ ቀይ መጐናጸፊያ ተጎናጽፎ ጨለማውን እየገፈፈ በጠፈር፤ በአየር ላይ እየተንሳፈፈ ወደ መሬት የሚወርድባት የመጨረሻዋን የምጽዓት ቀን ታስታውሳለች። የዕንቁጣጣሽ ሌሊት። አባቶች የችቦ ብርሃን ላሰባሰበው ሕዝብ ቡራኬና ምርቃት ያደርጋሉ ‘’ የተዘራውን እህል እክለ በረከት ፤ የዘነመውን ዝናም ዝናመ ምሕረት፣ ዘመኑን የሰላም ዓመት ያድርግልን። እህል ይታፈስ፣ ይርከስ። ሳቢ በሬውን፣ አራሽ ገበሬውን ይባርክ፣ ቁንጫ፣ ተባይ ተምች፣ አንበጣ፣… ጸረ ሰብል ሁሉ እንደችቦው ተቀጣጥለው ይንደዱ።…ይላሉ።
እናት አባት … በልጆቻቸው፣ በወዳጅ ዘመዶቻቸው የተበረከተላቸውን የእንግጫ ጉንጉን በራሳቸው ላይ በእንጀራ ማቡኪያና መሶቡ ላይ፣ ከቤቱ ምሰሶ ላይ…. ያሥራሉ። ይህም በአበባ የተጎነጎነ የእንግጫ ጉንጉን የመስቀል ደመራ ዕለት እሳቱም ዐመዱም ላይ ይጣላል። ተምሳሌቱም እንደቁንጫ ሁሉ ቁርጥማቱ ራስ ምታቱ፣ ምች ጎንፍ ቁርጠቱ፣ ምቀኛ ሸረኛ ሰላቢው፣ ሌላ ቀማኛ ቀጣፊው… እንዲቃጠልና እንዲጠፋ ነው። በቤቱም ( አባወራው ቤት) በረከትና ሞገስ (አግሟስ) እንዲቀርብ ነው ይባላል።
በየቤቱ ዳቦ፣ ሸምብራ ቂጣ፣ በሶ፣ የተወቀጠና የተለጠለጠ ኑግ፣ ፣ በቅቤ የታሸ ቆሎ፤ አዋዜ በእንጀራ ወይም በሽምብራ ቂጣ ይበላል። ጠላ፣ ቡቅር ነጣ ያለ( ጠላ) ይጠጣል። ሀብት ያለው እንደቤቱ አምላኩ በግ፣ ፍየል ያርዳል፤ ደም ያፈሳል። በወርሃ መስከረም ሴቶች አክርማ ቀጭተው ፤ ስንደዶ በወጉ ሠንጥቀው ድርብ (ዕንቅብ) ሠፌድ፣ ቁና፣ መሶብ… ይሠፋሉ። ከወራት ሁሉ ይህ መስከረም በበለጠ የሚወደደውና የሚናፈቀውም ያዲስ ተስፋና ምኞት መጠንሰሻ፣ ያዝርዕትና የሰብል ማበቢያ መዘርዘሪያ የእሸት መድረሻ፣ የጎመን ምንቸት ወጥቶ የገንፎ ድስት የሚገባበት፤ ሰመሬታ የሚደርስበት የረሃብ ማስታገሻ ወቅት በመሆኑ ጭምር ነው።
አዲስ ዘመን ጳጉሜ 3/2011
ታደለ ገድሌ ጸጋየ ዶ/ር