አዲስ አበባ፡- የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት ግብር በማይከፍሉ ነጋዴዎች ላይ የሚወስደውን እርምጃ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታወቀ። ለልማት የመሬት ጥያቄ አቅርበው ቦታ ከወሰዱ በኋላ ያላለሙና ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ያላደረጉ ባለሀብቶች ላይም ክትትል ይደረጋል ተብሏል።
የኦሮሚያ ገቢዎች ባለሥልጣን ትናንት በስካይላይት ሆቴል ለግንባር ቀደም ግብር ከፋዮች እውቅና ሰጥቷል። በፕሮግራሙ ላይ የተገኙት የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ እንደተናገሩት፣ አርሶ አደሩ ከመሬቱ ተፈናቅሎ በኢንቨስትመንት ስም በርካታ ባለሃብቶች መሬት ቢወስዱም የሚፈለገውን ያህል ውጤት አልመጣም።ይልቁንም አንዳንዶቹ በኢንቨስትመንት ስም መሬት ወስደው ከእህል እስከ የጦር መሳሪያ የሚያከማቹ እና ግብር የማይከፍሉት እንዳሉ የተደረሰባቸው መሆኑንና በቀጣይም የማያዳግም እርምጃ ይወሰዳል።
አቶ ሽመልስ ለግንባር ቀደም ግብር ከፋዮች ባስተላለፉት መልዕክትም፣ ውለታቸው መከፈል ያለበት ዋንጫና የምስክር ወረቀት በመስጠት ሳይሆን ለውለታቸው ልክ የሚሆን አገልግሎት በመስጠት ነው ካሉ በኋላ በየደረጃው ያሉ አካላት ለግንባር ቀደም ግብር ከፋዮች የሚገባቸውን አገልግሎት መስጠት እንደሚገባቸው አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።ከቀጣዩ በጀት ዓመት ጀምሮም ግብር ከፋዩን የሚመጥን አገልግሎት ለመስጠት በቂ ቅድመ ዝግጅት መደረጉንም አስረድተዋል።
‹‹ግብር የሚከፈለው ለመንግሥት አይደለም›› ያሉት አቶ ሺመልስ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ መንግሥት ማለትና በተግባርም የታየው በማሰርና በማሰቃየት ስለሆነ ሰዎች ለመንግሥት ጥሩ ስሜት የላቸውም። ግብር የሚከፈለው ለመንግሥት ሳይሆን መሰረተ ልማት ላጠው ህዝብ ነው። አንድ ዜጋ ግብር ሲከፍል ለሰፊው ህዝብ መንገድ እየሰራ ነው፣ መብራት እና ውሃ እያስገባ ነው ሲሉ አስረድተዋል።
የኦሮሚያ ገቢዎች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ እንደገለጹት፤ በክልሉ ውስጥ በታማኝነት ግብር በመክፈል ቀዳሚ የሆነው የመንግሥት ሠራተኛው ነው። ከመንግሥት ሠራተኛው ውጭ ያለው ላይ ከዚህ በፊት ተደጋጋሚ ማጭበርበር ይከሰት የነበረ ቢሆንም በ2011 ዓ.ም ግን መሻሻል መታየቱን ተናግረዋል። በበጀት ዓመቱም ባለስልጣኑ የዕቅዱን 65 በመቶ ግብር መሰብሰቡንም ገልጸዋል።
ከለገጣፎ ለገዳዲ የመጡት እና በግንባር ቀደም ግብር ከፋይነት እውቅና ያገኙት አቶ በላይ ሙላት በተለይም ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ ግብርን ማጭበርበር ራስን ማታለል ነው። ከመንግሥት 15 በመቶ ለመስረቅ ተብሎ የሚደረግ ማጭበርበር ነጋዴውን ብዙ ነገር ያሳጣዋል። መንግሥት አቅም ካጣ መሰረት ልማትን ሊሰራ አይችልም፤ መሰረተ ልማት በሌለበት ደግሞ ዞሮ ዞሮ ተጎጂው ነጋዴው ነው ሲሉ ደምድመዋል።
በዱከም ከተማ የሆቴል አገልግሎት እየሰጠ የሚገኘው አትሌት ወርቁ ቢቂላ በበኩሉ፤ ግብርን በታማኝነት እየከፈለ ያለው ለምስክር ወረቀት ሳይሆን የዜግነት ግዴታ መሆኑን አምኖ እንደሆነ ተናግሮ፣ መንግሥት አቅም የሚያገኘው ከህዝብ ነውና ግብር ከፋዩ ህዝብም ግብሩን በታማኝነት መክፈል እንደሚጠበቅበት አስረድተዋል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጳጉሜ 2/2011
ዋለልኝ አየለ