ዩኒቨርሲቲው ራስ ገዝ ለመሆን የሚያካሂደው የሽግግር ጊዜ በዚህ  ዓመት ይጠናቀቃል

 

አዲስ አበባ፡የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ራስ ገዝ ለመሆኑ የሚያካሂደው የሽግግር ጊዜ በተያዘው ዓመት የሚጠናቀቅ መሆኑን የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አስተዳደርና ልማት መሪ ሥራ አስፈጻሚ ሰሎሞን አብርሃ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ በኢትዮጵያ ራዝ ገዝ ከሚሆኑ የመንግሥት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ አንዱና ቀዳሚ የሆነው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ራስ ገዝ ለመሆን የሚያካሂደው የሽግግር ጊዜ በተያዘው ዓመት ያጠናቅቃል፡፡

በሀገሪቱ የከፍተኛ ትምህርት የተስፋፋ ቢሆንም የትምህርት ተቋማቱ ባላቸው አናሳ ብቃትና ውጤታማነት ምክንያትም የትምህርት ጥራት ላይ መሠረታዊ ችግር ይስተዋላል ያሉት ሰሎሞን (ዶ/ር)፤ ይህንንም ችግር በመፍታት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱን ብቁና ተወዳዳሪ ለማድረግ ራስ ገዝ ማድረግ አንደኛው መንገድ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲዎች ራስ ገዝ መሆን ተቋማዊ ብቃትና ተወዳዳሪነትን በማሳደግ ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ እንደሚያስችል አመልክተው፤

በዚህም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ባለፉት ሁለት ዓመታት የሽግግር ጊዜም ሽግግሩን የሚመራ አመራር ተመድቦለት ስትራቴጂ፣ ፖሊሲ ዶክመንቶች እና የተማሪዎች አድሚሽን ፖሊሲ እንዲሁም የተለያዩ የዩኒቨርሲቲው መተዳደሪያ አካዳሚክ ሕግ እና የፋይናንስ አስፈላጊ የሚባሉ ዶክመንቶች መዘጋጀታቸውን ሰሎሞን (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡

በተያዘው ዓመትም ቀሪ አስፈላጊ ዶክመንቴሽን ሥራ የማዘጋጀት ሥራውን የሚያከናወን ሲሆን ከሰኔ ወር በኋላ ዩኒቨርስቲው ራስ ገዝ የሚሆን መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲዎች ራስ ገዝ መሆን የአካዳሚ፣ የአስተዳደር፣ የፋይናንስ እና የሰው ሀብት አስተዳደራቸው ላይ ነፃነት እንዲኖራቸውና የራሳቸውን ሀብት ለማመንጨት የሚያስችል መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህም ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጥሩ የመማር ማስተማር የሚካሄድባቸው እና ለምርምር ሥራዎች የተለየ ትኩረት እንዲሰጡ የሚያደርግ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በሀገሪቱ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲን ጨምሮ ጎንደር ዩኒቨርስቲ፣ ሀዋሳ ዩኒቨርስቲ፣ ባሕር ዳር ዩኒቨርስቲ፣ ጅማ ዩኒቨርስቲ፣ አርባ ምንጭ እና ሐረማያ ዩኒቨርስቲ ጨምሮ በአጠቃላይ ዘጠኝ ዩኒቨርስቲዎች በቀጣይ ራስ ገዝ እንደሚሆኑ ጠቁመዋል፡፡

ዩኒቨርስቲዎች ራስ ገዝ መሆን ጠንካራ ተቋማት በመፍጠር ለትምህርት ጥራትና ተቋማዊና ሀገራዊ ተልዕኮን ለማሳካትም ሁሉም አካል በጋራ መተባበርና መሥራት አለባቸው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ማሕሌት ብዙነህ

አዲስ ዘመን ህዳር 14/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You