– ገቢን መሠረት ያደረገ የመዋጮ አሰባሰብ ሥርዓት ተግባራዊ ሊደረግ ነው
ቢሾፍቱ:- በዘንድሮ ዓመት በማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን አምስት ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ዜጎች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ የኢትዮጵያ ጤና መድኅን አገልግሎት አስታወቀ። ገቢን መሠረት ያደረገ የመዋጮ አሰባሰብ ሥርዓት ተግባራዊ ሊደረግ መሆኑንም ጠቁሟል።
የኢትዮጵያ ጤና መድኅን አገልግሎት በ2017 ዓ.ም የመጀመሪያ ሩብ ዓመት አፈፃፀም እና በቀጣይ ሥራዎች ዙሪያ ከክልል ጤና ቢሮዎችና ከጤና መድኅን አስተባባሪዎች ጋር ትናንትና በቢሾፍቱ ከተማ ተወያይቷል።
የኢትዮጵያ ጤና መድኅን አገልግሎት የሥራ አመራር ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ከፍያለው ሞቲ በወቅቱ እንደገለፁት፤ የጤና መድኅን ሥርዓት ዓላማው በየደረጃው የሚገኘውን ማኅበረሰብ፣ ጤናማ፣ አምራችና የበለፀገ ዜጋ ማድረግ ነው። ከዚህ አኳያም ዘንድሮም በማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን አምስት ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ዜጎች ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡
በአሁኑ ጊዜም የተጠቃሚዎችን መረጃ ዲጂታል የማድረግ ሥራ እየተሠራ ነው። ይህንንም ከሆስፒታሎች፣ ከጤና ጣቢያዎች፣ ከፋርማሲ ቤቶችና ከጤና ሚኒስቴር ጋር የማስተሳሰር ሥራ እንደሚሠራ ጠቁመዋል።
በ2017 በጀት ዓመት በማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን አምስት ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ዜጎች ተጠቃሚ ይሆናሉ ያሉት አቶ ከፍያለው፤ ይህም የተጠቃሚዎችን ቁጥር ከ53 ሚሊዮን ወደ 58 ሚሊዮን እንደሚያሳድገው ገልፀዋል።
ከአሥራ ሦስት ቢሊዮን ብር በላይ ለመሰብሰብ ታቅዷል ያሉት አቶ ከፍያለው፤ በዘንድሮ ዓመት ገቢን መሠረት ያደረገ የመዋጮ አሰባሰብ ሥርዓት ተግባራዊ እንደሚደረግ ተናግረዋል። መጠኑም ከሰባት መቶ ብር እስከ አንድ ሺህ 750 ድረስ መሆኑን ጠቁመዋል። በዚህ ውስጥ መንግሥት የሚደጉማቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች እንዳሉም ተናግረዋል።
የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ወርቁ በበኩላቸው፤ በማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን ዜጎች በሚከፍሉት አነስተኛ መዋጮ ያለምንም ተጨማሪ የክፍያ ተገቢና አፋጣኝ የሕክምና አገልግሎት እያገኙ ነው ብለዋል።
የዜጎችን ፍትሐዊ የጤና አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግና ጤናማና አምራች ዜጋ ለመፍጠር በርካታ ሥራዎች ተሠርተዋል ያሉት አቶ ተስፋዬ፤ በ2016 በጀት ዓመት ከ11 ሚሊዮን በላይ እማውራና አባወራዎች አባል ማድረግ ተችሏል ብለዋል፡፡
ከእነዚህ ውስጥ 2 ነጥብ 7 ሚሊዮን ዜጎች ከድህነት ወለል በታች የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች መሆናቸውን አንስተው፤ በአጠቃላይ ከ53 ሚሊዮን በላይ ዜጎች በማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን ሥርዓት ተጠቃሚ ሆነዋል ነው ያሉት፡፡
በሌላ በኩል ከከፋይ አባላትና ከተናጠል ድጎማ መዋጮ ከ9 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ መሰብሰብ ተችሏል ሲሉም ተናግረዋል። በውይይት መድረኩ የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን፣ የቋት አስተዳደር ማኑዋል፣ የጤና ተቋማት የቁርጥ ክፍያ ሥርዓት፣ የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን ቅስቀሳ ስትራቴጂ ሰነድ ላይ ውይይቶች መደረጋቸው ታውቋል።
ሳሙኤል ወንደሠን
አዲስ ዘመን ህዳር 14/2017 ዓ.ም