ደቡብ አፍሪካ በአፍሪካ ባለግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤት ከሆኑ አገራት አንዷ ስትሆን፤ በርካታ አፍሪካውያን ሠርተን እንቀየራለን በማለት ወደ አገሪቷ ያቀናሉ። በዚህም የአገሪቱ ዜጎች እትብታችን በተቀበረባት አፈር ላይ ‹‹የሌሎች አገራት ዜጎች ተደላድለው ተቀመጡ፣ የዕለት እንጀራችንን ነጠቁ፣ ሃብት አፈሩ›› የሚል ሰይጣናዊ ቅናት ያደረባቸው የተወሰኑ ደቡብ አፍሪካውያን ቆንጨራ ይዘውና ከላይ እስከ ታች ታጥቀው በተለያየ ጊዜ አደባባይ በመውጣት ሰርተን ያልፍልናል ብለው አገራቸውን ጥለው በደቡብ አፍሪካ የከተሙ አያሌ የውጪ አገር ዜጎችን ህይወት ቀጥፈዋል።
ለዓመታት ጊዜ እየጠበቀ ሲፈነዳ የቆየው ይህ የደቡብ አፍሪካዊያን የሌሎች አገሮችን ዜጎች ከአገራችን ይውጡልን የጥላቻ አባዜ ዳግም ከባለፈው ሳምንት ጀምሮ በመቀስቀሱ በደቡብ አፍሪካ ውጥረት ነግሷል። ይህም ሰሞኑን ባለቤትነታቸው የውጭ ዜጎች በተለይም ከሌሎች የአፍሪካ አገራት ዜጎች የሆኑ የንግድ ማዕከላት ኢላማ ያደረገውን ጥቃት፤ የአገሪቱ ፖሊስ ይህንን የጥፋት እሳት ለመግታት ደፋ ቀና ሲል ቢሰነብትም ቁጣና ጥፋቱ በየአቅጣጫው መሰራጨቱን ቀጥሏል፡፡ የደቡብ አፍሪካዊያን ስደተኞች ከአገራችን ይውጡልን ጥያቄም እየገነገነ ወደ ተለያዩ የደቡብ አፍሪካ ከተሞች እየተዛመተ ይገኛል፡፡ አገሬው ስደተኛውን እያሳደደ ማጥቃቱንም ገፍቶበታል፡፡
‹‹ሰርቼ ሰው እሆናለሁ›› ያሉ በሺዎች የሚቆጠሩ የሌሎች አፍሪካ አገራት ስደተኞች ከጥቃቱ ለማምለጥና ህይወታቸውን ለማትረፍ በየፖሊስ ካምፖችና ስቴዲየሞች ተጠልለው ይገኛሉ፡፡ ላባቸውን አንጠፍጥፈው ያፈሩትን ሃብትና ንብረት ታግለው ለማዳን የደፈሩ ጥቂቶችም ከሞት ጋር ተጋፍው ይገኛሉ፡፡
ዝርፊያውና አመጹ እሁድ ጠዋት ላይ በፕሪቶሪያ በተባለችው ከተማ የጀመረ ሲሆን፤ አመጹ ማክሰኞ ዕለትም ቀጥሎ አሌክሳንድሪያ ወደተባለችው ጆሃንስበርግ ክፍል መስፋፋቱ ተሰምቷል። አንዳንድ ነዋሪዎችም በሕገ- ወጥ መንገድ ወደሃገራችን የገቡ ስደተኞችን መንግስት ያባርልን ሲሉ ቁጣቸውን ለመንግስት እየገለጹ ይገኛሉ።
ጂፒ በተሰኘው አካባቢ የሬስቶራንት ባለቤት የሆነው አቶ ተከስተ ሹምዬ ስለሁኔታው ለቢቢሲ እንደገለጹት፤ <<የሌላ ሃገር ዜጎች የሆኑ አፍሪካውያን ላይ ነው ጥቃቱ እየተሰነዘረ ያለው። በተለይ ደግሞ የመኪና ሽያጭ ላይ የተሰማሩ ናይጄሪያውያን ላይ ከእሁድ ጠዋት ጀምሮ ጥቃት ተፈጽሟል። እስካሁን በሰማሁት ዜና ከ50 በላይ መኪና ተቃጥሏል>> በማለት ስለሁኔታው ተናግረዋል።
እሁድ ጠዋት ላይ ሶስት ሰዎች መገደላቸውን፣ አንድ ህንጻ እንደተቃጠለና ሁኔታውም እስካሁን እንዳልተረጋጋ ተከስተ የተናገረ ሲሆን፤ በግምት ከአስር ቀናት በፊት ፕሪቶሪያ በተባለችው ከተማ የሃገሬው ታክሲ ሾፌሮች ከናይጄሪያውያን ሾፌሮች ጋር ተጋጭተው በናይጄሪያውያን በተተኮሰ ጥይት አንድ ደቡብ አፍሪካዊ መሞቱን ተከትሎ ትልቅ ብጥብጥ ተነስቶ ነበር። በዚህም ምክንያት ላለፉት ቀናት ናይጄሪያውያንን ጨምሮ ከሌላ ሃገራት የመጡ ዜጎችን ንብረት መዝረፍና ማቃጠል ተበራክቶ እንደቀጠለ ተከስተ ተናግሯል።
በመሆኑም የያዝነው ሳምንት በደቡብ አፍሪካ ለሚገኙ የሌላ አፍሪካ ዜጎች መከራው እና ግፉ ከመቼውም በላይ ያየለበት ሲሆን፤ የአገሪቱ ፖሊስ እንዳስታወቀው በዚህ የጥፋት ዘመቻ ተሳታፊ የሆኑ 189 በላይ ደቡብ አፍሪካውያን ከሰኞ አመሻሽ ጀምሮ በቁጥጥር ስር አውሏል። ፖሊስ አመጸኞቹን ለመቆጣጠር አስለቃሽ ጭስ የተጠቀመ ሲሆን፤ ነገሮች ከቁጥጥር ውጪ መሆን ሲጀምሩ ደግሞ የጎማ ጥይቶችንም ጭምር መጠቀሙ ታውቋል።
በደቡብ አፍሪካ ቢያንስ አምስት ሰዎች መሞታቸውን ፖሊስ የገለጸ ሲሆን፤ ከሟቾቹ መካከል ሁለቱ ደቡብ አፍሪካውያን መሆናቸውን አረጋግጫለሁ ብሏል። የቀሪዎቹ ሶስት ሰዎች ዜግነት ግን እስካሁን አልታወቀም ተብሏል።
ይሄንን ተከትሎ የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ በሌሎች የአፍሪካ ሃገራት ዜጎች ንብረት ላይ የተፈጸመውን ዝርፊያና ጥቃት አውግዘዋል። በያዝነው ሳምንት ማክሰኞ ዕለት ፕሬዝደንቱ በቲውተር ገጻቸው እንደገለጹት፤ <<ለተፈጸመው ነገር ምንም አይነት ምክንያት ሊቀመጥለት አይችልም፤ ደቡብ አፍሪካውያን ሌሎች አፍሪካውያንን ማጥቃት አይችሉም። የተፈጸመው ዝርፊያ ሙሉ በሙሉ ተቀባይነት የሌለው ነው፤ ይህ ነገር ደቡብ አፍሪካ ውስጥ እንዲሆን አንፈቅድም። ድርጊቱም በአስቸኳይ መቆም አለበት>> ሲሉ ፕሬዝዳንቱ በትዊተር ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት የቪዲዮ መልእክት አስተላልፈዋል።
በሌላ በኩል የአፍሪካ ህብረት በበኩሉ ተቀባይነት የሌለው ድርጊት ያለውን ይሄንን የደቡብ አፍሪካዊያን እኩይ ተግባር በእጅጉ እንደሚቃወመው ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋቂ መሃመት በደቡብ አፍሪካ ባሉ የሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ላይ ኢላማ አድርጎ እየተፈፀመ ያለውን ጥቃት አውግዘዋል።
የአፍሪካ ህብረት ባወጣው መግለጫ ላይ ሊቀ መንበሩ እንደተናገሩት፤ ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ወደ ደቡብ አፍሪካ በማቅናት በንግድ ስራ ላይ በተሰማሩ ሰዎች ላይ ንብረት መዝረፍ እና ማውደምን ጨምሮ ሌሎች እየተፈፀሙ ያሉ ድርጊቶችን ክፉኛ ኮንነዋል። የደቡብ አፍሪካ ባለስልጣናት አጥፊዎችን በቁጥጥር ስር ማዋል መጀመራቸውንም ሊቀ መንበሩ የሚበረታታ ተግባር ነው ብለዋል።
አሁንም ቢሆን በሀገሪቱ የሚኖሩ የሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ዜጎችን ህይወት እና ንብረት ከጥፋት ለመታገድ አፋጣኝ እርምጃዎች ሊወሰዱ እንደሚገባም አሳስበዋል። በወንጀሉ የተሳተፉ አካላት በሙሉ በአፋጣኝ ለህግ እንዲቀርቡ እና ንብረታቸው ለወደመባቸው ሰዎችም በአፋጣኝ ፍትህ እንዲሰጣቸውም ጥሪ አቅርበዋል።
እርሳቸውም አክለው፤ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ችግሩን ከምንጩ ለመቅረፍ እና በሀገሪቱ ሰላም እና መረጋጋትን ለማስፈን ለደቡብ አፍሪካ መንግስት አስፈላጊውን ትብብር እንደሚያድርግም አስታውቀዋል።
የናይጄሪያው ፕሬዝዳንት ሞሃሙዱ ቡሃሪ በበኩላቸው የሃገራቸውን ቁጣ ለመግለጽና የዜጎቻቸውን ደህንነት ለማረጋገጥ ማክሰኞ ዕለት የልዑካን ቡድን ወደ ደቡብ አፍሪካ መላካቸውን ያስታወቁ ሲሆን፤ በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ ኤምባሲም ጉዳዩ እስኪጣራና ዝርፊያዎቹ እስከሚቆሙ ድረስ ዜጎች ሱቆቻቸውን እንዲዘጉ አሳስቧል። አመጽ ሊነሳባቸው ከሚችሉባቸው ቦታዎች እራሳቸውን እንዲያርቁና ውድ የሆኑ ጌጣጌጦችን እንዳያደርጉም አስጠንቅቋል።
የዛምቢያ ትራንስፖርት ሚኒስቴር መስሪያ ቤት በበኩሉ ትልልቅ የጭነት መኪኖች ወደ ደቡብ አፍሪካ የሚደረጉትን ጉዞ ለጊዜው እንዲያቆሙ ያገደ ሲሆን፤ ትናንት ቢቢሲ በድረገጹ ይዞት በወጣው መረጃ፤ ጥቂት የማይባሉ ተጽዕኖ ፈጣሪ አፍሪካውያን ከዚህ በኋላ እግራቸው ደቡብ አፍሪካን እንደማይረግጥ መግለጻቸውን አስታውቋል። ምክንያታቸውም በሰሞኑ ከሌላ አገራት የመጡ አፍሪካውያን ላይ እየተፈጸመ ያለውን ግድያና ዝርፊያ በመቃወም እንደሆነ ታውቋል።
በመሆኑም ናይጄሪያውያን ሙዚቀኞች እና የዛምቢያ ብሄራዊ ቡድን ውሳኔያቸውን ይፋ ካደረጉት መካከል ግንባር ቀደሞች ሲሆኑ፤ ናይጄሪያዊው ታዋቂ የአፍሮቢት ስልት አቀንቃኝ ‘በርና ቦይ’ የደቡብ አፍሪካ መንግሥት ከእንቅልፉ እስከሚነቃ ድረስ ወደ ደቡብ አፍሪካ ድርሽ አልልም ሲል መልእክቱን በትዊተር ገጹ ላይ አስፍሯል። ከዚህ በፊት እ.አ.አ. በ2017 ደቡብ አፍሪካ ውስጥ የጥላቻ መልዕክቶችና ጥቃቶችም ደርሰውብኝ ነበር ብሏል።
ሌላዋ ናይጄሪያዊ ዘፋኝ ‘ቲዋ ሳቬጅ’ በበኩሏ፤ በያዝነው ወር በደቡብ አፍሪካ ልታዘጋጀው የነበረውን የሙዚቃ ኮንሰርት መሰረዟን በትዊተር ገጿ አስታውቃለች። <<ደቡብ አፍሪካውያን በሕዝቦቼ ላይ እየፈጸሙት ያለው ኢ-ሰብአዊና ጭካኔ የተሞላበት ድርጊትን እቃወማለሁ>> ብላለች።
የናይጄሪያ መንግሥት ደግሞ በደቡብ አፍሪካዋ ኬፕ ታውን እየተካሄደ ከሚገኘው የዓለም ኢኮኖሚ ፎረም ስብሰባ ራሱን ማግለሉን አስታውቋል። ምክትል ፕሬዝዳንቱ ዬሚ ኦሲባንጆ ስብሰባውን እንደሚታደሙ ተገልጾ የነበረ ቢሆንም፤ ኬፕ ታውን እንደማይሄዱ ተገልጿል። ከዚህ በተጨማሪ ፕሬዝዳንት ሞሃመዱ ቡሃሪ ናይጄሪያውያን ወደ ደቡብ አፍሪካ እንዳይሄዱ በትዊተር ገጻቸው አስጠንቅቀዋል።
በሌላ በኩል የዛምቢያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የፊታችን እሁድ ከደቡብ አፍሪካ ጋር በዋና ከተማዋ ሉሳካ ሊያደርገው አስቦት የነበረውን የወዳጅነት ጨዋታ መሰረዙን አስታውቋል። ፌዴሬሽኑ ይሄንን የወሰንነው ከደህንነት ስጋት አንጻር ሲሆን፤ <<ምን ሊፈጠር እንደሚችል ማንም ሊያውቅ አይችልም። የደቡብ አፍሪካ ብሄራዊ ቡድንን ደህንነት ማረጋገጥ እንፈልጋለን>> ብለዋል የፌዴሬሽኑ ዋና ጸሃፊ አድሪያን ካሻላ።
የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ በበኩላቸው፤ አገራችን የሁሉም አፍሪካውያን ቤት ናት የሚል መልዕክት ቢያስተላልፉም፤ የአገሬው ሰው ሊሰማቸው ፍቃደኛ የሆነ አይመስልም። ብዙዎች አሁንም በንግድ ሥራ የተሰማሩ የሌሎች አገራት ዜጎች ከደቡብ አፍሪካ ይውጡልን ጥያቄ እያየለ መምጣቱን መረጃዎች ያሳያሉ።
በሌላ በኩል ቢቢሲ በድረገጹ እንዳስነበበው በናይጄሪያ የደቡብ አፍሪካውያን የሆኑ ድርጅቶች ላይ አጸፋዊ ጥቃት እየደረሰባቸው እንደሚገኝ የገለጸ ሲሆን፤ ‘ሾፕራይት’ የተባለው ታዋቂ የደቡብ አፍሪካ መደብር ናይጄሪያ ውስጥ ጥቃት ተፈጽሞበታል ብሏል። የአገሪቱ ፖሊስም ሁኔታውን ለመቆጣጠር አስለቃሽ ጭስ ለመጠቀም ተገዷል ብሏል። ‘ኤምቲኤን’ የተባለው የደቡብ አፍሪካ የቴሌኮም ድርጅትም በናይጄሪያ የሚገኙ ሁሉንም ሱቆቹን እየዘጋ እንደሆነ አስታውቋል።
እ.አ.አ በ2008 በደቡብ አፍሪካ ሶዌቶ ከተማ ውስጥ በተቀሰቀሰ ተመሳሳይ ጥቃት፤ ከ62 በላይ የሌሎች
አገራት ዜጎች ለህልፈተ ህይወት መዳረጋቸውን ያስታወሰው የቢቢሲ ዘገባ፤ ሰሞኑን በተቀሰቀሰው ግጭት አምስት ሰዎች ህይወታቸው ማለፉም
ታውቋል።
አዲስ ዘመን ጳጉሜ 1/2011
ሶሎሞን በየነ