ወይዘሮ ፋይዛ ሙሳ ሶስተኛ ልጃቸውን ለመገላገል ወደ አለርት ማእከል ከሳምንት በፊት እንደመጡና የጤና ክትትል እያደረጉ መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡ በማእከሉ በነበራቸው ቆይታ ሲደረግላቸው የነበረው የጤና ክትትል መልካም እንደነበርም ይገልፃሉ፡፡ እርሳቸው በሚገኙበት የእናቶች ማዋለጃ ክፍል የሃይማኖት አባቶች ከሰሞኑ ያደረጉት ጉብኝት ያልጠበቁትና ድንገተኛ መሆኑንም ያስረዳሉ፡፡ እንዲያውም የሃይማኖት አባቶች በአብዛኛው ህሙማንን የሚጠይቁት በዓመት በዓልና በአዲስ ዓመት በመሆኑ ቀኑ በዓል መስሏቸው እንደነበርም ይጠቁማሉ፡፡
ህሙማንን ለመጠየቅና ለማበረታታት ወደ ማእከሉ የመጡ የሃይማኖት አባቶች ምስጋና እንደሚገባቸው የሚገልፁት ወይዘሮ ፋይዛ፤ ጉብኝታቸው ለእርሳቸው ትልቅ የመንፈስ ጥንካሬ የሰጣቸው መሆኑን ይናገራሉ። ለሌሎች ህሙማንም ትልቅ የሞራል ስንቅና ለመዳን ያላቸውን ተስፋ ከፍ ያደረገ መሆኑንም ያመለክታሉ፡፡ በቀጣይም ይህ በጎ ተግባራቸው በሌሎች ሆስፒታሎችም ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባው ይጠቅሳሉ፡፡
ልክ እንደ ወይዘሮ ፋይዛ ሁሉ ሌሎች ሰዎችም አካላዊ፣ ስነ ልቦናዊና መንፈሳዊ ህመም ሊያጋጥማቸው ይችላል፡፡ ታዲያ ሊያጋጥማቸው የሚችለው አካላዊ ህመም በሳይንሳዊ መንገድ በመድሃኒት ሊፈወስ የሚችል ቢሆንም፤ የስነ ልቦናና የአእምሮ ህመሞቻቸው ግን በሳይንሳዊ መንገድ ብቻ ሳይሆን በመንፈሳዊ መንገድም ጭምር ሊታከም እንደሚገባ የዘርፉ ባለሙያዎች ይጠቁማሉ፡፡ መንፈሳዊ ህክምና ከሳይንሳዊ ህክምና በተጓዳኝ ለህመምተኞች ቢሰጥ ካጋጠማቸው ህመም የመፈወስ እድላቸውን ከፍ ሊያደርግ እንደሚችልም ባለሙያዎቹ ይመክራሉ፡፡
መንፈሳዊ ህክምና /Spirituality Therapy/ ከሳይንሳዊው ህክምና ባልተናነሰ መልኩ ለህሙማን የመንፈስ ጥንካሬና አጠቃላይ የአእምሮ ጤና ብሎም የተስተካከለ ህይወት የሚያበረከተው አስተዋፅኦ ከፍተኛ መሆኑ ይነገርለታል፡፡ ህክምናው ህመምተኞች በተለይም ከህይወታቸው ዓላማ ጋር እንዲስማሙ፣ በእምነታቸው እርግጠኛ እንዲሆኑና የሚያጋጥሟቸውን ሀዘንና ቀውሶች ለማስተካከል እንደሚያግዛቸውም ይገለፃል፡፡
ዶክተር ፅጌሬዳ ዳመነ በአለርት ማእከል የድንገተኛ ህክምና ክፍል የሰመመን ባለሙያ ናቸው፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት፤ ታማሚዎች ከመደበኛው ህክምና በተጨማሪ መንፈሳዊ ህክምና ቢያገኙ ከህመማቸው በቶሎ ከማገገም አልፈው ከአካላዊ ጉዳታቸውም ድነው ወደቀድሞው ሁኔታቸው መመለስ ይችላሉ፡፡
የድንገተኛ ህክምና ክፍል በአብዛኛው ሰዎች ድንገተኛና ያልተጠበቁ አደጋዎች ደርሶባቸው የሚመጡበት ቦታ በመሆኑና ታካሚዎችም በጭንቀትና ስቃይ ውስጥ ያሉ በመሆኑ መንፈሳዊ ህክምና ከሳይንሳዊው ህክምና ባልተናነሰ መልኩ ሊሰጥበት ይገባል፡፡ ለዚህ ደግሞ የሃይማኖት አባቶች በየጊዜው በማእከሉ በመገኘት የሚደርጉት ህሙማንን የማፅናናትና የማበረታታት ተግባር ጉልህ ሚና ይኖረዋል፡፡
‹‹ሁሉም ታማሚ የራሱ እምነት አለው›› የሚሉት ባለሙያዋ፣ የተለያዩ ሃይማኖት ተቋማት አባቶች በጤና ተቋማት መጥተው ሲጎበኙ ታማሚዎች ደስተኛ ከመሆናቸውም ባሻገር መንፈሰ ጠንካራና በቶሎ የመዳን ሁኔታ እንደሚታይባቸው ገልጸዋል፡ ፡ መንፈሳዊ ህክምና ከሳይንሳዊ ህክምና ባላነሰ መልኩ ለህሙማን መፈወስና ተስፋ ማግኘት ጉልህ አስተዋፅኦ ያለው በመሆኑ በሌሎች ሆስፒታሎች ላይም ሊሰፋና በየጊዜውም ሊሰጥ እንደሚገባም አመልክተዋል፡፡
በአለርት ማእከል የማህፀንና ፅንስ ስፔሻሊስት ሃኪምና የህክምና ክፍሉ ኃላፊ ዶክተር መንግስቱ ጉርሙ እንደሚገልፁት፤ እያንዳንዱ ሰው የጤና እክል ገጥሞት ለህክምና ወደ ማእከሉ ሲመጣ በህክምና ተቋሙ በሚያገኘው የህክምና አገልግሎት ብቻ ‹‹እድናለሁ›› ሊል አይችልም፡፡ ከዚህም በላይ ለመዳን ‹‹ፈጣሪ አለ›› ብሎ ያስባል፡፡ በመሆኑም ከሳይንሳዊው ህክምና ጎን ለጎን የመንፈሳዊ ህክምና ፋይዳ ጉልህ ነው፡፡
ኃላፊው እንደሚሉት፤ በአብዛኛው ማህበረሰብ ዘንድ ሃይማኖትና እምነት ከፍተኛ ተፅእኖ አለው። ይህ በመሆኑም በህክምና ተቋማት ውስጥ የሚገኙ አብዛኛዎቹ ተገልጋዮች አእምሯቸው አምኖበት በግልፅ ‹‹እኔን ለማዳን የሚደረግ ጥረትና ህክምና ነው›› ብለው መቀበል እንዲችሉ የሃይማኖት አባቶችን በመጠቀም እንዲያፅናኗቸውና እንዲያበረታቷቸው ማድረጉ ሳይንሳዊ ህክምናውን የበለጠ የተሳካ ያደርገዋል፡፡
መንፈሳዊ ህክምና ከሳይንሳዊው ህክምና ጎን ለጎን እንዲሰጥና በሌሎች ጤና ተቋማት ውስጥም እንዲስፋፋ ጤና ተቋማት በተለይም ሆስፒታሎች ትልልቅ ስራዎች የሚሰሩባቸው ናቸው፡፡ ሊታከሙ የሚመጡ ሰዎች እክል በገጠማቸው ሰዓት ብቻ ሳይሆን ገና ችግሩ ሳይገጥማቸው የህክምና አገልግሎቱን ማግኘት እንዲችሉና ምን አይነት ህክምናም እንደሚሰጥ እንዲያውቁ ብሎም መረጃ እንዲኖራቸው ከማህበረሰቡ ጋር ተቀራርቦ መስራት ያስፈልጋል፡፡
በዚህ ረገድ ከሃይማኖት ተቋማት ተውጣጥተው በመጡ የሃይማኖት አባቶች የሚደረጉ ጉብኝቶች ደግሞ በማህበረሰቡና የህክምና መስጫ ተቋማቱ መካከል እንደመገናኛ ድልድይ ሆነው ያገለግላሉ፡፡ ይህም በማህበረሰቡና በጤና ተቋማት መካከል ያለውን ግንኙነት በይበልጥ ያጠነክረዋል፡፡
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የብፁዕ ቅዱስ ልዩ ፅህፈት ቤት ኃላፊና የውጪ ጉዳይ የበላይ ኃላፊ ሊቀጳጳስ ብፁዕ ዶክተር አቡነ አረጋዊ መንፈሳዊ ህመም ከአካላዊና ስነልቦናዊ ህመም በላይ የከፋ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ይሁንና ሰዎች ለሚገጥማቸው የስነ አእምሮና ስነልቦና ህመም መንፈሳዊ ህክምና ሁነኛ መፍትሄ መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡ በተለይም ህሙማንን መጠየቅና ለህሙማን ክብር መስጠት ለህሙማንም ሆነ ለህክምና ባለሙያዎች ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለው ያስረዳሉ፡፡
‹‹ህሙማንን መጠየቅና ማበረታታት ሃይማኖታዊ ትእዛዝ ነው›› የሚሉት ኃላፊው፣ መንፈሳዊ ህክምና የሚሰጡ የሃይማኖት አባቶች በጤና ተቋማት ውስጥ በየጊዜው በመገኘት ጉብኝት ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ይገልፃሉ፡፡ ለዚሁ አላማ የተመደቡ አገልጋዮችም ህሙማንን ሁሌም እንዲጎበኙ የበለጠ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራበት ይገባል፡፡
እንደ ኃላፊው ገለፃ፣ መንፈሳዊ ህክምና ሁሉንም የመፈወስ አቅም ያለው በመሆኑ በአብዛኛው በስነልቦና የተጎዱና የመንፈስ ጭንቅት ያለባቸው ህሙማን ህክምናው ያስፈልጋቸዋል፡፡ አብዛኛዎቹ ህሙማንም የሃይማኖት ተከታዮች እንደመሆናቸው መጠን መንፈሳዊ ህክምናውን ከምንም በላይ ይፈልጉታል፡፡
በመሆኑም ህክምናው ተጠናክሮ እንዲቀጥልና መንፈሳዊ አባቶች በማስተማርና በመምከር እንዲሁም ቃለ እግዚአብሔርን በማካፈል ህሙማንን ማፅናናትና ማበረታታት ይገባቸዋል፡፡ ሰው ስጋዊ አካል እንዳለው ሁሉ መንፈሳዊ አካልም ያለው በመሆኑ መንፈሱ እንዲረጋጋና ውስጣዊ ሰላምና ተስፋ እንዲኖረው፣ በቁሳዊ ዓለም ብቻ ሳይሆን በመንፈሳዊ ዓለምም ተስፋ እንዲያደርግ ትልቅ ማበረታቻ ስለሚሆን ህክምናው በሁሉም ሆስፒታሎች መዘውተር ይገባዋል። ቤተክርስቲያንም የመንፈሳዊ ህክምና ማእከል እንደመሆኗ መጠን በፀሎት፣ በመስቀልና በቃለ እግዚአብሔር ስጋዊም ሆነ መንፈሳዊ አካልን መፈወስና ማዳን ትችላለች፡፡
ከአርባና ሃምሳ ዓመት በፊት መንፈሳዊ ህክምና በኢትዮጵያ በእያንዳንዱ ጤና ተቋማት ውስጥ ይሰጥ እንደነበርና የንሰሃ አባቶችም በሆስፒታሎች በመገኘት ህሙማንን እንደሚያፅናኑ የሚጠቅሱት ኃላፊው፣ ይህ በጎ ተግባር የበለጠ ቢጠናከር ህዝቡን በስነ ምግባር፣ በጤናም በመንፈስም የማረጋጋት ስራዎችን መስራት እንደሚቻል ይጠቁማሉ፡፡
የኢትዮጵያ እስልምና ጠቅላይ ምክር ቤት የቦርድ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መሃመድ አብዱል እንደሚሉት ደግሞ፤ ህሙማንን መጎብኘትና መንከባከብ ሞራላዊና ሃይማኖታዊ ግዴታ ነው፡፡ የሃይማኖት አባቶች በሆስፒታሎች ውስጥ በመገኘት ህሙማንን መጎብኘታቸውና የመንፈስ ጥንካሬ እንዲፈጠር ማድረጋቸው በበጎ ይታያል፡፡
እንደ ሰብሳቢው ገለፃ፤ አንድ ሰው የመዳን ተስፋ ሲኖረው ተስፋውን የሚያገኘው ከፈጣሪው በመሆኑ የመንፈሳዊ ህክምና ጠቀሜታው የጎላ ነው። ታማሚው ከፈጣሪው እምነት ካገኘ ከመደበኛው ህክምና ባሻገር መንፈሳዊ ህክምናም ስለሚያገኝ የመዳን እድል ይኖረዋል፡፡ የሃይማኖት አባቶች መጥተው ሲጎበኙትና ሲፀልዩለት ደግሞ የመዳን ተስፋው የበለጠ ይለመልማል፤ ከፍ ያለ ሞራልም ያገኛል፡፡
ሰብሳቢው እንደሚሉት፤ መንፈሳዊ ህክምናው ተጠናክሮ እንዲቀጥልና በሌሎችም ሆስፒታሎች ውስጥ እንዲሰፋ እያንዳንዳቸው የሃይማኖት ተቋማት አባቶች ቋሚ መርሃ ግብር ይዘው በተቀናጀ ሁኔታ በተወሰኑ ጊዜያት ውስጥ በየሆስፒታሎች ውስጥ እየዞሩ በመንፈሳዊ ህክምና አስተዋፅኦ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ የሃይማኖት ተቋማትም ለዚህ ጉዳይ ትኩረት ሰጥተው ለመስራት ዝግጁነታቸውን ማሳየት ይኖርባቸዋል፡፡ በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ ሳይሆን በሁለትና በሶስት ወር ጊዜ ውስጥ ወደጤና ተቋማት በመሄድ ህሙማንን ማበረታታትና መንፈሳዊ ህክምና መስጠት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ህሙማንን ብቻ ሳይሆን የተቸገሩትንም መርዳት ያስፈልጋል፡፡
በኢትዮጵያ በቀደሙት ዓመታት የሃይማኖት አባቶች በተለይ በበዓል ቀናት በጤና ተቋማት በመገኘት ህሙማንን የመጠየቅና የማበረታታት ልምድ የነበራቸው ቢሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ይህ በጎ ተግባራቸው እየቀዘቀዘ መምጣቱ በሁሉም ዘንድ ይታወቃል፡፡
ይሁንና የአለርት ማእከል በራሱ ተነሳሽነት የሃይማኖት አባቶች ህሙማንን እንዲጠይቁና እንዲያፅናኑ ብሎም እንዲያበረታቱ የማድረጉን ተግባር ከዓመት በፊት የጀመረ ሲሆን፣ ዘንድሮም ለሁለተኛ ጊዜ የሃይማኖት አባቶች በሆስፒታሉ ተገኝተው ታማሚዎችን እንዲጎበኙ አድርጓል፡፡ ይህም ህሙማን ከሳይንሳዊ ህክምና በተጨማሪ መንፈሳዊ ህክምናን እንዲያገኙ የሚያስችል በመሆኑ ሌሎች ሆስፒታሎችም ይህን አርያነት ያለው ተግባር ወስደው ተግባራዊ ያደርጉታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
አዲስ ዘመን ነሐሴ 28/2011
አስናቀ ፀጋዬ