
አዲስ አበባ፦ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሀገሪቷ የመጀመሪያ የሆነውንና የተሟላ ከወለድ ነፃ አገልግሎት መስጫ ቅርንጫፉን ሊከፍት መሆኑን አስታወቀ።
የባንኩ የወለድ ነፃ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ኑሪ ሀሰን ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፣ ባንኩ እስከ ዛሬ ድረስ በመስኮት ደረጃ ሲሰጥ የነበረውን አገልግሎት በማሳደግ በአዲስ አበባ ከተማ ቦሌ ሚካኤል አካባቢ ቢላል ቅርንጫፍ በሚል ጳጉሜ 2 ቀን 2011 ዓም ይከፍታል ብለዋል።
ከወለድ ነጻ የአገልግሎት ቅርንጫፉን መክፈት ያስፈለገው የደንበኞችን ፍላጎት መሰረት በማድረግ ነው ያሉት ምክትል ፕሬዚዳንቱ በተጨማሪም ባንኩን በወለድ አልባ መስኮቶች የተቀማጭ አገልግሎትን በመስጠት ቀዳሚ እንደሚያደርገውም ተናግረዋል።
ባንኩ በአሁኑ ወቅት በ1ሺ 382 ቅርንጫፎች 1ሺ 894 መስኮቶችን በመክፈት በመላው ሀገሪቱ አገልግሎቱን እየሰጠ መሆኑን ተናግረው በወለድ ነፃ አገልግሎት ተቀማጭ የሆነው የገንዘብ መጠንና የደንበኞች ቁጥር ዓመታዊ እድገቱ ከፍተኛ ከመሆኑም በላይ ከባለ ወለድ አገልግሎት ይበልጣል ብለዋል።
ምክትል ፕሬዚዳንቱ ጨምረው በአሁኑ ወቅት ከወለድ ነፃ አገልግሎት በሚሰጡ መስኮቶች አማካኝነት 23ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ተቀማጭ የተደረገ ሲሆን የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ቁጥርም ከሁለት ሚሊዮን በላይ መድረሱን ጠቁመዋል።
በቀጣይም ባንኩ የወለድ ነፃ አገልግሎት ፍላጎት ያለባቸውን አካባቢዎች በመለየት በአዲስ አበባ ከተማ 10 እንዲሁም በክልል ከተሞች 44 ተጨማሪ ቅርንጫፎችን ለመክፈት ዝግጅቱን ማጠናቀቁን ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከወለድ ነፃ አገልግሎትን በመስኮት ደረጃ መስጠት የጀመረው በ 2005 ዓ.ም በ26 ቅርንጫፎች ነበር።
አዲስ ዘመን ነሃሴ 29/2011
ቢላል ደርሶ