
አዲስ አበባ፡- የኩላሊት ህመምተኞችን በቋሚነት ለመደገፍና በነጻ ህክምና የሚያገኙበትን ሁኔታ ለማመቻቸት በኢትዮጵያ ለሚገኙ ለሁሉም ሥራ አስኪያጆች አገራዊ ጥሪ ቀረበ፡፡
የኩላሊት ህመምተኞች እጥበት በጎ አድራጎት ድርጅት “ድጋፍ ለኩላሊት ህሙማን” በሚል መሪ ሃሳብ በትናንትናው ዕለት ባዘጋጀው አገር አቀፍ ንቅናቄ የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን አሰፋ፤ ለህሙማኑ የሚያስፈልገው ህክምና ዋጋው በየጊዜው እየጨመረ በመምጣቱ ለተባባሪዎች ጥሪ ማድረግ ማስፈለጉን ተናግረዋል፡፡
ድርጅቱ ባለፉት ሰባት ዓመታት ለህብረተሰቡ ግንዛቤ በመስጠትና የሚሰጠውን ህክምና በገንዘብ በመደገፍ ህመምተኞችን ለመርዳት የበኩሉን አስተዋፅኦ ሲያደርግ መቆየቱንና በቅርቡም ከባንኮች ጋር በመተባበር በዘውዲቱና በዳግማዊ ምኒልክ መታሰቢያ ሆስፒታሎች ዘጠና የሚደርሱ የኩላሊት ህሙማን ሙሉ በሙሉ በነጻ የሚታከሙበትን ዕድል ማመቻቸቱን አቶ ሰለሞን ገልጸዋል፡፡
አቶ ሰለሞን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለህሙማኑ ህክምና የሚያስፈልገው ወጪ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ መምጣቱንና ከዚህ ቀደም በወር አሥራ ስምንት ሺ ብር የነበረው የኩላሊት እጥበት ወጪ በአሁኑ ሰዓት እስከ ሃያ ሁለት ሺ ብር መድረሱን አመልክተዋል፡፡
አቶ ሰለሞን ‹‹ወጪው በበጎ አድራጎት ድርጅቶች ብቻ የማይቻል በመሆኑ በአገሪቱ የሚገኙ ሁሉም ሥራ አስኪያጆች በሥራቸው የሚገኙ ሠራተኞቻቸውን በማስተባበር ሠራተኛው ከደመወዙ በየወሩ እያስቆረጠ ድጋፍ የሚያደርግበትንና ፔሮል ላይ ተተክሎ ህሙማኑ በቋሚነት የሚደገፉበትን ሁኔታ እንዲያመቻቹልን ለሁሉም ሥራ አስኪያጆች አገራዊና ወገናዊ ጥሪያችንን እናቀርባለን›› ብለዋል፡፡
የበጎ አድራጎት ድርጅቱ የቦርድ ሰብሳቢ ኢንጅነር ሳሙኤል ይርጋ በበኩላቸው፤ በሌሎች በርካታ የአፍሪካ አገራት መንግሥትና ህብረተሰቡ በመተባበር የኩላሊት ህሙማን በነጻ ህክምና የሚያገኙበት ሁኔታ መኖሩን አመላክተው፤ “በእኛም አገር ሁላችንም ከተባበርንና የምንችለውን ካደረግን ህሙማኑን ለማገዝና ህክምናቸውን በነጻ የሚከታተሉበትን ሁኔታ መፍጠር ይቻላል” ብለዋል፡፡
ሁሉም ህብረተሰብ የበኩሉን አስተዋጽኦ ማድረግ የሚገባው መሆኑን የገለጹት የቦርድ ሰብሳቢው፤ በተለይም መንግሥታዊም ይሁን መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና ልዩ ልዩ ተቋማት በሥራቸው የሚተዳደረውን ሠራተኛ በማሳመንና በሚችለው አቅም ህሙማኑን በዘላቂነት እንዲደግፍ በማድረግ ረገድ ትልቅ ሚና ሊጫወቱ እንደሚችሉ ያላቸውን ዕምነት ገልጸዋል፡፡
በአገራዊ ንቅናቄ መርሐ ግብሩ ታዋቂው አንጋፋ የዜማ ደራሲ አርቲስት አበበ መለሰ፣ ድምጻዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮን)፣ የበርካታ ታላላቅ ድምጻውያንን ሥራዎች ውስጥ የሚታወቀው ወጣቱ የሙዚቃ አቀናባሪ አማኑኤል ይልማና ታዋቂው የፊልም ተዋናይ አርቲስት ግሩም ኤርምያስን ጨምሮ በርካታ ታዋቂ ሰዎችና የጥበብ ሰዎች ተገኝተው መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
አርቲስቶቹ የሚችሉትን ሁሉ በማድረግ በሙያቸው ህሙማኑን ለመደገፍ ቃል ገብተዋል፡፡ ህብረተሰቡም ለኩላሊት ህመምተኞች የቀረበውን አገራዊ ድጋፍ ተቀብሎ በህመም የሚሰቃዩ ወገኖቹን ለመደገፍ የሚችለውን እንዲያደርግ ለሁሉም ኢትዮጵያውንና ለሥራ አስኪያጆች መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
የአገሪቱ ሥራ አስኪያጆች አገራዊ ጥሪውን ተቀብለው በፍጥነት ወደ ተግባር ከገቡና በቁርጠኝነት ከተንቀሳቀሱ ከሚቀጥለው የመስከረም ወር መጨረሻ ጀምሮ ሁሉም ህሙማን ህክምናቸውን በነጻ የሚያገኙበት አሰራር ይጀመራል የሚል ሙሉ ዕምነት እንዳላቸው የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን አሰፋ ተናግረዋል፡፡
አዲስ ዘመን ነሃሴ 29/2011
ይበል ካሳ