
2 ቢሊዮን ብር ሰብስቦ አንድ ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ብር ዕዳ ከፍሏል
– በሀሰት የትምህርት ማስረጃ 80 ሠራተኞቹንም አባሯል
ቢሾፍቱ፤- የቢሾፍቱ አውቶሞቲቭ ኢንጅነሪንግ ኢንዱስትሪ የምርቱ ተፈላጊነት ቢጨምርም በውጭ ምንዛሪ ችግር የሚፈለገውን ያህል እያመረተ እንዳልሆነ ገልጸ። ባለፈው በጀት ዓመትም 2 ቢሊዮን ብር ሰብስቦ አንድ ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ብር ዕዳ መክፈሉንም አሳውቋል።
በኢንዱስትሪው የግብይትና ሽያጭ ኃላፊ ሃምሳ አለቃ ባህሩ ዳባ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፣ ኢንዱስትሪው አውቶብስና ገልባጭ ተሽከርካሪዎችን በቀን በሦስት ፈረቃ 24 እንዲሁም ቀላል ተሽከርካሪዎችን 18 የማምረት አቅም አለው። ይሁን እንጂ በውጭ ምንዛሪ ችግር ላይ በቀን እያመረትን ያለነው 5 አውቶብሶችን ነው።
‹‹ምርቶቻችን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ የመንግሥት ሠራተኞች ፐብሊክ ሰርቪስ፣ የተለያዩ የከተማ አስተዳደሮች፣ የግል ድርጅቶችና ግለሰቦች ለመግዛት ውል ቢገቡም በውጭ ምንዛሪ ችግር ፍላጎታቸውን ለማርካት እንዲሁም ባለፈው ዓመት ለማምረት ውል የገባናቸውን ምርቶች ሙሉ ለሙሉ አምርተን ማስረከብ አልቻልንም›› ብለዋል።
እንደ ሃምሳ አለቃ ባህሩ ገለጻ፣ በ2012 በጀት ዓመት በቀን ወደ 10 ተሽከርካሪ ከፍ በማድረግ 472 አውቶብሶች፣ 150 ገልባጮችን፣ 350 አነስተኛ ተሽከርካሪዎችን በድምሩ 832 ተሽከርካሪዎችን በማምረት ከ2ነጥብ5 እስከ 3 ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ አቅደዋል። ሆኖም ከሚያስፈልጋቸው 20 ሚሊዮን ዶላር እስካሁን የተፈቀደላቸው 5ነጥብ2 ሚሊዮን ዶላር በመሆኑ ‹‹ስጋት ገብቶናል›› ሲሉ ተናግረዋል።
የኢንዱስትሪ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሌተናል ኮሎኔል ቢቂላ በቃና በበኩላቸው፤ ኢንዱስትሪው በዓመቱ ውስጥ ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ ሰብስቦ አንድ ነጥብ7 ቢሊዮን ብር ዕዳ እንደከፈለ አስታውቀዋል።
እንደ ኮሎኔል ቢቂላ ማብራሪያ፣ ከገቢዎችና ጉምሩክ ጋር የተያያዘ ዕዳ መንግሥት ሊሰርዝ፣ አንዳንዶቹ ደግሞ ወደ ‹‹አሴት›› ሊቀይር ይገባል። ከዚህም በተጨማሪ መንግሥት የውጭ ምንዛሪ ችግር መፍታት አለበት። እስካሁን ዕዳ በመክፈል ላይ ነው ያሉት። እነዚህ ችግሮች ካልተፉቱ የልማት ድርጅት ሆኖ መቀጠል አይቻልም።
ከሰባት እስከ አራት ዓመት ሳይሸጡ የቆሙ 600 ሚሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው 272 ተሽከርካሪዎች በግቢው ይገኛሉ ያሉት ኮሎኔል ቢቂላ፣ ዋጋቸው ቀንሰው መሸጥ ስለማይችሉ መንግሥት በተሽከርካሪዎቹ ላይ ውሳኔ ማሳለፍ አለበት ብለዋል። ለከፋ ብልሽት ከመዳረጋቸው በፊት የጎደላቸውን እቃ በማሟላት ከዋጋቸውም በታች መሸጥ እንደሚገባም ተናግረዋል።
እንደ ዋና ሥራ አስኪያጁ ማብራሪያ፣ ተቋሙን ካለበት የችግር አረንቋ ለማውጣት የተለያዩ ሥራዎች ማከናወን ተጀምሯል። እንደ ኢንዱስትሪ ችግሮቹን ለመፍታት ከደንበኞቻቸው ጋር ተወያይተዋል። ከደንበኞች ቅሬታ በመነሳት የዋጋ፣ በጊዜ የማስረከብ፣ የጥራትና የድህረ ሽያጭ አገልግሎት አሻሽለዋል።
ከመመሪያ ውጭ ለሙስና የሚያጋልጥ ግዥን አስቀርተናል ያሉት ዋና ሥራ አስኪያጁ፣ በንዑስ አምራቾች በኩል ይካሄድ የነበረውን ምዝበራ ለማስቀረት ከመመሪያ ውጭ ግዥን አግደናል ሲሉ አመልክተዋል።
ተቋሙ ምን ያህል ተሰብሳቢ፣ ተከፋይ በአጠቃላይ ምን ያህል ሀብት እንደነበረው አያውቅም ነበር። አሁን ላይ በተሰራው ሥራ መቶ በመቶ ባይጠናቀቅም የሀብቱንና የእዳውን መረጃ ተጠናክሮ አልቋል ብለዋል።
በ2011 በጀት ዓመት እስከ ህዳር ወር ድረስ ኢንዱስትሪው ምርት አያመርትም በሚባል ደረጃ ነበር ያሉት ሥራ አስኪያጁ፣ከህዳር መጀመሪያ ጀምሮ ወደ ሥራ በመግባትም በዓመቱ 800 ተሽከርካሪዎችን አምርቶ ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ ሽያጭ ማከናወኑን አመልክተዋል። የ2010 በጀት ዓመት ሲጠናቀቅ ኢንዱስትሪው 57 ሚሊዮን ብር ኪሳራ የነበረበት መሆኑን አስታውሰው፣ በ2011 በጀት ዓመት ግን ሙሉ በሙሉ ከኪሳራ መውጣቱን አመልክተዋል።
ኢንዱስትሪው ከ3ሺ400 በላይ የሰለጠነ የሰው ኃይል እንዳሉት የጠቀሱት ሌተናል ኮሎኔል ቢቂላ፣ሀሰተኛ ትምህርት ማስረጃ የተገኘባቸውን 80 ሠራተኞች ማባረራቸውን ገልጸዋል።
የሠራተኛውን የደመወዝ ጥያቄ ሠራተኛው በሚያ መጣው ውጤት መሰረት ለመክፈል እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፣ ዘንድሮ ሠራተኞች ድርጅቱ ከሚያገኘው ትርፍ ክፍፍል ያደርጋሉ ሲሉ አስታውቀዋል።
‹‹የሠራተኞች ማህበራት እያደራጀን ነው። ሠራተኛውም ተቋሙን ‹የእኔ ነው› የሚል አስተሳሰብ እየፈጠረ ነው። ከሠራተኞች አያያዝ ጋር ያለውን የመልካም አስተዳደር ችግር ለመፍታት የተለያዩ ሥራዎች እየተሰሩ ነው›› ብለዋል።
አዲስ ዘመን ነሃሴ 29/2011
አጎናፍር ገዛኸኝ