
አዲስ አበባ፤ በአራዳ ክፍለ ከተማ ስር በሚገኙ ጽህፈት ቤቶች የሚሰሩ ፈጻሚዎች ምቹ የሥራ ሁኔታ እንዲፈጠርና ግልጽነት የሰፈነበት አሰራር እንዲሰፍን ጠየቁ፡፡
ለዝግጅት ክፍሉ ቅሬታቸውን ያቀረቡት በክፍለ ከተማው የተለያዩ ጽህፈት ቤቶች የሚሰሩ ባለሙያዎች፤ ቀድሞ ከነበሩበት ቢሮ ቀይረው ወደ አዲሱ ህንጻ ሲገቡ ምንም አይነት የቢሮ ዕቃዎች ይዘው እንደማይሄዱ ለጽህፈት ቤቶች ቢነገራቸውም ሲገለገሉበት የነበረውን ወንበርና ጠረጴዛ ይዘው እንዲገቡ መደረጉን፤ ለቢሮ ዕቃዎች ግዢ ጨረታ ቢወጣም ተደጋጋሚ ጊዜ መሰረዙ ተገቢ እንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡
የጨረታ ኮሚቴ እያለ ሌላ ጨረታ ኮሚቴ መዋቀሩ ትክክል እንዳልሆነ ፤ ሌሎቹ ክፍለ ከተሞች ለመረጃ ግብዓትነት የሚጠቅሙባቸው ዓይነቶች መሳሪያዎች በአራዳ ክፍለ ከተማ ላይ እስካሁን አለመተከሉ አግባብ እንዳልሆነ፤ ህንጻው ሁለት ጊዜ በመመረቁ ለከፍተኛ ወጪ መዳረጉንም ቅሬታ አቅራቢዎቹ ጠቅሰዋል፡፡
የአራዳ ክፍለ ከተማ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አበባ እሸቴ፤ ለሠራተኞችና ለባለጉዳይ ምቹ የሆኑና ቦታ ሳይባክን በማደራጀት አገልግሎት መስጠት የሚያስችሉ እቃዎች በተፈለገው መስፈርት መሰረት ባለመደራጀታቸው እንዲሁም ባለመቅረባቸው ምክንያት ጨረታን ለመሰረዝ ምክንያት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ወንበርና ጠረጴዛ ይዛችሁ አትምጡ ያልነው ተጨማሪ ወጪ እንዳይኖር በማሰብ ነው፡፡ የቢሮ ዕቃዎች ግዢ በግልጽ ጨረታ እየተካሄደና ከአገር ውጭ ግዢ የተፈጸመ በመሆኑ ሂደቱ ለመዘግየቱ ምክንያት እንደሆነም ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ተናግረዋል፡፡
የጨረታ ኮሚቴ እያለ ሌላ የጨረታ ግዢ ኮሚቴ ተቋቁሟል የተባለው ስህተት መሆኑን በመጠቆምም፤ የተጨመረው መደበኛ የጨረታ ሥራውን ከሚሰራው ኮሚቴ በተጨማሪ እቃዎቹ በተቀመጠው መስፈርት መሰረት መመረጣቸውን የሚቆጣጠሩ በቂ ልምድ ያላቸው የግዢ ባለሙያዎች የተወከሉበት የቴክኒክ ኮሚቴ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ህንጻው ሁለቴ የተመረቀው ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ የወጣባቸው 80 ፕሮጀክቶች እንዲመረቁ በማድረግ ከሠራተኛው የተወከሉና ከክፍለ ከተማው 10ሩም ወረዳዎች የተውጣጡ ነዋሪዎች በመጋበዝ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ እንዳወቅ አብቴ በተገኙበት ለሚገባቸው ሰዎች እውቅና ለመስጠትና ሽልማት ለማበርከት መሆኑን ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ተናግረዋል፡፡
ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ‹‹በሂደቱ ህንጻ ምርቃት የተደረገ ስለመሰላቸው ህንጻ ውስጥ ገብተን የምንሰራው እኛ ሆነን ሳለ ለህንጻው ምርቃት አልተጠራንም›› በሚል ቅሬታ እንዳደረባቸው አንስተው፤ ሠራተኞች ማነቃቃት አንዱ እቅድ ስለነበር በእዚህ መነሻነት የሲቪል ሰርቪስ ቀንን ምክንያት በማድረግ በግቢውና ከግቢ ውጪ የጽዳት ዘመቻና የችግኝ ተከላ መርሐ ግብሮች መደረጉን ጠቁመዋል፡፡
የፋይናንስ ህግና አሰራርን በጠበቀ መንገድ ሠራተኞችን ለመጋበዝና ለማስደሰት ወስነናል ያሉት ኃላፊዋ፤ ለድግስ የወጣው ገንዘብ እጅግ አነስተኛ ነው፤ ይህ በዓመቱ ከሰራናቸው ሥራዎች ውስጥ በጥሩ ጎኑ የሚነሳ፣ በአመራሩና በሠራተኞች መካከል መግባባትንም የፈጠረ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ለተጠቃሚዎች ዝርዝር መረጃ ማስተላለፊያ መሳሪያ ግልጽ ጨረታ መካሄዱንና በግዢ ሂደት ላይ እንደሆነ ለማወቅ ችለናል፡፡
አዲስ ዘመን ነሃሴ 29/2011
ዘላለም ግዛው