
አዲስ አበባ፡- ለጌጥ ተብሎ የተለጠፈው እብነ በረድ እየወደቀ በመሆኑ ወደ ህንጻው በሚገቡና በሚወጡ ተገልጋዮችና ሠራተኞች ላይ ወድቆ አደጋ ሊያደርስ ስለሚችል ፈጣን መፍትሄ ሊሰጠው እንደሚገባ የአራዳ ክፍለ ከተማና ሠራተኞቹ አሳሰቡ።
የአራዳ ክፍለ ከተማ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አበባ እሸቴ በተለይ ለጋዜጣው ሪፖርተር እንደገለጹት፤ ለኮንስትራክሽን ቢሮና ለፐብሊክ ሰርቪስ ጽህፈት ቤት ከተገነባው ህንጻ በሚወድቀው እብነ በረድ ምክንያት ጉዳት እንዳይከሰት የማረሚያ ሥራ እንዲሰራ በተደጋጋሚ ቢጠይቁም አፋጣኝ ምላሽ አልተሰጣቸውም።
ህንጻውን በበጋ ወቅት ስለተረከቡ በወቅቱ ፍሳሽ እንዳልነበረ የተናገሩት ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አበባ ፤ ክረምት ላይ ፍሳሽ መኖሩን መመልከታቸውን ገልጸው፤ የህንጻውን የፍሳሽ ችግሮች የማስተካከል ሥራ መሰራቱንም ተናግረዋል።
ዘጠኝ የተለያዩ ቦታዎች ተበታትነን ስለምንገኝ፣ ከፍተኛ የቢሮ ችግርም ስላለብን፣ ለህንጻው አስፈላጊ ነገሮች በመሟላታቸውና የመጀመሪያ ርክክብ በመደረጉ ባለው ሁኔታ ገብተው እየሰሩ ሌሎች ቀሪ የግንባታ ሥራዎች መቀጠል እንደሚችሉ ከኮንስትራክሽን ቢሮ ጋር ተነጋግረው ወደ ህንጻው ለመግባት መወሰናቸውን የገለፁት ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ፤ ደንበኞችን እያስተናገዱ ክፍሎችን የመከፋፈል ሥራም እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።
የአዲስ አበባ ኮንስትራክሽን ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ አፈወርቅ ንጉሴ፤ የተጣበቀው ጥቁር እብነ በረድ የመውደቅ አዝማሚያ ሌሎች ክፍለ ከተሞች ላይም መታየቱንና ችግሩ ለምን እንደተከሰተ የህንጻ ግንባታው አማካሪ ድርጅት አጥንቶ እንዲያሳውቅ ትዕዛዝ ተሰጥቷል፤ ሪፖርቱ እንደደረሰን እናሳውቃለን ብለዋል።
ህንጻው የመጀመሪያ ርክክብ ሲደረግ ያን ያህል የከፋ ችግር አልነበረበትም ያሉት ምክትል ቢሮ ኃላፊው ፤ በተለይ ጥቅም ላይ የዋለው ማጣበቂያ ኬሚካል የዝናብ ወቅት በመሆኑ እርጥበት ሲሰማው እብነ በረዱ እየፈረሰ የመውደቅ አደጋ እንዳጋጠመው ተናግረዋል።
በአገር ውስጥ በተሰራው እና ከውጭ አገር በመጣው እብነ በረድ መካከል ልዩነት መታየቱን የገለፁት ምክትል ቢሮ ኃላፊው ፤ ከውጭ አገር የመጣው እብነ በረድ ችግር እንዳለበት፣ እርጥበት በሚያገኘው ሰዓት አደጋው መብዛቱንና በውሉ መሰረት ተቋራጩና አማካሪው ድርጅቶች የማስተካከል ኃላፊነት እንዳለባቸው ጠቁመዋል።
ፕሮጀክቱን የሰራው የአፍሮ ጺዮን ኮንስትራክሽን ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ላይችሉህ መጨጊያው፤ ፕሮጀክቱ ተጠናቅቆ ርክክብ መደረጉን ጠቁመው፤ የህንጻ ጥራት ችግር እንዳልሆነና ግንባታው በተቀመጠለት መስፈርት መጠናቀቁን ገልጸዋል።
ዲዛይኑ በጸደቀበት ግብዓት ከውጭ አገር ገብቶ በሚመለከተው አማካሪ መሐንዲስ ጸድቆ ባግባቡ ተሰርቷል፤ ከአማካሪ መሐንዲሱና ከፕሮጀክቱ ባለቤት ጋር በመሆን በጋራ መፍትሄ ለመስጠት ጥረት እየተደረገ በመሆኑ ትልቅ ችግር ሆኖ የሚነሳ እንዳልሆነ አቶ ላይችሉህ ገልጸዋል።
ጥናቱ ገና አላለቀም ያሉት አቶ ላይችሉህ ፤ ምናልባት እብነ በረዱ ጥቁር በመሆኑ ሙቀት በቀላሉ ስቦ የመወጠር ባህሪ የሚይዝና አካባቢው ከፍተኛ የንፋስ አቅጣጫ ያለበት በመሆኑም ንፋስ በቀላሉ ሊጥለው ይችላል የሚል የተለያዩ መላምቶች እንዳሉ ተናግረዋል።
የፕሮጀክቱ አማካሪ ኤም.ጂ. ኤም ኮንሰልት ረዘደንት ኢንጂነር ወንድሙ ጉዲሳ፤ ጥቁር እብነ በረድ በተቀመጠው መስፈርት መሰረት ከውጭ አገር መግባቱንና በቢሮአቸው በኩል በባለሙያዎችና በኮንስትራክሽን ቢሮ በኩል በዲዛይን ዘርፍ ተረጋግጦ ሥራ ላይ መዋሉን ተናግረዋል።
ኢንጂነር ወንድሙ ጥቁሩ እብነ በረድ በሚጣበቅበት በኩል ያለው ፋይበር አገር ውስጥ ካለው ማጣበቂያ ጋር ግድግዳው ላይ ሲገናኝና ሙቀት ሲያገኝ ከተሰራ ከሶስት ወራት በኋላ እየተቀረፈ መውደቅ መጀመሩን ተናግረዋል።
በተመሳሳይ በቦሌ፣ በጉለሌ፣ በተወሰነ መልኩ በቂርቆስና አቃቂ ክፍለ ከተሞች ላይ ችግሮች የታዩት ከውጭ አገር በገቡ ግብዓቶች ላይ ብቻ መሆኑን ኢንጂነር ወንድሙ ጠቅሰው፤ በአገር ውስጥ ምርት የተሰሩት ችግር እንዳልገጠማቸው ጠቁመዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ የአራዳ ክፍለ ከተማ ህንጻ ግንባታ የተጀመረው እ.ኤ.አ ኖቬምበር 09 /2015 ሲሆን፤ አጠቃላይ 730 ቀናት የውለታ ጊዜ ቢኖረውም፤ በጊዜው ባለማለቁ ርክክብ የተደረገው ከሁለት ዓመት በላይ ዘግይቶ ኦክቶበር 28/2019 ነው። በጥቅሉም ወደ 334 ተጨማሪ ቀናት ፈጅቷል። የወሰን ማስከበር ችግር፣ ዲዛይን በወቅቱ አለመቅረብ፣ ግብዓት በወቅቱ አለመጽደቅ ለመዘግየቱ በምክንያትነት ይጠቀሳል።
አዲስ ዘመን ነሃሴ 29/2011
ዘላለም ግዛው