
በየአካባቢው ያሉ በግልፅ የተነገሩም ሆነ ውስጥ ለውስጥ የሚብላሉ የቂምና የቁርሾ እሾኮችን ከስራቸው መንግሎ በይቅርታና በመተማመን መንፈስ ለመቀጠል የእርቀ ሰላም ኮሚሽን ወደስራ መግባቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ በዓመቱ ማጠናቀቂያ ሪፖርታቸው መናገራቸው ይታወቃል። በሰላም ጉዳይ በግንባር ቀደምትነት ጉልህ ሚናቸውን ሊጫወቱ የሚችሉት ደግሞ የኃይማኖት ተቋማት ስለመሆናቸው አያጠያይቅም።
እርቀ ሰላሙ ስኬታማ ይሆን ዘንድ ኮሚሽኑን ከመደገፍና በየቤተ እምነቶች እየተካሄደ ባለው ስብከትም ሆነ ትምህርት እየተደረገ ስላለው እንቅስቃሴ አስተያየታቸውን ለአዲስ ዘመን የሰጡ የሃይማኖት አባቶች እንደገለፁት፤ ሰላምን መስበክና ስለ ሰላም ማስተማር የሁል ጊዜ ስራ በመሆኑ ኮሚሽኑ ይዞት ለተነሳው ዓላማ ተግባራዊነት ዝግጁዎች ናቸው።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ፅህፈት ቤት የሚሰሩትን የቲዮሎጂ መምህር የሆኑትን መምህር ዳንኤል ሰይፈ ሚካኤል እንደሚሉት፤ በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ውስጥ የእርቅ ስራ የማያቋራጥ ስራ ነው። እያንዳንዱ ቅዳሴም የማስታረቅ አገልግሎት ነው ማለት ይቻላል። ቤተ ክርስትያንም ሰላምና እርቅ ዋና ተግባሯ ነውና ይህን ለማድረግ የሚከብዳት አሊያም እንደ ጫና የምታየው አይሆንም።
መምህር ዳንኤል፣ ‹‹እንደ ቤተ ክርስትያን ሳስብ አንድን የማስታረቅ ስራ ስንሰራ የምንከተላቸው ነገሮች አሉ። የመጀመሪያ ትልቁ ነገር ሰዎች ንፁህ ነኝ ብለው ማመን የለባቸውም። ምክንያቱም ሁሉም ሰው አጥፊ መሆኑን መረዳት አለበት። ሰው መሳሳቱን ካላመነ እርቅ መፈፀም አይቻልም። አንድ ሰው እኔ ትክክል ነኝ ብሎ ካመነ መጀመሪያውኑ ልቡ ለእርቅ ዝግጁ አይደለም። ስለዚህ ሁሉም ሰው ለይቅርታና ለፍቅር ልቡን ማዘጋጀት አለበት። ›› ይላሉ።
እርሳቸው እንደሚሉት፤ ቤተ ክርስትያኗ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባዔዋ አማካይነት ሰላምንና እርቅን የሚመለከት ኮሚቴም አዋቅራለች። በሊቀጳጳስ የሚመራ ሌሎች ጳጳሳትና ሊቃውንት ያሉበት የእርቀ ሰላም ኮሚቴ ተቋቁሟል። በተጨማም ደግሞ ቤተ ክርስትያኗ ዘመቻ እያካሄደች ነው።የተለያዩ ጉባኤዎችን እያዘጋጀች ነው። ባለፈው ዓመት ብቻ ሁለት ጊዜ ከ30 በላይ በአህጉረ ስብከቶች ተዙሮ ስለ ሰላም ስለእርቅ ትምህርት ተሰጥቷል።ፀብ፣ ጥላቻና ቂም ካሉ ሰላም የለም። ሰላም እንዲኖር የተከሸኑ ቃላትን በመጠቀም መናገር ሳይሆን ስራን ወደ ተግባር መቀየር አስፈላጊ ነው።ስለዚህም ከኮሚሽኑ ጎን በመቆም የያዘውን አጀንዳ ለመደገፍ ቤተ ክርስትያኗ ዝግጁ ናት።
‹‹ትዕቢትና ትምክህት የዲያቢሎስ ነው። በበቀል፣ በጠብና በቂም ውስጥ ያሉ ሰዎች እስረኞች ናቸው። የሚያስታርቁ ሰዎች ደግሞ ነፃ አውጪ ናቸው።ስለዚህም ኮሚሽኑ ነፃ አውጪ ነው ብዬ አምናለሁ። ነፃ የሚያወጣው ደግሞ ሁላችንንም ነው።›› በማለት ያመለክታሉ።
የኦሮሚያ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ፕሬዚዳንት የሆኑትን ሼህ ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ በበኩላቸው፤ የሰላም ጉዳይን ማስጠበቅ እንደ እስልምና ኃይማኖት አዲስ ነገር እንዳልሆነ ይናገራሉ። ለዚህ ምክንያታቸው ደግሞ በሰላም ጉዳይ ለዘመናት ሲሰበክ በመቆየቱ እንደሆነ ያስረዳሉ። እርሳቸው በግላቸው እንኳን ሰላም ይሰፍን ዘንድ ያልወጡት ውጣ ውረድ አለመኖሩንም ነው የገለፁት። ስለዚህም ከሁሉም በፊት ቅድሚያ የሚሰጡት ለሰላም፣ ለአገርና ለወገን እንደሆነ ያመለክታሉ። ፍላጎታቸው ብቻ ሳይሆን ዓላማቸውም ኢትዮጵያ ከዳር እስከ ዳር ሰላም እንድትሆን ነው። ስብከታውም ቢሆን በዚሁ ላይ የሚያተኩር መሆኑን አፅንዖት ሰጥተው ገልፀዋል።
እንደ ሼህ ሐጂ ገለፃ፤ የእርቀ ሰላም ፕሮግራም ይኑር አይኑር እነርሱ ግን ስለ ሰላም መደበኛ ስራቸው አድርገው ነው የሚንቀሳቀሱት። ምክንያቱም የትኛውንም ስራ ለመተግበር የሚያስችለው ሰላም ሲኖር ነውና ነው። ስለዚህም ለሰላም አዲስ ፕሮግራም ተይዞለታል ስለተባለ ብቻ ሳይሆን ተያዘም አልተያዘም ሁሌም ቢሆን ሰላም ወሳኝ ስለሆነ ሰላም ላይ የማያተኩሩበት ምክንያት አይኖርም። ስለዚህ ስለሰላም ብለው ከሚቆሙት ጋርም ሁሌም ለመተባበር ዝግጁዎች ናቸው። ከጎናቸውም ይቆማሉ።
‹‹እስላም ማለት በራሱ ሰላም ማለት ነው።›› የሚሉት ሼህ ሐጂ፣ ‹‹እንደ ስሙም የሚሰብከውም ሰላምን ነውና ኃይማኖት ካላቸው ጋር ይቅርና ከሌላቸው ጋር እንኳ ተቀራርበን የምንሰራ ነን። በሰላም ጉዳይ የምናመጣው አዲስ ነገር ሳይሆን የነበረንን መልካም እምነት አጠንክረን ከዚህ የተቀደሰ ዓላማ ይዘው ከሚንቀሳቀሱት ጎን በመሆን ለመስራት ዝግጁዎች ነን።››ብለዋል።
ሼህ ሐጂ እንደሚናገሩት፤ ኮሚሽኑ በሚያስቀምጠው መርሃግብር ለስኬታማቱም ከጎኑ ናቸው። በእርግጥ ሁሉም ለሰላም ግንባር ቀደም መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ በፊት አውራሪነት የሚንቀሳቀሱትን ደግሞ በታማኝነት ለመደገፍ ዝግጁዎች ናቸው።
የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስትያናት ህብረት የቦርድ ሰብሳቢ የሆኑትን መጋቤ ዘሪሁን ደጉ በበኩላቸው፤ ይህ አይነት እርቀ ሰላም ኮሚሽን ተቋቁሞ በሌሎች አገሮችም ውጤት ማምጣት የቻለ እንደሆነ ይናገራሉ።ከዘመን ዘመን እንዲሁም ከአንድ ትውልድ ወደ አንድ ትውልድ ሲገለባበጡ የመጡ መራራ ፍሬዎችና ቁርሾዎች ከማስወገድ አንፃር ውጤታማ አደረጃጀት እንደሆነ እንደሚገነዘቡ ያመለክታሉ። ከሌሎች የመንግስት ባለስልጣናት ሳይሆን ከኮሚሽኑም ብዙ እንደሚጠበቅ ነው ያስረዱት።
ለዚህ ምክንያት ያሉት ደግሞ ኢትዮጵያ የኃይማኖት አገር ናት ሲባል በርካታ የኃይማኖት ተከታዮች አሉ ማለት ነው። ይህ የሃይማኖት ተከታይ ደግሞ ክርስትያኑና ሙስሊሙ ህብረተሰብ ነው። ሁሉቱም ደግሞ በአስተምሯቸው ውስጥ ይቅር ባይነት፣ ይቅርታ መስጠትና ይቅርታ መቀበል የአስተምሮው አንኳሮች ናቸው። ስለዚህ አሁን ኢትዮጵያ የገጠማት ችግር ትናንትና እና ከትናንት ወዲያ የተፈጠረ አይደለም። ሲዞር የመጣ ነውና በጊዜ ውስጥ ያልተፈቱ ችግሮች ተደምረው ዛሬ የተደረሰበት ደረጃ ላይ መድረስ ችሏል። ስለዚህ ይህንን መፍታት የሚገባው በይቅርታ ነው።ይቅርታ ደግሞ ለእያንዳንዱ እምነት አለኝ ለሚል ሰው ሁሉ የማይቀበለው ከሆነ ኃይማኖተኛ ነኝ ሊል እንደማይችል ተናግረዋል።
መጋቤ ዘሪሁን፣ ‹‹ያልበደለ ማንም የለም፤ ሁሉም በድሏል። አንዱን በዳይ ሌላውን ተበዳይ አድርገን ፈርጀን የምንጓዝ ከሆነ ወደ ይቅርታ መድረስ አንችልም። ስለዚህ እንደ አገርና እንደ ህዝብ በባለስልጣናቱም የተፈፀመ ይሁን፣ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የተፈፀመ የሆነ ነገር ወንድም በወንድሙ ላይ፣ ቤተሰብ በቤተሰብም ላይ በአንድም ሆነ በሌላ የህዝባችን የታሪካችን አካል የሆነ ጥላቻ አድጓል። ይህንን ለማስወገድ ሁላችንም ተባብረን የእርቀ ሰላም ኮሚሽኑ በሚያወጣቸው እቅዶችና የስራ ዝርዝሮች ውስጥ ልንሳተፍ ይገባል።›› ብለዋል።
‹‹ኮሚሽኑ ብቻ የኢትዮጵያን ችግር ይፈታል ብለን አናስብም፤ ነገር ግን ከተባበርን የደቡብ አፍሪካን ችግር እንደፈታው ኮሚሽኑ አይነት ተቋም ነውና እኛም ከተባበርን ችግሮቹ ይፈታሉ የሚል እምነት አለኝ›› ሲሉም አክለዋል።
እንደ መጋቤ ዘሪሁን ገለፃ፤ በአዲሱ ዓመት አሮጌ ነገርን መዝጋት ያስፈልጋል። ሚዲያውም ስለሰላምና አንድነት ማውራት ይጠበቅባቸዋል።ጥላቻንና መለያየቱን የዘራነው እኛው ነን በሚል መንፈስ አሁን ደግሞ ሁላችንም የመፍትሄ አካል እንሁን በማለት መነሳት የግድ ይላል፤ የኢትዮጵያ ህዝብ አዛኝና ይቅር ባይ ህዝብ ነው፤ አንዱ ለሌላው ጠላት አይደለም።
አዲስ ዘመን ነሃሴ 28/2011
አስቴር ኤልያስ