
ባለፉት ሦስት ዓመታት ውስጥ 171 የሚሆኑ ቻይናውያን ካምፓኒዎች በተለያዩ የግንባታ ዘርፎች ወደኢትዮጵያ ገብተው እየሰሩ መሆኑንና ከነዚህ ውስጥ 30 ያህሉ በህንፃ ግንባታ ዘርፍ ተሳታፊ መሆናቸውን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ከሰሞኑ ለአዲስ ዘመን ገልጿል። በህንፃ ግንባታ ዘርፍ የሚሳተፉ ቻይናውያን ተቋራጮች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መሄድ በአንድ በኩል ተስፋ በሌላ በኩል ደግሞ ስጋት እንዳዘለ የጉዳዩ ባለቤቶች ይገልፃሉ።
ኢንጂነር አመሃ ስሜ የኢትዮጵያ ሥራ ተቋራጮች ማህበር ፕሬዚዳንት ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት አንዳንድ ህንፃዎች ከሚጠይቁት የግንባታ ቴክኖሎጂና አቅም አንፃር ቻይናውያን ተቋራጮች በዘርፉ መግባታቸው እንደ መልካም አጋጣሚ ይታያል። ይሁንና የውጭ ሀገራት ተቋራጮች በብዛት ወደ አገር ውስጥ ገብተው የእውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግርን በሚገባ ማሳለጥ የሚችሉት አገር በቀል የህንፃ ተቋራጮችን በተጓዳኝ በተለይም በሰብ ኮንትራት ማሳተፍ ሲቻል ነው።
እንደ ፕሬዚዳንቱ ገለፃ በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው የተሰማሩ ሀገር በቀል ህንፃ ተቋራጮች ከሀገር አልፈው የውጭ ተቋራጭ እንዲሆኑ ግብ የተቀመጠ ቢሆንም ተቋራጮቹን ባላሳተፈ መልኩ አብዛኛዎቹን የህንፃ ግንባታ ፕሮጀክቶች ለውጭ ህንፃ ተቋራጮች ጠቅልሎ መስጠቱ አግባብ አይደለም። ይህም የኮንስትራክሽን ዘርፉ እየተቀዛቀዘ ባለበት በአሁኑ ወቅት ከላይ እስከታች ያሉ የአገር ውስጥ ተቋራጮችን ከፍተኛ ችግር ውስጥ ከቷቸዋል። በአገር ውስጥ ባለው የገበያ ውጣ ውረድና የኢኮኖሚ ሁኔታም በርካታ ተቋራጮች ዋጋ እያስከፈሉ ይገኛሉ።
የአገር ውስጥ ተቋራጮች አቅም አነሳ መሆን፣ ተፎካካሪ እየሆኑ እንዲመጡ የሁኔታዎች አለመመቻቸትና የአቅም ግንባታ ሥራዎች አለመሰራታቸው የችግሩ ዋነኛ መንስኤዎች ናቸው የሚሉት ፕሬዚዳንቱ፣ ይህ ሁኔታ የውጭ አገራት የህንፃ ተቋራጮች በተለይም ቻይናውያን እንደልብ ወደ አገር ውስጥ ገብተው እንዲሰሩ እድል በር ከፍቶላቸዋል፤ ሀገሪቱም ተጨማሪ የውጭ ምንዛሪ እንድታወጣ አድርጓታል።
የውጭ ሀገራት ተቋራጮች የሚወዳደሩባቸው መስፈርቶች እንዳሉ ሆኖ በአገር ውስጥ ገብተው በሚሰሩበት ጊዜ የኮንስትራክሽን ህጉ ሊከለክላቸው ሲገባ በተቃራኒው እንደልባቸው በህንፃ ግንባታው ዘርፍ እንዲሳተፉ አስችሏቸዋል፡፡ ይህም ህግና ሥርዓቱ በሚገባ እየተከበረ አለመሆኑንና የአገር ውስጥ ተቋራጮች የዜግነት ድርሻቸውን እንዳይወጡ ብሎም ከዘርፉ ተጠቃሚ እንዳይሆኑ እንቅፋት እየሆነ ይገኛል፡ ፡ የቁጥጥር ሥራውንና የህግ አፈፃፀሙን ለመከታተልና ለማስፈም የተመደበው የመንግሥት አካል ሥራውን በሚገባ እየሰራ አለመሆኑንም ያሳያል፡፡
ፕሬዚዳንቱ እንደሚሉት ሀገር በቀል የህንፃ ተቋራጮች ከቻይናውያን ተቋራጮች እኩል ተወዳዳሪና ከዘርፉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በግንባታው ኢንዱስትሪው ዘርፍ በመንግሥት በኩል የወጡ ህጎችና አሰራሮች በአግባቡ ሥራ ላይ ሊውሉ ይገባል፡፡ የውጭ ህንፃ ተቋራጮች በአብዛኛው በሚሳተፉባቸው ዓለም አቀፍ ጨረታዎች ላይ መስፈርቱን ማሟላት የሚችሉ ሀገር በቀል ተቋራጮች የሚወዳደሩበትና የሚሳተፉበት እድልም መመቻቸት ይኖርበታል፡፡ ጉዳዩ የሚመለከተው የመንግሥት አካልም የአገር ውስጥ የህንፃ ግንባታ ተቋራጮችን አቅም መገንባት ይጠበቅበታል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚ መምህር ረዳት ፕሮፌሰር ብርሃኑ ደኑ በበኩላቸው እንደሚሉት የአንድ አገር ህዝብ በርትቶ መስራት ካልቻለ አሁን ባለው የሉላዊነት ዘመን የግንባታ ሥራዎችን ብቻ ሳይሆኑ ሌሎችም ሥራዎች በውጭ ባለሃብቶች ሊከናወኑ ይችላሉ፡፡ ቻይናውያን የህንፃ ተቋራጮችም ወደ ኢትዮጵያ በብዛት ሊገቡ የሚችሉት የአገር ውስጥ ተቋራጮች የሚሰጣቸውን ኮንትራት በአግባቡና በጊዜው ፈፅመው በተገቢው ዋጋና በሚገባው የጥራት ደረጃ ማስረከብ ሲያቅታቸው አልያም በመንግሥት በኩል ያለው የኮንትራት አሰጣጥ ችግር ያለበት በመሆኑ ነው፡፡
እንደ ረዳት ፕሮፌሰሩ ገለፃ ይህን ለማስተካከል በመንግሥት በኩል ያለው የኮንትራት አሰጣጥ ሥርዓት እንደገና መታየትና ተጠንቶ መስተካከል ይኖርበታል፡፡ ለአገር ውስጥ ተቋራጮች ቅድሚያ መስጠት አስፈላጊ በመሆኑ ትንንሾቹንም ሆነ ትላልቅ የህንፃ ግንባታ ፕሮጀክቶችን በየትኛውም ሁኔታ ለቻይናውያንና ለሌሎችም የውጭ ሀገር ህንፃ ተቋራጮች አሳልፎ መስጠት አይገባም፡፡
አንዳንድ የህንፃ ግንባታዎች ከፍተኛ ወጪ የሚፈልጉና ቴክኖሎጂ የሚጠይቁ ቢሆንም እንኳን ይህንኑ ቴክኖሎጂና ለህንፃው የሚያስፈልገውን ከፍተኛ ካፒታል መሸፈንና መስፈርቱን ማሟላት የሚችሉ የአገር ውስጥ ተቋራጮች ካሉ ቅድሚያ መሰጠት ይኖርበታል፡፡ ሀገር ውስጥ ያለው አቅም ይህንን መፈፀም ካልቻለ ብቻ ግን በሁለተኛ ደረጃ ለውጭ ተቋራጮች መስጠት ያስፈልጋል፡፡
ረዳት ፕሮፌሰሩ እንደሚሉት የአገር ውስጥ ህንፃ ተቋራጮች በትላልቅ ግንባታዎች እንዲገቡና በግንባታው ዘርፍ የራሳቸውን አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ ቢያንስ ከቻይናውያን ተቋራጮች ጋር በትብብር ተቀናጅተው የሚሰሩበት ሁኔታ ሊመቻች ይገባል፡ ፡ ይህም የእውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲሁም የአቅም ግንባታ እንዲኖር ያስችላል፡፡
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ መኮንን ሃይሉ የውጭ አገራት የህንፃ ግንባታ ተቋራጮች ወደአገር ውስጥ ገብተው ሲሰሩ ከሚፈጥሩት የሥራ እድልና ከሚያመነጩት የውጭ ምንዛሪ ባሻገር ለቴክኖሎጂና የእውቀት ሽግግር ያላቸው አስተዋፅኦ ከፍተኛ መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡ ተቋራጮቹ የተሻለ ልምድ፣ አስተዳደር፣ ቴክኒክና ልዩ ልዩ አሰራሮችንም ጭምር ይዘው ስለሚመጡ የአገር ውስጥ ተቋራጮች በተሻለ ሁኔታ አቅማቸውን እንዲያጎለብቱ እንደሚያስችላቸውም ይገልፃሉ፡፡
ቻይናውያን የህንፃ ግንባታ ተቋራጮች በአብዛኛው በደረጃ አንድ የግንባታ ዘርፍ ላይ እንደሚሰማሩ የሚገልፁት ዳይሬክተሩ፤ የአገር ውስጥ ተቋራጮች በዚህ ደረጃ ተሳትፈው በተሻለ ፍጥነት፣ጥራትና ዋጋ የሚሰሩበት የብቃት ደረጃ ላይ ያልደረሱ በመሆናቸው ደረጃው በኮሚሽኑ በኩል ለውጭ አገራት ካምፓኒዎች ተፈቅዷል፡፡
ይህም የአገር ውስጥ ህንፃ ተቋራጮችን ሥራ የሚሻማ ሳይሆን ይልቁንም የውጭ አገራት የህንፃ ተቋራጮች ወደ አገር ውስጥ ገብተው ሲሰሩ የአገር ውስጥ ተቋራጮች የተሻለ ልምድና ተሞክሮ ከእነርሱ በመቅሰም በቀጣይ በዚሁ ደረጃ ለመሳተፍ ያስችላቸዋል፡ ፡ በመሆኑም የኮንስትራክሽ ዘርፉ በኢትዮጵያ እያደገ በመምጣቱ የውጭ አገራት ተቋራጮች በዚህ ዘርፍ መሰማራታቸው ከጉዳቱ ይልቅ ጥቅሙ ያመዝናል፡፡
ዳይሬክተሩ እንደሚሉት ቻይናውያንን ጨምሮ ሌሎች የውጭ አገራት የህንፃ ተቋራጮች ስለማያዋጣቸው ከደረጃ አንድ በታች ባሉ የግንባታ ፕሮጀክቶች ላይ አይሳተፉም፤ በኮሚሽኑ በኩልም ፍቃድ አይሰጣቸውም፡፡ ከደረጃ አንድ በታች ባሉ ግንባታዎች የሚሳተፉት የአገር ውስጥ ህንፃ ተቋራጮች ብቻ ሲሆኑ በደረጃ አንድ ግንባታ የማይሳተፉበት ምክንያትም ከአቅም፣ ጥራትና በብቃት ከመስራት ጋር በተያያዘ ብሎም ግንባታውን በተገቢው ጊዜና ሰዓት አጠናቆ ከማስረከብ አንፃር ክፍተት ያለባቸው በመሆኑ ነው፡ ፡ ከደረጃ አንድ በታች ያሉ ሥራዎችን ለውጭ አገራት ተቋራጮች እንዲሰጥ ያልተደረገውም የአገር ውስጥ ተቋራጮችን የተሻለ ተወዳዳሪና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል ነው፡፡ በአገሪቱ ህንፃዎችን ለማስገንባት በሚወጡ ዓለም አቀፍ ጨረታዎችም የአገር ውስጥም ሆኑ የውጭ አገራት ህንፃ ተቋራጮች እኩል ተሳታፊ እንዲሆኑ ይደረጋል፡፡
ትልልቅ ቴክኖሎጂና እውቀት የሚጠይቁ የህንፃ ፕሮጀክቶች በውጭ ሀገራት ተቋራጮች እንዲገነቡ ማድረጉ የእውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግር ከማምጣት አንፃር ጉልህ ሚና ያለው ቢሆንም ሁሉንም የህንፃ ፕሮጀክቶች ለነዚሁ የውጭ ሀገራት ተቋራጮች አሳልፎ መስጠቱ ሀገሪቱን ለከፍተኛ ወጪ ከመዳረጉም በላይ ኢኮኖሚዋ ላይ በጎ ያልሆነ ተፅእኖ ያሳድራል፡፡ ከሁሉ በላይ ደግሞ አገር በቀል የህንፃ ተቋራጮችን አቅም በማዳከም ከግንባታው ዘርፍ እንዲወጡ ያደርጋቸዋል፡፡
አዲስ ዘመን ነሃሴ 28/2011
አስናቀ ፀጋዬ